ጥያቄው፦ “ዶ/ር አብይ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ያስችላል ወይ?” ነው! 

ከእስር ቤት ከወጣሁበት ዕለት ጀምሮ የተለያዩ ሰዎች በተደጋጋሚ የቀረቡልኝ ጥያቄ <<ጠ/ሚ አብይ ህዝቡ የሚጠይቀውን ለውጥ ያመጣሉ ብለህ ታስባለህ?>> የሚለው ነው፡፡ እኔም ለጥያቄው የምሰጠው ምላሽ <<ምን ዓይነት ለውጥ እንዲመጣ ትጠብቃለህ?>> የሚል ጥያቄ ነው፡፡ አሁን ካለው የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ አንፃር በጣም አንገብጋቢው ጥያቄ “ዶ/ር አብይ ለውጥ ያመጣል ወይስ አያመጣም?” የሚለው አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ “የምንፈልገው ለውጥ ምንድን ነው?” የሚለው ነው፡፡ ዛሬ ላይ “ዶ/ር አብይ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ወይስ አያመጣም?” ብሎ ለመገመት፣ ነገ ላይ “የሚፈለገውን ለውጥ አምጥቷል ወይም አላመጣም” ብሎ ለማለት በቅድሚያ የምንፈልገውን “ለውጥ” ምንነት በግልፅ ማወቅና መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ምን ዓይነት ለውጥ ነው የምንፈልገው?

በእርግጥ እያንዳንዳችን የራሳችን ፍላጎትና አመለካከት አለን፡፡ በመሆኑም የእያንዳንዳችን የለውጥ ፍላጎት የተለያየ ነው፡፡ በዚያው ልክ ዛሬ ላይ “ዶ/ር አብይ ለውጥ ያመጣል ወይስ አያመጣም?” በሚለው ዙሪያ የተለያየ አቋምና አመለካከት አለን፡፡ በተመሣሣይ ነገ ላይ “ዶ/ር የሚፈለገውን ለውጥ አምጥቷል ወይስ አላመጣም” በሚለው ላይ የተለያየ አቋም ይኖረናል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም ያለን የለውጥ ፍላጎት የተለያየ እንደመሆኑ ዛሬ “ዶ/ር አብይ ምን ዓይነት ለውጥ ማምጣት አለበት?” እና “የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ወይስ አያመጣም?” በሚለው ላይ የጋራ አቋምና አመለካከት ላይኖረን ይችላል፡፡ ነገር ግን፣ በዚህ የፍላጎትና አመለካከት ልዩነት ውስጥ አንድነት አለ፡፡

ሁላችንም የራሳችን የሆነ የለውጥ ፍላጎትና አመለካከት ያለን ሲሆን በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት ደግሞ ይህን ለውጥ ተግባራዊ እንዲያደርግ እንሻለን፡፡ መንግስት በእኛ ፍቃድና ምርጫ እንዲመራ ከመሻት አንፃር የጋራ አቋምና አመለካከት አለን፡፡ “የመንግስት ተግባራዊ እንቅስቃሴ በእኛ ፍቃድና ምርጫ ላይ የሚመራ መሆን አለበት” በሚለው ላይ ሁላችንም አንድ ነን፡፡ እያንዳንዳችን የራሳችን የሆነ የለውጥ ፍላጎትና አመለካከት  ስላለን መንግስት የሁላችንንም ፍላጎትና ምርጫ መመለስ አይችልም፡፡ ነገር ግን፣ ሁላችንም “መንግስት በእኛ ፍቃድና ምርጫ መሠረት መመራት አለበት” የሚል አንድ ዓይነት ፍላጎትና አመለካከት አለን፡፡ 

መንግስት በእኛ ፍቃድና ምርጫ እንዲመራ ለእኛ ፍላጎትና ምርጫ ተገዢ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግስት ስልጣን በእኛ ፍቃድና ምርጫ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ ይህ የሚሆነው መንግስት በነፃና ገለልተኛ ምርጫ የሚመረጥና የሚወገድ ከሆነና ከሆነ ብቻ ነው፡፡ስለዚህ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በማድረግ የእያንዳንዳችንንና የሁላችንንም ፍላጎት በተግባር መመለስ ይቻላል፡፡ 

በመሆኑም ዛሬ ላይ “ዶ/ር አብይ የሚፈለገውን ለውጥ ያመጣል ወይስ አያመጣም?”፣ ነገ  ላይ ደግሞ “የሚፈለገውን ለውጥ አምጥቷል ወይስ አላመጣም?” የሚሉት ጥያቄዎች መታየት ያለባቸው ከዚህ አንፃር መሆን አለበት፡፡ በአጠቃላይ ጥያቄው “እንደ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ያስችላል ወይ?” የሚል መሆን አለበት፡፡ የዚህን ጥያቄ መልስ በሌላ ፅሁፍ በዝርዝር የምንመለስበት ይሆናል፡፡ 

One thought on “ጥያቄው፦ “ዶ/ር አብይ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲካሄድ ያስችላል ወይ?” ነው! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡