ለቤቱ ባዳ፣ ለውጪ እንግዳ! 

በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በማዕከላዊ እስር ቤት ከታሰርኩበት ዕለት፣ የካቲት29/2010 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት የመጀመሪያ ሶስት ሳምንታት ከእስር ቶሎ የመፈታት ተስፋ አልነበረኝም፡፡ ከዚያ ይልቅ ከ6 ወር እስከ 5 አመት የሚደርስ እስራት በራሴ ላይ ፈርጄ፣ በቶሎ የመፈታት ጉጉቴን ከውስጤ አውጥቼ፣ ማዕከላዊ ከሚገኘው ቤተ-መፅሃፍት መፅሃፍ በመዋስ ማንበቤን ተያይዤው ነበር፡፡ ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ መመረጡን ተከትሎ ሁሉ ነገር ተቀያየረ፡፡ 


በመጀመሪያ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታሰርነው በሙሉ ወደ “09” ወይም “ሸራተን” ወደሚባለው ክፍል ተዘዋወርን፡፡ ከዚያ ቀጥሎ፣ ‘ማዕከላዊ ተዘጋ!” አሉንና ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ “ሶስተኛ” ወሰዱን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዶ/ር አብይ መመረጥ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በታሰርነው ላይ ከቦታ ለውጥ በተጨማሪ የተለየ ተስፋና ጉጉት አሳድሮብን ነበር፡፡ በዚህ መልኩ ከማዕከላዊ ወደ ሶስተኛ የተዘዋወርነው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እስረኞች (ታጋቾች) ስም እና አድራሻ፤ 

  1. አቶ ስዩም ተሾመ – የአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ጦማሪ፣ 
  2. አቶ ታዬ ደንደኣ  – የኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ፣
  3. ኮ/ር እያሱ አንጋሱ – የኦሮሚያ አድማ በታኝ ም/አዛዥ፣ 
  4. መ/አለቃ ጫሊ ጋዲሳ – የህዳሴ ግድብ ኢንጂነር፣ 
  5. መ/አለቃ አይዳ አሌሮ – በብላቴ የአየር ወለድ አሰልጣኝ፣
  6. አቶ አራርሶ ጀዋር – በአዲስ አበባ ኢትዮቴሌኮም ሰራተኛ፣ 
  7. አቶ አብዱርሃማን ዩዬ – በአዲስ አበባ የኦሮሚያ ኢንሹራንስ ሰራተኛ፣ 
  8. አቶ ውቤ ወርቁ – በጎንደርና ሁመራ በንግድ የተሰማራ እና 
  9. አቶ ሞላ ባህሩ – በቆቦ-ሮቢት በስዕል የተሰማራ 

በእርግጥ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ መሠረታዊ ዓላማ ህወሓቶች ሽፈራው ሽጉጤን ጠ/ሚኒስትር አድርጎ በመምረጥ ዶ/ር አብይ ወደ ጠ/ሚኒስትርነት የሚያደርጉትን ግስጋሴ መግታት ነው፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ሰዎች ዶ/ር አብይን ከጠ/ሚኒስትርነት ለመግታት በህገ-ወጥ መንገድ የወጣው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ሰለባዎች ናቸው፡፡ 

የዶ/ር አብይ የመጀመሪያ ተግባር መሆን ያለበት በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 93 መሠረት አግባብነት የሌለው መሆኑንና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ መደረጉን በመጥቀስ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ማንሳት ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የታሰሩ ከአንድ ሺህ በላይ እስረኞችን ማስፈታት ይቻላል፡፡ በእርግጥ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በማዕከላዊ ከታሰርነው ውስጥ 1-3 የተጠቀስነው በአንድ የትዕዛዝ ደብዳቤ ተፈትተናል፡፡ ነገር ግን፣ ሶስታችንን ብቻ አስፈትቶ የተቀሩትን ስድስት ሰዎች ላለፉት 18 ቀናት በእስር ላይ ማቆየት ፍፁም አድሏዊ ነው፡፡ እዚህ’ጋ የኦቦ በቀለ ገረባን አባባል ልዋስና “ሁላችንንም ፍቱን ወይም ሁላችንንም እሰሩን!” እላለሁ፡፡ 

“ሁላችንንም ፍቱን ወይም ሁላችንንም እሰሩን!” Photo Credit: Social Media

በአጠቃላይ የማዕከላዊ እስረኞች ሳይፈቱ “ማዕከላዊ ተዘግቷል” ይባላል፡፡ ነገር ግን፣ እስረኞችን ሳይፈቱ እስር ቤቱን መዝጋት ይቻላልን? የሚዲያ ተደራሽነትና የመንግስት ሃላፊነት ያላቸውን ጥቂት እስረኞች ፈትቶ ብዙሃኑን በእስር ማቆየት አቅም ማጣት ወይም አድሏዊነት አይደለምን? ጠ/ሚኒስትሩን ከስልጣን ለመግታት በወጣው አዋጅ የታሰሩ ከአንድ ሺህ በላይ ዜጎች ሳይፈቱ “የሁሉም ኢትዮጲያዊ መሪ ነኝ!” ማለት ይቻላልን? በሀገር ውስጥ ያሉትን የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱ፥ ሳያስፈቱ በውጪ የሚገኙ እስረኞችን ማስፈታት “ለቤቱ ባዳ ለውጪ እንግዳ” መሆን አይደለምን? 
Photo Credit: Social Media

One thought on “ለቤቱ ባዳ፣ ለውጪ እንግዳ! 

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡