ህወሓት እና ኦህዴድ፦ የጠፋችውን በግ ከሰረቃት ሌባ ጋር የምትፈልጋት ከሆነ መቼም አታገኛትም! 

ከጋዜጠኞች እና አንዳንድ ዲፕሎማቶች ጋር በተገናኘሁ ቁጥር ስለ አዲሱ የኦህዴድ አመራር መከራከር በጣም አድካሚ ነበር። አብዛኞቹ በኦቦ ለማ አመራር ቁርጠኝነት ላይ እምነት አልነበራቸውም። በእርግጥ እኔ ራሴ የአመራሮቹን እንቅስቃሴ በአንክሮ ከመከታተል ባለፈ ሙሉ እምነት አልነበረኝም። ነገር ግን፣ የለውጡን እንቅስቃሴ ለመቁረጥ ሳንጃውን ሰድሮ ከመጣው ህወሓት ጋር ኦህዴድ በባዶ እጁ ትንቅንቅ ውስጥ በገባበት ወቅት ዳር ቆሞ መመልከት ወይም “ገለልተኛ ነኝ” ብሎ ማለት አይቻልም። 
በእርግጥ ህወሓት ቆሞ-ቀር ድርጅት ነው። ትላንትም፥ ዛሬም፥ ነገም የህወሓት አቋምና አመለካከት “ፀረ-ለውጥ” ነው። የአዲሱን አመራር አንገት ለመቀንጠስ ሳንጃውን ሰድሮ የተንደረደረበት ምክንያት የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በአጭሩ ለመቅጨት ነው። ምክንያቱም የኦሮሞ ሕዝብን መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት የለውጥ እንቅስቃሴ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የህወሓትን የበላይነትና ተጠቃሚነት የሚጋፋ ነው። ስለዚህ ህወሓት የበላይነቱን ለማስቀጠል የኦህዴድ የለውጥ እንቅስቃሴ መቀጠል የለበትም። 

የህወሓት ቆሞ-ቀርነት ከራሱ አልፎ የተቀሩትን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችን ቆሞ የሚያስቀር ነው። ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በኦህዴድ እና ህወሓት መካከል የነበረው የለውጥ እና ፀረ-ለውጥ አቋም ግጭትና ፍጭት ነው። ለውጥ ተፈጥሯዊ ሕግ ነው። በሕይወት ውስጥ የማይለወጥ ነገር ቢኖር “ለውጥ” ራሱ ብቻ ነው። ይህን የተፈጥሮ ሕግ ተግባራዊ ለማድረግ በሚጥር እና እንዳይደረግ በሚታትር መካከል ትንቅንቅ ሲጀመር ገለልተኛ መሆን አይቻልም። 

ምንግዜም ቢሆን የለውጥ ኃይል መሻሻልና እድገት ያመጣል። በአንፃሩ የፀረ-ለውጥ ኃይል መላላጥና ውድቀት ያስከትላል። ስለዚህ ህወሓት የኦህዴድን የለውጥ እንቅስቃሴ በአጭሩ ለመቅጨት ሳንጃውን ሰድሮ ሲንደረደር ብዙዎቻችን የለማ ቡድን ደግፈን የተረባረብነው፤ በአንድ በኩል ለእውነትና እድገት ብለን፣ በሌላ በኩል ሀገሪቱን ከእርስ-በእርስ ግጭትና ውድቀት ይታደጋል ብለን ነው።

በዚህ መሰረት፣ በኦህዴድ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ እውነተኛ እንዲሆንና በሀገሪቱ ላይ የተሻለ እድገት ለማምጣትና በእኩልነት መርህ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመዘርጋት ምን መደረግ እንዳለበት በዝርዝር ማጤን ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር፣ “የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከዳር ለማድረስ ምን ዓይነት ለውጥ ያስፈልጋል?” የሚለውን በጥቅሊ ለመዳሰስ እንሞክራለን። በተለይ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከሰሞኑ ያወጣውን ድርጅታዊ መግለጫ መነሻ በማድረግ፤ የሕገ መንግስቱ ድንጋጌዎች አተገባበር እና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ እንዲሁም የፌደራሉ መንግስት አወቃቀር እና የክልሉ መንግስት በአዲስ አበባ ላይ ካለው ልዩ ጥቅምና ስልጣን አንፃር እንመለከታለን። 

ባለፈው ሳምንት በወጣው የኦህዴድ ድርጅታዊ መግለጫ መሰረት፤ “ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ዜጎች ካለምንም ስጋት ከቦታ ቦታ ተዘዋውረው እንዲሰሩ በማስቻል በፍትህ ስርዓቱና በፖሊሲ ስርዓታችን ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያስገኙ የሚችሉ ሁለንተናዊ ሪፎርም ማከናወን እንደሚገባ ከስምምነት ላይ ተደርሷል። በእርግጥ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን፣ የተሸራረፉ ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ ማድረግ አይቻልም። የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተስማማበት ሁለንተናዊ ሪፎርም እስከ ምን ድረስ ነው? የተሸራረፉ ድንጋጌዎችን ማስተካከል ወይስ ሳይሸራረፉ መተግበር?   

የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አምስት መሰረታዊ መርሆች አሉት። እነሱም፣ እነሱም፡- አንቀፅ (8)፡- የሕዝብ ሉዓላዊነት፣ አንቀፅ (9)፡- የሕግ-መንግስት የበላይነት፣ አንቀፅ (10)፡- ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ አንቀፅ (11)፡- የመንግስትና ሃይማኖት መለያየት፣ እና አንቀፅ (12)፡- የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት ናቸው። እነዚህ መርሆች መንግስታዊ ስርዓቱ የተመሰረተባቸው ምሶሶዎች (pillars) ናቸው። አንድ መንግስት የሕዝብ ሉዓላዊነትና የሕግ-መንግስቱን የበላይነት ማረጋገጥ ከተሳነው፣ እንዲሁም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበርና ማስከበር ካልቻለ፣ በሃይማኖት ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ-የሚገባ ከሆነ፣ እንዲሁም የመንግስት ሥራና አሰራር ግልፅነትና ተጠያቂነት ከሌለው ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ ሙሉ በሙሉ ፈርሷል።

በተለይ ባለፉት አስር አመታት በመንግስት ስራና አሰራር ውስጥ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተንሰራፋ ቢሆንም በጉዳዩ ተጠያቂ የሆኑ የመንግስት ኃላፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ አልተደረገም። በዚህና በሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች የተማረሩ ዜጎች ብሶትና አቤቱታቸውን ለማሰማት አደባባይ ሲወጡ “አመፅና ኹከት በማስነሳት ሕገ-መንግስቱን በኃይል ለመናድ” በሚል በፀረ-ሽብር ሕጉ ይከሰሳሉ። በተመሳሳይ የዜጎች መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲከበር በይፋ የተናገሩ የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ የመብት ተሟጋቾች፣…ወዘተ በአሸባሪነት ይከሰሳሉ። የኢህአዴግ መንግስት በሃይማኖታቸው ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን የተቃወሙ የዋልድባ ገዳም መነኩሴዎች እና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በፀረ-ሽብር ሕጉ አማካኝኘት በአሸባሪነት ተከስሰዋል። 

ስለዚህ በፀረ-ሽብር ሕጉ ብቻ የሕግ-መንግስት የበላይነት፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የመንግስትና ሃይማኖት መለያየት እና የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት የሚሉት አራቱ የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ተጥሰዋል። ነገር ግን፣ የሕገ-መንግስቱ አራት መሰረታዊ መርሆች በፀረ-ሽብር ሕጉ የተጣሱ ቢሆንም የኢህአዴግ መንግስት ግን አልወደቀም። ምክንያቱም የተጣሱት አራቱ መሰረታዊ መርሆች በዋናነት ስለ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚደነግጉ ናቸው። ነገር ግን፣ እነዚህን ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችለው የፖለቲካ ስልጣን ያለው “የሕዝብ ሉዓላዊነት” በሚለው ድንጋጌ ላይ ነው።

የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ (8) “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው” በማለት ይደነግጋል። “የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት” የሆነ አካል በሀገሪቱ ላይ ባለቤትነት፣ በመንግስት ላይ ደግሞ የስልጣን የበላይነት አለው። ሉዓላዊ ስልጣን ያለው አካል ፖለቲካዊ መብቱንና ነፃነቱን በራሱ መጠየቅና ማስከበር ይችላል። ነገር ግን፣ በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት መሰረት የኢትዮጲያ ዜጎች የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት አይደሉም። ስለዚህ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በራሳቸው መጠየቅ ሆነ ማስከበር አይችሉም። በሕገ መንግስቱ መሰረት የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ያላቸው “የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ደግሞ እንደ ዜጎች በራሳቸው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን መጠየቅ ሆነ ሉዓላዊ ስልጣናቸውን መጠቀም አይችሉም። 

ለዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ሰጥቶ መብታቸውን የመጠየቅና የማስከበር ስልጣን የሚገፍፍ ሕገ-መንግስት ተረቅቆ የፀደቀው በህወሓት መሪነት ነው። በዚህ ሕገ-መንግስት ላይ ምንም ዓይነት ለውጥና ማሻሻያ እንዳይደረግ “በመቃብሬ ላይ” በማለት አምርሮ የሚቃወመው ህወሓት ነው። ምክንያቱም ሕገ-መንግስቱ በብሔሮች ስም የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመግፈፍ የራሱን የበላይነት ለማስቀጠል እንዲያገለግል ተደርጎ ያዘጋጀውና በዚሁ አግባብ ተግባራዊ እየተደረገ ነው። 

ስለዚህ ሕገ-መንግስቱ በራሱ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመሸራረፍ ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባር ላይ እንዲውሉ በማድረግ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበር ሆነ ማስከበር አይቻልም። በፍትህ ስርዓቱና የመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ጥገናዊ ለውጥ በማድረግ ሁለንተናዊ ተሃድሶ ማረጋገጥ አይቻልም። 

ከላይ የተጠቀሰው ድርጅታዊ መግለጫ ከኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ ቢሆን ኖሮ ድርጅታዊና መንግስታዊ መዋቅርን ተከትሎ በሀገሪቱ ላይ ሁለንተናዊ ሪፎርም ማከናወን ይቻላል። ነገር ግን፣ ይህን ሥር-ነቀል የለውጥ እንቅስቃሴ የጀመረው ከአራቱ አባል ድርጅቶች አንዱ ብቻ ነው። በመሆኑም የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተግባራዊ መደረግ አለበት ያለው ሁለንተናዊ ሪፎርም በሀገር አቀፍ ደረጃ የታለመለትን ግብ ላይመታ ይችላል። ነገር ግን፣ በኦህዴድ መሪነት የተጀመረው የተሃድሶ እንቅስቃሴ የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይኖርበታል።

ባለፉት ሦስት አመታት በሀገሪቱ ለታየው የፖለቲካ አለመረጋጋት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ነው። በማስተር ፕላኑ አዘገጃጀትና አተገባበር ሂደት እክል እንዲገጥመው ያደረጉ መሰረታዊ ምክንያት ደግሞ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(5) መሰረት ከአገልግሎት አቅርቦት፥ የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የክልሉን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የሚያስችል ሕግና መመሪያ አለመውጣቱ ነው። በዚህ መሰረት፣ አዲሱ የኦህዴድ አመራር በሕገ-መንግስቱ መሰረት ክልሉ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ለመወሰን የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ የክልሉ ሕዝብ አስተያየት እየሰጠበት ይገኛል። ነገር ግን፣ በኦህዴድ መግለጫ መሰረት “ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባራዊ በማድረግ” ብቻ የክልሉን “ልዩ ጥቅም” ማስከበር ይችላል?

በአንቀፅ 49(2) መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር “ሙሉ” ስልጣን ስላለው የመስተዳደሩ ተጠሪነት በነዋሪዎቹ ድምፅ ለተመረጠ የከተማዋ ምክር ቤት መሆን አለበት። ነገር ግን፣ የሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(3) “የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት” እንደሆነ ተደንግጓል። ይህ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሕገ-መንግስቱ የተሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣኑን አጥቷል። በመሆኑም የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና በራሳቸው እድል የመወሰን ስልጣናቸው ተገፍፏል። ስለዚህ በኦህዴድ መግለጫ መሰረት “ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ማድረግ” ማለት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በፌደራሉ መንግስት መገፈፍ እንዳለበት መስማማት ነው። 

አዲስ አበባ የኦሮሚያና የፌደራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ ናት። ሆኖም ግን፣ በአንቀፅ 49(3) መሰረት የከተማ መስተዳደሩ ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት ስለሆነ የፌደራሉ መንግስት አዲስ አበባን የማስተዳደር ቀጥተኛ ስልጣን አለው። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ግን እንኳን የማስተዳደር ስልጣን በርዕሰ ከተማዋ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ መብት ማስከበር አልቻለም። ይህ የሆነበት ምክንያት በከተማው እና በክልሉ መስተዳደር መካከል ሳይሆን ከፌደራሉ መንግስት ጋር በተፈጠረ አለመግባባትና የጥቅም ግጭት ነው። 

ከዚህ አንፃር፣ የከተማ መስተዳደሩ ሆነ ነዋሪዎቹ በምንም አግባብ ተጠያቂ ሊሆኑ አይገባም። ምክንያቱም ራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸው በፌደራሉ መንግስት ስለተገፈፈ በራሳቸው የመወሰን ስልጣን የላቸውም። ስለዚህ በከተማዋ ላይ የመወሰን ስልጣን ያለው የፌደራሉ መንግስት ነው። ሕገ-መንግስቱ ተግባራዊ ከሆነበት ግዜ ጀምሮ በአንቀፅ 49(5) መሰረት ረቂቅ አዋጅ ያልተዘጋጀበት ምክንያት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ልዩ ጥቅሙ እንዲከበር ስላልፈለገ ነው? አይደለም! ከዚያ ይልቅ፣ የፌደራሉ መንግስት የክልሉ ልዩ ጥቅም እንዲከበር ስላልፈለገ ነው። በአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ሆነ በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከከተማ መስተዳደሩና ነዋሪዎች ይልቅ የፌደራሉ መንግስት፣ በተለይ ደግሞ የህወሓት አባላትና ደጋፊ ልሂቃን ሽንጣቸውን ገትረው ይሟገታሉ። ረቂቅ አዋጅም ቢሆን በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 41፥ 89፥ 90፥ 91፥ 92፥… የተደነገጉ መብቶችን እንደ “ልዩ ጥቅም” ይዞ የቀረበ ነው። 

በአጠቃላይ የፌደራሉ መንግስት በአንቀፅ 49(3) መሰረት የተሰጠውን ያልተገባ ስልጣንን በመቀማት የአዲስ አበባ መስተዳደር ተጠሪነቱ ለከተማ ምክር ቤቱ እስካልሆነ ድረስ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መብት ሆነ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም በፍፁም አይከበርም። ስለዚህ በኦህዴድ መግለጫ መሰረት ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ማድረግ የክልሉን “ልዩ ጥቅም” ማስከበር አይቻልም። በመሆኑም በድርጅቱ መግለጫ መሰረት የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ አይቻልም። ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባራዊ በማድረግ የክልሉ ልዩ ጥቅም፥ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መብት፥ እንዲሁም ቀደም ሲል በተገለፀው መሰረት፣ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዎ መብቶችን ማስከበር አይቻልም። ስለዚህ ከኦህዴድ የሚጠበቀው መሰረታዊ ነገር ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ሳይሸራረፉ ተግባራዊ ለማድረግ ከመሞከሩ በፊት የተሸራረፉ ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎችን ማስተካከል ነው።  

ወዳጄ መንግስቱ አሰፋ እንደነገረኝ በዚህ አመት ጥቅምት ወር መጨረሻ አከባቢ ኦቦ ለማ መገርሳ የኦሮሞ ድምፃዊን ሰብስቦ በሚያናግርበት ወቅት ድምፃዊ ታደለ ገመቹ እንዲህ አለ፦ <<የጠፋችውን በግ ከሌባው ጋር አብረህ የምትፈልጋት ከሆነ መቼም ቢሆን አታገኛትም>> በእርግጥ የድምፃዊ ታደለ ገመቹ አባባል አስገራሚ ነው፡፡ ህወሓት የራሱን የበላይነት ለማስቀጠል የነደፈውን ሕገ-መንግስት ሳይሸራረፍ ተግባራዊ በማድረግ የኦሮሞን ህዝብ መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ከህወሓት ጋር የተጠፋችውን በግ እንደመፈለግ ነው፡፡ ህወሓት ሌባው ነው፣ ኦህዴድ ደግሞ የጠፋችውን በግ ከሰረቃት ህወሓት ጋር እየፈለገ ነው፡፡