ሼር ኢትዮጲያ እና የባቱ/ዝዋይ ከተማ ነዋሪዎች ችግር

የሚከተሉት በፅሑፉ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቃላቶች የአካባቢ ነባር ስሞች ሲሆኑ ትርጉማቸውም እንደሚከተሉት ናቸው፤

 • ባቱ ማለት ዝዋይ ሲሆን ባቱ ከተማ ማለት ዝዋይ ከተማ ማለት ነው።
 • ሐሮ ደምበል ማለት የዝዋይ ሐይቅ ማለት ነው።

1. መግቢያ
ኢንቨስትመንት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ ከመሆኑም በላይ የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ አያጠራጥርም። ለዚህም የኢንቨስተሮች ሚና ትልቅ በመሆኑ ኢትዮጵያም የኢኮኖሚ እድገቷን ለማፋጠን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑ ቦታዎችን ለይታ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችንና የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮችን በማሳተፍ ላይ ትገኛለች። ኢንቨስተሮች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ የኢንቨስተመንት ሴክተሮች ቢኖሩም የኔዘርላንድ ኢንቨስተሮች ጌሪት እና ፔቴር ባርንሁን (Gerrit and Petere Barnhoon) የተባሉት የሼር ኢትዮጵያ ባለቤቶች በባቱና አዳሚ ቱሉ ከተሞች አካባቢ የተሳተፉበት የአበባ እርሻ አንዱ ነው። ይህ ድርጅት ከተሳተፈበት የኢንቨስትመንት ሥራ በተጨማሪ ለአካባቢው ህብረተሰብ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በመገንባት ማህበረሰቡ እየተገለገለበት ያለ ቢሆንም ድርጅቱ በአካባቢው ደህንነት ላይ እያመጣ ያለው የአካባቢው ብክለትና ጉዳት ከድርጅቱ ከሚገኘው ጥቅም በላይ ሚዛኑን የሚደፋ ሆኖ ይገኛል። ስለዚህ የዚህ ፅሑፍ ዋና ዓላማ በተጨባጭ በሼር ኢትዮጵያ ምክንያት በባቱ ከተማና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት በመዘርዘርና ጉዳቱን አስመልክተው የተፃፉ የተላያዩ ጥናቶችን በመዳሰስ በአካባቢው ላይ እየተከሰተ ያለውን አስከፊ ችግር ለህዝብና መንግስት ግልፅ በማድረግ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲበጅለት የመፍትሔ ሀሰብንም ጭምር ማቅረብ ነው። ፅሑፉ ሼር ኢትዮጵያ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት ብቻ ላይ ያተኮረ ሳይሆን ድርጅቱ ለፌዴራል መንግስትና ለአካባቢው ህብረተሰብ እያስገኘ ያለውን ጥቅምም ጭምር ይዘረዝራል። 

ፅሑፉ በስምንት ክፍል የተዘጋጀ ሲሆን 1ኛው ክፍል መግቢያ፣ 2ኛው ስለ ሐሮ ደምበል ጠቅላላ መረጃ፣ 3ኛው የተፈጥሮ ኃብቶችንና የአካባቢው ደህንነትን ለመጠበቅና ለማንከባከብ የወጡ የፌዴራልና የኦሮሚያ ክልል የህግ ማዕቀፎች፣ 4ኛው ስለሼር ኢትዮጵያ ጠቅላላ መረጃ፣ 5ኛው ሼር ኢትዮጵያ ለፌዴራል መንግስትና ለአካባቢው ህብረተሰብ ያስገኙአቸው ጥቅሞች፣ 6ኛው ሼር ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ኃብቶችና አካባቢው ህብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳቶች፣ 7ኛው ማጠቃለያ እና 8ኛው የመፍትሔ ሀሳቦችን የሚያቀርቡ ናቸው።

2. ሐሮ ደምበል
ሐሮ ደምበል ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በ160km ላይ የሚገኝ ሲሆን የሐይቁ ስፋት 434km2 እና የሐይቁ ዙሪያው ርዝመት 137km ነው። የሐይቁ ከፍታ ከውሃ ጠለል በለይ ከ1600m – 1700m ነው። የሐይቁ አማካይ ጥልቀት 2.5m ሲሆን ከፍተኛ ጥልቀት ደግሞ 9m። በጠቃላይ የሐይቁ ተፋሰስ 3 ወንዞችን የያዘ ሲሆን እነሱም የቃታር ወንዝ፣ የመቂ ወንዝ እና የቡልቡላ ወንዝ ናቸው። ከነዚህ ወንዞች የቃታርና የመቂ ወንዝ ከሰሜን በኩል ወደ ሐይቁ የሚፈሱ ሲሆኑ የቡልቡላ ወንዝ ደግሞ ከሐይቁ በስተደቡብ በኩል ወጥቶ ወደ አብጃታ ሐይቅ የሚፈስ ነው። ሐይቁ በ3 የምስሥራቅ ሸዋ ዞን ወረዳዎች የተከበበ ሲሆን እኚ ወረዳዎችም ከሐይቁ በስተምዕራብ በኩል የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረደ፣ ከሐይቁ በስተደቡብ ተነስቶ እስከ ሐይቁ በስተሰሜን ድረስ የዝዋይ ዱግዳ ወረዳ እና ከሐይቁ በስተሰሜን ምዕራብ በኩል የዱግዳ ቦራ ወረዳ ናቸው። ባጠቃላይ ወደ 2 ሚሊየን የሚጠጉ በአካባቢ የሚኖሩ ህዝቦችና ወደ 1.9 ሚሊየን የሚጠጉ እንሰሳቶች ህወታቸው በዝዋይ ሐይቅና ተፋሰሱ ላይ የተመሠረተ ነው (Hayal Desta, et al, 2017, pp. 61)። ስለዚህ የዚህ ሐይቅ መጎዳት ማለት የዚህ ሁሉ ስነ ሕይወት መጎዳት ማለት ስለሆነ ሐይቁ እንደ ሐረማያ ሐይቅ እንዳይደርቅ ለማዳን የሁሉም ዜጋ ድጋፍ ያስፈልጋል።

ሐሮ ደምበል ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ከሚገኙ ሐይቆች አነስተኛ የጨው መጠን ያለው ሲሆን ለመጠጥም ሆነ ለመስኖ ሥራ በጣም ምቹ የሆነ ሐይቅ ነው። ሐይቁ ብርቅዬ በሆኑ የተለያዩ ወፎችና የተለያዩ የአሳ ዚርያዎች እንዲሁም በጉማሬ ሃብት ይታወቃል። በተጨማሪም ሐሮ ደምበል 5 ደሴቶች ያሉት ሲሆን 5ቱም ደሴቶች ታሪካዊ የሆኑ የኦርቶዶክስ ሐይማኖት ገዳማት አሉት። ደሴቶች ላይ በ11ኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ዘመነ-መንግስት ታቦተ-ፅዮን እንዳረፈችበት ይነገራል።

ባቱ ከተማ ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በ160km ላይ የሚትገኝ ከተማ ሲትሆን ከተሟ የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ርዕሰ ከተማ ናት። ባቱ ለእንግዶችና ለመንገደኞች የተዘጋጁ ጥራታቸውን የጠበቁ የተለያዩ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ያላት ከተማ ሲትሆን ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ የሚጓዙ መንገደኞች ለቁርስ፣ ለሚሳና ለእራት እንዲሁም ለአዳርም ጭምር የሚያርፉባት ምቹ ከተማ ናት። ከሐይቁ የሚቀርብ የአሳ ምግብና በአካባቢዋ ከሚገኘው የካስትል (Castel) እና የወይን (Wine) እርሻ የሚዘጋጁ መጠጦች ከተሟን ምቹ የእንግዶች ማረፊያ ያረጓታል።

ምስል 1፡ ሐሮ በምበል (የዝዋይ ሐይቅ)ና ተፋሰሶቹ ከሀያል ደስታና ሌሎቹ የተወሰደ።

3. የተፈጥሮ ኃብቶችንና የአካባቢ ደህንነትን ለመጠበቅና ለማንከባከብ የወጡ የህግ ማዕቀፎች 

የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱ ዜጎችና ነወሪዎች ደህንነታቸው የተጠበቀላቸው አካባቢ ውስጥ እንዲኖሩ እና የተፈጥሮ ሀብቶችን ለመጠበቅም ሆነ ለማንከባከብ በፌዴራል መንግስትመ ሆነ በክልሎች መንግስታት በመርህ ደረጃ የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን ነድፎ እየሰራ ይገኛል። ሆኖም ግን በተግባር በባቱ አካባቢ በነዋሪዎች ላይም ሆነ በተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ካሉት የህግ ማዕቀፎቹ ጋር ከመቃረኑም በላይ ነዋሪዎቹ ለመጠጥ ውሃ ችግር እየተጋለጡ ይገኛሉ።

3.1 በፌዴራል መንግስት የወጡ የህግ ማዕቀፎች

የተፈጥሮ ኃብቶችንና የአካባቢ ደህንነትን ለመጠበቅ ከወጡት ህጐች በመጀመሪያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህግ-መንግስት እናገኛለን። የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ፤ የተፈጥሮ ኃብቶችንና የአካባቢ ደህንነትን ለመጠበቅ ከወጡት ህጐች በመጀመሪያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህግ-መንግስት እናገኛለን። 

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀፅ፤ 

 1. “ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አለቸው” ይላል። 
 2.  “መንግስት በሚያከሄዳቸው ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸው የተነካባቸው ሰዎች ሁሉ በመንግስት በቂ እርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ መዘዋወሪን ጨምሮ ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት አላቸው” ይላል። 

በተጨማሪም አንቀፅ 92 ንዑስ አንቀፅ፤

 1. “መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንጹህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖረው የመጣር ኃላፊነት አለው” ይላል።
 2. “ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአካባቢውን ደህንነት የሚያናጋ መሆን የለበትም” ይላል።
 3. “የህዝብን የአካባቢ ደህንነት የሚመለከት ፖሊሲና ፕሮግራም በሚነደፍበትና ሥራ ላይ በሚውልበት ጊዜ የሚመለከተው ህዝብ ሁሉ ሀሳቡን እንዲገልፅ ማደረግ አለበት” ይላል።
 4. “መንግስትና ዜጎች አካባቢያቸውን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸው” ይላል።


የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን በ1995 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 9/1995 የተቋቋመ ሲሆን የባለሥልጣኑ ዓላማ፤

የአገሪቱን የሶሻልና የኢኮኖሚ ልማት እንቅስቃሴዎች የሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉ የሰውን ልጅ ደህንነት ለመንከባከብ እንዲሁም ህልውናው የተመሠረተበትን የአካባቢ ሀብቶች ዘላቂነት ባለው መንገድ ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ለመጠቀም በሚያስችል ሁኔታው መካሄዳቸውን ማረጋገጥ ይሆናል” ይላል።

ይህ ባለሥልጣን በ1997 ዓ.ም የኢትዮጵያ አካባቢ ፖሊሲ ያወጣው ሲሆን የፖሊሲው ወና ዓላማ (ተቀራራቢ ትርጉሙ) ፤

“የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጤንነትና የህይወት ጥራትን ለማሻሻልና ለማሳደግ እና ባጠቃላይ ተፈጥሮአዊ፣ ሰው-ሰራሽና ባህላዊ ሀብቶችንና አካባቢን በከፍተኛ ቁጥጥርና ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የወደፊቱ ትውልድ የራሳቸውን ፍላጎቶች የመሟላት አቅማቸውን ሳይሻማባቸው የዛሬውን ትውልድ ፍላጐቶች የሚያሟላ ቀጣይነት ያለው መህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ማስቀጠል ነው”። “በጣም ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የመሬት፣ የአየርና የውሃ ብክለትን መከላከል ነው” ይላል(EPE, 1997, PP. 3)።

የኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አዋጅ ቁጥር 769/2012 በአንቀፅ 38 ሥር እንዲህ ይላል፤ 

“ማንኛውም ባለሀብት የአገሪቱን ህጐች በማክበር የኢንቨስትመንት ተግባሩን ያከናውናል። በተለይም የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ሲያደርግ ለአካባቢ ጥበቃ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል”።

የኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶች ማኔጅምንት ፖሊሲ ዓላማ ተቀራራቢ ትርጉሙም እንዲህ ይላል፤

“ሁሉንም የውሃ ሀብቶችንና ውሃ ውስጥ የሚኖሩትን ዕፅዋቶችን ዘለቄታዊነት ላይ በተመሠረተ መልኩ ማቆየት፣ መጠበቅና መንከባከብ ነው” ይላል(EWRMP, 2010, pp 10)።

በስተመጨረሻም እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም የወጣው ብሔራዊ የመጠጥ ውሃ ጥራት ቁጥጥርና ስትራቴጂ ዋና ዓላማው፤

“ንፁህ ያልሆነ ውሃን በመጠጣት የሚመጡትን በሽታዎችንና ሞትን ለመቀነስ እና የህብረተሰቡን ጤንነት ማሳደግ” ይላል (WQMS, 2011, pp. 20)።


3.2 በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የወጡ የህግ ማዕቀፎች

በክልል ደረጃም የተፈጥሮ ኃብትና አካባቢ ጥበቃን የተመለከቱ ህጎች ከክልሉ ሕገ መንግስት የሚጀምሩ ሲሆኑ በፌዴራል ህገ-መንግስት ውስጥ አንቀፅ 44 ሥር የተደነገገው በክልሉ ህገ-መንግስት ውስጥም በተመሳሳይ አንቀፅ 44 ሥር ተደነግጓል። በተጨማሪም በፌዴራል ህገ-መንግስት አንቀፅ 92 ሥር የተደነገገው ደግሞ በክልል ህገ-መንግስት አንቀፅ 107 ሥር ተደነግጓል። ድጋሚ መፃፍ አያስፈልግም።

በኦሮሚያ ክልል ለኢንቨስተመንት ተግባር የሚውል የገጠር መሬት አጠቃቀምን ለመወሰን በወጣው አዋጅ 3/1987 አንቀፅ 5 ንዑስ አንቀፅ፤ 

(1) የክልሉን ሕዝብ በተለይም የአርሶ አደሩንን መብት በማንኛውም መልኩ በሚቃረን ሁኔታ መሬት ለኢንቨስተሮች ሊሰጥ አይችልም።

የኦሮሚያ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን መቋቋመያ አዋጅ 43/1993 

 • አንቀፅ 5 ንዑስ አንቀፅ፤ 

(1) የተፈጥሮ ሀብት ጉዳት ሳይደርስበት ተጠብቆ በሥርዓት በመጠቀምና በማልማት ለአሁኑና ለቀጣዩ ትውልድ የኢኮኖሚና ማኀበራዊ ልማት እድገት ዘላቂ ጥቅም መስጠት እንዲችል ማድረግ።
(3) ማንኛውም ልማት የአካባቢ ጥበቃና የኢኮሎጂ ሚዛን ደንብና ሥርዓት ላይ ተመርኩዞ አካባቢን ሳይበክልና የተፈጥሮ ሚዛን ሰያዛባ መካሄዱን ማረጋገጥ።

 • አንቀፅ 8 ንዑስ አንቀፅ፤ 

(2) የገጠር መሬት የኪራይ ውል ከሰላሣ ዓመት ሊበጥ አይችልም።

የኦሮሚያ የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀምን ለመወሰን በወጣው አዋጅ 56/1994 

 • አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ፤

(1) ማንኛውም አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር በይዞታቸው ሥር ያለውን መሬት እስከ ግማሽ ድረስ የማከራየት መብት አለው።
(2) የክራይ ዘመንን በተመለከተ በባሕላዊ አስተራረስ ዘዴ በሚጠቀሙ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች መካከል የሚደረገው የክራይ ዘመን እስከ 3 ዓመት ሲሆን የክራይ ዘመን ለዘመናዊ የግብረና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች እስከ 15 ዓመት ይሆናል።

 • አንቀፅ 12 ንዑስ አንቀፅ፤

(1) መንግስት በአርሶ አደሩ ወይም በአርብቶ አደሩ ያልተያዘውን መሬት ሊያከራይ ይችላል።
(2) በዚህ አንቀፅ በንዑስ አንቀፅ (1) መሠረት የሚደረገው ስምምነት የአካባቢውን አርሶ አደር ወይም አርብቶ አደር ጥቅም የሚነካ መሆን የለበትም።

 • አንቀፅ 13 ንዑስ አንቀፅ፤

(1) ተግባራዊ እየሆነ ባለው የክልሉ የኢንቨስትመንት ሕግ መሠረት ማንኛውም የግል ባለሀብቶች የገጠር መሬት ማግኘት ይችላሉ፣ ያገኙትን መሬት በአግባቡ የመንከባከብና የመጠበቅ ኃላፊነት አለባቸው።
(2) የግል ባለሀብቶች የተሰጣቸውን መሬት ቢያንስ 1% በአካባቢው ተስማመሚ በሆነ የዛፍ ዝሪያ መሸፈን አለባቸው።

የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ ለመወሰን በወጣው አዋጅ 176/2005 አንቀፅ 11 ንዑስ አንቀፅ፤

(4) ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ በአጥጋቢ ሁኔታ ለማስቀራት የማይቻል ከሆነ የሚደርሰው ተፅዕኖ በአካባቢው ተፈጥሮ ሀብት ወይም በህዝብ ኑሮና ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን ካመነና ፕሮጀክቱ ሥራ ላይ እንዳይውል መከላከል አለበት።

 • አንቀፅ 14 ንዑስ አንቀፅ፤

(1) የፕሮጀክት ባለቤት የአካባቢ ተፅዕኖ ግምገማ በማካሄድ በአካባቢ ላይ የሚደርሰውን ተፅዕኖ አስቀድሞ በመለየት የሚደርሰውን ተፅዕኖ የሚያስቀርበት ወይም ማጠቃለያ ዘዴ በጥናት ዘገባ ውስጥ በማካተት ሕጋዊ ከሆኑ ሰነዶች ጋር የአካባቢ ተፅዕኖ የጥናት ዘገባውን ለኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የገጠር መሬትና አካባቢ ጥበቃ ቢሮ ማቅረብ አለበት።

 • አንቀፅ 16 ንዕስ አንቀፅ፤

(2) ፈቃድ ያገኘ የፕሮጀክት ባላቤት የተሰጠውን ግዴታ በገባው ቃል መሠረት ፕሮጀክቱን ካልተገበረ ቢሮው መወሰድ ያለበትን የእርምት እርምጃ በመግለጽ የፅሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠት አለበት።
(3) የፕሮጀክቱ ባለቤት ፈቃድ አግኝቶ የተሰጠውን ግዴታ ቃል በገባው ማስጠንቀቂያ ሊጽፍበት ወይም ፈቃድ እንዳይታደስ ማድረግ ይችላል። ፈቀድ ሰጪው አካልም ቢሮው ያስተላለፈውን ውሳኔ በማክበር የተሰጠውን ፈቃድ መከልከል ወይም መሠረዝ አለበት።

4. ሼር ኢትዮጵያ (Sher Ethiopia)

4.2 የባቱ ከተማ ሼር ኢትዮጵያ

ሼር ኢትዮጵያ (Sher Ethiopia) ከሐሮ ደምበልና ከባቱ ከተማ በስተደቡብ በኩል ሐሮ ደምበልን በመጠቀም የተለያዩ አበባዎችን እያመረተ ለውጭ ገበያ በዋናነት ለሆላንድ ገበያ በተለይም በቫላንቲን ዴይ (Valentine Day) የሚያቀርብ የአበባ እርሻ ነው። የእርሻው ባለቤቶችና አንቀሳቃሾች እንዲሁም ኃላፊዎች የሆላንድ ባለሃብቶች የሆኑት ጌሪት እና ፔቴር ባርንሁን (Gerrit and Peter Barnhoon) ሲሆኑ በሀገራችን ውስጥ በ3 ቦታዎች ማለትም በዝዋይ፣ በቆቃና በአዳሚ ቱሉ ከተሞች አካባቢ የአበባ እርሻ አላቸው። እኚ ኢንቨስተሮች ወደ ሀገራችን ከመግባታቸው በፊት ኬኒያ የነበሩ ሲሆን ወደ ሀገራችን የገቡት በ1996 (እ.ኤ.አ 2004) የኢትዮጵያ መንግስት በሀገራችን ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ባቀረበላቸው ጥሪ እንደሆነ እራሳቸው በተባለው ዌብሳይት ላይ እንዲ በማለት ይገልፁታል።

“In 2004, Gerrit and Peter Barnhoorn were asked by the Ethiopian Government to set up a farm in Ethiopia similar to their successful socially responsible flower farm in Kenya.”

ከላይ እንደተመለከትነው ኬኒያ በነበሩበት ወቅት እራሳቸውን በኬኒያ ውስጥ ለማህበራዊነቱ ኃላፊነት ያለው ውጤታማ የአበባ እርሻ (… their successful socially responsible flower farm in Kenya), ብለው ቢገልፁም በኬኒያ ውስጥ እነሱ ተሰማርተው በነበሩበት አካባቢ የሚገኘውን Naivasha ሐይቅ ላይ ያደረሱትን ጉዳት (አሁን ደግሞ በሐሮ ደምበል ላይም እየደረሱ ያለውን ጉዳት) በተመለከተ Melafia (2009) እንዲህ ይላል፤ የአበባ እርሻ ከመቋቋሙ በፊት Naivasha ሐይቅ በተለያዩ ወፎች ከሚታወቁ ዋና ዋና 10 የዓለም ሀገራቱ አንዱ እንደ ነበር እና የአባባ እርሻ ከተቋቋመ በኃላ የሰውን ልጅ ጨምሮ የብዙ የተለያዩ እንሰሳት እየጠፉ እንደሆነ ይገልፃል፤

“Prior to the proliferation of the flower farms and the subsequent decline in water levels, Lake Naivasha was “one of the world’s top ten sites for birds, with more than 350 recorded species. …It was also renowned for its sparkling clear water and the papyrus plants and water lilies that could be found at its edges. Much of this plant life has disappeared… The pesticides applied on the farms and in the greenhouses eventually end up in Lake Naivasha and in the ground water, endangering the areas people and wildlife, including hippos, fish and birds” (Melafia, 2009, pp. 18).

ሼር ኢትዮጵያ በ1997 (እ.ኤ.አ በ2005) በባቱ ከተማ አካባቢ 450 ሄክታር መሬት በሊዝ ከኢትዮጵያ መንግስት ወስዶ የተለያዩ አበባዎችን እያመረተ ለውጭ ገበያ እያቀረበ ይገኛል። ይህ የአበባ እርሻ ያረፈበት ባቱ ከተማ አካባቢ የሚገኘው መሬት በጣም ለም አፈር ያለ በመሆኑ እና ከጎኑ የሚገኘው አሁን የወይኒ እርሻ (Castel Vineyard) ያረፈበት መሬትን ጨምሮ በጣም ሰፊ የሆነ የመንግስት እርሻ (State Farm) የነበረበት መሬት ነበር። ሼር ኢትዮጵያ ከመቋቋሙ በፊት ያንን መሬት ላይ ካረፈው የመንግስት እርሻ የሚመረቱ የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች በዋናነት ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚውሉ ሲሆኑ የአካባቢ ተወላጆችም የዚሁ ተረፈ ምርት ተጠቃሚ ነበሩ። አሁን ግን በሚመረተው የአበባ ምርት እንኳን የአካባቢ ተወላጅ ይቅርና እንደ ሀገርም በዋናነት ለሀገር ውስጥ ገበያ የማይቀርብ (የማይፈለግ) ምርትን ለማምረት ሲባል ያን የመሰለ ለም መሬት ለወደፊት ምንም ዓይነት ሌላ ምርት ላላመምረት በአበባ ኬሚካል እየተበከለ ይገኛል። ይህ ማልማት ነው ወይስ ማጥፋት ነው?

ምስል 2፡ ባቱ ከተማ አካባቢ የሚገኘው ሼር ኢትዮጵያ ከfloralife.com የተወሰደ

4.2 በአዳሚ ቱሉ ከተማ አካባቢ የተቋቋመ አዲሱ የሼር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት

ባቱ ከተማ የሚገኘው ሼር ኢትዮጵያ ፕሮጄክቱን ለማስፋፋት ሌላ መሬት ስላስፈለገው ሌላ ተጨማሪ ሰፊ መሬት ከባቱ ከተማ በ6km ርቀት ላይ ከሚትገኘው አዳሚ ቱሉ ከተማ ከ200 ሄክታር በላይ መሬት ተከራይቶ በቡልቡላ ወንዝ ላይ የአበባ እርሻ እያመረተበት ይገኛል። ይህ መሬትም ባቱ ከነበረው መሬት ጋር የሚያመሳስለው በጣም ለም መሬት ስለሆነ ምርታማነቱ በጣም ከፍተኛ ነበር። ለየት የሚያደርገው ነገር ደግሞ ባቱ አካባቢ የነበረ የመንግስት መስኖ እርሻ የነበረበት ሲሆን በአዳሚ ቱሉ አካባቢ የሚገኘው የአበባ እርሻ ደግሞ የአርሶ አደሮች የይዞታቸው መሬት ነበር። የመሬቱ ባለቤቶች የሀለኩ ጉለንታ ቦቄ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ሲሆኑ ለዓመታዊ ቀለባቸው የሚሆናቸውን የተለያዩ ሰብሎችን በዝናብ ተጠቅሞ እየዘሩ ይጠቀሙበት ነበር። ይህ መሬት ከሚየመርታቸው ጤፍ፣ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ገብስ እና ቦሎቄ ዋና ዋና ምርቶች ሲሆኑ መሬቱ በጣም ለም ከመሆኑ የተነሳ የተዘራበትን ዘር ሁሉ ያመርት ነበር።

የአዳሚ ቱሉ ሼር ኢትዮጵያ የረፈበት መሬት ሙሉ ለሙሉ የኃለኩ ጉለንታ ቦቄ አርሶ አደሮች ሲሆን የነዚህን አርሶ አደሮች የመልማት ፍላጎታቸውን የተረዳ የልጆችና የሴቶች ልማት ማህበር ሪፍት ቫሊ (Rift Valley Children and Women Development Association) የተሰኘ ኢ-መንግስታዊ ነገር ግን ልማታዊ ድርጅት ከ1990 ጀምሮ ለአርሶ አደሮቹ ድጋፍ በማድረግና በብድር መልክ እየገዛቸው በወንዝ በኩል በሚገኘው ግማሽ መሬታቸው ላይ መስኖ እንዲጀምሩ አድርጓቸው ነበር። ከጊዜ ቆይታ በኃላ አርሶ አደሮቹ በሥራቸው ውጤታማ በመሆን የነበረባቸውን የድርጅቱን ብድር በመለስ እራሳቸውን ችሎ እስከ ዛሬ ድረስ እየሰሩበት ይገኛሉ። ሼር ኢትዮጵያ ያረፈበት መሬት ላይ አርሶ አደሮቹ ከጊዜ በኃላ የመስኖ ሥራቸውን ለማስፋፋት ዕቅድ ያላቸው ቢሆንም ከአቅም ማነስ የተነሳ ለጊዜው ሊሰሩበት አልቻሉም። መንግስት አግዟቸው መሬቱ ሙሉ በሙሉ በመስኖ ቢሸፈንላቸው የአርሶ አደሮቹ ትልቅ ምኞታቸው ነበር። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ መንግስት እንኳን ድጋፍ አድርጐላቸው የመስኖ ልማት ሊያስፋፋለቸው ይቅርና በዝናብ ተጠቅሞ አመታዊ የምግብ ፊጆታቸውን የሚያገኙበትን ለም መሬት ጫና አሳድሮባቸው አርሶ አደሮቹ መሬታቸውን ለሼር ኢትዮጵያ እንዲያከራዩ አደረገ። ይህንኑ Murphy የተባለ ፃፊው እንዲ በማለት ይገልፃል።

“Instances have also been reported of excessive government pressure on local land owners to sell their plots of land to the expanding flower companies. Many locals say they do not benefit at all from the flower farm presence” (Murphy, na, pp. 3).

በተጨማሪም በመርህ ደረጃ ግን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ‘ለውጪ ኢንቨስተሮች የሚከራየው መሬት አርሶ አደሮች የሌሉበት እንደሆነና በኢንቨስትመንት ምክንያት አርሶ አደሮች እንዳልተፈናቀሉ’ ይሉ ነበር። ይህንኑ Riedel, et al ከዚህ በታች ባለው መልኩ ያስቀምጣሉ፤

“Though the actual impact often is portrayed in a negative manner where displacement, forced work, low salaries and involuntary loss of land among small scale farmers is prominent, the Ethiopian Prime Minister Meles Zenawi argues that the land leased for foreign investors is unutilized lowland and states that no farmers have lost their land or have become displaced as a result of the investments” (Riedel, et al 2011, pp. 6).

ምስል 3፡ በአዳሚ ቱሉ የተጀመረ አዲሱ የሼር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት

ባጠቃላይ ሼር ኢትዮጵያ (የባቱና የአዳሚ ቱሉ) ብዙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ700 ሄክታር በላይ የያዘ (የኢንቨስትመንቱ ባለቤቶች 500 ሄክታር ብሉም) ሲሆን ጠቅላላ ከ17,000 በላይ (በአዳሚ ቱሉ ከተማ 6,000 እና በባቱ ከተማ 11,000) ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። የዚህ የአበባ እርሻ ባለሃብቶች የአካባቢ ነዋሪዎችን ለመደገፍ በተለያዩ የማህበራዊ የሥራ ዘርፎች ላይም የተሰማሩ ሲሆኑ ዋና ዋናዎቹ ትምህርት ቤቶችን መገንባት (ከ አፀደ ህፃናት ጀምሮ እስከ መሰናዶ ድረስ)፣ ለባቱ ከተማ የመጀመሪያ ሆስፒታል ግንባታ፣ ስታዲዮም ግንባታ እና የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያን ግንባታ ሲሆኑ በሌሎች ዘርፎችም ብዙ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ። ጥያቄው ግን ከሚያድርጉት ድጋፍና ከሚያደርሱት ጥፋት የቱ ያመዝናል? ነው።

5. ሼር ኢትዮጵያ ለፌዴራል መንግስትና ለአካባቢው ህብረተሰብ የስገኙኣቸው ጥቅሞች

5.1 ለፌዴራለ መንግስት ያስገኙአቸው ጥቅሞች

ሼር ኢትዮጵያ ለፌዴራል መንግስት ያስገኙአቸው ዋና ዋና ጥቅሞቹ፤

 • የመሬት ኪራይ፡ – የባቱ ሼር ኢትዮጵያ ያረፈበት መሬት የመንግስት እርሻ የነበረበት መሬት ሲለሆነ የመሬቱ የሊዝ ኪፍያ ሙሉ ለሙሉ ለፌዴራል መንግስት ነው። የመሬቱን የሊዝ ዋጋ በተመለከተ አንድ ሄክታር ለአንድ ዓመት በ25 ዶላር እንደተከራየ Gebhardt (2014) የተባለው ፃፊው ያስቀምጣል፤ 

“The Dutch flower growers I interviewed mentioned ten, fifteen, and twenty-five year leases, paying twenty five dollars per year per hectare” (Gebhardt, 2014, pp. 240)

 • የግብር ገቢ፡ – የአበባ እርሻ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ወደ ሥራ በመግባትና ምርቱን በመሻጥ ትርፍ እየገኘ ከሆነ በፊስካል ዓመቱ የትርፉ 30% ግብር ለኢትዮጵያ መንግስት እንደሚከፈል ድርጅቱ እራሱ የራሱ ዌብሳይት በሆነ afriflora.com ላይ ZEMBALA ለተባለው ሚዲያ ምላሽ ስሰጥ ገልጿል (ZEMBALA በሼር ኢትዮጵያ ላይ ድርጅቱ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በማሰመልከት ዶክዩመንተሪ አዘጋጅቶ እ.ኤ.አ መጋቢት 23 ቀን 2016 ዓ.ም ዘግቦ የነበረ የሆላንድ ሚዲያ ነው)። 

“Over the complete operating profit, full profit-based taxes are paid in Ethiopia or in the Netherlands, of 30% and 25% respectively of the fiscal profits.

በተጨማሪ Fasika Tadesse እ.ኤ.አ ኦክቶበር 11 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ ፎርቹን ላይ ባሳተመው ፅሑፍ ሼር ኢትዮጵያ ለፌዴራልና ለክልል መንግስት በወር ከ5 ሚሊየን ብር በላይ እንደሚከፍል ገልጿል።

“Sher pays more than five million Birr a month in the form of taxes and other expenses to the national and the regional governments.

 • የውጭ ሚኒዛሪ፡ – የአበባ ምርት ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች የመጀመሪያ ደረጃ ከሚይዙት አንዱ በመሆን ለሀገሪቱ ዋነኛ የውጭ ሚኒዛሪ ማስገኘ ሆኗል።
 • መሰረተ ልማት፡ – ለአካባቢ ህብረተሰብ መንግስት ሊያቀርባቸው የነበረውን የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶችን (ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታል፣ ስታዲዮም እና ወዘተ) በማቅረብ የመንግስትን ወጪ እየሸፈነለት ይገኛል።

5.2 ለአካባቢው ህብረተሰብ ያስገኙአቸው ጥቅሞች 

ሼር ኢትዮጵያ ለፌዴራል መንግስት ከሚያስገኘው ጠቅሞች በተጫማሪ በተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ በመሰማረት ለአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ የማህበራዊ ኃለፊነቶችን እየተወጣ ይገኛል። ከነዚህም ዋና ዋናዎቹ፤

 • የመሬት ኪራይ፡ – የአዳሚ ቱሉ ሼር ኢትዮጵያ የተቋቋመበት መሬት የአርሶ አደሮች መሬት በመሆኑ ለአርሶ አደሮቹ ለምን ኃይል ጊዜ እንደሆነ ባይገለፅላቸውም የመሬቱ ኪራይ ተሰጥቶአቸዋል። ይህም በመንግስት ደረጃ በምን ኃይል ብርና  በምን ኃይል ጊዜ እንደተስማሙ ባይታወቅም በተጨባጭ በአርሶ አደሮች እጅ የደረሰው ዋጋ ለአንድ ሄክታር መሬት ወደ 140 ሺህ ብር ገደማ የሚሆን ነው። 
 • የሥራ ዕድል ፈጠራ፡ – ባጠቃላይ ሼር ኢትዮጵያ (የባቱ ከተማና የአዳሚ ቱሉ ከተማ) ብዙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ17,000 በላይ (በአዳሚ ቱሉ 6,000 እና በባቱ 11,000) ለሚሆኑ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮላቸዋል።
 • ትምህርት ቤት ግንባታ፡ – ሼር ኢትዮጵያ ለባቱ ከተማ ነዋሪዎች ከአፀደ ሕፃናት ጀምሮ እስከ መሰናዶ ትምህርት ቤት ገንብቶላቸዋል። በገነባቸው ሁሉም ትምህርት ቤቶች የወንበሮቹ 50% ለሼር ኢትየጵያ ሰራተኞች ልጆች የሰጠ ሲሆን ቀሪው 50% ደግሞ ለአካባቢው ነዋሪዎች ነው። ቤተሰቦቻቸው የሼር ኢትዮጵያ ሰራተኞች የሆኑት ተማሪዎች በሼር ኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች በነፃ ይማራሉ።
 • ሆስፒታል ግንባታ፡ – ሼር ኢትዮጵያ ለባቱ ከተማ ነዋሪች ለከተማ የመጀመሪያ የሆነ ሆስፒታል ገንብቶላቸዋል። በዚህ ሆስፒታል የሼር ኢትዮጵያ ሰራተኞችና ልጆቻቸው በነፃ የሚታከሙ ሲሆን ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች እንደማንኛውም ሆስፒታል (እንደውም የዚህ ሆስፒታል ዋጋ በጣም ከፍተኛ ነው) እየከፈሉ ይታከማሉ።
 • ስታዲዮም ግንባታ፡ – ሼር ኢትዮጵያ የሼር ኢትዮጵያ ሰራተኞች እንዲጫወቱበትና እንዲሁም የተለያዩ ባዓላትን ለምሳሌ ሼር ዴይ (Sher Day) በማለት በዓመት አንድ ቀን ሰራተኞቹ እንዲያከብሩት ያዘጋጀውን የበዓል ቀን ሰራተኞቹ እንዲያከብሩት በራሱ ግቢ ውስጥ ስታዲዮም ገንብቶላቸዋል። ሆኖም ግን ይህ ስታዲዮም በባቱ ከተማ እና በአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረደ ውስጥ እንዲሁም እንደ ኦሮሚያ ክልል የሚደረጉ የተለያዩ የእግር ኳስ ውድድሮችን እያስተናገደ ይገኛል።
 • የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ቤተክርስቲያን ግንባታ፡ – ሼር ኢትዮጵያ ለሼር ኢትዮጵያ ሰራተኞች በራሱ ግቢ ውስጥ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ቤተክርስቲያን ገንብቶላቸዋል።
 • የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረደ ፍርድ ቤት ዕድሳት፡ – ሼር ኢትዮጵያ የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረደ ፍርድ ቤትን በማደስ እንዲሁም ኔትወርክድ (Networked) በማድረግ በፍርድ ቤት የሚሰጥ አገልግሎት እንዲቀላጠፍ አድርጎታል።
 • ሌሎች የተለያዩ ድጋፎች፡ – በባቱ ከተማ ውስጥ ለውስጥ ለሚሰሩ መንገዶች ድጋፍ ያደርጋል። በተጨማሪም የከተማ አስተዳደርም ሆነ የወረደ አስተዳደር የተለያዩ ፕሮግራሞችና ዝግጅቶች ሲኖራቸው በስፖንሰርነት መልክ የተለያዩ ድጋፎችን ያደርግላቸዋል።

6. ሼር ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ኃብቶችና አካባቢው ህብረተሰብ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት

ሼር ኢትዮጵያ በባቱና አዳሚ ቱሉ ከተማዎች አካባቢ በመቋቋሙ እና ከላይ የተጠቀሱ ሶስቱን ግብዓቶች በመጠቀሙ ምክንያት በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ እየደረሱ ያሉ ተያያዢነት ያላቸው ጉዳቶች የሚከተሉት ናቸው። 

 • የመሬት ንጥቂያ፡ – የአዳሚ ቱሉ ከተማ ሼር ኢትዮጵያ የተቋቋመበት መሬት የአርሶ አደሮች መሬት በመሆኑ አርሶ አደሮቹ ለምን ኃይል ጊዜ እንዳከራዩት ባያቁም ከመሬታቸው ተነስቷል። በባቱ አካባቢ እየታያ ያለው መንግስት በመርህ ደረጃ እንጂ በተግባር አርሶ አደሮች በመስኖ ልማት ተሰማርተው በምግብ እራሳቸውን ከመቻል አልፈው ምርቶቻቸውን ለገበያ እንዲያቀርቡ ከማገዝ ይልቅ ትኩረቱን ኢንቨስተሮች ላይ ብቻ በማድረግ ከአርሶ አደሮች መሬት ሲነጥቅ ማያት የተለመደ ሆነዋል። ይህንኑ ሀሳብ Gebhardt (2014) እንዲህ በማለት ይጋራል፤  

“It seems likely that his, (melles zenawi’s), agenda has been aimed not to benefit the majority of Ethiopians and protect the country’s natural resources, but rather to strengthen the position of the central government, both in the international arena and in relation to its own population” (Gebhardt, 2014, pp. 240).

 • የሰው ጉልበት ብዝበዛ፡ – ማንኛውም ሰራተኛ በሁለት ሳምንት ውስጥ አንድ ቀን ብቻ የእረፍት ቀን ይኖረዋል። የሚሰሩት ደግሞ ሙቀቱ እስከ 40 ዲግሪ ሴልሺየስ በሚደርስ Green house ውስጥ ነው።

“For eight hours each day, workers toil in temperature that touches 40 degree celsius. A single day-off each fortnight is the only respite (Murphy, na, pp. 2).

ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታወቀው የሥራ ሰዓት ጠዋት 1፡30 ወደ ሥራ የሚገቡበት ሲሆን ከቀኑ 6፡30 ላይ ለሚሳ ከወጡ በኃላ በ7፡00 ላይ ይመለሱና ማታ 11፡30 ሰዓት ላይ ወደ ቤታቸው እንደሚሄዱ ነው። ይህ እንዳለ ሆኖ አብዛኛውን ጊዜ ምሽት ላይ ሥራ ስለሚበዛ አብዛኞቹ ሰራተኞች ሳይፈልጉና ሳይወዱ ማታ ላይ እያመሹ የያዙት ሥራ እስከያልቅ ድረስ እስከ ከሚሽቱ 2 ወይም 3 ሰዓት ድረስ ይቆያሉ። በተጨማሪም ሰራተኞቹ ድንገት ማህበራዊ ችግር ገጥሞአቸው ሳያስፈቅዱ ቢቀሩ ብዙ ጊዜ የተለመደ ነገር ወደ ሥራ እንደማይመለሱ ነው። ሼር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ለመብታቸው እንኳ ለመታገል ተደራጅተው የተለያዩ ማህበራትን መቋቋም አይችሉም፣ የተከለከለ ነው። በተጨማሪም ለሰራተኞቹ አንድ የአበባ ፍሬ በAmsterdam መንገድ ላይ በValentine Day ከሚገዛበት ዋጋ በታች በሆነ በቀን አንደ ዶላር ገደማ ይከፈላቸዋል ይላል Murphy፤

“And yet, workers have no collective bargaining power because they have been forbidden from forming trade unions. He described one instance where workers were even fired from one flower farm when they tried to form a union to ensure safe working conditions. Workers earn around dollar a day, much less than the price of a single stem bought in the streets of Amsterdam on Valentine’s Day” (Ibid).

 • የተፈጥሮ ኃብት ብክነት፡ – ሼር ኢትዮጵያ የሚጠቀሚባቸው ዋና ዋና የሀገሪቱ የተፈጥሮ ኃብቶች መሬት፣ የሐይቅ ውሃ እና የሰው ሃይል ናቸው። የአበባ እርሻ የተለያዩ ኬሚካሎችን ስለሚጠቀም ድርጅቱ ካረፈበት መሬት ቢነሳም ያ መሬት ለወደፊት ተመልሶ ለእርሻ እንደማያገለግል ይነገራል። Getu (2009) እንዲህ በማለት ይጋራል፤

“But continued use of chemical fertilizers may destroy these nitrogen-fixing bacteria and many other micro- and macro- organism of the soil. In addition, acids in chemical fertilizers, such as sulfuric acid and hydrochloric acid, which tends to increase the acidity of the soil, reduces the soil’s beneficial organism population and interferes with plant growth” (Getu, 2009, pp. 244).

በተጨማሪም ድርጅቱ የሐይቁን ውሃ ያለምንም ክፍያ እንደፈለገው እየተጠቀመበት ነው ይላል Gebhardt (2014) 

“Water is free: growers simply bore holes, or in the case of Lake Ziway, build an irrigation system connected to the resource” (Gebhardt, 2014, pp. 240).

 • ሐሮ ደምበልና የቡልቡላ ወንዝ መቀነስ፡ – የአበባ ምርት በየጊዜው ጥሩ ምርት ለመስጠት ብዙ ውሃ የሚፈልግ ከመሆኑ የተነሳ የሐይቁ መጠን በፍጥነት እየቀነሳ ይገኛል (OBN ዘገበ፡ ነሓሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም)። በተጨማሪ Adugna (2017) እንዲህ በማለት ይጋራል፤

“One of the major environmental issues in which floriculture industry accused is the intensive uses of water… The consumption of water for the production of cut flowers reached 60,000 liters/ ha/ day (Adugna, 2017, pp. 4).

የቡልቡላ ወንዝ መጠንም በጣም ከመቀነሱ የተነሳ በበጋ ወቅት በአንዳንድ ቦታዎች በመቆራራጥ የአካባቢውን ህብረተሰብ ለሌላ እንግልት እየዳረገ ይገኛል። 

 • የሙቀት መጠን መጨመር፡ – በዓለም አቀፍ ክስተት በሆነው ኢሊኖና ላሊኖ ምክንያት የዓለም ሙቀት መጨመር እንዳለ ሆኖ ሼር ኢትዮጵያ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ ከተሞች (ባቱና አዳሚ ቱሉ) እንዲሁም በከተሞቹ አካባቢዎች ሙቀት ከመጠን በላይ ጨምሯል። ይህ ደግሞ የአካባቢውን ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን በባቱ ከተማ አርፈው ምሳቸውን ለሚመገቡ መንገደኞችና በሐይቁ ዙሪያ ለሚዝናኑ ቱሪስቶችም ጭምር አስቸጋሪ ሆኗል።
 • የሰራተኞቹ የጤና ችግር፡ – እንደሚታወቀው የአበባ እርሻ የአበባን ጤንነት ለመጠበቅም ሆነ ምርታማነቱን ለማሳደግ የተለያዩ ኬሚካሎችን ይጠቀምበታል። Murphy እንዲህ በማለት ይገፃል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የአበባ እርሻዎች ባጠቃላይ 120 የኬሚካል ዓይነትን የሚጠቀሙ ሲሆን ከነዚህ 15ቱ በዓለም ጤና ድርጅት ካንሰር የሚያስዙ መሆናቸው የታወቁ ናቸው። 

“Furthermore,  one  hundred  and  twenty  chemicals  are  used  in  Ethiopia’s  floriculture industry, of which fifteen are classified as carcinogenic by the World Health Organization (Murphy, na, pp. 2).

የአበባ እርሻ የሚጠቀመው ፀረ-ተባይ ኬሚካል በሰው ላይ የካንሰር በሽታ፣ የወሊድ ችግር፣ መራቢያና የነርቭ ሥርዓት መጥፋት እና የተለያዩ በሽታዎችን የሚያደርስ ሲሆን ምልክቶቹ ደግሞ ራስ ምታት፣ የእጆቹ መንቀጥቀጥ፣ የአይን ብዥታ፣ ማስመለስ እና የመሳሰሉት ናቸው ይላል Melafia (2009)

“Pesticides can cause cancer, birth defects, reproductive and nervous system damage, and floriculture workers are exposed at numerous stages of plant growth. Symptoms include pesticide poisoning, such as headache, dizziness, nausea, diarrhea, skin eruptions or fainting (Melafia, 2009, pp. 12).

 • የውሃ ብክለት፡ – ኢዩትሮፊኬሽን በሚባለው ህደት ማዳበሪያው ታጥቦ ወደ ሐይቁ ሲገባ የፀሃይ ብርሃንን የሚከለክል አልጌይ በማብቀል የሐይቁ ዕፅዋቶችን አደጋ ላ ይጥላቸዋል። ይህ የምግብ ሰንሰለትን በመረበሽ ጠቃሚ የሆኑ የሐይቅ ዕፅዋቶች እንዲሞቱ ያደርጋቸዋል ይላል Getu (2009)፤

“In a process known as eutrophication, fertilizer washed from fields into surface waters stimulates algae growth, which blocks sunlight needed by aquatic vegetation putting their survival at stake. This loss in vegetation disrupts the food chain, leading to the death of economically important aquatic life (Getu, 2009, pp. 245).

 • የአካባቢ ነዋሪዎች የጤና ችግር፡ – የባቱ ከተማ ነዋሪዎች ለመጠጥ የሚጠቀሙበት ውሃ ከሐሮ ደምበል ከተወሰደ በኃላ ተጣርቶ ለመጠጥ ያገለግላል። ሆኖም ግን ሼር ኢትዮጵያ ወደ አካባቢ ከመጣ በኃላ የመጠጥ ውሃ ከአበባ እርሻ በሚወጣው ኬሚካሎች እንደተበከለ በተደጋጋሚ ጥርጣሬዎች ቢነሱም (OBN ዘገበ፡ ነሓሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም) ያላመበከሉን ያረጋገጠ ሰው ሳይገኝ ከቅርብ ጊዚያት ጀምሮ የሚጠጣው ውሃ የተለያ ሽታና ጣዕም በመስጠት እንደተበከለ እራሱን በራሱ አጋልጧል። የከተሟ ነዋሪዎች ይህን ችግር ለጊዜው ተቀብሎ ዘለቄታዊ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ 25km ላይ ከሚገኘው ቡልቡላ ከተማ ‘ጡፋ’ የተባለውን ውሃ አንድ ጃሪካን (ባለ 20 እሰከ 25 ሊትር) ከብር 12 እስከ 15 እየገዙ እየተጠቀሙ ለዘለቄታዊ መፍትሔ ደግሞ በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ቢያሰሙም የሚሰማቸውን አካል ሳያገኙ ቀርተው እስከ ዛሬ ድረስ አብዛኛው የህብረተሰቡ ክፍል የመጠጥ ውሃ ከቡልቡላ እየገዙ እየተጠቀሙበት ያለ ሲሆን አቅም ያነሳቸው የህብረተሰብ ክፍል ደግሞ ያንኑ በኬሚካል የተበከለ ውሃውን እየጠጡ ይገኛሉ። 
 • የአየር ብክለት፡ – የአየር ብክለት ግሪና (Green house) ውስጥ በሚሰሩት ሰራተኞች ላይ የሚደርስ እንዳለ ሆኖ በየጊዜው ኬሚካሉ ሲነፋ ከግሪና አልፎ በአቅራቢያ የሚገኙ የከተማ ነዋሪዎችን በጣም እየጎዳ ይገኛል። በተጨማሪ ከአበባ እርሻ የሚወጣው በጣም የሚሸት የአበባ ተረፈ-ምርት የሚጣልበት ቦታ ከተማ ጫፍ በመሆኑ በአካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች በተረፈ-ምርቱ ሽታ በጣም እየተጎዱ ይገኛሉ (OBN ዘገበ፡ ነሓሴ 14 2009 ዓ.ም)። 

7. ማጠቃለያ

የሐሮ ደምበል እና የባቱ ካታማና አካባቢዋ ነዋሪዎች የችግር መነሻው ሼር ኢትዮጵያ ከመቋቋሙ በፊት በአካባቢው ላይ ሊያድርስ የሚችልውን የተፅዕኖ ጥናት ሳይካሄድ ጥቅሙ ብቻ ታይቶ በቀጥታ በፌዴራል መንግስት ትዕዛዝ ፈጥኖ ወደ ስራ እንዲገባ መደረጉ ነው። ከዛ በፊት በዛው መሬት ላይ የነበረው የመንግስት እርሻ በአካባቢው ህብረተሰብም ሆነ ሥነ-ሕይወት ላይ ጉዳት ሳያደርስ የአከባቢው ነዋሪዎችና መንግስት ሲጠቀሙበት የነበረ ሲሆን የአሁኑ የአበባ እርሻ ደግሞ የአካባቢውን ህብረተሰብና ሥነ-ሕይወትን እያናጋ ፌዴራል መንግስትን እየጠቀመ ይገኛል። ይህ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ጥቅም እንጂ ጉዳት ከማያደርሰው የመንግሰት እርሻ ወደ የአካባቢውን ሥነ-ሕይወት የሚያናጋና ጉዳት የሚያደረሰው የአበባ እርሻ መቀየር በብዙዎቹ የአካባቢ ነዋሪዎች ላይ ልማት ነው ወይስ ጥፋት ነው? የሚል ጥያቄ ያጭርባቸዋል።  

በሼር ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓይነት (ደረቅ እና ፈሳሽ) ቆሻሻዎች በመኖራቸው ድርጅቱ ሁለት ዓይነት የቆሻሻ ማስወገጃ (የደረቅ እና የፈሳሽ ቆሻሻ) ስልትን ለመተግበር ቢሞክርም ሳይሳኩ ቀርቶ በህብረተሰቡ ላይ ትልቅ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል። የደረቅ ቆሻሻ (የአበባ ተረፈ-ምርት) ማስወገጃ ከከታማ ሳይርቅ እዛው ከተማ ጫፍ የሚወገድ በመሆኑ የቆሻሻው ሽታ የአካባቢ ነዋሪዎችን በጣም እየጎዳቸው ይገኛል። የፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ደግሞ ከአበባ እርሻ ቦይ ተሰርቶለት በቀጥታ ወደ ሐይቁ የሚወገድ ሲሆን በአበባ እርሻ ምክንያት እየደረሱ ከሚገኙ ጉዳቶች ሁሉ ዘርፈ-ብዙ ጉዳቶችን እያደረሰ ያለው ይህ ነው። የፈሳሽ ቆሻሻው ለአበባ የሚጠቀሙትን ግብዓቶች ሁሉ (የሚረጩትን መድሃኒቶች እና የሚዘሩትን ማዳበሪያዎችን) ኣጥቦ በጎርፍ መልክ የተዘጋጀለትን ቦይ ይዞ በቀጥታ ወደ ሐይቁ ይገባል። ይህ ደግሞ ኣሳን ጨምሮ የተለያዩ ዕፅዋቶችን ብቻ ሳይሆን ሐይቁን እንደመጠጥ ውሃ የሚጠቀሙትን የአካባቢው ነዋሪዎችንና እንሰሳቶችንም ጭምር እየጎዳቸው ይገኛል። ከተሟ በሐይቅ ተከባ በውሃ በልፅጋ እያለች በአበባ እርሻ ምክንያት የመጠጥ ውሃ እስከማጣት ድረስ ደርሳለች። ለአበባ እርሻ ብሎ የመጠጥ ውሃ ማጣት ማለት ለሀገሪቱ ልማት ብሎ ህይወትን መሰዋት እንደ ማለት ነው። ጥያቄው ግን የአካባቢውን ነዋሪዎች ህይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ልማት ለማን ነው? በአካባቢው ነዋሪዎች መስዋትነት የሚለመው ማን ነው?

በተጨማሪም ሼር ኢትዮጵያ የተለያዩ የማህበራዊ አገልግሎቶችን በመገንባት ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጣ ይገኛል። በነዚህ ማህበራዊ አገልግሎቶች ሰራተኞቹና የሰራተኞቹ ልጆች በነፃ የሚገለገሉበት ሲሆን ሌሎች የአካባቢ ነዋሪዎችና ልጆቻቸው ግን ከፍሎ ነው የሚገለገሉበት። ነገር ግን የባቱ ከተማ ነዋሪዎችንና የድርጅቱን ሰራተኞች ይዘት ሲንመለከት ብዙ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሼር ኢትዮጵያ ከመቋቋሙ በፊት በባቱ ከተማ የነበረው የሰው ኃይል ወደ 6,000 ገደማ ይሆናል የሚባል ሲሆን ከተቋቋመው በኃላ ደግሞ 11,000 እንደደረሰ ይገለፃል። ይህ ማለት 9000 ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም ለሥራ ብሎ ከተለያዩ አካባቢ ወደ ከተማ የገቡ ናቸው ማለት ነው። ስለዚህ ድርጅቱ ከገነባቸው ማህበራዊ አገልግሎቶች በዋናነት በነፃ እየተጠቀሙ የሚገኙ የአካባቢ ተወላጆችና ነዋሪዎች ሳይሆኑ ለሥራ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ከተማ የገቡት የድርጅቱ ሰራተኞችና ቤታሰቦቻቸው ናቸው ማለት ነው። ይህ ደርጅቱ ለአካባቢ ነዋሪዎች የማህበራዊ አገልግሎቶችን አቅርቧል ቢባልም አጠቃቀሙ ላይ ግን የድርጅቱ ሰራተኞችና ቤታሰቦቻቸውን በነፃ እያገለገሉ የአካባቢው ተወላጆችና ነዋሪዎችን ደግሞ እያስከፈሉ ማገልገላቸው በአካባቢው ተወላጆች ላይ ትልቅ ቅሬታ ፈጥሮባቸዋል። 

በመጨረሻ ከሼር ኢትዮጵያ ወጥቶ ወደ ሐሮ ደምበል የሚለቀቀው በኬሚካል የተበከለ ፈሳሽ ቆሻሻ ሐይቅ ውስጥ የሚኖሩትን ዕፅዋቶችና የባቱ ከተማ ነዋሪዎችን ብቻ የሚጎዳ ሳይሆን በዋናነት ሐይቁን ከቦ የሚገኙ የሶስቱ ወረዳዎች ነዋሪዎችን (የአዳሚ ቱሉ ጂዶ ኮምቦልቻ ወረዳ ነዋሪዎች፣ የዝዋይ ዱግዳ ወረዳ ነዋሪዎች እና የዱግዳ ቦራ ወረዳ ነዋሪዎች) በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ህወታቸው ከሐሮ ደምበል ጋር ቁሪኝት ስላላቸው በጣም ተጎጂዎች ናቸው፣ እየተጎዱም ይገኛሉ። ስለዚህ ሐሮ ደምበልን መጠበቅና መንከባከብ እንዲሁም እንዳይደርቅ ማድረግ ሐይቁን ብቻ ማዳን ሳይሆን ሐይቅ ውስጥ የሚኖሩትን ዕፅዋቶችንም ጨምሮ በሐይቁ አካባቢ የሚኖሩትን ወፎች፣ እንሰሳቶችና ህብረተሰቡን መጠበቅና መንከባከብ ነው።

8. የመፍትሔ ሀሳብ

የተፈጠረ የሀሮ ደምበል ችግር ኣሳን ጨምሮ በሐይቁ ውስጥ የሚኖሩትን ዕፅዋቶችን እንዲሁም የሰው ልጅ ሕይወትን እየጎዳ ስለሆነ ሁሉም የማህብረሰቡ ክፍል ተሳትፈውበት ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ ልበጅለት ስለሚገባ የሚከተሉት የማህበረሰብ ክፍሎች በዋናነት ለሐይቁ ትኩረት በመስጠት ሐይቁን ለማዳን ቢጥሩ የተሻላ ይሆናል።

 • የአካባቢው ህብረተሰብ፡ – “Abbaan iyyatu ollaan birmata” ይላል የኦሮሞ ተረት። ትርጉሙ ጐረቤት የሚደርስለት አባቱ (ባላችግሩ) ሲያመለክት ነው። የአካባቢው ህብረተሰብ የድርጅቱ ሰራተኞችም ጭምር በአካባቢው እየደረሰ ያለውን ጉዳት በተግባር እያዩና እራሳቸውም እየተጐዱ ስለሆነ ለዚሁ ችግር መፍትሔ እስኪገኝለት ድረስ በግንባር ቀደምትነት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል። ይህም በየደረጀ ላለው የመንግስት አስተዳደር (ከወረዳ እሰከ ፌዴራል) ማመልከት ብቻ ሳይሆን የሕይታቸውን ጤንነት ለመጠበቅም ሆነ ሐሮ ደምበልንና ዕፅዋቶችን ለማዳን ዘለቄታዊ መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ በመንግስት ላይ ጫና ማፍጠር ይጠበቅባቸዋል። በአበባ ኬሚካል የተበከለውን ውሃ እየጠጡ የመኖር ህልውናቸው ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።
 • የወረዳ፣ ዞንና ክልል አስተዳደሪዎች፡ – እንደሚታወቀው ሼር ኢትዮጵያ የተቋቋመው በወረዳ፣ ዞንና ክልል አስተዳዳሪዎች ውሳኔ ሳይሆን ቀጥታ በፌዴራል መንግስት የተቋቋማ በመሆኑ በዚህ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግስት አስተዳዳሪዎች በራሳቸው ብቻ መፍትሔ ያመጣሉ ለማለት ሊያስቸግረን ይችላል። ቢሆንም ግን ለጉዳዩ ቅርብ በመሆናቸው ህብረተሰብ ውስጥ ገብተው የህብረተሰቡን ችግር በተግባር በማያት ህብረተሰቡ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎችና ችግሮችን አቀናጅተው ለፌዴራል መንግስት በማቅረብና ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን  ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲገኝ ማድረግ ይችላሉ። ይህ ካልተቻለ በተፈጥሮአዊ ኃብቶችና አካባቢያዊ ደህንነት ጥበቃ ላይ የተሰጣቸውን ህግ በመጠቀም የህብረተሰቡ ጤንነት አደጋ ላይ ከሚወድቅ በድርጅቱ ላይ አግባቢነት ያለው እርምጃ ሊወሰድ ይገበዋል። 
 • የተለያዩ ሚዲያዎች እና OBN: – ሚዲያዎች ሁሉ በባቱ ከተማና አካባቢዋ በሼር ኢትዮጵያ ምክንያት በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ እየደረሰ ላለው ችግር ትኩረት ሰጥቶ በመዘገብ ችግሩ የመንግስትና የሁሉም ህዝብ ጆሮ እንዲገባ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ኦሮሚያንና የኦሮሞን ህዝብ ወክሎ የሚሰራ ሚዲያ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (OBN) ለችግሩ ትኩረት ሰጥቶ አልዘገበም። OBN Sagalee Uummataa (ኦ.ቢ.ኤን የህዝብ ድምፅ) በመሆኑ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚካሄዱትን የልማት ሥራዎችን መዘገብ ብቻ ሳይሆን በልማቱ ምክንያት እየደረሱ ያሉ ጉዳቶችንም ጭምር ትኩረት ሰጥቶበት ከተለያዩ ቦታዎች የተለያዩ ዘገባዎችን በማዘጋጀት ለህብረተሰቡና ለመንግስት እያቀረበ ይገኛል። በሚቀርቡ ዘገባዎች ላይ ተንተርሶ የክልሉ መንግስትም የህብረተሰቡን ችግር እየፈታላቸው ይገኛል። ሆኖም ግን ይህ የህዝብ ሚዲያ ሼር ኢትዮጵያ ላይ ሁለት ቀን ብቻ – አንድ ቀን በሐይቁ ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት (OBN ዘገበ፡ ነሓሴ 14 2009 ዓ.ም) እና ሌለኛውን ቀን ደግሞ የዋናው ችግሩ ቅርንጫፍ የሆነውን የተወገደው የአበባ እርሻ ደረቅ ቆሻሻ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ እያደረሰ ያለውን ችግር (OBN ዘገበ፡ ነሓሴ 21 ቀን 2009 ዓ.ም) – በመዘገብ በአካባቢው ላይ ዋና ችግር እየፈጠረ ያለውን እራሱን የአበባ እርሻ ውስጥ ገብቶ ሙሉ ይዘቱንና በቅርቡ ደግሞ በድርጅቱ ምክንያት የተፈጠረውን የከተሟ የመጠጥ ውሃ ችግር ሳይዘግብ ቀረ። ምናልባት ከብዙ ኢንስተሮች እንደሚናየውና እንደሚንሰመው ሼር ኢትዮጵያም የኦ.ቢ.ኤን (OBN) ጋዜተኞችን ወደ ግቢው አላስገባም ካላለ በቀር አሁንም ቢሆን ሚዲያው ይህን የህዝብ ችግር ትኩረት ሰጥቶበት ለመዘገብ ጊዜው አላለፈም።
 • በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ ለሚሰሩ የአካባቢው ተወላጆችና ምሁራን፡ – የመማር ዋና ጥቅሙ በትምህርት ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ያልተማሩና ያላወቁትን ህብረተሰብ ማገልገል በመሆኑ የአካባቢውን ችግር በተግባር የሚያቁ ምሁራንና በተለያዩ ከፍተኛ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የአካባቢ ተወላጆች የዚህን ችግር አሳሳቢነት በመረዳት በያሉበት ሆነው ችግሩ ለመላው የሀገሪቱ ህዝብ ጆሮ እና ለሚመለከተው አካል ሁሉ እንዲደርስ በማድረግ ለችግሩ ዘለቄታዊ መፍትሔ እስኪገኝ መታገል ይኖርባቸዋል።
 • ፌዴራል መንግስት፡ – ፌዴራል መንግስት በአካባቢ ከሚገኙት ህብረተሰብና በየደረጀ ካሉ የመንግስት አስተዳዳሪዎች (ወረዳ፣ ዞንና ክልል) የሚቀርቡለትን ችግሮች በማያት በአግባቡ መፍታት ብቻ ሳይሆን የራሱ አጣሪ ኮሚቴ ወደ አካባቢው በመላክ የተፈጠረውን ችግር በጥልቀት በመገምገም ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲገኝ ማድረግ ይጠበቅበታል። ወደ ሐይቁ የሚፈሰው የፈሳሽ ቆሻሻ ሐይቁ ውስጥ እንዳይገባ የሚከማችበት ሌላ አማራጭ ከተገኘ እሴዮ። ካልሆነ ግን የሰው ልጅ ጤንነት ለመጠበቅ እንዲሁም ሐይቁንና የሐይቁን ዕፅዋቶችን ለማዳን ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ ነው። ሼር ኢትዮጵያን ማዝጋት። 
 • የሀገር ውስጥና የሀገር ውጪ አክቲቪስቶች፡ – እንደሚታወቀው አክቲቪስቶች መንግስት ያላያቸውና እያያቸው እንዳላያቸው የሚሆነውን በየቦታው የሚገኙ የህብረተሰብ ችግሮችን ነጥሮ በማውጣት የሚዲያ ሽፋን እንዲያገኙና የህዝብ ጆሮ እንዲገቡ በማድረግ ለችግሮቹ ዘለቄታዊ መፍትሔዎች እንዲገኙ ስለሚያደርጉት በሐሮ ደምበልና አካባቢው ላይ እየደረሰ ላለው ጉዳትም ትኩረት በመስጠት በመንግስት ላይም ሆነ በተለያዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማቶች ላይ ጫና በማድረስ  የህብረተሰቡ ችግር እስኪፈታ ድረስ መታገልን ይጠይቃል።
 • ዓለም አቀፍ የአካባቢያዊ ጥበቃ ተቋማቶች፡ – በአሁኑ ጊዜ ዓለም በተፈጠረው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በኢሊኖና በላሊኖ እየተጎዳች በመሆኑ የተለያዩ የአካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ፎረሞች በተደጋጋሚ ሲካሄዱ ማያት የተለመደ ሆኗል። ኢትዮጵያም የአፍሪካ ሀገራትን በመወከል በተደጋጋሚ በሚካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ፎረሞች ላይ በመሳተፍ የአፍሪካዊያን ድምፅ ሲታሰማ ቆይታለች። ሆኖም ግን ሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተለያዩ ዛፎችን በመትከልና እርከኖችን በመሥራት ለአካባቢ ጥበቃ ጉልህ ሚና በመወጣት ለዓለም ዓቀፍ ህብረተሰብ አርያ እየሆነች ያለ ቢሆንም ወደ ሀገር ውስጥ የሚታስገባው እንቨስተሮች ላይ ልዩ ትኩረት ባላመድረጓ በተለይ በአበባ እርሻ ላይ የተሰማሩ ኢንቨስተሮች የተፈጥሮ ኃብቶችን ለተለያዩ ጉዳቶች እንዲጋለጡ እያደረጉ መሆኖንና ለዚህም መንግስት ምንም ዓይነት መፍትሔ አለመበጀቱ የዓለም አቀፍ ህብረተሰቡ አውቆ መንግስት ላይ ጫና በመፍጠር የህብረተሰቡ ችግሩ እንዲፈታ ማድረግ ይኖርባቸዋል። 

ባጠቃላይ ድርጅቱ ሥራ ከመጀመሩ በፊት የጠፅዕኖ ጥናት ተካሄደው ሊያደርስ ለሚችለው ጉዳቶች ሁሉ በቅድሚያ የመከላከል ሥራ ቢሰራ ጥሩ ነበር። በሀገሪቱ ውስጥ ደግሞ ይህን እንዲያደርግ የሚያስገድዱ ብዙ አዋጆች ቢኖሩም ሼር ኢትዮጵያ ይህንን ሳያደርግ ፈጥኖ ወደ ሥራ በመግባቱ የመጠጥ ውሃውን እስከ መበከል ደርሶታል። ሀገሪቱ እንዲትለማ የሁሉም ዜጋ ምኞት በመሆኑ ሼረ ኢትዮጵያ አሁን ያለው አማራጭ በህብረተሰቡ ላይ ያደረሰውን ችግር በመፍታት መቀጠል የሚችል ከሆነ እሴዮ ካልሆነ ግን በፌዴራል ሕገ መንግስተም ሆነ (አንቀፅ 92 ንዑስ አንቀፅ 2) በክልሉ ሕገ መንግስት (አንቀፅ 107 ንዑስ አንቀፅ 2) ‘ማንኛውም የኢኮኖሚ ልማት እርምጃ የአካባቢውን ደህንነት የሚያናጋ መሆን የለበትም’ በማለት በመደንገጉ እና ከላይ የተጠቀሰው የአበባ እርሻ ደግሞ የአካባቢውን ደህንነት ከማናጋት አልፎ በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ መዘጋት ይኖርበታል። 

9. የዋቢ ምንጮች

****

   አዘጋጅ፡ – በዳኔ አቦ

   Facebook: Bedhane A. Guyo

   ኢ-ሜይል፡ – bedaneabo1@gmail.com 

   One thought on “ሼር ኢትዮጲያ እና የባቱ/ዝዋይ ከተማ ነዋሪዎች ችግር

   አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡