ሕገ-መንግስቱ ሳይሻሻል ለውጥ ማምጣት ይቻላል?

በመጋቢት ወር አጋማሽ ላየ ሰማያዊ ፓርቲ በወቅታዊ የሀገራችን ፖለቲካዊ ሁኔታ ዙሪያ አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ አንደነበር ይታወሳል። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ መምህርና ጦማሪ ስዩም ተሾመ ሀገራችን አሁን ካለችበት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የገባችበትን መሰረታዊ ምክንያት አስመልክቶ ዝርዝር ትንታኔ ሰጥተውበታል። በዚህ የ20 ደቂቃ ቪድዮ በህወሓት/ኢህአዴግ መሪነት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት በተሳሳተ የመርህ፥ እሳቤና ድንጋጌ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አስረድተዋል። ለዚህ ደግሞ የሚከተሉት ሦስት ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡-

  1. በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 መሰረት ብሔሮች የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤት እንደሆኑ ይጠቅሳል። ነገር ግን፣ ብሔሮች ግብር አይከፍሉም፣ ምርጫ አይመርጡም፥ አይመረጡም። ስለዚህ የሉዓላዊ ስልጣን ባለቤትነት ወይም በመንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ሊኖራቸው አይችልም። ከዚህ አንፃር፣ ሕገ መንግስቱ ፍፁም በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው።
  2. ሀገር የሚመሰረተው በወደፊት አብሮነት (common future) ላይ ነው። ሆኖም ግን፣ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 39(1) መሰረት የብሔሮች የራስን እድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብታቸው በማንኛውም መልኩ ያለ ገደብ የተጠበቀ እንደሆነ ተደንግጓል። ስለዚህ ሕገ-መንግስቱ ከወደፊት አብሮነት ይልቅ በልዩነትና መለያየት ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ ከመሰረታዊ የሀገር አመሰራረት እሳቤ ጋር ይጋጫል።
  3. በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49(2) መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለው ይደነግጋል። ከዚያ ቀጥሎ አንቀፅ 49(3) ላይ “የከተማ መስተዳደሩ ተጠሪነቱ ለፌደራል መንግስት ይሆናል” በማለት የመስተዳደሩን ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን ይገፍፋል። በዚህ ምክንያት የከተማዋ ነዋሪዎች ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን ተገፍፏል፣ አዲስ አበባ ባለቤት አልባ ከተማ ሆናለች። ከዚህ በተጨማሪ፣ በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ለተፈጠረው አለመግባባት መሰረታዊ መንስዔ ሆኗል።

ሀገራችን ለገባችበት የፖለቲካ ቀውስ መሰረታዊ ምክንያት ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ናቸው። ስለዚህ የተጠቀሱትን ችግሮች በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው በሕገ-መንግስቱ ውስጥ ያሉትን የተሳሳቱ መርሆች፥ እሳቤዎችና ድንጋጌዎች ማስተካከል ሲቻል ነው። ለዚህ ደግሞ ሕገ-መንግስቱን ማሻሻል የግድ አስፈላጊ ነው። ከዚህ መለስ የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ “ጥገናዊ ለውጥ” ከመሆን የዘለለ ፋይዳ የለውም። በመሆኑም ችግሮቹን በዘላቂነት መፍታት አይቻልም፤ ሀገሪቱም አሁን ከገባችበት ቀውስ አትወጣም። አቶ ስዩም በጉዳዩ ዙሪያ የሰጡትን ሙሉ ትንታኔ ለማዳመጥ ይህን ሊንክ ይጫኑ፡፡

በቀጣይ ክፍል ደግሞ “አዲሱ የኢህአዴግ አመራር ሕገ መንግስቱን በማሻሻል ሥር-ነቀል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ወይ?” በሚለው ዙሪያ በተመሳሳይ ዝርዝር ትንታኔ ይዘን እንቀርባለን።