​የኢትዮጲያ ሕዝብ በህወሓት/ኢህአዴግ ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ አለበት! 

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ዝርዝር መመሪያ ለሕዝብ ይፋ በተደረገበት መድረክ ላይ የነበሩትን ተሰብሳቢዎች ተመልከቷቸው? ከመከላከያ ሚኒስትሩና በጣት ከሚቆጠሩ ባለስልጣናት በስተቀር ሁሉም የፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት ሬንጀር (የደንብ ልብስ) የለበሱ ናቸው። የስብሰባው ድባብ በአጠቃላይ በዜጎች ላይ ፍርሃትና ሽብር የሚፈጥር ነው። 

በእርግጥ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የሚያስከብሩ ፖሊሶች እና ሀገርን ከውጪ ወራሪ የሚከላከሉ ወታደሮች በዜጎች ላይ ፍርሃትና ሽብር መፍጠር የለባቸውም። ነገር ግን፣ እዚህ ሀገር ፖሊሶች የህዝብን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ይለቅ በሕዝብ ላይ ፍርሃትና ሽብር ይፈጥራሉ። የሀገራችን ወታደሮች ንፁሃን ዜጎችን ልክ እንደ ወራሪ ጦር በጥይት ተኩሰው ይገድላሉ። በተመሳሳይ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት ሰራተኞች ተግባርና ኃላፊነት ከሀገርና ሕዝብ ድህንነት ይልቅ የህወሓትን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። 
በአጠቃላይ የኢትዮጲያ ፀጥታ ኃይሎች ተግባርና እንቅስቃሴ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ላይ ፍርሃትና ሽብር መፍጠር ነው። ለምሳሌ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ከኤርትራ ወይም ከግብፅ ጦር ይልቅ የኢትዮጲያ መከላከያ ሰራዊት ያስፈራዋል፤ በአሸባሪነት ከተፈረጁት እንደ ግንቦት7፣ ኦነግና ኦብነግ ያሉ ቡድኖች ይልቅ የፌደራል “ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል” ያሸብረዋል፤ የማዕከላዊ እስር ቤት መርማሪዎች ጭካኔ ከ“ISIS” አሸባሪዎች የሚተናነስ አይደለም። ታዲያ እነዚህ ሰዎች በአንድ ቦታ ተሰብስበው “ያለ ኮማንድ ፖስቱ ፍቃድ ምንም ነገር ማድረግ ክልክል ነው!” የሚል መመሪያ ሲሰጡ ማየት በራሱ ያስፈራል። ነገር ግን፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታወጀበት መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? 

በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት፣ የተፈጥሮ አደጋ ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ተከስቷል? አልተከሰተም! ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ተደርጓል? አዎ! መቼና በማን? በ1997 ዓ.ም፣ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት! ለምንና እንዴት? በሕዝብ ምርጫ ከስልጣን የተወገደው ህወሓት/የኢህአዴግ የሕዝብን ድምፅ በማጭበርበር እና በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በመጨፍጨፍ የመንግስት ስልጣን በኃይል ተቆጣጥሯል። ይህ የፖለቲካ ቡድን ከሕዝብ ፍቃድና ምርጫ ውጪ በሕገ-ወጥ መንገድ የመንግስት ስልጣን በመያዙ ምክንያት ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ተንዷል። 

የህወሓት/ኢህአዴግን ተግባር በተለመደው የሕግ ማስከበር ስርዓት ማስከበር ይቻላል? አይቻልም! ምክንያቱም ህወሓት/ኢህአዴግ ሕዝብን በማጭበርበር፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በመጨፍጨፍ እና በተቀሩት የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚኖረውን ሕዝብ በማስፈራራት የተቆጣጠረውን ስልጣን ለማስቀጠል የሀገሪቱን የፍትህ ስርዓት አፍርሶታል። የሕዝብን ድምፅ አጭበርብረው በተመረጡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካኝነት ከሕገ መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች የሚቃረኑ፣ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥሱ እና የሀገሪቱን የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ከአገልግሎት ውጪ የሚያደርጉ አፋኝና አፍራሽ የሕግ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎች በማውጣት ተግባራዊ አድርጓል። በመሆኑም ይህ ጨቋኝና ጨካኝ የሆነ የፖለቲካ ቡድን በሀገርና ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በተለመደው የሕግ ማስከበር ስርዓት መከላከል፥ መቆጣጠር ወይም ማስቀረት አይቻልም። 

ይህ የፖለቲካ ቡድን በፌደራልና የክልል ፀጥታ ኃይሎች አማካኝነት በሦስት አመታት ውስጥ ብቻ ከ700 ሺህ በላይ ዜጎች እንዲፈናቀሉ፣ ከ1200 በላይ ንፁሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉ አድርጓል። በዚህ አሰቃቂ ተግባር ላይ የተሰማሩ የመንግስት ኃላፊዎች እና የጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር በማዋል ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ ድጋፍና ከለላ ሰጥቷል። ከሶማሊያ ሞቃዲሾ የመጡ ወታደሮች ከሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል ጋር በመሆን ከ200 በላይ ንፁሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ ሲገድሉ ምንም ዓይነት እርምጃ አልወሰደም። ዚያድባሬ ኢትዮጲያን በወረረበት ወቅት ከዚህ የተለየ ምን አደረገ? በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው አልሸባብ በኢትዮጲያ ላይ ጦርነት ለማወጅ ከመዛት በዘለለ ስንት ኢትዮጲያዊያንን ገደለ? ስንት አባወራዎች አፈናቀለ? ስንት ሴቶችን አስገድዶ ደፈረ? የሀገራችን መከላከያ ሰራዊት በዚህ ዓመት ብቻ በአምቦ፥ በጨለንቆ፥ በወልዲያ፥ በቆቦ፥ … ወዘተ በንፁሃን ዜጎች ላይ የፈፀመውን ግድያ የውጪ ወራሪ ከሚፈፅመው በምን ይለያል? 

በአጠቃላይ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት፤ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ንዷል፣ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት አስደፍሯል። በመሆኑም ይህን ኃይል ከስልጣን ለማስወገድ የኢትዮጲያ ሕዝብ በመንግስት ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ አለበት። ነገር ግን፣ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በሀገርና ሕዝብ ላይ የፈፀመው ግፍና በደል ሳያንስ የሕዝቡን ጩኸት በመቀማት ለሦስተኛ ግዜ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አውጇል። ለምን? የህዝብን ድምፅ በማጭበርበር እና ዜጎችን በማስፈራራት የያዘውን ስልጣን ለማስቀጠል ነው። 

በመሰረቱ የሕዝብን ድምፅ የሚጭበረብር መንግስት ማንኛውም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴን ይፈራል። ስለዚህ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት መገደብ አለበት። ዜጎች ይህን ገደብ በመጣስ የመብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዳይነሳ ሕዝቡን በፀጥታ ኃይሎች ማስፈራራት አለበት። ስለዚህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መነሻ ምክንያት የህወሓት/ኢህአዴግ ፍርሃት ሲሆን የመጨረሻ ግቡ ደግሞ ዜጎችን ማስፈራራት ነው። በአጠቃላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መሰረታዊ ፋይዳ ፍርሃትና ማስፈራራት ነው። 

በእርግጥ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ያወጀው የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ነው። ይህን ያደረገበት ምክንያት፣ ከላይ በተገለፀው መሰረት በ1997ቱ ምርጫ በሕዝብ ድምፅ ከስልጣን መወገዱን ተከትሎ በሕገ መንግስቱ ከተደነገገው አግባብ ውጪ በስልጣን ለመቆየት ባደረገው ጥረት፤ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ገድቧል፥ ጥሷል…፣ በመከላከያ ሰራዊትና የፌደራል ፖሊሶች አማካኝነት በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል፣ ጋዜጠኞችን፥ የመብት ተሟጋቾችን፥ ምሁራንን፥ የሃይማኖት መሪዎችን፥ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፥… ወዘተ ለእስር፥ ስደት፥ ሞትና እንግልት ዳርጓል፣ የክልል ፖሊሶች ከውጪ ሀገር ከመጡ ታጣቂዎች ጋር በማበር ከ700ሺህ በላይ ዜጎች ሲያፈናቅሉና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲገድሉ ጥቃቱን ለመከላከል ሆነ ለማስቆም ተስኖታል፣ እንዲሁም በዜጎች ላይ የሚደርሰው በደልና ጭቆና አሁንም ድረስ ቀጥሏል። 

በዚህ ምክንያት፣ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 93 መሰረት፣ የሕዝብ ሰላምና ደህንነት፣ እንዲሁም በሀገሪቱ ሉዓላዊነት እና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የተቃጣ ቀጥተኛ አደጋ የተቃጣ ሲሆን ሁኔታውን በተለመደው የሕግ ማስከበር ስርዓት መቋቋም አይቻልም። በመሆኑም የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በጉልበት በስልጣን ላይ ለመቆየት በሚያደርገው ጥረት ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ ከመናድ አልፎ በሕዝብና ሀገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ በመንግስት ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጅ አለበት። ስለዚህ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን መንግስት በሕዝብ ላይ ሳይሆን የኢትዮጲያ ሕዝብ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ላይ ማወጅ አለበት። 

የኢትዮጲያ ሕዝብ ህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚያውጅበት መሰረታዊ ምክንያት የራሱን መብትና ነፃነት ለማስከበር ነው። የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በሕዝቡ ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የሚያውጅበት ምክንያት ግን ሕዝቡን ፈርቶ ለማስፈራራት ነው። ሌላው ቀርቶ አዋጁ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 93 ላይ የተደነገገውን “የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ” ይጥሳል። የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስችል ሁኔታ በሌለበት አዋጁን ማወጅ በራሱ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለአደጋ ያጋልጣል። ይህን አዋጅ ደግሞ በተለመደው የሕግ ማስከበር ስርዓት መሰረት መቋቋም አይቻልም። በመሆኑም የሀገርና ሕዝብን ሰላም ለማስከበር ሲባል የኢትዮጲያ ሕዝብ በመንግስት ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ አለበት። 

(የካቲት 05/2010 ዓ.ም በወሊሶ ከተማ የተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ) 

2 thoughts on “​የኢትዮጲያ ሕዝብ በህወሓት/ኢህአዴግ ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማወጅ አለበት! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡