ጠ/ሚኒስትሩ ስለ “ዳበረ ዲሞክራሲ” ይናገራል፣ ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤቱ ስለ “ከረረ ብሔርተኝነት” ይደሰኩራል!

የኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች የመወሰን ስልጣን ከጠ/ሚኒስትር ወይም ፕረዜዳንት ጋር አይነፃፀርም። ነገር ግን፣ የፕረዜዳንቱ ወይም የጠ/ሚኒስትሩ ስም ሲጠራ የእነሱም ስም አብሮ ይጠራል። ይህ በኢትዮጲያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ሀገራትም ያለ ነገር ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ ከፕረዜዳንቱ እንዲሁም በእንግሊዝ ከጠ/ሚኒስትሩ ቀጥሎ የቃል-አቀባያቸው ስም ይጠራል። በኢትዮጲያ ደግሞ የአቶ መለስ ዜናዊ ስም ሲነሳ የአቶ በረከት ስምዖን ስም መጠቀሱ አይቀሬ ነው። በተመሳሳይ ከገዱ አንዳርጋቸው ጎን የአቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ ከለማ መገርሣ ጎን ደግሞ የአቶ አዲሱ አረጋ ስም ሲጠቀስ ይሰማል።

አቶ መለስ ጠ/ሚኒስትር ሳለ አቶ በረከት በመጀመሪያ የማስታወቂያ ሚኒስትር፣ ቀጥሎ ደግሞ የፌደራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዪች ፅ/ቤት ኃላፊ እንደነበር ይታወሳል። በተመሳሳይ አቶ ንጉሱ የአማራ ክልላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዪች ቢሮ ኃላፊ ሲሆኑ አቶ አዲሱ አረጋ ደግሞ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዪች ቢሮ ኃላፊ እንደነበሩ ይታወሳል። እነዚህ ቃል-አቀባዮች በእንግሊዘኛ “Spokesperson” የሚባሉ ሲሆን ከስራና ተግባራቸው ጋር አብሮ የሚሄደው ስያሜ ግን “ስፒን ዶክተር – “Spin Doctor” የሚለው ነው።

“ስፒን ዶክተር” የፖለቲካ መሪዎችን ንግግርና ተግባርን ወይም ፖለቲካዊ ክስተቶችን በአንድ አቅጣጫ እንዲታዩና በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው። በመሆኑም የፖለቲካ መሪዎችን ንግግርና ተግባር፣ የተለያዩ ፖለቲካዊ ክስተቶችና ውሳኔዎችን አስመልክቶ ለሚዲያዎች መግለጫና ማብራሪያ ይሰጣል። በዚህም ነገሩ በተፈለገው አቅጣጫ እንዲታይ፣ በማህብረሰቡ ዘንድ እንዲሰርፅና ተቀባይነት እንዲያገኝ ያደርጋል።

የፖለቲካ መሪዎች ዛሬ አንድ የፖለቲካ ውሳኔ ይወስናሉ፣ ነገ ሌላ መግለጫ ይሰጣሉ፣ ከነገ ወዲያ አዲስ የፖለቲካ ክስተትን አስመልክቶ ንግግር ያደርጋሉ፣ … ወዘተ። እነዚህ ነገሮች በተለያየ አንድምታና አውድ ውስጥ የሚነገሩ ወይም የሚደረጉ ናቸው። “ስፒን ዶክተሩ” ደግሞ ወጥ በሆነ መርህ ወይም አቋም ላይ ተመስርቶ፤ ሀገሪቱ ከምትመራበት ብሔራዊ ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ ከዜጎች ጥያቄ፣ ከደጋፊና ተቃናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች ነባራዊ ፍላጎት፣ እንዲሁም ከመሪ የፖለቲካ ተቀባይነት አንፃር በመቃኘት በጉዳዩቹ ዙሪያ መግለጫና ማብራሪያ ይሰጣል። ስለዚህ አንድ “ስፒን ዶክተር” ሥራውን በአግባቡ ለመስራት በቅድሚያ በመሪው እና በፖለቲካዊ ስርዓቱ ላይ ፅኑ እምነት፣ እንዲሁም ተጨባጭ የሆነ ዕውቀትና ግንዛቤ ሊኖረው ይገባል።

“ስፒን ዶክተሩ” ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ከተሳነው የፖለቲካ መሪው ንግግርና ተግባር እንደ ደመና አየር ላይ ተበትኖ ይቀራል። የመሪው ምግባር አዎንታዊ በብዙሃኑ ዘንድ ሰርፆ ተቀባይነት ሳያገኝ ይቀራል። የመሪው ምግባር አሉታዊ ከሆነ ደግሞ ያለ-ቅጥ ይጋነናል፣ በዚህም ለተቀናቃኝ ኃይሎች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። መልካም የሆኑ ፖለቲካዊ ክስተቶች በአግባቡ ጥቅም ላይ አይውሉም። መጥፎ የሆኑት ክስተቶች ደግሞ በስፋት በማህብረሰቡ ውስጥ ይሰራጫሉ። በዚህ መሰረት፣ “የስፒን ዶክተሩ” ኃላፊነቱን መወጣት አለመቻል የፖለቲካ መሪውን ለሽንፈት ወይም ለውድቀት ይዳርገዋል። የፖለቲካ መሪው ስኬታማ ከሆነ ግን “ስፒን ዶክተሩ” ከስኬቱ በስተጀርባ እንዳለ ይታወቃል። ስለዚህ የመሪው ስም ሲነሳ “የስፒን ዶክተሩ” ስም አብሮ ይነሳል።

ኦህዴድና ብአዴን ከህወሓት ጋራ ባደረጉት ትንቅንቅ አቶ ለማ መገርሣ እና ገዱ አንዳርጋቸው የመሪነት ሚና ነበራቸው። ከእነሱ ጎን ደግሞ አቶ አዲሱ አረጋ እና አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደ “ስፒን ዶክተር” ሚናቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል። ሁለቱ ኃላፊዎች በጋራ ካከናወኗቸው ተግባራት ውስጥ፤ በበኖ-በደሌ የተከሰተውን ግጭት ከማጣራት ጀምሮ እስከ የእንቦጭ አረም ነቀላ፣ እንዲሁም የአማራና ኦሮሞ ምሁራን የውይይት መድረክ እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ። ከዚህ በተጨማሪ ሁለቱም በህወሓት ጥርስ የተነከሰባቸው መሆኑ ይታወቃል። ከጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ሊያደርገው በነበረው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግለጫ እንዳይሰጥ የሚከለክል መሆኑ እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል።

በእርግጥ ህወሓትን ለሽንፈት የዳረገው የሁለቱ ኮሚኒኬሽን ቢሮዎች ጥንካሬ ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ ህወሓት በፌደራልም ሆነ በክልል ደረጃ ያስቀመጣቸው የኮሚኒኬሽን ኃላፊዎች ስራቸውን በአግባቡ ባለመስራታቸው ጭምር ነው። በዚህ ረገድ የቀድሞ የፌደራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው ረዳን መጥቀስ ይቻላል። አቶ ጌታቸው ረዳ በተለይ ከኦሮሞና አማራ ሕዝቦች ትብብርና አንድነት ጋር በተያያዘ የተናገረው ንግግር ብንመለከት እሱ ራሱ ሌላ “ስፒን ዶክተር” እንደሚያስፈልገው እንገነዘባለን። ይህንን ደግሞ አቶ ጌተቻው ጠንቅቆ ያውቃል። በመሆኑም እንደ ዳንኤል ብርሃኔ፥ ሚሚ ስብሃቱ፥ ፍፁም ብርሃኔ፣ ሰናይት መብራቱ፣ ዳዊት ከበደ፣… የመሳሰሉትን አፈ-ቀላጤዎች “ስፒን ዶክተር” አድርጎ ቀጠራቸው። የትግራይ ክልል ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊዎች ደግሞ በማህበራዊ ሚዲያዎች ተሳዳቢዎችን አሰልጥኖ እንዳሰማራ እንደ አብርሃ ደስታ ያሉ ሰዎች በይፋ ሲገልፁ እንደነበር ይታወሳል።

ከዚህ አንፃር፣ “የጠ/ሚ አብይ አህመድ “ስፒን ዶክተር” ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ አንገብጋቢ ነው። ዶ/ር አብይ ባለፉት ሁለት ወራት “ማራኪ” የሚባሉ ንግግሮችን አድርጓል፣ መልካም የሚባሉ ተግባራት ፈፅሟል። ላለፉት 27 ዓመታት ህወሓት/ኢህአዴግ ከሀገር ውስጥ እና ውጪ የሚገኙ ዜጎችን እያፈነ አስሯል። ዶ/ር አብይ ደግሞ ከሀገር ውስጥና ውጪ የሚገኙ እስረኞችን በማስፈታት ላይ ይገኛል። በተለይ በሱዳን፥ ኬኒያና ሳውዲ አረቢያ ለአመታት በሰው ሀገር እስር ቤት ውሰጥ ተረስተው የከረሙ ዜጎችን በማስፈታት ወደ ሀገራቸውና ቤታቸው እንዲመለሱ አድርጓል። እኔም ጨምሮ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የታሰሩትን አስፈትቷል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች በመሄድ ከማህብረሰቡ ጋር ግልፅ ውይይት አድርጓል። በውጪ ሀገር ለሚገኙ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች እና ሚዲያዎች፣ እንዲሁም ለዲያስፖራው ማህብረሰብ ተከታታይ የሆነ ጥሪ አቅርቧል።

አቶ አህመድ ሽዴ፣ የኢፊዴሪ መንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሃላፊ

እነዚህ ተግባራትና ንግግሮች በታሰበው መልኩ በአብዛኛው ማህብረሰብ ዘንድ እንዲሰርፁና ተቀባይነት እንዲያገኙ ከማድረግ አንፃር የተሰራ ሥራ አለ ለማለት አያስደፍርም። የጠ/ሚ አብይን ንግግርና ተግባር ከስር-ከስር እየተከታተለ “የስፒን ዶክተር” ሚናውን መወጣት ያለበት የፌደራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ የጠ/ሚኒስትሩን እግር ተከትሎ ከሀገር-ሀገር ይዞራል። የኮሚኒኬሽን መስሪያ ቤቱ ግን አሁንም ድረስ የህወሓት ጀሌዎችና ጋሻ-ጃግሬዎች መፈንጫ ሆኗል። ዶ/ር አብይ ስለ ህዝቦች አንድነት እና እኩልነት በተናገረ ማግስት እነዚህ የህወሓት ጀሌዎች ስለ ጠባብነት እና ትምክህት 30 ገፅ ቅራቅንቦ ፅፈው “27ኛው የግንቦት 20 የድል በዓልን አስመልክቶ የተዘጋጀ የመወያያ ሰነድ” ብለው አቅርበዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ስለ “ዳበረ ዲሞክራሲ” እየተናገረ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤቱ ስለ “ከረረ ብሔርተኝነት” ይደሰኩራል። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ የጠ/ሚኒስትሩ መጨረሻ አሳዛኝ ሽንፈት ወይም ውድቀት መሆኑ አይቀሬ ነው።

One thought on “ጠ/ሚኒስትሩ ስለ “ዳበረ ዲሞክራሲ” ይናገራል፣ ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤቱ ስለ “ከረረ ብሔርተኝነት” ይደሰኩራል!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡