መለያየት እና ፍርሃት የህወሓት መርህ እና መመሪያ ናቸው!

እንደ ፖለቲካዊ እንስሳ “እኩልነት” (equality) የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። በየትኛውም ሰርዓተ ማህበር ውስጥ ቢሆን ሁሉም ሰው በእኩል ዓይን መታየት ይፈልጋል። እያንዳንዱ ሰው ከሌሎች እኩል መብቱ እና ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ ይሻል። ስለዚህ በአንድ ፖለቲካዊ ስርዓት ስር ያሉ ሰዎች እኩል መብትና ተጠቃሚነት ይገባቸዋል። እያንዳንዱ ግለሰብ “ከሌሎች ሰዎች እኩል መብትና ነፃነት፣ ጥቅምና ተጠቃሚነት ይገባኛል” ብሎ ያምናል። የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍል፥ ቡድን ወይም ግለሰቦች ከሌሎች የተሻለ መብትና ነፃነት፣ የበለጠ ጥቅምና ተጠቃሚነት ካላቸው የተቀረው የሕብረተሰብ ክፍል የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄ ያነሳል። በዚህ መሰረት፣ የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነት ባለበት ቦታና ግዜ ሁሉ ዜጎች የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄ ያነሳሉ። 
በመሰረቱ ከሀገሪቱ ሕዝብ ውስጥ የተወሰነ የሕብረተሰብ ክፍልን የስልጣን በላይነት እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዊ ስርዓት ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የሚያነሳውን የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በአግባቡ ተቀብሎ ማስተናገድ አይችልም። ምክንያቱም የብዙሃኑን እኩልነት ጥያቄ ተቀብሎ ምላሽ ከሰጠ የአንድ ወገን የበላይነትን ማስቀጠል አይችልም። የብዙሃኑን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ካረጋገጠ ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ እያገኘ ያለው ያልተገባ ጥቅምና ተጠቃሚነት ይቋረጣል። ስለዚህ የስልጣን የበላይነቱን እና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ለማስቀጠል ከብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄ መነሳት የለበትም። 

ሆኖም ግን፣ የብዙሃን ዴሞክራሲያዊ መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ ዜጎች የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄ ከማንሳት ወደኋላ አይሉም። የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ፖለቲካዊ ስርዓት ባለበት ሀገር ዜጎች የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄ የማያነሱት መንግሱት መንግስት በፍርሃት (fear) መርህ የሚመራ ከሆነ ብቻ ነው። ስለ መንግስታዊ ስርዓት አወቃቀር እና መለያ ባህሪያት ጥልቅ ትንታኔ በመስጠት የሚታወቀው ፈረንሳዊው ፈላስፋ “Baron de Montesquieu” እያንዳንዱ መንግስታዊ ስርዓት የራሱ የሆነ የተግባር መርህና መመሪያ እንዳለው ይገልፃል። እንደ እሱ አገላለፅ፣ “እኩልነት” የዴሞክራሲያዊ መንግስት የተግባር መርህ ሲሆን “ፍርሃት” ደግሞ የጨቋኝና አምባገነናዊ መንግስት መርህ ነው። (In a republic the principle of action is virtue (love of equality); and in a tyranny, the principle of action is fear) 

በዚህ መሰረት፣ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ መንግስት ያለማቋረጥ የብዙሃኑን እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት ያደርጋል። በተቃራኒው በአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጨቋኝና አምባገነን መንግስት ላይ በሀገሪቱና ሕዝቡ ላይ የፍርሃት ድባብ (climate of fear) ለማስፈን ጥረት ያደርጋል። ነገር ግን፣ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ እንዴት የፍርሃት ድባብ መፍጠር ይቻላል? 

በመሰረቱ ጨቋኝና አምባገነን መንግስት የፍርሃት ድባብ የሚፈጥረው የሀገሪቱን ሕዝብ በመለያየት ነው። ሕዝብን ለመለያየት በዜጎች መካከል ልዩነትን መፍጠርና ማስረፅ ያስፈልጋል። ስለዚህ የሀገሪቱን ሕዝብ በጎሳ፥ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ሃይማኖት፥ ስነ-ልቦና፥ ታሪክ፥…ወዘተ መከፋፈል አለበት። በማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ረገድ ያሉትን ልዩነቶች ይበልጥ ያሰፋል፥ ያስፋፋል። የተዛቡ ማህበራዊ ግንኙነቶች፣ አስከፊ የታሪክ አጋጣሚዎችን ይበልጥ በማጉላት በማህብረሰቡ ዘንድ ቂምና ጥላቻን ያዳብራል። በዚህ መልኩ ሕዝብን በመለያየት በግለሰብ፥ ቡድን እና ማህብረሰብ ደረጃ ያለመተማመን እና ጥርጣሬ መንፈስ ይፈጥራል። 

ነገር ግን፣ ነፃ የሆነ የሃሳብና መረጃ ልውውጥ ካለ ያለመተማመንና ጥርጣሬው ቀጣይነት ሊኖረው አይችልም። ከዚህ በተጨማሪ፣ያለመተማመንና ጥርጣሬ መንፈሱ ቀጥይነት ቢኖረው እንኳን የሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነት እስካለ ድረስ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የፍርሃት ድባብ የመፍጠር እድሉ አነስተኛ ነው። በዚህ መሰረት፣ በብዙሃኑ የሀገሪቱ ሕዝብ ላይ የፍርሃት ድባብ ለማስፈን፤ አንደኛ፡- በዜጎች መካከል ያለውን ነፃ የሆነ የሃሳብና መረጃ ልውውጥ መገደብ ወይም ማቋረጥ ያስፈልጋል፣ ሁለተኛ፡- ነፃ የሃሳብና አመለካከት ነፃነት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ዋስትና እንዳይኖረው ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ መሰረት፣ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ላይ የፍርሃት ለመፍጠር በሕገ መንግስቱ የተደነገጉ፤ የአመለካከት እና ሃሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት፣ የመሰብሰብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመደራጀት መብት፣ ፍትህ የማግኘት መብት እና የመሳሰሉትን ዴሞክራሲያዊ መብቶች መገደብ ወይም መጣስ ያስፈልጋል። 

ቀደም ሲል በተገለፀው መሰረት፣ መንግስት በዜጎች መካከል ያለውን የዘር፥ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ሃይማኖት፥ ስነ-ልቦና፥ ታሪክ፥…ወዘተ ልዩነት ይበልጥ ለማስፋት ጥረት ያደርጋል። በታሪክ የነበሩ የተዛቡ ግንኙነቶችን እና መጥፎ የታሪክ አጋጣሚዎች በማጉላት በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች መካከል ቂምና ጥላቻ እንዲሰርፅ ያደርጋል። በሌላ በኩል በዜጎች መካከል ምንም ዓይነት የሃሳብና መረጃ ልውውጥ እንዳይኖር የሃሳብና አመለካከትን የመግለፅ፣ እንዲሁም የመሰብሰብና የመደራጀት መብትን ይገድባል፥ ይጥሳል። ለዚህ ደግሞ ሕገ መንግስቱን የሚጥሱ የሕግ አዋጆች፥ ደንቦችና መመሪያዎችን ያወጣል፣ አሰራሮችን ይዘረጋል፣ ውሳኔዎችን ያሳልፋል። በሌላ በኩል ከመንግስት የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸውን ዜጎች “ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን በኃይል ለመናድ አሲረዋል፥ አቅደዋል፥ ተንቀሳቅሰዋል፥ ከአሸባሪዎች ተገናኝተዋል፥…ወዘተ” በሚል ሰበብ ለእስር፥ ስደት፥ እንግልት፥ ሞትና የአካል ጉዳት ይዳርጋል። 

ጋዜጠኞች፥ ምሁራን፥ የመብት ተሟጋቾች፣ የሲቭል ማህበራት፥ የፖለቲካ እና የሃይማኖት መሪዎች ይታሰራሉ፥ ይሰቃያሉ፥ ይሰደዳሉ። በዚህ ምክንያት ነፃና ገለልተኛ ሚዲያዎች፥ የሲቪል ማህበራት፥ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት ይፈርሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ፣ የምርጫ ቦርድ፥ የፀረ-ሙስና፥ የእምባ ጠባቂ፥ ሰብዓዊ መብት እና የመሳሰሉት ተቋማት ከመንግስት ተፅዕኖ ገለልተኛ መሆን ይሳናቸዋል። የሕግ የበላይነት እና ተጠያቂነት በሌለበት ሁኔታ የዜጎች ፍትህ የማግኘት መብት ሙሉ በሙሉ ይጣሳል። 

የተለየ የፖለቲካ አቋም እና አመለካከት ለእስራት፥ ቅጣትና ስደት የሚዳርግ ከሆነ፣ እንዲሁም በዚህ መልኩ ለሚደርሰው በደልና ጭቆና ፍትህ የማግኘት መብት ከሌለ ዜጎች ሃሳብና አስተያየታቸውን ለመግለፅ፣ እርስ በእርስ መነጋገር ይፈራሉ። ዜጎች እርስ-በእርስ የማይነጋገሩ ከሆነ አይግባቡም፣ ዜጎች እርስ-በእርስ የማይግባቡ ከሆነ አይተማመኑም፣ ዜጎች እርስ-በእርስ የማይተማመኑ ከሆነ ይፈራራሉ፣ ዜጎች እርስ-በእርስ የሚፈራሩ ከሆነ በመላ ሀገሪቱ የፍርሃት ድባብ ይሰፍናል። 

በዚህ መሰረት፣ የሀገሪቱን ሕዝብ በዘር፥ ብሔር፥ ቋንቋ፥ ባህል፥ ልማድ፥ ሃይማኖት፥ ስነ-ልቦና፥ ታሪክ፥…ወዘተ የመለያየቱ ፋይዳ በዜጎች መካከል ያለመተማመን እና ጥርጣሬ መንፈስ በመፍጠር የፍርሃት ድባብ ለማስፈን ነው። በፍርሃት ቆፈን በተያዘ ማህብረሰብ ውስጥ ነፃ ውይይትና መረጃ በሹክሹክታና አሉባልታ ይተካል። ተግባራዊ እንቅስቃሴያችን በዕውቀት ሳይሆን በፍርሃትና ስጋት ይመራል። በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ዜጎች የመብትና ነፃነት ጥያቄዎች አያነሱም። በመንግስታዊ ሥርዓቱ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን በጋራ አይንቀሳቀሱም። በዚህ መልኩ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የእኩልነት እና ፍትህ ጥያቄ የማያነሳ ከሆነ መንግስት የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን ማስቀጠል ይቻላል። 

የአንድ ወገን የበላይነት (The Class Domination Theory of Power) የሚረጋገጠው ሁሉንም ነገር በመቆጣጠር ሳይሆን ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ቡድኖች የሚተዳደሩበትን ደንብና ስርዓት በመወሰን ነው። ይህንን “Vergara L.G.” (2013) የዘርፉ ምሁር ፅንሰ-ሃሳቡን “Domination by the few does not mean complete control, but rather the ability to set the terms under which other groups and classes must operate” በማለት ይገልፀዋል። ነገር ግን፣ የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በፍርሃት ነው። ስለዚህ የፍርሃት ድባብ ለመፍጠር ዜጎችን መለየትና መለያየት ያስፈልጋል። የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ቡድኖች የሚተዳደሩበት ደንብና ስርዓት በልዩነትና መለያየት ላይ የተመሰረተ ሊሆን ይገባል። ደንብና ስርዓቱ ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎችን በፍርሃት ቆፈን ለማስያዝ ያገለግላል። ብዙሃኑ በፍርሃት ቆፈን ሲያዝ የአንድ ወገን የበላይነት እና ተጠቃሚነትን ማስቀጠል ይቻላል። 

በዚህ መሰረት፣ የኢፊዲሪ ሕገ መንግስት በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተ ሲሆን ከህወሓት በስተቀር ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች እና ቡድኖች የሚተዳደሩበት ነው። በመሆኑም፣ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱ፤ አንደኛ፡- በመለያየትና ፍርሃት መርህ ላይ የተመሰረተ ነው፣ ሁለተኛ፡- መሰረታዊ ፋይዳው የህወሓትን የበላይነት እና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ስለዚህ “የሕግ-የበላይነትን ማስከበር” ማለት “የህወሓት የበላይነትን ማስከበር” ከሚለው ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። በተመሳሳይ “ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱ አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ” ማለት “የህወሓት የበላይነት እና ተጠቃሚነትን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ” እንደማለት ነው። ሕገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የሚወጡ የሕግ አዋጆች፤ ደንቦችና መመሪያዎች፣ የመንግስት ተቋማት፥ አሰራርና ውሳኔዎች፣ የመንግስት የሆነ ሁሉም ነገሮች የህወሓትን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በአጠቃላይ የህወሓት የፖለቲካ መርህና መመሪያ፣ ሃሳብና እንቅስቃሴ፣ አቋምና አመለካከት፣ ሥራና አሰራር፣ … በሙሉ በመለያት እና ፍርሃት ላይ የተመሰረተ ነው። በአጠቃላይ መለያየት እና ፍርሃት የህወሓት መርህ እና መመሪያ ናቸው። 

One thought on “መለያየት እና ፍርሃት የህወሓት መርህ እና መመሪያ ናቸው!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡