ጦር፥ ግብር እና ምርጫ: “ከዶ/ር አብይ ምን ዓይነት ለውጥ ይጠብቃሉ?”

እርስዎ ምን ዓይነት ለውጥ እንዲያመጣ ይጠብቃሉ?
​ሰሞኑን አብዛኛው የጠየቀው ወይም የተጠየቀው ጥያቄ “ዶ/ር አብይ ለውጥ ያመጣል ብለህ ታስባለህ?” የሚለው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን፣ “አንተ በራስህ ዶ/ር አብይ ምን ዓይነት ለውጥ እንዲያመጣ ትሻለህ?” ብላችሁ ብትጠይቁት አብዛኛው ጠያቂ ሆነ ተጠያቂ ግራ የሚጋባ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቻችን “ለውጥ ያመጣል ወይስ አያመጣም?” ከማለት በዘለለ የምንፈልገውን ለውጥ በተጨባጭ የተገነዘብን አይመስኝም፡፡ በእርግጥ አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ መሻሻል እንዳለበት እንገነዘባለን፡፡ ነገር ግን፣ በየትኛው የህይወት ዘርፍ ምን ዓይነት ለውጥና መሻሻል መምጣት እንዳለበት የጠራ ግንዛቤ ያለን አይመስለኝም፡፡ ስለዚህ ይህ ፅሁፍ “አንደ ዜጋ እርስዎ ምን ዓይነት ለውጥ እንዲያመጣ ይጠብቃሉ?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ያጠነጥናል፡፡ 

በመጀመሪያ ደረጃ “አንድ ዜጋ መንግስት ምን ዓይነት ለውጥ እንዲመጣ ይሻል?” የሚለው ጥያቄ ከመሠረታዊ የመንግስት ዓላማና ፋይዳ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄውን በአግባቡ ለመመለስ የመንግስት አመሠራረትና ፋይዳን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ጂኦግራፊያዊ ክልል ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች የራሳቸው ሀገርና መንግስት የሚመሰርቱበት መሠረታዊ ዓላማ የጋራ ሰላምና ደህንነታቸውን፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ 

ጦር፥ ግብር እና ምርጫ

በዚህ መሠረት መንግስት፤ አንደኛ፦ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር የሀገር መከላከያና ፀጥታ ሃይሎችን ያቋቁማል፥ ያደራጃል፥ ይመራል፣ ሁለተኛ፦ የዜጎችን ጥቅምና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የልማት ሥራዎችን ይሰራል፡፡ መንግስት የተጠቀሱትን ተግባራት በሚገባ እንዲያከናውን ዜጎች እንደ አቅማቸው ግብር ይከፍላሉ፡፡ ሶስተኛ፦ ዜጎች ለመንግስት የተሰጡትን ስልጣን እና ገንዘብ ለመቆጣጠርና በመንግስት ላይ ያላቸውን የስልጣን የበላይነት ለማረጋገጥ በየወቅቱ ምርጫ ያካሂዳሉ፡፡ በአጠቃላይ በመንግስት እና በዜጎች መካከል ያለው ግንኙነት በሶስት ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እነሱም፦ ጦር፥ ግብር እና ምርጫ ናቸው፡፡ 

ጠ/ሚ አብይ አህመድ

የሀገሪቱ ጦር ሰራዊትና የጦር መሣሪያ የታጠቁ የፀጥታ ሃይሎች የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ይልቅ ፍርሃትና ስጋት የሚፈጥሩ ከሆነ፣ የመንግስት የልማት ሥራዎች የብዙሃኑን ጥቅምና ተጠቃሚነት የማያረጋግጡ ከሆኑ፣ እንዲሁም በነፃና ገለልተኛ ምርጫ አማካኝነት ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸውን የስልጣን የበላይነት ማረጋገጥ ከተሳናቸው መንግስት እንደ መንግስት የተፈጠረበትን መሠረታዊ ዓላማ ስቷል፡፡ የተፈጠረበትን መሠረታዊ ዓላማ የሳተ ነገር ደግሞ ፋይዳ-ቢስ ነው፡፡

የኢህአዴግ መንግስት በተለይ ከ1997 ዓ.ም በኋላ የሀገሪቱን የጦር ሰራዊት፣ የፖሊስና ደህንነት ተቋማት በመጠቀም የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከማስከበር ይልቅ በፍርሃትና ሽብር ሲያርድ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ያልተመጣጠነ ግብርና ታክስ በዘፈቀደ ግምት በዜጎች ላይ መጫኑ ሳያንስ በልማት ሥራዎቹ አማካኝነት የብዙሃኑን ጥቅምና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ዝርክርክና በቢሮክራሲ የተተበተበ ከመሆኑም በላይ ስር-የሰደደ ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት የተንሰራፋበት ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ ዜጎች ከኢህአዴ በተሻለ ሰላምና ደህንነታቸውን የሚያስከብር እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ መንግስት እንዳይመርጡ ምርጫው ይጭበረበራል፡፡ በዚህም ላይ አማራጭ የፖለቲካ ሃይሎች ከሞላ-ጎደል ከሀገሪቱ እንዲጠፉ ተደርገዋል፡፡ በዚህ መልኩ ዜጎችን ምርጫና አማራጭ  አሳጥቶ “ምርጫውን መቶ ፐርሰንት (100%) አሸነፍኩ” ይላል፡፡ ምርጫ ከዜጎች የስልጣን የበላይነት ይልቅ የኢህአዴግ መንግስት በዜጎች ላይ ያለውን የበላይነት ለማረጋገጥ ውሏል፡፡ 

ከላይ በተገለፀው መሠረት የኢህአዴግ መንግስት ሥራና ተግባር ከተመሠረተበት ዓላማና ፋይዳ አንፃር የተገላቢጦሽ ሆኗል፡፡ ሀገሪቱ አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ የገባችበት  መሠረታዊ ምክንያት ይህ ተገላቢጦሽ ነው፡፡ ስለዚህ የችግሩ መፍትሄ አንድና አንድ ነው፡፡ በተመሣሣይ የችግሩም መፍትሄ  አንድና አንድ ሲሆን እሱም የመንግስትን ሥራና ተግባር መልሶ መገልበጥ ነው፡፡ በዚህ መሠረት፣ 

  • አንደኛ፦ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት እንዲያስከብሩ የተሰጣቸውን ጦር መሣሪያ በመጠቀም በዜጎች ላይ ፍርሃትና ሽብር የሚፈጥሩ የፀጥታ ሃይሎችን በህግ አግባብ ሊጠየቁና ሊቀጡ ይገባል፡፡ ሁሉም የፀጥታ ሃይሎች እያንዳንዱን ዜጋ ማክበርና ማገልገል ይኖርባቸዋል፡፡ ሁሉም ዜጎች የፀጥታ ሃይሎችን መፍራት ሳይሆን ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ 
  • ሁለተኛ፦ እያንዳንዱ ዜጋ በግብርና ታክስ መልክ የከፈለው ገንዘብ እንዴትና ለምን አገልግሎት እንደዋለ መጠየቅና ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ በመንግስት ከሚሰሩ የልማት ስራዎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱ እንዲረጋገጥ መጠየቅና ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን መለየትና እንዲሻሻሉ መጠየቅ አለበት፡፡ 
  • ሶስተኛ፦ 1ኛና 2ኛ ላይ በተጠቀሰው መሠረት የዜጎች ሰላምና ደህንነት የሚከበረው፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነታቸው የሚረጋገጠው የዜጎች የስልጣን የበላይነት ሲረጋገጥ ነው፡፡ ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸው የስልጣን የሚረጋገጠው ለህዝብ ፍቃድና ምርጫ ተገዢ ሲሆን ነው፡፡ ይህ እውን የሚሆነው ነፃና ገለልተኛ ምርጫ በማካሄድ ነው፡፡ 

በዚህ መሠረት ከዶ/ር አብይ የሚጠበቀው መሠረታዊ ለውጥ ከጦር፥ ግብር እና ምርጫ አንፃር ያለውን የመንግስት ሥራና ተግባር መቀየር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው ተግባር ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ ነው፡፡ በህዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግስት የህዝብን ሰላምና ደህንነት እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህን ማድረግ ከተሳነው ደግሞ በህዝብ ድምፅ ከስልጣን ይወገዳል፡፡ 

በአጠቃላይ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ማካሄድ የለውጡ መጀመሪያና መጨረሻ ነው፡፡ “አንደ ዜጋ ዶ/ር አብይ ምን ዓይነት ለውጥ እንዲያመጣ ይሻሉ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “ነፃና ገለልተኛ ምርጫ” የሚለው ነው፡፡ በቀጣይ “ዶ/ር አብይ ነፃና ገለልተኛ ምርጫ ማካሄድ ይችላሉን?” የሚለውን የምንመለከት ይሆናል፡፡ 

One thought on “ጦር፥ ግብር እና ምርጫ: “ከዶ/ር አብይ ምን ዓይነት ለውጥ ይጠብቃሉ?”

  1. You have just made an interesting logical connection between Law enforcement , Vote and Tax payers’ sovereignty as the only source of power from which all governments acquire their legitimacy

    Liked by 1 person

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡