​የቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ትግል እስከ ምን ድረስ?

የዓለማችንን ታላላቅ አብዮቶችን ስናጠና ከምናገኘው ተመሳሳይ ባህርያት መካከል በለውጥ ፈላጊዎች ግፊት ነባሩ ስርአት ተቀይሮ አዲስ ስርአት ሲመጣ  አዲሱ ስርአት የሚወስዳቸው እርምጃዎች በአብዛኛው የለውጥ ፈላጊውን ቡድን ማስደሰት የሚያስችለውና ብዙ ህዝባዊ ድጋፍ የሚያስገኝለት መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ የተወሰዱ እርምጀዎች ዘላቂ ሳይሆኑ ሲቀሩ ሌላ አስከፊ ቀውስ ማስከተላቸው የማይቀር ነው፡፡ በሀገራችን ታሪክ እንኳን ብንመለከት ደርግ ንጉሱን ከስልጣን ባስወረደ ማግስት የወሰዳቸው እርምጀዎች ብዙዎቹን የሀገራችንን ለውጥ ናፋቂ ህዝቦችንና የአብዮቱን ደጋፊዎች ያስደሰተ ነበር፡፡ 

የወሊሶና አከባቢዋ ቄሮዎች የካቲት 03/2010 ዓ.ም በወሊሶ ከተማ ያደረጉት ሰልፍ

በተለየ መልኩ በሀገራችን ላለፉት ሶስት አመታት በዋነኝነት በቄሮ የተቀጣጠለው የለውጥ ናፍቆት በመጀመሪያ ቲም ለማን የመሰለ ጠንካራ አመራር በኦሮሚያ ፈጥረ፡፡ ከዚያም በፋኖና ዘርማ ተደግፎና በኢትዮጲያዊነት አሸብርቆ ዶ/ር አብይን ወደ 4 ኪሎ አስገብቷል፡፡ ዶ/ር አብይ እየሰሩትና እያወሩት ያለውን ነገር ለተመለከተ የቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ የለውጥ ህልም ግቡን የመታ ይመስላል፡፡ 

ቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ማን ነው?

በእኔ እይታ ቄሮን፣ ዘርማንና ፋኖን በሶስት መልኩ መመልከቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በመጀመሪያ ለሁሉም ግልጽ የሆነው እይታ ቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ በእድሜ ደረጃ የሚገለጽ አንድ ትውልድ ነው፡፡ ይህ ትውልድ መንግስት ባሻሻላ መሰረት ከ18-32 የእድሜ ደረጃ የሚገኝ አፍላና ጠንካራ የወጣት ቡድን ነው፡፡ ምንም እንኳን ተጽዕኖው የተለያየ ቢሆንም ይህ የቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ትውልድ በዋነኝት የአሁኑን የሀገሪቱን አጠቃላይ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እየዘወረ የሚገኝ ነው፡፡ 

ሁለተኛውና ለብዙ የኢህአዴግ ሰዎች ያልገባቸው ነገር ቄሮነት፣ ዘርማነትና ፋኖነት   መንፈስ መሆኑ ነው፡፡ ቄሮነት፣ ዘርማነትና ፋኖነት በሁለት ትውልዶች (በጎልማሳውና ታዳጊው) መካከል ያለ ድልድይ (አገናኝ) ትውልድ ነው፡፡ ይህንን ውብ ጊዜ ጎልማሶቹ ወይም ከዚያ እድሜ በላይ ያሉት ሲያስታውሱት ከታች (ከ18 ዓመት በታች) ያሉት ደግሞ ሊድርሱበትና የዚህ ትውልድ አባል መሆንን ይናፍቁታል፡፡ በዚህ መሰረት እነዚህ ከቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ጋር የማይመደቡት ትውልዶች ከቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ጋር በአስተሳሰብ፣ በፍላጎት፣ በአቋምና ምኞት በመንፈስ ይቆራኛሉ፡፡ 

ለዚህ ሁለት ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ክስተቶች እንመልከት፡፡ በ1967 ዓ.ም ህወሓት ወደ በረሃ ሲወርድ በአብዛኛዎቹ መስራቾች ከዩኒቨርስቲ አቋርጠው የወጡ ወጣቶች (ቄሮዎች/ዘርማዎች/ፋኖዎች) ነበሩ፡፡ ነገር ግን በእነዚህ አፍላ ወጣቶች (ቄሮዎች/ዘርማዎች/ፋኖዎች) ጋር አንድ በእድሜ የገፉ ነገር ግን የወጣቶቹን (ቄሮዎቹን) መንፈስ የተጋሩ ኣዛውንት ነበሩ ፡፡ጋሽ ስዑል፡፡ እኚህ አዛውንት በትውልድ ሲታዩ ከወጣቶቹ (ቄሮዎቹ/ዘርማዎች/ፋኖዎች) ጋር አይመደቡም ነገር ግን የትግራይ ቄሮዎችን ፍላጎት፣ ህልህ፣ አስተሳሰብና አላማን ተጋርተው ለዛሬው ህወሓት ምስረታ ታላቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ሌላኛው የቄሮ፣ዘርማና ፋኖ መንፈስ ያለው ታዳጊ ጣሊያንን መከራ ያበላው የኦሮሚያው አቢቹ ነው፡፡ አቢቹ ከጣሊያን ጋር የራሱን ቡድን አዋቅሮ ሲዋጋና ሲያዋጋ ገና ታዲጊ ነበር ነገር ግን የቄሮ/ዘርማ/ፋኖ መንፈስ ያለው ታዳጊ ነበር፡፡

በተመሳሳይ በኦሮሚያ፣ አማራና ደቡብ ውስጥም እንዲሁ በእድሜ ከቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ጋር የማይመደቡ ነገር ግን ቄሮው፣ ፋኖው እና ዘርማው ያነሳውን አስተሳሰብ፣ ፍላጎትና አላማ የሚደግፉ ብዙ ሚሊዮን ጋሽ ስዑሎችና አቢቹዎች አሉ፡፡ እነዚህ እንግዴ ወደድንም ጠላንም በእድሜ ሳይሆን በመንፈስ ቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ የሆኑ ናቸው፡፡

ሶስተኛው ቄሮነት፣ ዘርማነት፣ ፋኖነት የማንነትና የብሶት መድረክ ነው፡፡ የኃላውን ታሪክ እንኳን ትተን ኢህአዴግ መንበረ ስልጣኑን ከተቆጣጠረበት ዘመን ወዲህ ያለውን የሀገራችንን ታሪክ ብንመለከት ኦሮሞና አማራ በፖለቲካውና ኢኮኖሚው የነበረው ቦታ ብዙ ኦሮሞዎችንና አማራዎችን ያስኮረፈ ነበር፡፡ ባለፉት አመታት ኦሮሞ ማለት ጠባብ፣ መገንጠል የሚፈልግ፣ ኢትዮጲያ ስጋት፣ … እየተባለ አማራ ደግሞ ትምህክተኛ የሚል ታርጋ ተለጥፎበት ኖሯል፡፡ ይህም የኦሮሞንና አማራን ከብዙ ወሳኝ መድረኮች ገለል እንዲሉና የበይ ተመልካች እንዲሆኑ ያደረገ ነበር፡፡ 

ከ2008 ዓ.ም በኃላ ግን እጅግ በተጠናከረ መልኩ በመጀመሪያ “ቄሮ” ቀጥሎም “ፋኖ” የሚባል በኢህአዴግ ቤት ነውጥን የፈጠረ አንድ ነገር ብቅ አለ፡፡ ይህም “የቄሮ ማንነት” በኦሮሚያ “የፋኖ ማንነት” በአማራ ውስጥ ውስጡን ብሶት ያሳረረውን ለውጥ ፈላጊውን ህዝብ በአንድ መድረክ ማቆም ቻለ፡፡ 

በተለይ በኦሮሚያ የቄሮ ማንነት ለኦቦ ለማንና ቡድኑን ትልቅ የጀርባ አጥንት ሆኖ መላው ኦሮሞን በአንድ የብሶት መድረክ ማቆም ቻለ፡፡ ለዚህም ነው በቄሮው እንቅስቃሴ የኦሮሚያ ክልል ፖሊሱ፣ ባለስልጣኑ፣ ምሁሩ፣ የመንግስት ሰራተኛና ነጋዴ በአጠቃላይ ከሊቀ እስከ ደቂቅ  ሳር ቅጠሉ ኦኦ ብሎ አብሮ የቆመውና የደገፈው፡፡ በተጨማሪም የቄሮ ማንነት መላው ኦሮሚያን የፋኖ ማንነት ደግሞ መላው አማራን ከምን ጊዜውም በላይ በአንድ ውስብስብ መረብ ማገናኘት የቻለ ማንነት ነው፡፡ በዚህ መሰረት ኦሮሚያና ኦሮሞ በሙሉ “ቄሮ”፣ አማራ በሙሉ ፋኖ  ነው፡፡ አቦ ለማ በአንድ ወቅት እንዳሉት ኦሮሚያ ውስጥ 6 ሚሊዮን ቄሮ ብቻ ሳይሆን ያለው ከ40 ሚሊዮን በላይ ነው ፋኖም በአማራም እንደዛው፡፡ 

የለውጥ ፈላጊው ህልም…

አሁን ላይ ሆነን ስናየው በሀገራችን ለውጥ ፈላጊው ቡድን በመጠኑም ቢሆን ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል፡፡ ዶ/ር አብይ ቤተ መንግስት ከገቡባት እለት አንስቶ አብዛኛው ኢትዮጲያዊ (በተለይ ለውጥ ፈላጊው) በእሳቸው ስለ ሀገሪቱ ብሩህ ተስፋ ያየና ተስፋ የጣለ ይመስላል፡፡ የእርሳቸውንም ንግግር (በብዙ ወደ ስራ አልገቡምና) ላደመጠ የለውጥ ፈላጊው ቡድን (በተለይ የቄሮ፣ ዘርማና፣ ፋኖ) ህልም ግቡን የመታ ያስመስለዋል፡፡ ነገር ግን እጅግ የበዛ ስራ ይቀራል፡፡

ዶ/ር አብይ የሚናገሩትን ነገር በተግባር ካሳዩን በእርግጠኝነት የሀገሪቱ ትንሳኤ ጥንት አይሆንም፡፡ ነገር ግን የጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ወደ ተግባር እንቀይር ቢባል እንኳን ቀላል የማይሆኑ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች በተለያዩ ቦታዎች የእርሳቸውን ስራ ለማበላሸት የሚጥሩ አካላት አይጠፉም፡፡

ቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ህዝብ ውስጥ ያለ ራሱ ህዝብ ስለሆነ ባለፉት ጊዜያት ከድሮው በተጨማሪ የቄሮ፣ የዘርማና የፋኖ ስራም እነዚህን አካላትን በግልጽም በአይነ ቁራኛ መከታተል ላይ ማተኮር ይኖርበታል፡፡ ይህችን ቀንና ለውጥ ለማየት ሲባል ብዙ ወንድና ሴት ልጆች መስዋእት ሆነዋል፡፡ ባለፉት ጊዜያት እንዳየነው በየአካባቢው የለውጡ መሪ ቄሮ፣ ዘርማና ፋኖ ከሆነ በመሪዎች የተነገረውን በተግባር ለማየት እድል ይኖረናል፡፡    


ዳንኤል መኮንን ይልማ 
በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር
ኢሜል፦ yalewyalew3@gmail.com