​ኦህዴድ እና ብአዴን፡ ህወሓት ቃሊቲ ሊስገባቸው ሲያስብ እነሱ የገቡትን ያስወጡት እንዴት ነው?

ባለፉት ጥቂት አመታት በኦሮሚያ ክልል እና በኦህዴድ ውስጥ የተካሄደው ለውጥ እንቅስቃሴ በዘፈቀደ የመጣ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ በ2005 ዓ.ም አከባቢ በተወሰኑ የኦህዴድ አመራሮች እና የኦሮሞ ልሂቃን ተግባራዊ እቅድ ተዘጋጅቶለት የተጀመረ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው። የኦህዴድ አመራሮች ከውስጥ፣ የኦሮሞ ልሂቃን ደግሞ ከሀገር ወይም ከድርጅቱ ውጪ በመሆን የጀመሩት ንቅናቄ በ2006 ዓ.ም የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም በአምቦና ጊንጪ ከተሞች ተጀመረ። ከዚያ በመቀጠል በ2008 ዓ.ም የአማራ ክልል እና የተወሰኑ የብአዴን መሪዎችን በማሳተፍ ህዝባዊ ንቅናቄው በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲስፋፋ አደረጉ። ከአምስት አመት በኋላ ዛሬ ያለንበት ደረጃ ላይ ደረስን።

የንቅናቄው መሪዎች “የኢትዮጲያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መንግስታዊ ስርዓቱ የህወሓትን የስልጣን የበላይነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የተመሰረተ ከመሆኑ የመነጨ እንደሆነ ፅኑ እምነት አላቸው። በዚህ መሰረት፣ ሀገሪቱ ከገባችበት ግጭትና አለመረጋጋት እንድትወጣ ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚነሱ የዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት እንዲሁም የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ ማግኘት አለባቸው። በዚህ መልኩ የብዙሃኑን መብትና ነፃነት እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው በእኩልነት መርህ የሚመራ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ሲኖር ነው። 

በዚህ መሰረት የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚቻለው የህወሓትን የስልጣን የበላይነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማስወገድ ነው። በሌላ በኩል የኦህዴድ እና ብአዴን ሕልውና የተመሰረተው የሚወክሉትን የህዝብ እያነሳ ላለው የዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ተገቢና ተጨባጭ የሆነ ምላሽ መስጠት ሲችሉ ነው። በኦሮሚያ ከ2005 ዓ.ም፣ በአማራ ደግሞ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደና በፍጥነት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎች እየተስፋፋ ያለው ሕዝባዊ ንቅናቄና ተቃውሞ በሁለቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ላይ የህልውና አደጋ ጋርጧል። 

ቀደም ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የህወሓት አባላት እና አመራሮች ከሦስት አመታት በፊት የተዛባ አመለካከት እና የፈጠራ ወሬ ሲሉት እንዳልነበር ዛሬ ላይ “የህወሓት የበላይነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት” መኖሩን አምነው ተቀብለዋል። ሕዝባዊ ንቅናቄው የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል እንደመሆኑ ብዛት ያላቸው የኦሮሞ ልሂቃን የሕዝቡን የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ። የሕዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ያላቸው የኦህዴድ አባላት ወደ አመራርነት መጥተዋል። 

በአማራ ክልል ሕዝባዊ ንቅናቄው ዘግይቶ የተጀመረ ቢሆንም ባለፉት ሦስት አመታት ውስጥ ብቻ ብዛት ያላቸው የአማራ ልሂቃን የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ማስተጋባት ጀምረዋል። የክልሉ ሕዝብ ለሚነሳው የእኩልነት እና ተጠቃሚነት ጥያቄ የድጋፍ አዝማሚያ ያላቸው የብአዴን አመራሮች በድርጅቱ ውስጥ የበላይነት እየያዙ መጥተዋል። በእርግጥ የብአዴን አመራር ልክ እንደ ኦህዴዶች የአመራርነት ሚናውን ሙሉ በሙሉ አልተቆጣጠሩም። ነገር ግን፣ በክልሉ ፕረዜዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና በኮሚዩኒኬሽን ፅ/ቤት ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ላይ ከሚያካሂዱት የውሸት ፕሮፓጋንዳ እና የስም ማጥፋት ዘመቻ የትኛው ቡድን ብአዴን ውስጥ የበላይነት እያገኘ እንደመጣ ይጠቁማል። 

ባለፉት ጥቂት አመታት የታየው ሕዝባዊ አመጽና ተቃውሞ ኦህዴድ እና ብአዴንን “የመኖር ወይም የመጥፋት” አማራጭ ውስጥ ከትቷዋል። በዚህ መሰረት፣ ዛሬ ላይ ኦህዴድ እና ብአዴን ያላቸው ብቸኛ አማራጭ “የሚወክሉት ሕዝብ ለሚያነሳቸው የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ በመስጠት መኖር” ወይም “የህወሓት የበላይነት እና ተጠቃሚነት እንዲቀጥል በመፍቀድ ከህወሓቶች ጋራ አብሮ መጥፋት” ናቸው። ከሁለቱ አማራጮች ሌላ ሦስተኛ አማራጭ የለም። ምክንያቱም የህወሓት የበላይነት እና ተጠቃሚነት እስካለ ድረስ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አይረጋገጥም። 

በሌላ በኩል የሁለቱ ሕዝቦች እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከተረጋገጠ የህወሓቶች የበላይነት እና ተጠቃሚነት ያከትማል።   የህወሓትን የበላይነት እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማስቀጠል የሚሹ አመራሮችና ልሂቃን ያላቸው አማራጭ መንግስታዊ ስርዓቱን ማስቀጠል ወይም ማፍረስ ነው። በዚህ መሰረት ቀንደኛ የህወሓት አመራሮችና ደጋፊዎች መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስቀጠል የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ለሚያነሱት ጥያቄ የድጋፍ አዝማሚያ ያላቸውን የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን መወገድ እንዳለባቸው በይፋ አሳውቀዋል። በዚህ ረገድ ጥቅምት 21/2010 ዓ.ም አንድ የህወሓት ክፍተኛ አመራር “የኢህአዴግ የመፍረስ አደጋና የኢትዮጲያ ቀጣይ እጣ ፋንታ” በሚል ርዕስ ባወጡት ፅሁፍ የህወሓትን አቋም እንደሚከተለው ገልፀዋል፡-  

 “… ኢህአዴግ ለህዝቡና ለዓላማው የሚቆረቆር ከሆነ ለግለ-ሰዎች ዝና መበገር የለበትም። ህዝበኞች እንደሆነ የአንድ ሳምንት አጀንዳ ከመሆን አያልፉም፡፡ ስለሆነም በተጨባጭ መረጃ የተገኘባቸው በቀጥታ ወደ ቃሊቲ እንዲወርዱ ማድረግ የተለያየ የፖለቲካ ሴራ የፈፀሙ ግን ደግሞ ተጨባጭ መረጃ ከሌለ መረጃ እስከሚመጣ መጠበቅ ሳይሆን ፖለቲካዊ እርምጃ መውሰድ፡፡ ሂደቱ እንደተለመደው ላይ ላላ ብሎ ታች መጠንከር ሳይሆን ድርጅቱ እንደ አሳ ከጭንቅላቱ እየሸተተ ስለሆነ ከበላይ አመራር መጀመር አለበት፡፡ ከበላይ አመራር የሚጀመረው አበል መጨመር ብቻ ሳይሆን ቅጣትም ከበላይ አመራር መጀመር አለበት፡፡ ይሄ ተጠናክሮ በሚሄድበት ይህን ስርዓት ማስቀጠል የሚፈልግ ህዝብና አገር ወዳድ በርካታ ስለሆነ ከነዚህ ሆዳሞችና ከሃዲዎች በኋላ የሚፈጠር ስጋት አይኖርም።” 

ከላይ በፅሁፉ በተገለፀው መሰረት የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን ወደ ቃሊቲ እስር ከማውረድ ይልቅ በቃሊቲና ሌሎች እስር ቤቶች የሚገኙ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው ይታወሳል። በዚህ መሰረት፣ የህወሓት በኦህዴድና ብአዴን ጥምረት መሸነፉን መረዳት ይቻላል። ሆኖም ግን፣ ሰሞኑን የታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ጨምሮ ህወሓት የሚከተለው አቅጣጫ ከላይ በተጠቀሰው ፅሁፍ በተገለፀው መሰረት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። ስለዚህ የድርጅቱ አመራሮችና ልሂቃን የህወሓትን የበላይነትና ተጠቃሚነት ከማስቀጠል በዘለለ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዲካሄድ አይፈልጉም። 

የአማራ ክልል ፕረዜዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የኦሮሚያ ክልል ፕረዜዳንት ኦቦ ለማ መገርሳ

በተቃራኒው ኦህዴድና ብአዴን ሰሞኑን ያካሄዱትን ስብሰባ ተከትሎ ባወጡት ድርጅታዊ መግለጫ መሰረት፣ መንግስታዊ ስርዓቱን ለመታደግ ፍትሃዊ የስልጣንና የሃብት ክፍፍል ሊኖር እንደሚገባ በግልፅ አስቀምጠዋል። የኦህዴድና ብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ በየፊናቸው ባወጡት ድርጅታዊ መግለጫ መሰረት ህወሓት በመንግስታዊ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን የበላይነት እና ተጠቃሚነት ለመጋፈጥ መወሰናቸውን እንደሚከተለው ገልፀዋል፡-   
ከኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ፡- 

“የፌዴራላዊ ስርዓታችንን አደጋ ላይ የጣሉ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን፣ ሕዝቡ በመሪ ድርጅቱ ላይ እንዲያምጽ ያስቻሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን፤ ስልጣን ህዝብን ማገልገያ መሳሪያ መሆኑን በመዘንጋት በርስትነት ይዞ ለግል ምቾትና ጥቅም ቅድሚያ መስጠትን፣ በነጻነት ተዘዋውሮ የመስራት መብትን ነፍጎ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን እስከማፈናቀል የደረሰ ድርጊትን፤ በኢንቨስትመንት ስም የመንግስትና የህዝብ መሬት መመዝበሩን፤ እንዲሁም የሕዝቦች ሰላምና ጸጥታ መደፍረሱን እና የመሳሰሉትን እየተፈጸሙ ያሉ አደገኛ ድርጊቶችን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ አምርሮ በመታገል የሀገራችንን ሕልውና መታደግ ልዩ ትኩረት የሚሹ አበይት ጉዳዮች መሆናቸውን በዝርዝር ተመክሮባቸዋል፡፡” ከኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ፥ ጥር 29/2010 ዓ.ም 

የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ የሰጠው ድርጅታዊ መግለጫ፡- 

 “የፌደራል ስርዓታችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ እና የህዝባችንን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚጐዱ ማናቸውንም ዝንባሌዎችና ተግባራት ያለምንም ማመንታት መታገል እንደሚገባ አፅንኦት ሠጥቶ ተወያይቷል፡፡ በፌደራል ስርዓታችን  ውስጥ የፍትሃዊነት መጓደል የሚታይባቸውን ማናቸውም ዘርፎች የማስተካከል ስራ እንዲሠራና ለወደፊቱም ጥርጣሬ የሚያነግሱ መሰል ተግባራት  እንዲታረሙ ተገቢ ትግል እንዲደረግ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡ የፌደራል ተቋማት የሰው ሃይል አደረጃጀት ብቃትንና ብሄራዊ ተዋጽኦን ማእከል በማድረግ እንዲደራጅ እና የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ተቋማቱን ሪፎርም የማድረግ ስራ እንዲሰራም የበኩሉን ሚና መጫወት እንደሚገባው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡” የብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ፥ ባህር ዳር፡ የካቲት 16/2010 ዓ/ም 

ሆኖም ግን፣ እንደ አቶ አባይ ፀሃየ ያሉ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የህወሓትን የበላይነት እና ተጠቃሚነት የሚጋፋ ማንኛውም ዓይነት ለውጥን ለመቀበል ፋቃደኛ አለመሆናቸውን ገልፀዋል። አቶ አባይ ፀሃየ ወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታን ኣስመልክተው በትግሪኛ በሰጡት አስተያየት “ቁጥር የሚጠቅመው ለፖለቲካ ሳይሆን አራቱን የሂሳብ ስሌቶች ለመለማመድ ነው” ማለታቸው ተገልጿል። በዚህ መሰረት አብላጫ ድምፅ ያላቸው የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቀዋል። በሌላ በኩል የኦህዴድና ብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የክልላቸውን ሕዝብ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ምርጫና አማራጭ የሌለው የህልውና ጉዳይ መሆኑን በይፋ አስታውቀዋል። “በሁለቱ የለውጥ እና ፀረ-ለውጥ ኃይሎች መካከል ያለው ፍጥጫ ሀገራችንን ወዴየት ይወስዳት ይሆን?” የሚለው በቀጣይ ክፍል እንመለከታለን።      

One thought on “​ኦህዴድ እና ብአዴን፡ ህወሓት ቃሊቲ ሊስገባቸው ሲያስብ እነሱ የገቡትን ያስወጡት እንዴት ነው?

  1. As usual great analysis, Seyoum . I think ANDM and OPDO should approach the international community regarding the formation of a coalition party that can take power from EPRDF. If they get support from the international community they will be the rightful leaders, and can size power legally and peacefully. If TPLF tries to undermine that government it won’t be recognized by the international community including the OAU as a legal government. ANDM and OPDO can form the government, and immediately ask UN for a peace-keeping force to maintain law and order until a smooth transition is ascertained.

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡