ከጥይት ተርፎ በሆስፒታል ቀጠሮ ከሞት አፋፍ የደረሰው ወጣት! 

ይህ ወጣት ኦብሳ መሃመድ ይባላል፡፡ የትውልድ ቦታው ምስራቅ ሀረርጌ፥ ደደር (Eastern Hararge, Dadar) ሲሆን እድሜው 16 አመት ነው፡፡ ከስድስት ወር በፊት ይኖርበት በነበረው ጅግጅጋ ከተማ (Jigjiga) ከተማ የሶማሌ ክልል ልዩ ፖሊሶች በሁለት ጥይት ከመቱት በኋላ “ሞቷል” ብለው በወደቀበት ጥለውት ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን፣ ትረፍ ሲለው በአከባቢው የነበሩ ሰዎች ከወደቀበት አንስተው ወደ ጅግጅጋ ሆስፒታል ይወስዱታል፡፡

ኦብሳ በጥይት የተመታው የጀርባ አጥንቱ (spinal cord) ላይ ሲሆን ከወገቡ በታች ያለው የሰውነቱ ክፍል ፓራላይዝድ (paralysed) ሆኗል፡፡ ህክምና ለማግኘት በመጀመሪያ ወደ ድሬዳዋ ሆስፒታል፣ ቀጥሎ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፈር ይደረጋል፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከገባ በኋላ የነርቭ ቀዶ-ጥገና (Neurosurgery) ለማድረግ ከ3 ሳምንት በኋላ እንዲመጣ ቀነ ቀጠሮ ይሰጠዋል፡፡ ከ3 ሳምንት በኋላ ወደ ሆስፒታሉ ግን ተጨማሪ የ3 ወር ቀጠሮ ይሰጠዋል፡፡ ይህ የ3 ወር ቀጠሮ ግን ኦብሳን ለሌላ በሽታ ዳረገው፡፡ በተጠቀሰው ግዜ ውስጥ ኦብሳ በሀኪሞች አገላለፅ “sacral bed sore (grade 4)” ለሚባለው በሽታ በመዳረጉ ምክንያት የፕላስቲክ ቀዶ-ጥገና (plastic surgery) እንዲያደርግ ወደ የካቲት ሆስፒታል ሪፈር ይደረጋል፡፡

ኦብሳ ወደ የካቲት ሆስፒታል ሪፈር የተደረገው በሰውነቱ ውስጥ የቀሩትን ሁለት ጥይቶች እንዲወጣለት ሳይሆን በቀነ ቀጠሮ መራዘም ምክንያት የያዘውን በሽታ ለመታከም ነው፡፡ በየካቲት ሆስፒታል ህክምናውን ሲጨርስ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ይመለሳል፡፡ የጤና ሁኔታው ግን እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

ይህ ወጣት አባቱን የት እንዳለ አያቀውም፣ ወላጅ እናቱ የሚጥል በሽታ “epilepsy” ህመምተኛ ስትሆን፣ የቀረው ታናሽ ወንድሙ ሲሆን እሱም ገና 15 አመቱ፡፡ ወንድሙን ለማስታመም ሆነ ለመደገፍ የሚያስችል አቅም የለውም፡፡ በግልፅ ለመናገር ከእኛ በስተቀር ጠያቂ፥ አስታማሚ ሆነ መታከሚያ የለውም፡፡

ወጣት ኦብሳ መሃመድ