ዶ/ር አብይ እና ህወሓቶች፡ ለይቶ ማስር ወይስ አብሮ መስራት?

ኢህአዴግ ውስጥ ስለተደረገው አመራር ለውጥና ለውጡ የተካሄደበትን ሁኔታ አስመልክቶ የተለያዩ ሃሳቦችና አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚዎች ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ ያደረገው በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ለመግታት እንደሆነ ሲገልፁ ይሰማል፡፡ በሌላ በከል አንዳንድ የህወሓት/ኢህአዴግ ደጋፊዎች የአመራር ለውጡ የተካሄደው በተለመደው የፓርቲው ደንብና ስርዓት እንደሆነና የአዲሱ ሊቀመንበር ምርጫ በአባል ድርጅቶች የጋራ መግባባት የተመሠረተ እንደሆነ ሲገልፁ ይሰማል፡፡ ነገር ግን፣ ሁለቱም አመለካከቶች በተሳሳተ ግንዛቤ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያሉ አስተያየቶች፤ አንደኛ፦ የለውጡን መነሻ ምክንያት በጥልቀት ካለመረዳት፣ ሁለተኛ፦ የአመራር ለውጡ የተካሄደበትን ሁኔታ በግልፅ ካለመገንዘብ የመነጩ ናቸው፡፡

ኢህአዴግ የአመራር ለውጥ እንዲያደርግ ያስገደደው ምንድነው? በመጀመሪያ ደረጃ ከሌሎች ክልሎች በተለየ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ቀድሞ የተጀመረው በኦሮሚያ ክልል መሆኑ ይታወሳል፡፡ በተመሣሣይ ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በተለየ የአመራር ለውጥ ያደረገው ኦህዴድ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በመቀጠል ኢህአዴግ ውስጥ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ ግንባር-ቀደም ሚና የተጫወተው አዲሱ የኦህዴድ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡

በመጨረሻም የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ጠ/ሚኒስትር የሆነው የኦህዴድ ሊቀመንበር ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸው፡፡ በመሆኑም በኢህአዴግ ውስጥ የተደረገውን የአመራር ለውጥ ለመገንዘብ፤ በኦህዴድ አመራሮች እና በክልሉ ህዝብ፣ እንዲሁም በኦህዴድ እና በተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራሮች መካከል የነበረውን ግንኙት በዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡

በተለይ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት በቄሮዎች እና በኦህዴድ አመራሮች መካከል የነበረው ግንኙነት በጠላትነት ስሜት የሚመራ ነበር፡፡ በ2008 ዓ.ም አጋማሽ በተለይ በቀበሌ፥ ወረዳና ዞን ደረጃ ላይ የሚገኙ የኦህዴድ ባለስልጣናትና የፀጥታ ሰራተኞች ህይወትና ንብረት ጠፍቷል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጲያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባቀረበው ሪፖርት መሠረት በስድስት ወር ውስጥ ብቻ 14 የፀጥታ ሰራተኞች እና 14 የመንግስት ባለስልጣናት ተገድለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ በወረዳና ዞን ደረጃ የሚገኙ የኦህዴድ ባለስልጣናት ቤትና ንብረት ወድሟል፡፡ ቄሮዎች በወሰዱት ቀጥተኛ የሃይል እርምጃ የክልሉ ባለስልጣናትና የፀጥታ ሰራተኞች የህዝቡን ጥያቄ እንዲቀበሉና ከቄሮዎች ጎን እንዲቆሙ አስገድዷቸዋል፡፡

በ2008 ዓ.ም መጨረሻ በዞንና ወረዳ ደረጃ የሚገኙ ኦህዴዶች ከክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ የቄሮዎችን ጥያቄ በመቀበል ከህዝቡ ጎን ከመቆም በስተቀር ሌላ ምርጫ እንደሌላቸው በግልፅ ተናግረዋል፡፡ የኦህዴድ ከፍተኛ አመራሮች ይህን ማድረግ ከተሳናቸው የድርጅቱ ህልውና ያከትማል፣ የባለስልጣናቱ ህይወትና ንብረት ይወድማል፡፡ ስለዚህ ኦህዴዶች በወቅቱ የነበራቸው አማራጭ የመኖር ወይም የመጥፋት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ኦህዴድ ከክልሉ ህዝብ ጎን ከቆመ ድርጅቱ ህልውናውን ያረጋግጣል፣ የህወሓት የበላይነት ያከትማል፡፡ ነገር ግን፣ ኦህዴድ እንደቀድሞው ተገዢ ሆኖ የሚቀጥል ከሆነ የህወሓት የበላይነት ይቀጥላል፣ የኦህዴድ ህልውና ግን ያከትማል፡፡

በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ ነው እንግዲህ አዲሱ የኦህዴድ አመራር ወደ ስልጣን የመጣው፡፡ የኦቦ ለማ አመራር ወደ ስልጣን እንደመጣ ቀዳሚ ተግባሩ ከክልሉ ህዝብ ጎን በመቆም እንደ ፖለቲካ ድርጅት ህልውናውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ኦህዴድ ህልውናውን ለማረጋገጥ የሚወስደው እርምጃ የህወሓትን የበላይነት የሚፃረር ነው፡፡ ምክንያቱም ህወሓት ከአመሠራረቱ ጀምሮ ዓላማው የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለዚህ ኦህዴድ የኦሮሞን ህዝብ እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚወስደው ማንኛውም ዓይነት የለውጥ እርምጃ በህወሓት ላይ ቀጥተኛ የህልውና አደጋ ይጋርጣል፡፡

ጠ/ሚ አብይ አህመድ

በአጠቃላይ በኦህዴድ እና ህወሓት መካከል ያለው ግንኙነት የመኖር ወይም የመጥፋት ነው፡፡ ኦህዴድ ካሸነፈ የህወሓት የበላይነት ያከትማል፣ ህወሓት ካሸነፈ ደግሞ የኦህዴድ ህልውና ያከትማል፡፡ ስለዚህ አዲሱ የኦህዴድ አመራር እና ህወሓት ያላቸው አማራጭ ከመጥፋታቸው በፊት አጥፊያቸውን ቀድሞ ማጥፋት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ህወሓት በህዝቦች መካከል ያለመተማመን መንፈስና ግጭት በመፍጠር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ዜጎች ገድሏል፣ አፈናቅሏል፡፡ በዚህ መሠረት ዜጎችን ሰላምና ደህንነት በማሳጣት ህወሓት ተቀባይነት ለማግኘት፣ ኦህዴድን ደግሞ ለማሳጣት ከፍተኛ ጥረት አድርጏል፡፡ ኦህዴድ ደግሞ በብሔሮች መካከል ያለውን ግንኙነትና የትብብር መንፈስ በማጠናከር በሀገር-አቀፍ ደረጃ ያለው ተቀባይነት ለማሳደግ፣ ህወሓትን ደግሞ ተቀባይነት ለማሳጣት ከፍተኛ ትግል አድርጏል፡፡

ህወሓት በዚህ አመት የመጀመሪያ ወራት ባደረገው 35 ቀናት የፈጀ ስብሰባ ዋና የመወያያ አጀንዳ የነበረው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ዳግም በማወጅ፣ “ህዝበኞች – Populist” ያሏቸውን የኦህዴድና ብአዴን መሪዎች ማሰርና የለውጡን ንቅናቄ መቀልበስ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት፣ በመጀመሪያ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ላይ ብቻ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ ሞከሩ፡፡ ይህ ሙከራ ከኦህዴድና ብአዴን ባጋጠመው ጠንካራ ተቃውሞ ውድቅ ተደረገ፡፡ በመቀጠል “ብሔራዊ የደህንነት ምክር” በማቋቋም በእጅ አዙር የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ ሞከሩ፡፡ በተለይ ከኦሮሚያና አማራ ክልል መስተዳደሮች ተቀባይነት በማጣቱ ምክንያት ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ፡፡

በመጨረሻም በ17ቱ ቀን የኢህአዴግ ስብሰባ ህወሓት ስልታዊ ማፈግፈግ አደረገ፡፡ በዚህ መሠረት፣ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ በአንፃሩ ‘ሁከትና ብጥብጥ ከተነሳ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ ከስምምነት ላይ ደረሰ፡፡ በድርድሩ ወቅት የህወሓት መሠረታዊ ዓላማ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማወጅ ፀረ-ህወሓት አቋም የሚያራምዱና በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን የኦህዴድና ብአዴን አመራሮች በማሰር የለውጡን እንቅስቃሴ መቀልበስ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከህወሓት ፍላጎትና ምርጪ ውጪ ከደኢዴን እና ብአዴን ጋር በፈጠረው ጥምረት ኦህዴድ የጠ/ሚኒስትርነት ቦታውን ያዘ፡፡

የዶ/ር አብይ መመረጥ የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን በማሰር የለውጡን እንቅስቃሴ መቀልበስ ለሚሻው ህወሓት የህልውና አደጋ ነው፡፡ የአዲሱ አመራር የመወሰን አቅምና ነፃነት የሚረጋገጠው ደግሞ የህወሓትን የበላይነት በማስወገድ ነው፡፡ በመሆኑም የዶ/ር አብይ ውጤታማነት የሚወሰነው የህወሓት ልሂቃን በፖለቲካና ኢኮኖሚው ውስጥ የነበራቸውን አድራጊ-ፈጣሪነት እንዲያከትም በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የዶ/ር አብይ አፈፃፀም ብቃት የሚለካው የህወሓትን የበላይነት በማስወገድ ሲሆን የህወሓት ህልውና ደግሞ በፖለቲካና ኢኮኖሚው ረገድ የነበረውን የበላይነት በማስቀጠል ነው፡፡

ህወሓቶች በተለያዩ ብሔሮች መካከል ግጭት በመፍጠር የለውጡን ንቅናቄ ለማኮላሸት ጥረት አድርገዋል፡፡ ይህን የማድረጉ ዋና ዓላማ በሀገሪቱ ላይ የፍርሃትና ስጋት ድባብ በመፍጠር በተለይ አዲሱን የኦህዴድ አመራር ተቀባይነት ማሳጣት ነበር፡፡ ይህን ማድረግ ሲሳናቸው ደግሞ በተለይ በቀድሞ ጠ/ሚ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አማካኝነት፣ እንዲሁም በመከላከያ፥ ደህንነቱ እና የፍትህ ተቋማት ላይ ያላቸውን የበላይነት ተጠቅመው አዲሱን የኦህዴድ አመራሮችን በማሰር የፖለቲካ ስልጣናቸውን እና በህዝቡ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት ለማሳጣት ጥረት አድርገዋል፡፡

የዶ/ር አብይን መመረጥ ተከትሎ ህወሓቶች በሥራ አስፈፃሚው ላይ የነበራቸውን ስልጣን አጥተዋል፡፡ ነገር ግን በተለይ በመከላከያና ደህንነት መዋቅሩ ላይ የነበራቸውን ስልጣን ሙሉ በሙሉ አጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት ያላቸውን የበላይነት ተጠቅመው በዜጎች ላይ የፍርሃትና ስጋት ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ በዚህ መልኩ አዲሱ አመራር በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ለማሳጣት ከመንቀሳቀስ ወደኋላ አይሉም፡፡ በሌላ በኩል፣ ዶ/ር አብይ ያለውን የፖለቲካ ስልጣን በመጠቀም በህዝብ ላይ ፍርሃትና ሽብር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱትን የህወሓት አመራሮችና ልሂቃን ማሰር ይችላል፡፡

በዚህ መሠረት ህዝቡን ከህወሓቶች እኩይ ተግባር በመከላከል ተቀባይነቱን ማሳደግ ይችላል፡፡ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ማስከበር ከተሳነው ግን ተቀባይነቱንና የመወሰን ስልጣኑን ያጣል፡፡ ህወሓቶች የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን ማስር የተሳናቸው፤ አንደኛ፦ አመራሮቹ በህዝብ ዘንድ አንፃራዊ ተቀባይነት ስለነበራቸው፣ ሁለተኛ፦ አመራሮቹን ለማሰር የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ ስላልነበራቸው ነው፡፡ ቀንደኛ በሆኑ የህወሓት አመራሮች ላይ ማስረጃ ማግኘት ግን በጣም ቀላል ነው፡፡ በመሆኑም አፍራሽ በሆኑ ተግባራት የተሰማሩና ሊሰማሩ የሚችሉት የህወሓት አመራሮች በማሰር ለፍርድ ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህን በማድረግ የህወሓትን የበላይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ማስወገድ ይችላል፡፡

2 thoughts on “ዶ/ር አብይ እና ህወሓቶች፡ ለይቶ ማስር ወይስ አብሮ መስራት?

 1. ሁልጊዜም ላክልኝ ስዩሜ ቀን ሰራ ውየ ካመለጠኝ እንዳየው
  አንተን በክፉ ያየህ አላህ የጀሃነም ያድርጋቸው!

  Like

 2. የጠ/ሚ/ር አብይን የለውጥ መንገድ ለመርዳት ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

  ዶ/ር አብይ ከሚናገሩትም ሆነ ከገዱ ቡድንና ከለማ ቡድን ጋር ያላቸውን አንድነትና ቅርበት በማየት መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት እንዳላቸው መገመት ይቻላል፣ ነገር ግን ይህን ፍላጎታቸውን በተግባር ለማሳየት ይችላሉ ብሎ ለማመን ግን ጠ/ር አብይ ያሉበትን የተቆላለፈ የሥልጣን እርከን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ፍላጎት አንድ ነገር ሲሆን፣ ፍላጎትን ወደተግባር መለወጥ መቻል ደግሞ በጣም የተለየ ነገር ነው። ፍላጎትና ችሎታ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ለውጥ ሊኖር የሚችለው ግን ሁለቱም በአንድ ላይ ሲቀናጁ ነው።
  ዶክተር አብይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ያልተቋረጠ ትግልና በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ የኦህዴድንና የብአዴንን ሙሉ ድጋፍና ከደኢህዴንም የተወሰነ ድጋፍ በማግኘት ጠ/ሚ ለመሆን ችለዋል። የሊቀመንበርነቱ ምርጫ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ቢሆን ኖሮ አብይ ጠ/ሚ ለመሆን አይችሉም ነበር። ምክንያቱም የህወሃት የበላይነት በኢህአዴግ ምክር ቤት ውስጥ እየተወገደ ቢሆንም በተቃራኒው ግን የህወሃት የበላይነት በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ እንደቀጠለ ነው። የህወሃትን የፓለቲካ አቅም ለመገንዘብ እነዚህን የኢህአዴግ ሁለት ቁልፍ የፓለቲካ መዋቅሮች ማለትም የኢህአዴግ ምክር ቤትንና የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴን በሚገባ መረዳት ይገባል።
  የኢህአዴግ ምክር ቤት አንድ መቶ ሰማንያ አባላት ሲኖሩት፣ እነዚህም ከአራቱ ድርጅቶች ማለትም ከህወሃት፣ ከደኢህዴን፣ ከብአዴንና ከኦህዴድ ከእያንዳንዳቸው አርባ አምስት አባላት የተወከሉበት ነው። የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ ደግሞ ከአራቱ ድርጅቶች ከእያንዳንዳቸው ዘጠኝ አባለት የተወከሉበት በጠቅላላው ሰላሳ ስድስት አባላት ያሉት ነው። መቶ ሰማንያ አባላት ያለውን የኢህአዴግ ምክር ቤት በተለይ በብአዴንና በኦህዴድ አባላት ውስጥ የገዱ ቡድንና የለማ ቡድን ጠንክረው በመውጣታቸው ህወሃት የኢህአዴግ ምክር ቤትን እንደቀድሞው ሊጠቀምበት አልቻለም። የኢህአዴግ ምክር ቤት ከህወሃት ሎሌነት እራሱን ነፃ በማውጣት ላይ የሚገኝ አካል ቢሆንም በህወሃት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የመጠፍነጊያ አሰራር መሰረት የፌደራል መንግስቱን ሥልጣን የሚቆጣጠረውና የሚዘውረው ግን ቱባ ቱባ ባለሥልጣኖች ያሉበትና በህወሃት የሚጋለበው ሰላሳ ስድስት አባላት ያሉት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሜቴ ነው።
  የጠ/ሚ አብይ ሕገ መንግስታዊ ሥልጣንም ህወሃት እንደፈለገ በሚዘውረው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተገደበ ነው። ምክንያቱም በኢህአዴግ አሰራር የግንባሩ ሊቀመንበር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የሚወስነውን የሚያስፈፅም ነው። ይህንንም በሚገባ ለመቆጣጠር ህወሃት የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊነትን በሞንጆሪኖ (ፈትለወርቅ) አማካኝነት የተቆጣጠረ ሲሆን፣ ሞንጆሪኖ በቅርቡ ከህወሃት ውስጥ የመለስ ዜናዊን አንጃ በማዳከምና ህወሃትን እንደድርጅት ለማጠናከር እየደከመች ያለች በህወሃት የበላይነት የምታምን ፅኑ የህወሃት ካድሬ ናት። በህወሃት ኢ-ዴምክራሲያዊ ማዕከላዊነት አሰራር መሠረት የኢህአዴግ ሊቀመንበር (አሁን ዶክተር አብይ) የሚሰራው በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውሳኔ መሠረት ብቻ ሲሆን፣ ይህንንም በየቀኑ የሚቆጣጠረውና የሚከታተለው የኢህአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊዋ ሞንጆሪኖ ነት።
  በቀላል አገላልፅ ሞንጆሬኖ ጠንካራ የህወሃት ታማኝ ካድሬ የዶክተር አብይ ተቆጣጣሪ እንድትሆን በህወሃት ተመድባለች። በዚህ አሰራር ያልተገደበው መለስ ዜናዊ ብቻ ነበር። መለስ ዜናዊ አምባገነናዊ ሥልጣኑን የተቆናጠጠው የደህንነት (የማሸበሪያ) እና የመከላከያ (የማጥቂያ) መዋቅሮችን በታማኞቹ በማስያዝና በኢህአዴግ ውስጥ ሎሌዎቹን በማጠናከር በኢትዮጵያ ላይ የህወሃትን የበላይነት በማስጠበቅ ነበር። ህወሃቶችን የመለስ ዜናዊ አምባገነንነት ባያስደሰታቸውም የህወሃትን የበላይነት በማስጠበቁ ብቻ ብዙም አልተጨነቁም። የህወሃት ስሌት የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው በመሆኑ ነበር። አሁን ዶክተር አብይ ግን መለስ ዜናዊን ሊሆኑ አይችሉም። ከኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ሲነፃፀር ጠ/ር አብይ አህመድ የታሰሩበት ገመድ ረዘም ብሎ ሊሆን ይችላል እንጂ ከእስሩ ነፃ አይደሉም።

  ስለዚህ ለጠ/ር አብይ ጊዜ ስለተሰጣቸው ብቻ መሠረታዊ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ብሎ መጠበቅ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን የለውጥ ፍላጎት ለመርዳት ምን ማድረግ ያስፈልጋል ቢሆን ለሕዝባዊ ትግሉ ጥሩ ጠቀሜታ ይኖረዋል። ይህም የጠ/ር አብይን እውነተኛ የፖለቲካ ሥልጣን ከህወሃት የበላይነት ነፃ ለማድረግ የሚቻልበትን የትግል ዘዴ ለይቶ በማወቅ የሚደረገውን ሕዝባዊ ትግል የህወሃትን የበላይነት ከፖለቲካው ሙሉ በሙሉ ለማስወገድ በሚቻልበት መንገድ ላይ ለማድረግ ይጠቀማል። ሕዝባዊ ትግሉ የገዱንና የለማን ቡድን በመፍጠር የኢህአዴግን ምክር ቤት ከህወሃት የበላይነት እያላቀቀ የመጣ ሲሆን፣ አሁንም ሕዝባዊ ትግሉ የኢህአዴግን ሥራ አስፈፃሚ ከህወሃት የበላይነት ነፃ በማውጣት ሕዝቡ ለመሠረታዊ ለውጥ የሚያደርገውን ትግል በአንድ እርምጃ ማሳደግ ይችላል።

  ስለዚህ አንዱ የወቅቱ የትግል ዘዴ ሊሆን የሚገባው የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚን ከህወሃት የበላይነት እንዴት ማላቀቅ ይቻላል የሚለው ሊሆን ይችላል። ለዚህም የመጀመሪያ ሥራ በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ የለማና የገዱ ቡድን ደጋፊ የሆኑትን እና የህወሃት ታማኝ የሆኑትን የብአዴንና የኦህዴድ አባላቶች መለየት ነው። ህወሃት የኢህአዴግን ሥራ አስፈፃሚ በበላይነት የሚቆጣጠረውና እንደ ፈረስ የሚጋልበው ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ባሉ የህወሃት ታማኝ በሆኑ የደኢህዴን፣ የብአዴንና የኦህዴድ አባላት አማካኝነት ነው። እነዚህ ግለሰቦች ውክልናቸው ተመርጠን መጥተንበታል ለሚሉት ሕዝብ ሳይሆን የትግራይ ክልል ተወካይ ነኝ ለሚለው ህወሃት ስለሆነ ይህንን እውነታ ተመርጠን መጥተንበታል ለሚሉት የምርጫ ወረዳ ሕዝብ በተገቢውና በጥንካሬ በማስረዳት ሕዝቡ አመኔታውን እንዲነሳቸው የማድረግ ሕገ መንግስታዊ መብት ሕዝቡ አለው። ይህ እንግዲህ የቄሮና የፋኖ ዋናው የሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል አቅጣጫ ሊሆን ይችላል።

  በተለይ ከኦህዴድና ከብአዴን የተወከሉ ግን ለህወሃት ታማኝ የሆኑ የኢህአዴግ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ከአስር የማይበለጡ ግለሰቦችን ሕዝቡ ሕገ መንገስታዊ መብቱን በመጠቀም በማንኛውም ጊዜ በሰላማዊ ትግል ከፓርላማም ሆነ ከክልል ምክር ቤቶች ማባረር ይችላል። ይህንንም በማድረግ እነዚህ የህወሃት ታማኞች በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ያላቸውን ወንበርና በመንግስት ውስጥ ያላቸውን ስልጣን እንዲለቁ በማድረግ በሌሎች የህወሃትን የበላይነት በሚቃወሙና ለውጥ በሚፈለጉ አባላቶች እንዲተኩ ሕዝቡ በሰላማዊ ትግሉ ሊያስገድድ ይችላል። አሁን ባለው ሕገ መንግስ አንቀፅ አምሳ አራት ቁጥር ሰባት መሰረት ”ማንኛውም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሠረት ከምክር ቤቱ አባልነት ይወገዳል” ይላል። ስለዚህ በሕዝብ አመኔታ በማጣት የተወገደን አባል የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ በአመራር ለማስቀጠል ስለማይችል የብአዴንና የኦህዴድ ማዕከላዊ ምክር ቤቶች በሌሎች አባላቶች እንዲተኩ ማድረግ ይችላሉ።

  የኦህዴድና የብአዴንና ማዕከላዊ ምክር ቤቶች ከህወሃት ሎሌነት ነፃ በመውጣት ላይ የሚገኙ በመሆኑ ለህወሃት ሳይሆን ለድርጅታቸው ታማኝ የሆኑ አዳዳሲ አመራሮችን መሾማቸው የግድ ይሆናል። በዚህ መንገድ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚን ከህወሃት ታማኞች በማፅዳት የህወሃትን የበላይነት ከፖለቲካው ሙሉ በሙሉ ማስወገድ ይቻላል። ጠ/ር አብይን ለመርዳት የሚቻለው አንዱ መንገድ የለውጥ አካል የሆነው የነለማና የነገዱ ቡድን በኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ውስጥ የበላይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ሕዝባዊ ትግሉ ይህንን የማድረግ ብቃት አለው። ስለዚህ ሕዝባዊ ትግሉ የለውጥ ኃይልንና የለውጥ እንቅፋት ቡድንን በመለየት፤ በአሁኑ ወቅት የህወሃት ሎሌ ሆነው የለውጥ እንቅፋት የሆኑትን ግለሰቦች ከኦህዴድና ከብአዴን ውስጥ አሁን ያለው ሕገ መንግስት በሚፈቅደው መሠረት በሰላማዊ ሕዝባዊ ትግል ማስወገድ ይቻላል። ህወሃትን በፓለቲካው መዋቅር ውስጥ በተለይም ቁልፍ በሆነው በፌደራል መንግስቱ ውስጥ ያለውን የበላይነቱን ማስወገድ ከተቻለ ለሕዝባዊ ትግሉ የለውጥ ጥያቄ አንድ ታላቅ ድል ይሆናል።

  በህወሃት የዘረፋ መር በሆነው መርዕ መሠረት ፓለቲካ የማጭበርበሪያ፣ ኢኮኖሚ የመዝረፊያ፤ ዳኝነት የመበቀያ፣ ደህነነት የማሸበሪያ እና መከላከያ የማጥቂያ መዋቅሮች ናቸው። ህወሃት የፖለቲካ (የማጭበርበሪያ) የበላይነቱን ከተነጠቀ የሚቀረው የኢኮኖሚ (የዘረፋ)፣ የደህንነት (የማሸበሪያ) እና የመከላከያ (የማጥቂያ) ኃይል የበላይነት ናቸው። እነዚህ የዘረፋና የመጨቆኛ መዋቅሮቹ ብቻቸውን ያለፖለቲካ መዋቅር የህወሃትን አገዛዝ ሊያስቀጥሉ አይችሉም። ያለኦህዴድ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ሎሌነት የህወሃት የግፍና የዘረፋ አገዛዝ በኢትዮጵያ ውስጥ እውን ሊሆን አይችልም ነበር አሁንም አይቻልም። ህወሃት የፓለቲካ (የማጭበርበሪያ) የበላይነቱን በመነጠቁ የእብደት መንገድ የሚመርጥ ከሆነ የሚቀረው አማራጭ በጥቂት ጀነራሎች የሚመራ ግልፅ የወጣ ወታደራዊ መንግስት መመስረት ሊሆን ይችላል። ይህም ደግሞ በኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ በአፍሪካና በዓለም በፍፁም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ የህወሃትን የአገዛዝ እድሜ በፍፁም ሊያራዝመው አይችልም። ከአሁን በኃላ የኢትዮጵያ ሕዝብ የህወሃትን የግፍ አገዛዝ የሚሸከምበት ትዕግስትም አቅምም የለውም።

  Liked by 1 person

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡