ጠባብነት እና ትምክህት፦ ከ2 አመት በፊትና በኋላ

ከ2 አመት በፊት፦ ጠባብነት እና ትምክህት

ኢህአዴግ እንደ ፓርቲና መንግስት የችግሮች ሁሉ መንስዔ አድርጎ የሚወስደው የጥገኝነት አስተሳሰብና ተግባራትን ነው። ለህዝቡ ሰላም እና ለፌደራል ሥርዓቱ አደጋ ናቸው ከሚላቸው ውስጥ፡- ጠባብነት እና ትምክህተኝነት የሚሉት በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ቃላት በመንግስት ድክመት ምክንያት ለተፈጠሩ ችግሮች ሌሎችን ተጠያቂ (externalize) ለማድረግ ነው።

በመሠረቱ “ትምክህተኛ” የሚለው እሳቤ የአማራ ብሔር ተወላጆችን በባህላቸውና በታሪካቸው ላይ ያላቸውን የራስ መተማመን ስሜት የሚሸረሽር ነው። በዚህ መልኩ የሚደረገው ተፅዕኖ በአማራ ልሂቃን ላይ የማንነት ቀውስ (identity crisis) ይፈጥራል። በዚህ መሰረት፣ አንድ ሰው በአማራነቱ ብቻ “ትምክህተኛ” እየተባለ ታሪኩና ማንነቱ እንደ ጥፋት ሲቆጠር በውስጡ የብሔርተኝነት ስሜት ያቆጠቁጣል።

በተመሣሣይ “ጠባብ ብሔርተኛ” የሚለው እሳቤ የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጲያ ታሪክ ውስጥ ያለውን ድርሻ የሚያንኳስስ፤ በሀገሪቱ አንድነት ላይ ያለውን የምሶሶነት ሚና ወደ አንድ ግንጣይ ቅርጫፍነት የሚያሳንስ ነው። በሀገሪቱ የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ የሚገባውን መጠየቁ እንደ ጥፋት ተቆጥሮ “በጠባብነት” ሲፈረጅ በኃይል ሚዛኑን ውስጥ የሚገባውን ድርሻ ለመያዝ በራሱ መንቀሳቀስ ይጀምራል።

ከላይ በተገለፀው መሠረት ላለፉት 25 አመታት ኦሮሞ “ጠባብ ብሔርተኛ” እየተባለ በሀገሪቱ አንድነት ውስጥ የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለቆየ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከብሔርተኝነት ወደ “የኢትዮጲያ አንድነት” እየቀየረ መጥቷል። አማራ ደግሞ “የትምክህት አንድነት” በሚል እንደ ብሔር የሚገባውን ጥቅምና ኃላፊነት ተነፍጎ ስለቆየ የፖለቲካ አሰላለፉን በሂደት ከአንድነት ወደ “አማራ ብሔርተኝነት” እየቀየረ መጥቷል። በዚህ የሽግግር ሂደት የሁለቱ ሕዝቦች ጥያቄ ከተቃራኒ ጫፎች ወደ መሃል በመምጣት አሁን ላይ ያልተጠበቀ ጥምረት ፈጥሯል።

ይህ አንደ ቀድሞው በሁለት ተቃራኒ ፅንፈኞች መካከል የተፈጠረ ጥምረት አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ሁለቱም ሕዝቦች በሆኑትና በሚገባቸው ልክ ጥቅምና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ በሚያደርጉት የጋራ እንቅስቃሴው የተፈጠረ ጥምረት ነው። በመሆኑም፣ የኦሮሞና አማራ ህዝቦች የፖለቲካ እንቅስቃሴ ረገድ እየታየ ያለው ጥምረት በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አስችሎታል።

ከ2 አመት በኋላ፦ ጠባብነት እና ትምክህት

ኦሮማራ” በሚል የሚታወቀው የሁለቱ ህዝቦች ትብብርና አንድነት በሀገራችን ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በዋናነት በኦህዴድና ብአዴን መካከል የተፈጠረውን ጠንካራ ጥምረት መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሀገራችን ፖለቲካ መሠረታዊ ችግር የነበረው የህወሓት የበላይነት እንዲያከትም በማድረጉ ሂደት የማይተካ ሚና ተጫውቷል፡፡ ስለዚህ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት የቻሉት በዚህ ጥምረት አማካኝነት ነው፡፡

ስለዚህ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጣበት ግዜ ጀምሮ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ከሚገቡ ተግባራት ጠባብነት እና ትምክህት ከመንግስት መዝገበ-ቃላት ውስጥ መሰረዝ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ አንደኛ፦ የእነዚህ ቃላት አጠቃቀም የኦሮሞና አማራ ህዝቦችን የእኩልነት ጥያቄ ለማፈን፥ ለማጣጣል፥ ለማንኳሰስና ተቀባይነት እንዳያገኙ ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ ሁለተኛ፦ በኢህአዴግ የአመራር ለውጥ እንዲመጣ የቻለው እነዚህን አፍራሽ ቃላትና አመለካከት በመቃወም በተፈጠረ የኦሮማራ ጥምረት አማካኝነት ነው፡፡

በመሆኑም ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ ከተመረጠበት ዕለት አንስቶ ጠባብነት እና ትምክህት የሚሉት ቃላት ከስነ-ምግባር ሆነ ነባራዊ እውነታ ያፈነገጡ እንደሆኑ ታሳቢ በማድረግ ከመዝገበ-ቃላት ውስጥ መሰረዝ ነበረባቸው፡፡ ነገር ግን፣ ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጣ ከሁለት ወራት በኋላ እነዚህ ቃላት በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት 27ኛው የግንቦት 20 የድል በዓልን አስመልክቶ ባዘጋጀው የመወያያ ሰነድ ላይ ጠባብነት እና ትምክህት የኢትዮጵያ ፌዴራል ስርዓት ዋና ተግዳሮቶች መሆናቸው ተገልጿል፦

በተጠቀሰው ሰነድ መሠረት የፌዴራል ስርዓቱ የመጀመሪያ ተግዳሮት “ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አለመዳበር” እንደሆነ ይገልፃል፦

“ብዝሃነትን በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችል የዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አስተሳሰብ በሚፈለገው ደረጃ ባለመዳበሩ ሳቢያ ጥበትና ትምክህት በብሄር ካባ የግል ጥቅም ማሳደጃ መሆን በመጀመራቸው የፌዴራል ስርዓታችን የመጀመሪያ ተግዳሮቶች ሆነዋል። የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና የዴሞክራሲያዊ አንድነት ጠላት የከረረ ብሔርተኝነት ነው። የከረረ ብሔርተኝነት ትምክህትን ወይንም ጠባብነትን ይወልዳል። ትምክህት በገዥ መደብነት በመሰለፍ የሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ማንነት በስመ ኢትዮጵያዊነት ካባ የሚንድ አስተሳሰብ ነው። ጠባብነት ደግሞ ተስፈኛ የሆነ የገዥ መደብ አስተሳሰብ ሲሆን ጭቆናን ምክንያት በማድረግ ያለአግባብ በሚሰጠው መፍትሄ የብሄሩ ገዥ መደብ የመሆን ፍላጎትን የሚያሳይ ነው። ሁሉም አስተሳሰቦች ፀረ እኩልነትና ፀረ ዴሞክራሲ ናቸው። እነዚህ አስተሳሰቦች ኢ-ምክንያታዊነትን በማጎልበትና በማሳደግ አንዱን ህዝብ በማቅረብ ሌላውን በማራቅ ፋሺስታዊ የዘር ፍጅትን የሚያመጡ አስተሳሰቦች ናቸው። በተለይም በአሁኑ ጊዜ ጥገኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት የጋራ አጀንዳቸው በመሆኑ ምክንያት ጠባብነትና ትምክህት በአንድነት የሚሰለፉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በዓለማችን በከረረ ብሔርተኝነት የተነሳ በጀርመን እንዲሁም በ1990ዎቹ መጀመሪያ በጎረቤታችን ሩዋንዳ ለሚሊዮን ህዝቦች እልቂት ምክንያት ሆኗል።”

የፌዴራል ስርዓቱ ሁለተኛው ተግዳሮት “የልማታዊነት አስተሳሰብ የበላይነት አለመረጋገጥ” ሲሆን ለዚህም በመንስዔነት የተጠቀሱት ጠባብነትና ትምክህት ናቸው፦

“የፌዴራል ስርዓት ተግዳሮት ተደርገው ከሚወሰዱት መካከል ኪራይ ሰብሳቢነትና ውላጆቹ የሆኑት ትምክህትና ጥበት ናቸው። እነዚህ ሁለት ፅንፎች እርስ በርስ በመጓተት የአገራችንን የፌዴራል ስርዓት በመፈታተን ላይ ናቸው። የትምክህት ሃይሉ የቀድሞው አህዳዊ ስርዓት መመለስ አለበት፤ እኛ ካላስተዳደርነው “አንድነትና ኢትዮጵያዊነት” ሊኖር አይችልም እኛ አዋቂ ነን በማለት ኢትዮጵያዊነትን በሃይል ለመጫን የሚፈልጉ አካላት ናቸው።… ሌላኛው አካል ደግሞ አብረው የኖሩ ህዝቦችን ለመነጣጠል፣ ኢትዮጵያ የሚለውን ስያሜ ፈጽሞ መስማት የማይፈልግ፣ አብሮ የመኖር ፈይዳ የማይታያቸው፣ ያለፈው ስርዓቶች አደረሱ የተባለውን በደል አሁን ላይ ያለው ትውልድ ለማወራረድ ህዝቦችን የሚያነሳሱ፣ ንጹሃንን በማጋጨት ወደ ስልጣን መሰላል መሰቀል የሚፈልጉ ናቸው። ሁሉም ፀረ ልማትና ዕድገት ሆነው በአንድ ጎራ ተሰልፈው ፌዴራላዊ ሥርዓቱን እየተፈታተኑት ይገኛሉ።”