ከሰው እና ከወርቅ የቱ ይበልጣል? 

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ለገ-ደንቢ (Lege Dembi) እና ሳካሮ (Sakaro) በሚባሉ አከባቢዎች ከሚገኙት የሜድሮክ (MIDROC) ወርቅ ማውጫዎች የሚወጣው መርዛማ የሆነ ኬሚካል በአከባቢው ነዋሪዎች፣ እንስሳት እና ስነ-ምህዳር ላይ የከፋ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡

ፎቶ፦ በመንገዱ በስተግራ ያለው ውሃ በኬሚካል የተበከለ ነው! Photo Credit ©Gaurdian

የአዶላ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ቡሻ ባላኮ ለOBN በሰጡት አስተያየት ከፋብሪካው የሚወጣው መርዛማ ኬሚካል በሰውና እንስሳት ፅንስና አወላለድ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል፡፡ ለምሳሌ ባሳለፍነው የፈረንጆች አመት (2017) ብቻ ከ157 በላይ ህፃናት ገና በእናታቸው ማህፀን ውስጥ (በፅንስ) እንዳሉ መሞታቸውን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ በተለይ የአከባቢው እናቶች ከፅንስ ማስወረድ ጋር ተያይዞ ባጋጠማቸው የስነ-ልቦና ችግር ምክንያት እስከሚወልዱ ድረስ እርግዝናቸውን እንደሚደብቁ ተገልጿል፡፡

Photo Credit: ©Social Media

በተመሣሣይ አንድ በቢቢሲ የቀረበ ጥናታዊ ዘገባ የተጠቀሰው መርዜማ ኬሚካል በቤት እንስሳት ፅንስና አወላለድ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ገልጿል፡፡ ይህ የሜድሮክ የወርቅ ማውጫ ባለፈው አመት ኮንትራቱ የተጠናቀቀ ቢሆንም ሰሞኑን ውሉን በአስር (10) ዓመት እንዲያራዝም ተፈቅዶለታል፡፡ በመሆኑም በአከባቢው ማህብረሰብ፣ እንስሳትና ስነ-ምህዳር ላይ ሲደርስ የነበረው ጉዳት ለአስር አመት እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡ በዛሬው ዕለት የአከባቢው ነዋሪዎች ይህን ሃላፊነት የጎደለው ውሳኔ በመቃውም የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል፡፡ ጥያቄው በአስቸኳይ ምላሽ የማያገኝ ከሆነ የነዋሪዎቹ ተቃውሞ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

የሜድሮክ (MIDROC) ወርቅ ማውጫዎች ኮንትራት መራዘምን በመቃወም የተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ Photo Credit @ Social Media

የልማት፥ ዴሞክራሲ፥ ሀገር ሆነ መንግስት ትርጉምና ፋይዳ ሰውና ሰው ብቻ ነው፡፡ የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብትና ክብር የሚፃረር ተቋም ሆነ አሰራር ትርጉም-አልባ፥ ፋይዳ-ቢስ ነው፡፡ የወርቅ ማዕድኑን ለማውጣት ጥቅም ላይ የሚውለው መርዛማ ኬሚካል በለገ-ደንቢ እና ሳካሮ የሚገኙ እናቶችን ፅንስ እያስወረደ ነው፡፡ በእርግጥ ወርቅ ውድ ማዕድን ነው! ነገር ግን፣ ምንም ያህል ውድ ቢሆን ከሰው ልጅ ህይወት አይበልጥም፡፡ ያለ ምንም ለውጥ የድርጅቱን ኮንትራት በአስር አመት እንዲራዘም የፈቀደው የመንግስት አካል ከሰው ይልቅ ለወርቅ ዋጋ መስጠቱን በግልፅ ይጠቁማል፡፡ ሆኖም ግን፣ ለአከባቢው ወላጆች ልጆቻቸው ከወርቅ በላይ ውድ ናቸው፡፡ በመሆኑም በኬሚካሉ ምክንያት የእናቶች መሃፀን ከሚዘጋ ወርቅ ማውጫው ቢዘጋ ይመርጣሉ፡፡

One thought on “ከሰው እና ከወርቅ የቱ ይበልጣል? 

  1. ውድ የ ተከበሩ(በፓርላማ ቋንቋ) መ/ር ስዪም
    ሁሌም ለአንተ አድናቆቴ ከፍ ያለ ነው:: መቼም መንግስቲቱ ደም ግፊቷ ከፍ ማለቱ አይቀር አንተ ብቻ ለእውነት ዘብ ቁም:: ቅር ቢሉት የማይቀር ነገር ለውጥ ብቻ ነው::

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡