የወልቃይት ጥያቄ: መነሻው አፓርታይድ፣ መድረሻው ጦርነት ነው!

የወልቃይት ጥያቄ ምንድነው?

“የወልቃይት ጥያቄ ምንድነው?” የመልካም አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ጥያቄ ነው? አይደለም! የማንነት ጥያቄ ነው? አይደለም! የግዛት መስፋፋት ወይስ የግዛት ማስመለስ? ሁለቱም አይደሉም! እሺ… ወልቃይቶች ከመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ፣ ከማንነትና የመሬት ባለቤትነት፣ እንዲሁም የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት ጋር በተያያዘ ጥያቄ የላቸውም? አላቸው! በእርግጥ “የወልቃይት ጥያቄ” ዘርፈ-ብዙ ለሆኑ ፖለቲካዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ከመሻት የመነጨ ነው፡፡ ስለዚህ ‘የወልቃይት ህዝብ ጥያቄ የተለያዩ ችግሮች ስብስብ ወይም ድምር ውጤት ነው’ ማለት ይቻላል? በፍፁም አይቻልም! ምክንያቱም የወልቃይት ጥያቄ አንድና አንድ ሲሆን እሱም “አፓርታይድ” ይባላል፡፡

ወልቃይት እንደ የትኛውም የሀገሪቱ አከባቢ ሥር-የሰደዱ ዘርፈ-ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ ነገር ግን፣ ከሁሉም የሀገሪቱ አከባቢዎች በተለየ የአፓርታይድ ስርዓት ገፈት ቀማሽ ነው፡፡ በህወሓት መሪነት የተዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት የወልቃይትን ችግር ብዙ እጥፍ ውስብስብ፣ ከሌሎች አከባቢዎች በተለየ ሥር እንዲሰድ አድርጎታል፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ጥያቄ አጭርና ግልፅ ሲሆን እሱም “ከአፓርታይድ ነፃ መውጣት!” የሚል ነው፡፡

ምንም ያህል መልካም አስተዳደር ቢረጋገጥ፣ የዳበረ ዴሞክራሲ ቢዘረጋ፣ ይህ የአፓርታይድ ቀንበር እስካልወደቀ ድረስ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ምላሽ አያገኝም፣ የመሬታቸው ባለቤት መሆን አይችሉም፣ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን እና ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደርና መምራት አይቻላቸውም፡፡ ለወልቃይቶች ማንኛውም ዓይነት የፖለቲካ ጥያቄ ለሞት፥ ለአካል ጉዳትና ስደት እየዳረጋቸው ይገኛል፡፡ ፖለቲካዊ መብታቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ በህይወት የመኖር፥ ከአካል ጉዳት የመጠበቅ እና በነፃነት ተንቀሳቅሶ ሃብት፥ ንብረት የማፍራት ሰብዓዊ መብታቸው እንዲገፈፍ ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለዚህ የወልቃይት ህዝብ እያነሳ ያለው “ነፃነት ወይም ባርነት” የሚል የሞት-ሽረት ጥያቄ ነው፡፡

የወልቃይት ውለታ እና የህወሓት ክህደት

ወልቃይቶች ለህወሓት የምንግዜም ባለውለታ ናቸው፡፡ እንደ ሌሎች የሀገሪቱ አከባቢዎች ከህወሓት ጋር የተገናኙት በድል አድራጊት ወደ መሃል ሀገር ሲገሰግስ አልነበረም፡፡ ከደርግ ጦር መሸሸያ፥ መሸሸጊያ ጥጋት ባጣበት ወቅት ከጏዳቸው ደብቀው ታድገውታል፡፡ የህወሓት ታጋዮች በቄያቸው ሲልፉ ስንቅ ማቀበልና መንገድ መጠቆም ብቻ አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ የትጥቅ ትግሉ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ደርግን ለመጣል ተዋግተዋል፡፡ ከለውጥ በኋላ በተዘረጋው ቋንቋን መሠረት ያደረገ የክልል አወቃቀር ወደ ትግራይ ክልል መካተታቸው ለወልቃይቶች ይህን ያህል አሳሳቢ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ከህወሓቶች ጋራ ለ17 አመታት አብረው ኖረዋል፥ አብረውት ታግለዋል፡፡ በዚህም ደርግን አሸንፎ በሀገሪቱ ላይ አድራጊ-ፈጣሪ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይሁን እንጂ፣ አሁን በወልቃይት ህዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ግፍና በደል ይፈፅማል ብሎ ማሰብ በጣም ከባድ ነው፡፡

ኮ/ል ደመቀ ዘውዴ

በእርግጥ ከደርግ ጦር በጉያው ሸሽጎ የታደገውን፣ በጦር ሜዳ አብሮት የተዋደቀውን ህዝብ በዚህ ደረጃ ይክዳል፥ ይጠላል፥ ይበቀላል ብሎ ይከብዳል፡፡ ህወሓት የዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት በተለያዩ ብሔሮች መካከል መተማመንና መግባባት እንዳይኖር አድርጏል፡፡ ወልቃይቶችን ግን ከትግሬዎች ጋር አብረው እንዳይሰሩና እንዳይኖሩ አድርጏቸዋል፡፡ ሌላውን የኢትዮጲያ ክፍል በብሔር ሲከፋፍል ወልቃይቶችን ግን “ትግሬ ናችሁ” በማለት ማንነታቸውን እንዲክዱ ነው ያስገደዳቸው፡፡ ሌሎች በኢንቨስትመንት ሰበብ በአነስተኛ ካሣ ከመሬታቸው ሲፈናቀሉ ወልቃይቶች ግን የተፈናቀሉት በሰፈራ ፕሮግራም፡፡ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ትግራዎች ከሌሎች የክልሉ አከባቢዎች በመምጣት፣ እንዲሁም የቀድሞ የህወሓት ታጋዮች (የጦር ተቀናሾች) በሰፈራ የአያት-ቅድመ አያቶቻቸውን መሬት ተቀራመቱት፡፡

የአፓርታይድ መጨረሻው ጦርነት ነው!

በመሠረቱ “አፓርታይድ” ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል በዘር፥ ብሔር፥ ቋንቋ በመከፋፈል አብላጫ ድምፅ (Majority) እንዳይኖር በማድረግ የተቀናጀ የፖለቲካ ንቅናቄን ማዳከም፣ በዚህም የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገ ስርዓት ነው፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ የነበረው የአፓርታይድ ስርዓት የነጮችን የበላይነት ለማረጋገጥ በቅድሚያ የወሰደው እርምጃ በዘር፥ የቆዳ ቀለም፥ ቋንቋ፥ ጎሳና ብሔር ጥቁሮችን በአስር (10) ክልሎች መከፋፈል ነው፡፡ በመቀጠል ደግሞ ከሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር 85% የሚሆኑትን ጥቁሮች ከመሬታቸው በማስነሳት በ15%ቱ መሬት ላይ እንዲሰፍሩ ካደረገ በኋላ 15% የሚሆኑትን ነጮች 85% የሚሆነውን መሬት እንዲቆጣጠሩ አድርጏል፡፡ በዚህ መሠረት፣ አብላጫ ድምፅ ያላቸው ጥቁሮች የተቀናጀ የፖለቲካ ንቅናቄ እንዳያደርጉ በማድረግ የነጮችን የስልጣን የበላይነት፣ አብዛኛውን የመሬትና ተፈጥሮ ሃብት በመቆጣጠር ደግሞ የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን አረጋግጧል፡፡

በተመሣሣይ በህወሓት መሪነት የተዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት፤ አንደኛ የወልቃይትን ህዝብ ከተቀረው የአማራ፣ በተለይ የጎንደር ህዝብ በመነጠል፣ ሁለተኛ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ትግሬዎች በማስፈር በአከባቢው የሚኖሩ አማራዎች ቀድሞ የነበራቸውን አብላጫ ድምፅ አሳጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንዳያነሱ ለማድረግ ከፍተኛ አፈና እንደሚፈፅም ይታወቃል፡፡ በዚህ መልኩ የወልቃይት አማራዎችን ፖለቲካዊ መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በጉልበት በመደፍጠጥ የትግሬዎችን የበላይነትና ተጠቃሚነት አረጋግጧል፡፡

እንደ አፓርታይድ ስርዓት የህወሓት ዓላማ የብዙሃኑን ፖለቲካዊ መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በመግፈፍ የጥቂቶችን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የወልቃይት አማራዎችን ከጎንደር ህዝብ በመነጠል በአከባቢው የነበራቸውን አብላጭ ድምፅ ያሳጣቸው የትግሬዎችን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ነው፡፡ በሌላ በኩል፣ በወልቃይት የሚኖሩ ትግሬዎች አብላጫ ድምፅ እንዲኖራቸው ከአስቻለ በኋላ እንኳን የአማራዎችን ፖለቲካዊ መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፍፁም ፍቃደኛ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ የመብትና ፍትህ ጥያቄ ያነሱ የወልቃይት ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ቀርቶ በስደት ከሚኖሩበት እያደነ ግፍና በደል ይፈፅምባቸዋል፡፡

ስለዚህ የወልቃይት አማራዎች አንደኛ፦ በአከባቢው ያላቸውን አብላጫ፡ድምፅ እንዲያጡ ተደርገዋል፣ ሁለተኛ፦ እንደ አናሳ ድምፅ (minority) መብታቸው አይከበርም፡፡ በመሆኑም ህወሓት በዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት ውስጥ የወልቃይት አማሮች መብት በፍፁም አይከበርም፡፡ ይህ መሠረታዊ የዴሞክራሲ መርህን ይፃረራል፦

“As democracy is understood today, the minority’s rights must be protected no matter how alienated a minority is from the majority society; otherwise, the majority’s rights lose their meaning.”

ከላይ በተጠቀሰው መሠረት በህወሓት መሪነት የተዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት የወልቃይት አማራዎችን መብት ከመግፈፉ በተጨማሪ አሁን ላይ በአከባቢው አብላጫ ድምፅ ያላቸውን ትግሬዎች መብት ትርጉም ያሳጣዋል፡፡ ከመሠረታዊ የዴሞክራሲ መርህ ተፃራሪ የሆነው የአፓርታይድ ስርዓት በዴሞክራሲያዊ መንገድ ማስተካከል ሆነ ማስወገድ አይቻልም፡፡ በመሆኑም የወልቃይት ጥያቄ መልስ የሚያገኘው፤ አንደኛ፦ በትግራይ ህዝብ ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ በአማራዎች የትጥቅ ትግል ነው፡፡

የመጀመሪያው መንገድ ህወሓት በተለይ በትግራይ የዘረጋው የአፓርታይድ ስርዓት ለወልቃይት አማሮች ብቻ ሳይሆን ለብዙሃኑ የትግራይ ህዝብ የማይበጅ መሆኑን ተገንዝቦ ይህን ቡድን በፖለቲካ ምርጫ ወይም በአመፅ ከስልጣን ማስወገድ ነው፡፡ ሁለተኛው መንገድ ግን ህወሓትን በትጥቅ ትግል ማስወገድ ነው፡፡ በዚህ መንገድ በሚካሄድ ትግል የወልቃይት አማሮች ህልውና በተለይ ከጎንደር ጋር የተሳሰረ እንደመሆኑ የጎንደር ብሎም የአማራ ህዝብ በግጭቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በተመሣሣይ በወልቃይት የሚኖሩ ትግሬዎች ህልውናቸው ከተቀረው የትግራይ ህዝብ ጋር እንደመሆኑ የክልሉ ህዝብ በግጭቱ ተሳታፊ ይሆናል፡፡ በዚህ መሠረት ሁለተኛው መንገድ በአማራና ትግራይ ህዝቦች መካከል ማለቂያ የሌለው የእርስ-በእርስ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል፡፡

በአጠቃላይ የወልቃይት ጥያቄ ከአፓርታይድ ጭቆና ነፃ የመውጣት ነው፡፡ የወልቃይት አማሮች እና የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ጭቆና ነፃ እስካልወጡ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የእርስ-በእርስ ጦርነት የመከሰት ዕድሉ በየቀኑ እየሰፋ ይሄዳል፡፡

One thought on “የወልቃይት ጥያቄ: መነሻው አፓርታይድ፣ መድረሻው ጦርነት ነው!

  1. About 4 years ago , i posted a series of arguements regarding the potential danger around Welkait question , i came with the same set of scenarios that might end up with northern Ethiopia as a Balakan like state , Sandwiched with antagonist Hamasen and resenting Amhara TPLF has left the people of Tigray in a precarious situation , that is why the emphasise on Ethiopian unity is all the more important for Tigreans than any other ethnics groups in ethiopia

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡