​የቱኒዚያ የዴሞክራሲ ሽግግር እና የሠራተኛ ማኅበራት ሚና

የኖቤል ተሸላሚው አራትዮሽ የቱኒዚያ የሲቪል ማኅበራት ጥምረት
መንደርደሪያ
የዓለም መገናኛ ብዙኃን ስለዝነኛ መሪዎች አሸናፊ መሆን አይቀሬነት ትንታኔ በመስጠት ሥራ ላይ ተጠምደዋል። ግምቶችም በእነኝህ ታላቅ ስብዕናን በተላበሱ ሰዎች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ። ጥያቄው ሚዲያው ስኬታቸውን ከሚያነሳሳለቸው ግንባር ቀደም ተፎካካሪዎች መካከል ማን አሸናፊ ይሆናል ወደሚለው ያዘነበለ መስሎ ነበር። በእርግጥም ማንም የሆነው ይሆናል ብሎ የጠበቀ የለም። ያልተጠበቀው ሆነ፣ ያልተገመተውም ተፈጸመ። ግምቶችም ፉርሽ ሆኑ። ዝነኛው የኖቤል ሽልማት ድርጅት የ2015ቱ የሰላም ሽልማት ተሸላሚውን ሲያሳውቅ እነዚያ ሚዲያው ቤተኛ ያደረጋቸው ስሞች ሳይጠቀሱ ቀሩ።  በእነሱ ፋንታ እምብዛም ስሙ የማይታወቀው የሰሜን አፍሪካዊቷ ቱኒዚያ የሲቪል ማኅበራት ጥምረት አሸናፊ መሆኑ ተገለጸ። ዜናው ያልተጠበቀ ነበር። የቴሌግራፉ የመካከለኛው ምስራቅ አርታኢ ሪቻርድ ስፔንሰር ያልተጠበቀው ሽልማት የኖቤል የሽልማት ድርጅት የተጠናቀቁ ስኬቶችን ከመሸለም ተስፋ የሚያጭሩና የሚያበረቱ ሙከራዎችን የሸለመበት ሌላው አጋጣሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብሏል ያልተጠበቀው የሆነበትን ምክንያት ለማብራራት ሲሞክር።

Photo Credit: EPA/HO
በእርግጥ ከቱኒዚያው የሲቪል ማኅበራት ጥምረት ጋር ለኖቤል የሰላም ሽልማት የታጩትን ሰዎች ስም ዝርዝር ለተመለከተ የጥምረቱ ግንባር ቀደም እጩ ሆኖ ብቅ ሳይል መቅረት አያስገርምም። ከተወዳዳሪዎቹ መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ተራማጅ ሀሳቦችን በመተግበርና ቤተክርስትያኗን ዓለም አቀፍ ሚናዋን በማሳደግ በተለይም በኩባና አሜሪካ መካከል አንጻራዊ ሰላም እንዲወርድ የተሳካ ጥረት ያደረጉትና የተገፉት ወዳጅ መሆናቸው የሚጠቀስላቸው የሮማ ካቶሊክ ቤተክርሰትያን ሊቀ ጳጳስ አባ ፍራንሲስ ናቸው። ሊቀጳጳሱ ላለፉት አሥርት ዓመታት በውጥረት የተሞላ ግንኙነት ላይ የቆዩት ግዙፏ አሜሪካና ሚጢጢዋ ጉረቤቷ ኩዩባ አለመተማመናቸውን ቀንሰው በየአገራቱ መዲና ኢምባሲ ወደ መክፈት ያሸጋገራቸውን ሁኔታ እውን እንዲሆን በማስቻል ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወታቸው ይነገራል። ከዚህም ባሻገር ያለፈው ዓመትም የኖቤል የሰላም ሽልማት ዕጩ የነበሩት አባ ፍራንሲስ በኮሎምቢያ መንግሥትና በአማጺ ኃይሉ መካከል እርቅ እንዲወርድ ጥረት በማድረግ፣ ወሳኝ በሚባሉ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የሃብት አለመመጣጠንና የሰዎች ፍልስትን በተመለከተ ዓለም የጋራ አቋም እንዲወስድ ግፊት በማሳደር ለተሻለ ዓለም ግንባታ የበኩላቸውን ድርሻ ተወጥተዋል።
ለሽልማቱ የቅድሚያ ግምት ያገኙት ሌላዋ ዕጩ የጀርመኗ መራሂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ናቸው። ሜርክል በአውሮፓ ኅብረት የመሪነት ሚና የያዘችውን አገራቸውን ጠንካራ የኢኮኖሚ ማዕከል ሆና እንድትቀጥል በማድረግ በተለይም የአውሮፓ ኅብረትን በቁርጠኝነት በመደገፍ ከፍ ያለ ስኬትን አስመዝግበዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ አውሮፓ በጦርነት ከሚታመሱት ከመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በሚነሱ ስደተኞች ስትጥለቀለቅ ከሌሎች የአህጉሩ አገራት በተቃራኒ አገራቸው ስደተኞችን ለመቀበል በሯ ክፍት መሆኑን በመግለጽ አድናቆት የተቸረው ተግባርን ፈጽመዋል። በዚህ ረገድ ያሳዩት የሞራል ልዕልና መራሂተ-መንግሥቷን ለሽልማቱ ቅርብ ተደረገው እንዲወሰዱ አድርጓቸዋል።

በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱት ዕጩዎች ባሻገር በሜዲትራኒያን ባህር ሰጥመው ለሞት የሚዳረጉ ፍልሰተኞችን  ሕይወት ለመታደግ ጥረት በማድረግ የሚታወቁት ዘርአይ የተባሉ ኤርትራዊ የካቶሊክ ቄስ፣ የኢራን የኒዩክሌር ውዝግብን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመሥጠት አድካሚና ረጅም ድርድር ያደረጉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪና የኢራኑ አቻቸው ሙሃመድ ዛሪፍና ራሱን ለአደጋ በማጋለጥ ከ30 ሺህ በላይ የአስገድዶ መደፈር ተጠቂዎችን በማከም አስደናቂ ተግባርን የፈጸመው የዴሞክራቲክ ኮንጎው ጋይናኮሎጅስት በዘርፉ እጩ ሆነው ቀርበው ነበር። ይሁንና የሽልማት ድርጅቱ እነኝህን ሁሉ ስኬታማ ሰዎች ወደ ጎን ትቶ የቱኒዚያውን የሲቪል ማኅበራት ጥምረት ለመሸለም ለምን ወሰነ? የቱኒዚያው የሲቪል ማኅበራት ጥምረቱ ለአንጻራዊው የቱኒዚያ የተሳካ የዴሞክራሲ ሽግግር ምን አሳካ? በጥምረቱ ውስጥና በአጠቃላይ በዴሞክራሲ ሽግግሩ የሠራተኛ ማኅበራት ሚና ምን ነበር? የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክር። 

የአረብ ጸደይ እና ቱኒዚያ

የኋላኋላ «የአረብ ጸደይ» የሚል ስያሜ የተሰጠውና እ.አ.አ. ከታኅሣሥ 2011 ጀምሮ የሰሜን አፍሪካና የመካከለኛው ምሥራቅ አረብ አገራትን ቁም ስቅል ያሳዬ ሕዝባዊ አመጽ የተቀሰቀስው በቱኒዚያ ነው። ከሁለት ዓመታት ገደማ ቆይታ በኋላ የሕዝባዊ አመጽነቱና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ መገለጫዎቹ እየተዳከሙ ሲጠፉ ቱኒዚያ፣ ግብጽ፣ ሊቢያና የመንን ሲመሩ የነበሩ አምባገነኖች ከሥልጣናቸው ተፈንገለው ለሥደት፣ ለእስር ወይም ለሞት ተዳርገዋል። አመጹ በሶሪያ የአሳድን መንግሥት ከሥሩ መንግሎ መጣል ሳይሳካለት በመቅረቱ አገሪቱን እሳካሁን የመቅዝቀዝ አዝማሚያ ላልታየበት ለአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነትና የኃያላን የመፋለሚያ ሜዳ እንድትሆን አድርጓት አልፏል።  በባህሬን የተቀሰቀሰው ጠንካራ የሕዝብ እንቅስቃሴ መንግሥቱን በማንገዳገድ የተወሰነ የማሻሻያ እርምጃዎች ተወስደው የነበረው ሁሉ እንደነበረ እንዲቀጥል ማድረግ ብቻ ነው የተሳካለት። በአልጀሪያ፣ ዮርዳኖስ፣ ኩዌት፣ ሞሮኮና ሱዳን እንዲሁም በሞሪታኒያ፣ ኦማን፣ ምዕራብ ሳህራ ከአረቡ አመጽ ተደምረው የሚታዩ ደረጃቸው የተለያዬ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ተመዝግበዋል።

Photo Credit: CNN
እነዚህ አመጾቹ በመነሻቸው፣ በሂደታቸውና በውጤታቸው የተለያዬ ገጽታ ያላቸው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አድማዎችን፣ ሰልፎችን የመሰሉ በቀጣይነት የሚከናወኑ የተቃውሞ መንገዶችን መጠቃማቸው፣ እንደ ፌስቡክና ቲውተር ዓይነት አዳዲስ የማኅበራዊ ትስስር ሚዲያዎችን በሚገባ ጥቅም ላይ ማዋላቸውና በዋነኝነት በወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል ድጋፍ መዘወራቸው ሕዝባዊ አመጾቹ የሚጋሯቸው መልኮች አድርጎ መውሰድ ይቻላል። 
እውቁ የኖቤል ተሻላሚ ጆሴፍ ስቲግሊዝን ጨምሮ በርካታ ተንታኞች እንደሚስማሙት የሀብት አለመጣጠን፣ ሥር የሰደደ ሙስናና ድህነት፣ ከፍተኛ ሥራአጥነት፣ ጭቆናና ኢ-ፍትሐዊነት የሰፈነበትን ሥርዓት በፀጋ ተቀብሎ መቀጠልን የሚጠየፍ ወጣትና የተማረ የህብረተሰብ ክፍል መከማቸትን የመሰሉ ምክንያቶች ከእንቅስቃሴው ጀርባ የሚጠቀሱ መሠረታዊ መንስኤዎች ናቸው።

የኮሌጅ ድግሪውን ቤቱ አስቀምጦ በጎዳና ላይ አትክልትና ፍራፍሬ የሚቸረችረው ሙሃመድ ቡአዚዚ ይህንንም ሥራ መሥራት እንደማይችል ተነግሮት የሥራ መሣሪያውን በግፍ ሲቀማ በአማኑ ቀን ፍራፍሬ ይዞ በሚዘዋወርበት አደባባይ በራሱ ላይ ቤኒዚን አርከፍክፎ ክብሪት ለኩሶ ራሱን አቃጠለ። ሙሃመድ ራሱን ማቀጠሉ እንደ ሰበብ ሆኖ የተጠራቀመው ሕዝባዊ ብሶት ገንፍሎ በቱኒዚያዊ አምባገነን ዘይን ኤል ቤን አሊ አነጣጠሮ ተነሳ። ቶማስ ሺምዲነገር «ሠራተኛ ማኅበርተኝነትና የአረብ ዓለሙ አብዮት» በሚል ጽሑፉ ቱኒዚያ በርካታ አገራትን የነካካው ሕዝባዊ አመጽ አልፋ የመሆኑ ጉዳይ እንዲሁ በአጋጣሚ የተፈጠረ እንዳልሆነ ይከራከራል። በርካታ የተማረ ዜጋና መንግሥትን በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሲገዳደር የቆየ በአንጻራዊነት ራስ-ገዝነቱን ተከላክሎ የጠበቀ ነፃ የሠራተኛ ማኅበር የነበራት ቱኒዚያ እንዲህ አይነቱን የተደራጀ ተቃውሞ ለማስተናገድ የተመቻቸች ነበረች። 

ሌሎች መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ቱኒዚያ የአረብ ፀደይ ተብሎ የታወቀው አመጽ በይፋ ከተቀሰቀሰበት ሦሰት አሥርት ዓመታት በፊት ጀምሮ በመንግሥቱ ላይ ተከታታይ ተቃውሞዎችና ግጭቶች ይከሰቱ ነበር። አገር አቀፉ የቱኒዚያ አጠቃላይ የሠራተኛ ማኅበር (UGTT) አመራር ከመንግሥት ጋር በመሞዳሞድና ነፃነቱን በመጠበቅ መሀል ሲዋልል ቆይቶ ወደ አብዮቱ መቃረብም ወደ ራስ-ገዝነቱን ያደላ ቢሆንም ከሥር ያሉት ማኅበራት ግን ለነፃነታቸው ፍጹም ቀናኢ የነበሩና መብታቸውን ለማስከበርና ጥቅማቸውን ለመጠበቅ ከመንግሥትም ጋርም በተከታታይ ግጭቱ ውስጥ የሚገቡ ነበሩ። መንግሥትም አገሪቷን ከቅኝ ግዛት በማላቀቅ ሂደት ቁልፍ ሚና የተጫወተውን በሕዝብ ዘንድም ከፍተኛ ክብር የሚቸረውን የሠራተኛውን እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ከማዳከም ይልቅ የሕዝብ የስሜት ግለት መለኪያ አድርጎ መጠቀሙ የአባል ማኅበራት ከነበራቸው ነፃነት ጋር ተዳምሮ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጭ የሆነ አማራጭ የፖለቲካ ኃይል በሠራተኛ ማኅበሩ ዙሪያ የሚከማችበት ዕድል ሰጥቶታል። ሠራተኛ ማኅበሩ በተለምዶ የሠራተኛ መብትና ጥቅም ጉዳይ ተብለው በሚወሰዱት ጉዳዮች ሳይገደብ በአገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሕይወት ላይ ተሳትፎ በማድረግ ልማዱም የሚታወቅ ነበር። ይህም ሁኔታ ሠራተኞች በአመጹ መቀስቀስ ማግሥት ተከታታይና ስኬታማ የሥራ ማቆም አድማ በማካሄድ የመንግሥትን አቅም ሽባ በማድረግ ባልጸና መሠረት ላይ የቆመ መሆኑን አጋለጡ። በሌላ አነጋገር የሕዝቡን ብሶትና ጥያቄ ቀምሮና አደራጅቶ የራሱን እርምጃ የሚወስድ አንጻራዊ ነፃነት ያለው የፖለቲካ ማዕከልና ድርጅት በሌለበት ሁኔታ እንኳን አንድ ሙሃመድ ቡአዚዚ ቀርቶ ሌሎች በርካቶች ራሳቸውን ቢያጋዩ ጉዳዩ «ጉድ አንድ ሰሞን!» ተብሎ የሚታለፍ ክስተት ከመሆን አልፎ ትርጉም ያለው እንቅስቃሴ መፍጠር አይሳካለትም ነበር ማለት ነው።

በተመሳሳይ መልኩ ሊዛ አንደርሰን የተባሉ ጸኃፊ ቱኒዚያ በአመጹ ማግስት በእስላማዊ ወንድማማችነት መንግሥት ቁጥጥር ሥር ትንሽ ዘግይቶም በወታደራዊ ኃይሉ መዳፍ ከወደቀችው ግብጽና በእርስ በርስ ጦርነት አሳሯን ከምታዬው ሊቢያም የተለየች አገር እንደነበረች ያወሳሉ። እንደ እሳቸው እምነት የቤን አሊ መንግሥት የመናገር ነፃነትን በማፈንና የፕሬስ ነፃነትን ባለመፍቀድ ቢነቀፍም ቱኒዚያ ከአረቡ ዓለም ምርጥ የተባለ የትምህርት ሥርዓት፣ ሰፊ የመካከለኛ መደብና ጠንካራ የተደራጀ የሠራተኛ እንቅስቃሴ የነበራት አገር እንዲኖራት አስችሏል። የንግዱ ዘርፍ ከፕሬዝዳንቱ ጋር በተለያየ መልኩ በተሳሰሩ ሰዎች ቁጥጥር ስር ቢወድቅም የመንግሥት ቢሮክራሲው ግን በጥቃቅን ጉቦዎች ያልተተበተበ በአንጻራዊ ጤነኝነት ላይ የሚገኝ እንደነበርና የመከላከያ ኃይሉም ግብጽን ከመሰሉ አገራት በተቃራኒው በኢኮኖሚውም ሆነ በአገሪቱ ፖለቲካ ሕይወት የረባ ሚና ያልነበረው ደካማ እንደነበረ ይከራከራሉ። ይህም ቱኒዚያን የዓረቡ ዓለም አብዮት ከዳሰሳቸው አገራት «በስተቀር» ሆና ብቅ እንድትል አድርጓታል ነው የእሳቸው ሙግት።

የቱኒዚያ የዴሞክራሲ ሽግግርና የሠራተኛ ማኅበራት ሚና

አመጹ በተቀሰቀሰ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በቱኒዚያ ሁሉም ነገር እንዳልነበር ሆነ። ፕሬዝዳንት ቤን አሊ ለሃያ ሦሰት ዓመታት አዛዥ ናዛዥ ያደረጋቸው የሞቀ ፎቴያቸውን የሕዝብ አመጽ ሲለበልበው እግሬ አውጭኝ ብለው ወደ ሳውዲአረቢያ ኮበለሉ። ይህን ወሳኝ ፍጻሜ ተከትሎ ቱኒዚያ አምባገነን መሪዋን ሸኝታ አዲስ ባለአደራ መንግሥት በማቋቋም ለዴሞክራሲ ሽግግር የተዘጋጀች መሰለች። የቱኒዚያ አጠቃላይ የሠራተኛ ማኅበር (UGTT) የቤን አሊን መንግሥት በመጋፋት አቅሙን ያሰመሰከረ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በሥራ ማቆም አድማ ባለበት አቁሞ ሊያጫጫው እንደሚችል በተግባር ያሳዬ፣ በውስጠ ዴሞክራሲ አሠራሩና በአደረጃጀቱም በቱኒዚያውያን ልብ ውስጥ ከፍ ያለ ክብርን የተጎናጸፈ በመሆኑ የሽግግሩ ሂደት ይህን የመሰለ ድርጅት ወደ ጎን መግፋት አይቻለውም ነበር። በሽግግሩ ሂደት ከተሳተፉት ከየትኛዎቹም የፖለቲካ ማኅበራት በላይ የታፈረውና የተከበረውም የሠራተኛ ማኅበሩ ነበር። በተለይም በሽግግሩ ማግስት አቅማቸውን አስባሰበው ብቅ ያሉ እስላማዊነትን የሚያቀነቅኑ የፖለቲካ ኃይሎችን ለመገዳደርና ወደ መስመር ለማስገባት የሠራተኛ ማኅበሩን ያህል የፈረጠመ ጡንቻ ያለው የተደራጀ ኃይል ቱኒዚያ አልነበራትም። 

በ2011 በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምርጫ ኢናሃዳ የተሰኘው ለዘብተኛው እስላማዊ ፓርቲ ከፍተኛውን የፓርላማ ወንበር ቢያሸንፍም በጽንፍ ረጋጭ እስላማዊ ኃይሎችና የሃይማኖትና የመንግሥትን መለያየት የሚያቀነቅኑ ዓለማዊ ሊበራል ኃይሎች መካከል የተካረረ ፍጥጫ ተከሰተ። በተለይ የሊበራል ኃይሉን የሚመሩት ሰዎች የጽንፍ ረጋጮቹ የጥቃት ኢላማ መሆናቸው የቱኒዚያን ማኅበረሰብ የከፋፈለ ነበር።  የሽብር ጥቃቶች ቁጥራቸው ያሻቅብ ገባ። ዝነኛ የተቃውሞ ፖለቲካ አመራሮች በጽንፈኞች በተቀነባበር ጥቃት ድንገት ተቀጠፉ። ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት በመከሰቱ ኑሮው የሚቀመስ አልሆን አለ። ይህ ውጥረት ቀስበቀስ የአገሪቱን ጅምር ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ቅርቃር ውስጥ ከተተው። ትንሿ የሰሜን አፍሪካ አገር የዴሞክራሲ ተስፋዋ ተጨናግፎ ወደ መፈራረሱ የምታዘግም መሰለች።

የአገሪቱ የዴሞክራሲ ሽግግር የተቀለበሰ በመሰለበት በዚያ አስጨናቂ የ2013 በጋ በቱኒዚያ አጠቃላይ የሠራተኛ ማኅበር (UGTT) ፊታውራሪነት የሚመራው አራትዮሾ የሲቪል ማኅበራት ጥምረት እጁን አስረዘመ። የተለያየ ጽንፍ ይዘው እየተጓተቱ አገሪቷን ወደ መፍርሻ መንገዷ ሲያመላክቷት የነበሩትን የፖለቲካ ኃይሎች ፍጥጫውን አርግበው ጉዳያቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ የሚፍቱበት ጊዜ ያኔ መሆኑን በሚገባቸው ቋንቋ ነገራቸው። የካርኒጌ ኢንዳውመንት ለዓለማቀፍ ሰላም ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሳራ ቼየስ እንደሚያስረዱት የአራትዮሹ የሲቪል ማኅበራት ጥምረት ጣልቃ መግባት ልዩነት ፈጣሪ ነበር። የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲገቡ ያስቻለና መነጋገር የማይፈቅዱት ኃይሎችን ወደዱም ጠሉም አንዳቸው ያንዳቸውን ሀሳብ እንዲያደምጡና ውይይት እንዲጀምሩ ያደረገ ነበር።

የፖለቲካ ፍጥጫው ጡዘቱ ላይ በነበረበት ወቅት የሲቪል ማኅበራቱ ጥምረት የውይይትና የፖለቲካዊ መቸማቸሚያ ወሳኝ መሣሪያ ሆኖ ብቅ አለ። ፈርጣማውና በቱኒዚያውያን ዘንድ እጅግ የተከበረው የሠራተኛ ማኅበሩ ዋና ጸኃፊ ሁሴኒ አባሲ ቱኒዚያ አንጻራዊ ሰላም እንድትጎናጽፍ ያሳችላትን የፖለቲካ መቻመቸም ያስገኘውን ድርድር በቁልፍ አደራዳሪነት ለመምራት ቻሉ። ብዙ ውጣ ውረድ የታየበት ድርድር የእሰላማዊ መንግሥት ሥልጣኑን ለሽግግር አስተዳደር እንዲያስረክብ፣ የመንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሌላ ኃላፊነት ይዞ ባለበት እንዲቀጥል፣ አዲስ ምክር ቤት በምርጫ እንዲቋቋምና ከሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሁለት ሁለት ተወካይ ያለ ምርጫ እንዲሳተፍ፣ ረቂቅ ሕገ-መንግሥት ይፋ የሚሆንበት ዕቅድ የሰፈረበት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ። በእርግጥ ድርድሩ በመጀመሪያ ሁሉንም ጉዳይ በስምምነት ለመፈጸም አላስቻለም ነበር። ስምምነት ላይ ለመድረስ የተቸገሩበት ነጥቦች ቢኖርም በድርድሩ ሂደት የተገኙ ልምዶች፣ እንደ ቀለድ ወደ ጎን ከማይገፉት የሲቪል ማኅበራቱ ጥምረት አደራዳሪዎችና የውጭ ኃይሎች ለድርድር የሚያስገድድ ድጋፍ ተዳምሮ በራስ መተማመን ስሜት ወደ ድርድር በመግባታቸው መልካም ውጤት መመዝገብ ችሏል።

በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ወደ መፍረስ ጠርዝ ተቃርባ የነበረችው ቱኒዚያ አሁን በሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲ መንገድ ላይ ነች። በኅብረተሰቡ መካከል ያሉት ክፍፍሎች ሙሉ በሙሉ ባይወገዱም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች በንቃት ከተሳተፉበት ድርድርና መቻመቸም የፈነጠቀው ተስፋ የሚሰጥ ሁሉም ያሸነፈበት ሁኔታ በአብዛኛው ቱኒዚያዊ በበጎ ታይቷል። የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ሽልማቱን ለአራትዮሹ ቡድን የሰጠበትን ምክንያት ሲያብራራ ይህንኑ ሀቅ ነው ያሰመረበት። «የሽልማቱ ዓላማ አሁንም ከባድ ችግሮች ቢደቀኑባቸውም ለአገራዊ ወንድማማችነት መደላድል ማበጀት የተሳካላቸውን ቱኒዚያዊያን ለማበርታታትና ይህም ለሌሎች አገሮች እንደ ማሳያ ሆኖ እንደሚያገለግል ኮሚቴው ተስፋ በማድረጉ ነው።» ብሏል ኮሚቴው በይፋዊ መግለጫው። ለዚህ ወሳኝ ስኬት መገኘትም የአራትዮሽ ቡድኑ ወሳኙን ሚና መጫዎቱንና አገሪቱን ለዴሞክራሲ ሽግግር እንድትበቃ እንዳደረጋት ኮሚቴው ጠቅሷል። 

በተመሳሳይ መልኩ የካርኒጌ ኢንዳውመንት ተመራማሪ የሆኑት ሳራ ቼየስ «የአራትዮሽ ቡድኑ የተገኘው ውጤት እንዲመጣ እጅግ ጠንክሮ ሰርቷል። ነገሩ ያማሩ ቃላትን መጠቀም የሆነ ዓይነት አቋም የማያዝ ጉዳይ አልነበርም። የአራትዮሽ ጥምረቱ አመራሮች ድርድሮ ተጀምሮ እሰኪጨርስ ሙሉ ሌሊቶችን የፖለቲካ ተሳታፊ ኃይሎችን በማግባባት፣ በማስተማር፣ በመርዳትና ቆፍጠን ብለው አገሪቱ ወጥሮ ለያዛት ቀውስ መፍትሔ እንዲፈልጉ ግፊት በማድረግ አሳልፈዋል።» 

የሠራተኛ ማኅበሩ መሪ የሆኑት ሁሲን አባሲ ከሽልማቱ በኋላ ለሮይተርስ እንደተናገሩት “ሽልማቱ ውይይት ወደ ቀናው መንገድ እንደሚወስድና በአካባቢያችን የሚገኙ አገራት ነፍጥ ጥለው ለንግግር ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመለሱ መልዕክት ያስተላለፈ ነው።» አባሲ በአሜሪካ የሠራተኛ ማኅበሩን ሥራዎች ለማክበር በተካሄደ ፕሮግራም «የኖቤል ሽልማቱ ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የሠራተኛ ንቅናቄዎች የተሰጠ ነው።  ሽልማቱ በተጨማሪም ሠራተኛ ማኅበራት በመንግሥት አስተዳደር፣ በማኅበራዊ ምክክሮሽ እኩል ሚና መጫወት እንደሚችሉና ብዙ ጊዜም ወሳኝ አመራር መስጠት እንደሚችሉ ያስገነዘበ ነው።» የአባሲ አስተያየት በአሁኑ ወቅት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት፣ በየካቲቱ አብዮትም ጨዋታ ቀያሪ ታሪካዊ ሚና የነበረውን የኢትዮጵያ ላባደሮች ንቅናቄ ከፖለቲካ ስሌቱ ውጭ አድርገው ለሚያስቡ ሰዎች መልሰው ጉዳዩን እንዲፈትሹ የሚያስገነዝብ ነው፡፡


ፀሃፊ፦ Biniyam Menberework (ቢኒያም መንበረወርቅ)