​ለህወሓት ለውጥ እና ሞት አንድ ናቸው! ቀድሞ መጥፋት ወይስ ማጥፋት…? 

ትላንት ባወጣኋቸው ሁለት ተከታታይ ፅሁፎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የህወሓት የበላይነት መኖሩን አምነው መቀበላቸውን፣  በተለይ የኦህዴድና ብአዴን ማዕከላዊ ኮሜቴዎች በየፊናቸው ባወጡት የአቋም መግለጫ የህወሓትን የበላይነት ለመታገል መወሰናቸውን ተመልክተናል። ነገር ግን፣ እንደ አባይ ፀሃየ ያሉ የህወሓት ነባር አመራሮች የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በኦህዴድ እና ብአዴን በኩል የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል። በወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ በሰጡት አስተያየት አቶ አባይ ፀሃየ የሚከተለውን ብለዋል፡- 

“ፌዴራል ፕሮጀክቶች በክልል ህዝብ ብዛትና የመሬት ስፋት ይለካ የሚለው በአማራና ኦሮሞ የጋራ መድረኮች ላይ የተነሱት ጉዳዪች የብአዴንና ኦህዴድ አመራር አባላትንም ያካተተ አስተሳሰብ ስለሆነ፣ እንዲህ አይነት አመለካከት ይዘው ‘አንድ ድርጅት ነን፥ ደህና ነን እያልን’ አብረን መቀጠል አንችልም። ይህ አስተሳሰብ በተግባር ከሚውል ኢህአዴግን መቅበር ይቀላል።”

ከዚህ በተጨማሪ፣ አቶ አባይ “ቁጥር የሚጠቅመው ለፖለቲካ ሳይሆን አራቱን የሂሳብ ስሌቶች ለመለማመድ ነው” በማለት የኦህዴዶች እና ብአዴኖችን አቋም አጣጥለዋል። ከአስር አመት በፊት በተካሄደው ሀገር አቀፍ የህዝብና ቤት ቆጠራ መሰረት የአማራና ኦሮሞ ሕዝብ በድምሩ ከኢትዮጲያ ጠቅላላ የሕዝብ ብዛት ውስጥ ስልሳ ፐርሰንቱን (60%) ይሸፍል። በዚህ መሰረት፣ ከሀገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ ውስጥ አብላጫ ድምፅ ያላቸውን የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገው እንቅስቃሴ ኢህአዴግን ሊያፈርሰው እንደሚችል አቶ አባይ ጠቁመዋል። 

ሆኖም ግን፣ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና የህዝባችንን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚጐዱ ማናቸውንም ዝንባሌዎችና ተግባራት ያለምንም ማመንታት ለመታገል መወሰኑን ገልጿል። የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ቀደም ብሎ ባወጣው ድርጅታዊ መግለጫ መንግስታዊ ስርዓቱን እና የክልሉን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት የሚጎዱ ድርጊቶችን ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ አምርሮ በመታገል የሀገሪቱን ሕልውና ለመታደግ መወሰኑን አሳውቋል። ከዚህ በተቃራኒ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦችን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ከኢህአዴግ በተጨማሪ ኢትዮጲያንም ሊያፈርስ እንደሚችል አቶ አባይ ፀሃየ ጠቁመዋል፡- 

“ኢትዮጵያ ዉስጥ ከእንግዲህ የኣንድ ብሄር የበላይነት ኣክትሞለታል። የኣማራ ትምክህት በሃይል እገዛለሁ ቢል፣ የኦሮሞ ጠባብ በሃይል እገዛለሁ ቢል… በፍጹም ተፈጻሚነት የለውም፡፡ …ኣንድ ኣድርጌ ጨፍልቄ እገዛለሁ የሚል ህልመኛ ቢመጣ እስከ ሞት እንዋጋዋለን እንጂ ኣይታሰብም። ቁርጡን ይወቅ:: ግፋ ቢል ሃገሪቱ ወደ መበታተን ያደርሳት እንደሆነ እንጂ ኢትዮጵያ ዳግም የገዢዎች መፈንጫ ልትሆን ኣትችልም። መገነጣጠል ድግሞ ኣማራጭ ሊሆን ኣይችልም፣ ተያይዘን መጥፋት ነው የሚሆነው።” 

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ፍጥጫ እየከረረ መጥቷል። በኦህዴድ እና ብአዴን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ዓላማ የሚወክሉትን ሕዝብ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። የሕዝቦችን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ በሌሎች ሕዝቦች መብት እና ተጠቃሚነት ላይ የሚያስከትለው ጉዳት የለም። “እኩልነት” በዜጎች መካከል ያለው ልዩነት ያጠብባል እንጂ አያሰፋም። “ፍትሃዊ ተጠቃሚነት” ደግሞ አድሏዊ አሰራርና ያልተገባ ጥቅምን ያስቀራል። 

በዚህ መሰረት፣ በኦህዴድ እና ብአዴን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በትግራይ ክልል እና ሕዝብ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ የለም። ከዚያ ይልቅ፣ ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተስፋፋ የመጣውን አለመግባባትና ያለመተማመን ስሜት፣ እንዲሁም ግጭት እና ጥቃቶች ያስቀራል። የኦሮሞና አማራ ሕዝብ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ቢረጋገጥ የትግራይ ሕዝብ ከሁለቱ ሕዝቦች ጋር ያለው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ይሻሻላል። በዚህም የትግራይ ክልል ተወላጆች በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች በነፃነት መንቀሳቀስ እና መስራት ይችላሉ። 

ነገር ግን፣ በኦህዴድ እና ብአዴን የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በህወሓት ላይ ቀጥተኛ የሕልውና አደጋ ጋርጧል። የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ተጎጂ የሚሆኑት የህወሓት አባላት እና ደጋፊ ልሂቃኖች ናቸው። ምክንያቱም የህወሓት አባላትና ደጋፊ ልሂቃን ከድርጅቱ ጋር ባላቸው አድሏዊ ግንኙነት የማይገባቸውን የመወሰን ስልጣን እና የኢኮኖሚ ሃብት አካብተዋል። በመሆኑም የኦሮሞ እና አማራ ሕዝብ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ተረጋገጠ ማለት እነዚህ ልሂቃን፤ አንደኛ፡- እስካሁን የያዙትን ያልተገባ ስልጣን ያጣሉ፣ ሁለተኛ፡- በኢኮኖሚው ውስጥ የነበራቸው ኪራይ ሰብሳቢነት እና የሚያገኙት ያልተገባ ጥቅም ይቋረጣል። ህወሓት በመንግስታዊ ስርዓቱ ውስጥ ያለው የስልጣን የበላይነት እና ኢ-ፍትሃዊ የጥቅም ግንኙነት ከተቋረጠ እንኳን ሀገርና ሕዝብን ራሱን ማስተዳደር ይሳነዋል። ስለዚህ  የኦሮሞና አማራ ሕዝብ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ የህወሓት ሕልውና ያከትማል። 

አቶ አባይ ፀሃየ

የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ መንግስታዊ ስርዓት በምንም አግባብ ቢሆን የብዙሃኑን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት አያረጋግጥም። የአንድ ወገን የበላይነት እና የብዙሃኑ እኩልነት፣ የአንድ ወገን ተጠቃሚነት እና የብዙሃኑ ተጠቃሚነት ፍፁም ተቃራኒ ናቸው። የአንዱ መኖር ሌላውን ያጠፋዋል፣ የሌላው መጥፋት አንዱን ያኖረዋል። 
መንግስታዊ ስርዓቱ የብዙሃኑን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲያረጋግጥ ከተፈለገ የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን ማስወገድ የግድ ያስፈልጋል። የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን ማስቀጠል ከተፈለገ ደግሞ የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄን በኃይል ማፈንና ማስወገድ ያስፈልጋል። ይህን መርህ “Aristotle” እንደሚከተለው ገልፆታል፡- 

“…it is evident that if we know the causes which destroy constitution, we also know the causes which preserve them; for opposites produce opposites, and destruction is the opposite of preservation.” Aristotle, Politics (Politika), Tran. by Jowett, B. Book-5, Part–8, Para-1  

ከላይ በተገለፀው መሰረት፣ ሁለቱም ወገኖች ሕልውናቸውን ለማረጋገጥ የሚወስዱት የለውጥ እርምጃ ሌላኛውን ወገን ሕልውናው እንዲያከትም ያደርገዋል። የኦህዴድ እና ብአዴን አመራሮች “የፌዴራል ፕሮጀክቶች በክልል ህዝብ ብዛትና የመሬት ስፋትን መሰረት ያደረጉ ይሁኑ” ማለታቸው ኢህአዴግን የሚያፈርሰው ከሆነ ድርጅቱ የተቋቋመበት መሰረታዊ ዓላማ የህወሓቶችን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ለማስፈፀም እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል። 

መንግስታዊ ስርዓቱ የተዘረጋው በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ ነው። “መንግስታዊ ስርዓቱ ከሚቀየር ሞቴን እመርጣለሁ” ማለት ምንም ነገር የህወሓት አይበልጥም እንደማለት ነው። እንደ አቶ አባይ ፀሃየ ያሉ የህወሓት አባላትና አመራሮች ከኢህአዴግ ፓርቲ፣ ከኢትዮጲያ አንድነት እና ከህዝብ ሰላምና ደህንነት በፊት ቅድሚያ የሚሰጡት ለህወሓትና ለህወሓት ነው። 

በአጠቃላይ ችግሩ በድርጅታዊ ግምገማ፣ በማስጠንቀቂያ ወይም በማስተካከያ እርምጃ የሚፈታ አይደለም። ምክንያቱም ይሄ የተሃድሶ ወይም የለውጥ ጉዳይ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የመኖር ወይም የመጥፋት ጉዳይ ነው። እንደ ህወሓት ላለ “ቆሞ-ቀር” የፖለቲካ ቡድን ለውጥ እና ሞት አንድ ናቸው። ስለዚህ ኦህዴድና ብአዴን የጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴ መጨረሻው ወይ “ህወሓትን ማጥፋት” ወይም “በህወሓት መጥፋት” ይሆናል። አሁን ላይ ጨዋታው “ጅብ ከሚበላኝ ጅብ በልቼ ልጠመቅ” የሚሉት ነው።     

በቀጣይ ክፍል ኦህዴድ እና ብአዴን የሚወክሉትን ሕዝብ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ሕልውናቸውን ለማስቀጠል፣ ህወሓት ደግሞ በፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን የበላይነት በማስቀጠል ሕልውናውን ለመታደግ የሚከተሏቸውን የፖለቲካ ስልቶች በዝርዝር እንመለከታለን።

3 thoughts on “​ለህወሓት ለውጥ እና ሞት አንድ ናቸው! ቀድሞ መጥፋት ወይስ ማጥፋት…? 

  1. አንዱ ትልቁ ስራ ህወሓትን የበላይነት ትቅም ሳይሆን ጉዳት እንደሆነ ማሳመን ነው። በዛሬው የኢትዮጵያ ፖለቲካ የጎሳ የበላይነት ለሁሉም ከበላይም ለሆነ ከባድ ጉዳትና አደገ ነው። ጎሰኝነትም የበላይነትም ከፖለቲካ ምድሩ በቀነሱ ቁጥር ለሁሉም ይበጃል። ውይይቱ ይህን ነው መምሰል ያለበት የነ ለማ መገርሳንም አቋም ሳዳምጥ ይህ የገባቸው ይመስላል።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡