የቄሮዎች እና የታጋዮች ትውልድ ግጭት፡ በጦርነት ያሸነፈ በጦር አይገዛም!

1: የኢትዮጲያ ፖለቲካ የኋሊት ጉዞ
በሀገራችን ፖለቲካ ባለፉት 15 ቀናት የታዩት ለውጦች በ2009 ዓ.ም 365 ቀናት ውስጥ ከታዩት ለውጦች በላይ ጉልህ ሚና አላቸው።ባለፉት 3 አመታት የታዩት ለውጦች ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት 13 አመታት ከታዩት ለውጦች የበለጠ ፖለቲካዊ አንድምታ አላቸው። “ለምን እና እንዴት?” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ በቅድሚያ “በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ምን እየተካሄደ ነው?” ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። የሁለተኛው ጥያቄ መልስ በአጭሩ “የትውልድ ግጭት” የሚል ነው። 

አንድ “ትውልድ” ማለት አንድ ሰው ከተወለደበት ግዜ ጀምሮ የራሱን ልጆች ወልዶ ማሳደግ እስከሚጀምርበት ድረስ ያለው ግዜ ነው።በአብዛኛው የአንድ “የትውልድ ዘመን” በአማካይ 30 አመት ተደርጎ ይወሰዳል። በዚህ መሰረት፣ የ1960ዎቹ ትውልድ ዘመን 1990ዎቹ ላይ ያበቃል፣ የ1990ዎቹ ትውልድ ዘመን ደግሞ 2020ዎቹ ላይ ያበቃል። እያንዳንዱ ትውልድ ከቀድሞ ትውልድ ጥሩና መልካም የሆኑ ማህበራዊ እሴቶችን ይወርሳል። ከቀድሞ ትውልድ በወረሰው ላይ የራሱን ዕውቀትና ልምድ አክሎበት ለቀጣይ ትውልድ ያስረክባል። 

እያንዳንዱ ትውልድ ከቀድሞ ትውልድ በወረሰው ጥሩና መልካም ነገሮች ላይ የራሱን ጥሩና መልካም ነገሮች አክሎበት ለቀጣዩ ትውልድ ያስተላልፋል። በትውልዶች መካከል የሚደረገው ቅብብሎች እንዲህ እያለ ይቀጥላል። የሕይወት ትርጉምና ፋይዳ በግለሰብ ሆነ በማህብረሰብ ደረጃ መልካም ነገሮችን ለማሰብ፥ ለማድረግ፥ ለመፍጠር፥ ለመስራት፥.. የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት፣ ባህልና እሴት፣ ደንብና ስርዓት፥…ወዘተ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ነው። ይህ በሰው ልጆች ዘንድ ብቻ ሳይሆን የሁሉም እንስሳት ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው።

የትውልድ ግጭት የሚፈጠረው የቀድሞ ትውልድ የአዲሱን ትውልድ የሕይወት አቅጣጫ እና የተግባር እንቅስቃሴ በራሱ ሃሳብና አመለካከት ለመወሰን ጥረት ሲያደርግ ነው። የቀድሞ ትውልድ ከእሱ በፊት ከነበረው ትውልድ በወረሰው ላይ የራሱን ዕውቀትና ልምድ አክሎ ለአዲሱ ትውልድ ከማስረከብ ይልቅ የቀጣዩን ትውልድ እጣ ፋንታ በራሱ ለመወሰን ጥረት ሲያድግ በሁለቱ ትውልዶች መካከል የከረረ ግጭት ይፈጠራል። ይህ ግጭት በሰው ልጆች ኢኮኖሚያዊ፥ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ሊከሰት ይችላል። 

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ በ1967 ዓ.ም የራሱን የፖለቲካ ትግል የጀመረ ትውልድ 1997 ዓ.ም ላይ መልካምና ጥሩ ያለውን ነገር በሙሉ ለአዲሱ ትውልድ አስረክቦ መድረኩን መልቀቅ አለበት። በ1960ዎቹ የነበረውን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በአዲሱ ትውልድ ላይ በመጫን መቀጠል አይችልም። ነገር ግን፣ የቀድሞ ትውልድ የራሱን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በቀጣዩ የትውልድ ዘመን ላይ ማስቀጠል የሚሻ ከሆነ አዲሱ ትውልድ የተለየ፥ የተሻሻለ ወይም አዲስ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዳይኖረው ማድረግ አለበት። 

የአዲሱ ትውልድ አባላት የተለየ ሃሳብና አመለካከት እንዳይኖራቸው ለማድረግ፤ በራሳቸው ትክክል የመሰላቸውን ሃሳብ የመያዝና አመለካከታቸውን የመግለጽ ነፃነት፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብት፣ እንዲሁም ሌሎች ፖለቲካዊ መብቶችና ነፃነቶችን ማጥበብ፥ መገደብ እና/ወይም መንፈግ አለበት። ይህ ሲሆን የሀገሪቱ ፖለቲካ የኋልዮሽ ጉዞ ይጀምራል። በህወሓት/ኢህአዴግ መሪነት የተዘረጋው ፖለቲካዊ ስርዓት የ1960ዎቹ ትውልድ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ውጤት ነው። 

በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ቡድን ከሃያ አመት በፊት በ1990ዎቹ ፖለቲካዊ ስርዓቱን የማስተዳደር ስልጣን ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ነበረበት። ይህን ከማድረግ ይልቅ የራሱን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በቀጣዩ የትውልድ ዘመን በመጫን ለማስቀጠል ጥረት አደረገ። በዚህ መሰረት አዲሱ ትውልድ የተለየ ሃሳብና አመለካከት እንዳይኖረው ለማድረግ ፖለቲካዊ መብቶችና ነፃነቶችን ከግዜ ወደ ግዜ በማጥበቡ፥ በመገደቡ እና በመንፈጉ የሀገሪቱ ፖለቲካ የኋልዮሽ ጉዞ ጀመረ። 

የኢትዮጲያ ፖለቲካ ከ1997 – 2007 ዓ.ም ባደረገው የኋልዮሽ አስር አመታት ወደኋላ ተመልሶ 1987 ዓ.ም ላይ ደርሷል። የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት አፍራሽና አፋኝ በሆኑ አዋጆች፥ ደንቦች፥ መመሪያዎች፥ አሰራሮች እና ውሳኔዎች አማካኝነት፤ ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎችን፣ ሲቭል ማህበራትን፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማትን በማስወገድ የኋሊት መንደርደር ጀመረ። የቀድሞ የአየር ኃይል አዛዥ ሜ/ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) በ2007 ዓ.ም “ድርግነት እያቆጠቆጠ – ዴሞክራሲ እየጨላለመ ነው – ሕዝቦች ጠንቀቅ በሉ” በሚል ርዕስ አንድ ማሳሰቢያ አዘል ፅሁፍ ማውጣታቸው ይታወሳል። በእርግጥ የቀድሞ የጄኔራል ስጋት እውን ሆኗል። 

በመሰረቱ የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በ2007ቱ ምርጫ “100% አሸነፍኩ” በማለት በ1987 ዓ.ም ራሱ ተግባራዊ ያደረገውን ሕገ መንግስት “100% ማፍረሱን” በተግባር አረጋግጧል። ከ2008 ጀምሮ ባሉት ሦስት አመታትም ቢሆን የኋሊት ጉዞው ቀጥሎበታል። በመጨረሻም በዘንድሮ ቸመት ሀገሪቱ በ1984 ዓ.ም በነበረችበት ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ አድርሷታል። ጉዞውን በዚህ መልኩ ከቀጠለ በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 1983 ዓ.ም ላይ እንደርሳለን። እንዲህ እያለ በቀጣዩ ዓመት መንግስታዊ ስርዓቱ ወደፊት በመጣበት መንገድ ወደኋላ ይወድቃል።  

በተመሳሳይ ሜ/ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ግንቦት ሃያን አስመልክቶ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ በእሳቸው ትውልድ እና በአዲሱ ትውልድ መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት “…ኢሕአዴግ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የእኛ ትውልድ የአማፂ ትውልድ ነው። የአማፂ ትውልድ የዴሞክራሲ ትውልድ መሆን አይችልም። …ስለዚህ የእኛ ትውልድ የዴሞክራሲ ትውልድ አይደለም። የአመፅ ትውልድ ነው” በማለት ገልፀውታል። በ1960ዎቹ የትጥቅ ትግል የጀመሩትን የእነ ሜ/ጄኔራል አበበ ትውልድ “ታጋዮች”፣ አሁን ያለውን አዲስ ትውልድ ደግሞ “ቄሮዎች/ፋኖዎች” በማለት ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። በዚህ መሰረት፣ ሀገራችን አሁን ላለችበት የፖለቲካ ቀውስ መንስዔ የሆነውን የትውልድ ግጭት በአጭሩ “የቄሮዎች እና ታጋዮች ግጭት” በሚል ንዑስ ርዕስ በዝርዝር ማየት እንችላለን።   

2: የቄሮዎች እና ታጋዮች ግጭት 

ቄሮዎች እና ታጋዮች የጋራ የሆኑ ባህሪያት አሏቸው። በመጀመሪያ ደረጃ ሁለቱም የአንድ ሀገር ዜጎች ናቸው። በመቀጠል ሁለቱም የራሳቸውን የወደፊት እድል በራሳቸው የመወሰን ፍላጎት አላቸው። በመጨረሻም ቄሮዎች እና ታጋዮች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ሁለቱም ባለ ጎፈሬ ናቸው። ከዚህ በተረፈ በሁለት ጎፈሬያሞች መካከል መግባባት ሆነ ስምምነት ብሎ ነገር የለም። ቄሮዎች እና ታጋዮች በቅደም ተከተላቸው መሰረት ድሮና ዘንድሮ፣ የቀድሞ ትውልድ እና አዲስ ትውልድ ናቸው።  

በቄሮዎች እና ታጋዮች በመካከል ፀብና ግጭት ተፈጥሯል። ቄሮዎች (ፋኖዎች) አምፀዋል፣ የቀድሞ ታጋዮች ተቆጥተዋል። ቄሮዎች ሲቆጧቸው አይፈሩም፣ ሲገርፏቸው አይተውም፣ ቢያስሯቸውም አይቆሙም። ታጋዮች አለማወቃቸውን አያውቁም፣ ስህተታቸውን ሲነግሯቸው አይሰመሙም፣ ጥፋታቸውን አምነው አይቀበሉም። 

ቄሮዎች አመፅና ተቃውሟቸውን አላቆሙም፣ ታጋዮች ከአቋምና አመለካከታቸውን አልቀየሩም። ቄሮዎች ለታጋዮች፥ ታጋዮች ለቄሮዎች ያላቸው አመለካከት አንድና ተመሳሳይ ነው። አንዳቸው ለሌላቸው፤ የቅርብ ሩቅ ናቸው፣ አቋምና አመለካከታቸው በቀላሉ አይታወቅም፣ ሁሌም የስጋትና ፍርሃት ምንጭ ናቸው። በመሆኑም አንዳቸው ለሌላቸው በጥላቻና ጥርጣሬ የተሞላ አመለካከት አላቸው። 

ታጋዮች አመፅና ብጥብጥ በማስነሳት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ፣ በስርዓቱ የተገኘውን ሰላምና ልማት የሚቀለብሱ ስለሚመስላቸው የቄሮዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ጥርጣሬና ስጋት ይፈጥርባቸዋል። በተቃራኒው ቄሮዎች ታጋዮችን የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የብዙሃኑን መብትና ነፃነት የሚነፍጉ ጨቋኞችና ጨካኞች አድርገው ይመለከታሉ። በዚህ ምክንያት ቄሮዎች “ሰላማዊ ሰልፍ” ሲሉ ታጋዮች “አመፅና ብጥብጥ” ይሏቸዋል፣ “ሰላማዊ” ሲሉ ታጋዮች “ፀረ-ሰላም” ይሏቸዋል፣ራሳቸውን “ህዝብ” ሲሉ ታጋዮች “ፀረ-ሕዝብ” ይሏቸዋል። ሁለቱም “ሕገ-መንግስት” እና “የሕግ የበላይነት” ይላሉ። ነገር ግን፣ ስለ አንድ ነገር እየተናገሩ በሃሳብ አልተግባቡም። 

በአጠቃላይ በሁለቱ ትውልዶች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት ሀገሪቱን አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ከትቷታል። በመሰረቱ የቄሮዎች እና ተጋዮች ግጭት አንድን ስርዓት ለማስቀጠል እና ለመቀልበስ የሚደረግ ትግል ነው። ለምሳሌ እንግሊዝ በ1960ዎቹ ተመሳሳይ ፖለቲካዊ ቀውስ አጋጥሟት እንደ በር ”Edmund Leach” እንዲህ ይገልፃል፡-  

“Tension between the generations is normal for any society; every son is a potential usurper of his father‘s throne; every parent feels under threat; but the present anxiety seems altogether out of proportion. Young people are being treated as an alien category: ‘wild beasts with whom we cannot communicate’. They are not just rebels but outright revolutionaries intent on the destruction of everything which the senior generation holds to be sacred. …Let us be clear about this. What is odd is not the behaviour of the young but the reaction of the old. …It is because the old allow themselves to feel separated from the young that the young create anxiety.” REITH LECTURES 1967: A Runaway World – Lecture 3: Ourselves and Others 

ቄሮዎች በአድማ ላይ…

በተለይ ባለፉት ሦስት አመታት በቄሮዎች እና ታጋዮች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ እየሰፋ ሄዶ የትውልድ ግጭት ለመሆን በቅቷል። ከዚህ በኋላ ሁለቱ ትውልዶች እርስ-በእርስ ተነጋግረው መግባባት አይችሉም። ይህ የሆነው ቄሮዎች የሚናገሩትን ሳያውቁ ወይም ታጋዮች ለእነሱ የሚነግሯቸው ነገር ሳይገባቸው ቀርቶ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እንደ ”Edmund Leach” አገላለፅ፣ ቄሮዎች የሚናገሩትን ነገር ታጋዮች የመረዳት ሆነ ምላሽ የመስጠት ብቃትና ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። 

“They [youths} are the involuntary heirs to a generation of incompetents. Their seniors, who still keep all the power in their own hands, have made a total mess of things. …The whole set-up is rigged to fit the belief that, when the young grow up and come to power, they too will carry on running the show just as before. But this assumption makes co-operation impossible. If the old expect the young to participate in planning the future, then they might at least take the trouble to find out what sort of future the young would actually like to have.” REITH LECTURES 1967: A Runaway World – Lecture 3: Ourselves and Others 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የቄሮዎች አመፀኝነት እና ተቃውሞ የተገነባውን የማፍረስ፥ ስርዓቱን የመቀልበስ፣ ሰላምና መረጋጋትን የማደፍረስ አባዜ ስለተጠናወታቸው ሳይሆን የሚገባቸውን በመጠየቅና የማይገባውን ነገር በማስቀረት በወደፊት እድላቸው ላይ የመወሰን ብቃትና መብት ስላላቸው ነው። ታጋዮች የሚወስዷቸው እርምጃዎችና ውሳኔዎች በተደጋጋሚ ትችትና ተቃውሞ የሚያጋጥማቸው ለቄሮዎች ሃሳብና አስተያየት ትኩረት ሳይሰጡ በወደፊት እድላቸው ላይ የራሳቸውን ፍላጎትና አመለካከት ስለሚጭኑ ነው። 

በአጠቃላይ በቄሮዎች እና ታጋዮች መካከል ለተፈጠረው ግጭትና አለመግባባት መሰረታዊው ምክንያት ታጋዮች እንኳን የቄሮዎችን የወደፊት ፍላጎትና ምርጫ ትክክለኛ ማንነታቸውን በአግባቡ አለማወቃቸው ነው። ታጋዮች የቀሮዎችን ሃሳብና አመለካከት በግልፅ አልተረዱም፥ አይረዱም። የቄሮዎችን ጭኸት አይሰሙም፥ አልሰሙም፣ ለጥያቄዎቻቸውን ተገቢ ምላሽ አልሰጡም፥ መስጠት አይችሉም። 

ታጋዮች ከራሳቸው በስተቀር የቄሮዎችን ሃሳብና አስተያየት አልሰሙም፥ አይሰሙም። ቄሮዎች ደግሞ በወደፊት እድላቸው ላይ በራሳቸው መወሰን እስካልቻሉ ድረስ ከታጋዮች ጋር አይስማሙም፥ አይግባቡም። የታጋዮች ሃሳብና አስተያየት በቄሮዎች ዘንድ ተቀባይነት ካላገኘ ሀገሪቱን መግዛትና ማስተዳደር አይችሉም። 

3: በጦርነት ያሸነፈ በጦር አይገዛም!

በስልጣን ላይ ያለ የፖለቲካ ቡድን ምንም ያህል ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥንካሬ ቢኖረው በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ከሌለው ሀገሪቱን መግዛትና ማስተዳደር አይችልም። በእርግጥ ሀገርና ሕዝብን በጦር ኃይል ቁጥጥር ስር ማዋል ይቻል ይሆናል።  ነገር ግን፣ በወታደሮችና በጦር መሳሪያ መግዛትና ማስተዳደደር አይቻልም። 

የፖለቲካ ኃይል ለውጥ ወይም የስልጣን ሽግግር ማለት በራሱ የብዙሃኑ አስተያየትና አመለካከት ለውጥ ነው። የብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ለውጥ በሌለበት የፖለቲካዊ ስርዓት ለውጥ በራሱ ትርጉም አልባ ነው። ምክንያቱም ሀገርና ሕዝብን ለመምራት የሚያስችል ኃይል (ruling power) የሌለው የፖለቲካ ስልጣን ፋይዳ-ቢስ ነው።  

እንደ ናፖሊዮን (Napoleon) ያሉ ጦረኛ መሪዎች እንኳን አንድ ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት የሕዝብን ሃሳብና አስተያየት ይጠይቃሉ። ይህ የፈረንሳይ ንጉስ “ስፔንን በወታደራዊ ወረራ በቁጥጥሩ ስር ካዋላት ብዙ አመታት ቢያልፉም ሀገሪቱን መግዛት ግን አልቻለም ነበር። ስለዚህ በአንድ ወቅት “ስፔንን መቼ ነው የምንገዛት?” ሲል አማካሪውን ይጠይቀዋል። አማካሪውም “በሳንጃ የፈለከውን ማድረግ ትችል ይሆናል ከላዩ ላይ ግን መቀመጥ አትችልም” (You can do everything with bayonets, except sit on them) በማለት እንደመለሰለት ይነገራል።

አንድን ሀገር በጦር ኃይል መቆጣጠር እንጂ ሕዝቡን በጦር ኃይል መግዛትና ማስተዳደር አይቻልም። ምክንያቱም፣ እንደ “Jose Ortega y Gasset” አገላለፅ፣ አንድን ሀገር መግዛት (“rule”) በመሪነት ቦታ ላይ መቀመጥና ህዝብን ከፊት ሆኖ መምራት ይጠይቃል። በዚህ መልኩ የመሪነት ሚናን በአግባቡ ለመወጣት ደግሞ በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት ሊኖር ይገባል። 

የመንግስት ተቀባይነት የሚወሰነው በብዙሃኑ አስተያየት/አመለካከት ነው። ስለዚህ ሀገርን መግዛት የሚችለው በብዙሃኑ አመለካከት (public opinion) ዘንድ ተቀባይነት ሲኖር ነው። ይህንን “Jose Ortega y Gasset” እንደሚከተለው ገልፆታል፡-  

“By “rule” we are not here to understand primarily the exercise of material power, of physical coercion. This stable, normal relation amongst men which is known as “rule” never rests on force.…It is necessary to distinguish between a process of aggression and a state of rule. Rule is the normal exercise of authority, and is always based on public opinion,.. Never has anyone ruled on this earth by basing his rule essentially on any other thing than public opinion…. In Newton’s physics gravitation is the force which produces movement. And the law of public opinion is the universal law of gravitation in political history.” THE REVOLT OF THE MASSES፡ CH.XIV፡ Page 71 – 80  

በአጠቃላይ ታጋዮች ግዜ ያለፈበት የፖለቲካ አቋምና አመለካከታቸው በቄሮዎች ላይ ለመጫን የሚታትሩ ብኩኖች ናቸው። በመሆኑም ከራሳቸው ግትር የፖለቲካ አመለካከት በስተቀር የሌሎችን ሃሳብና አስተያየት ለመቀበል ዝግጁ አይደሉም። የእነሱን ግትር አመለካከት በቄሮዎች ላይ ለመጫን ጥረት ከማድረግ በዘለለ እንደ ቀሮዎች የራሳቸውን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እንዲያራምዱ አይፈቅዱም። 

በዚያው ልክ ቄሮዎች የታጋዮችን ግትር የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በፍፁም አይቀበሉም። ምክንያቱም እንደ ማንኛውም ትውልድ የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ለቀድሞ ትውልድ አሳልፈው መስጠት አይሹም። መቼም፥ እንዴትም ቢሆን የቀድሞ ትውልድ አዲሱን ትውልድ የወደፊት እጣ ፈንታ እንዲወስንለት አይፈቅድም። 

የቄሮዎች የተቃውሞ ምልክት!