ግንቦት ሃያ ለአዲሱ ትውልድ ምኑ ነው?

ከዘመናዊው ታሪካችን ጅማሬ አንስቶ በሶስት ስርአቶች (በአጼዎቹ፣ ሶሻሊስቱ ደርግና በአቦዮታዊው ዲሞክራሲ ኢህአዴግ) ብቻ ሀገራችን ወደ አስር የሚጠጉ መሪዎችን አስተናግዳለች፡፡ በሶስቱም ሰርአቶች መንበሩን የተቆጣጠሩት መሪዎች አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር ባለጊዜው መሪ ከእርሱ በፊት የነበረውን ስርአት/መሪ ጠላት አድርጎ መቁጠሩና ያለፈውን “ባለጊዜ” ጥላሼት በመቀባትና ስራዎቹን በዜሮ በማባዛት በህዝቡ ዘንድ ያለው ቅቡልነት መመስረት ነው፡፡

የአጼ ቴውድሮስ ስልጣን የራሳቸውን ፍላጎት በሚያሳድዱና ሀገሪቱንና ህዝቧን በረሱ መሳፍንት ጥላቻ የተመሰረተ፣ የዋቅ ሹም ጎበዜ የንግስና ዘመን ሸዋንና ትግራይን ፍራቻና ጠላት በማድረግ የተዋቀረ፣ የአጼ ዮሀንስ የስልጣን ዘመን የሸዋን እና የጎጃምን ነገስታ ፍራቻና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ፣ አጼ ሚኒሊክ ዘመን ትናንሽና ራስ ገዝ ግዛቶችን በመደምሰስና በማጥፋት የተመሰረተ፣ የአጼ እያሱ ዘመነ ስልጣን የአያቱን “ኃላ ቀር” ስርአቶችና አገልጋዮች የሆኑትን የሸዋ መሳፍንትን ጥላቻ የተመሰረተ፣ የአባ ጠቅልል (አጼ ኃ/ስላሴ) ዘመንም እንዲሁ ባለፈው ስርትአት ታላቅ የነበሩትን መሳፍንት በማዳከም ጥላቻ ተጀምሮ ሁሉን በመጠቅለል ሲጠናቀቅ ሶሻሊስቱ ደርግም እንዲሁ በፊውዳሊስቱ የአጼዎቹ ስርአት ጥላቻ ተመሰረተ፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ በደርግን ጥላቻ ተመሰረተ፡፡

ከዮዲት ጉዲት ዘመን ጀምሮ ኢህአዴግ መንበረ ስልጣኑን እስከ ያዘበት 1983 ድረስ ባሉት 1662 ዓመታት ውስጥ ከ360 አመታት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ማሳለፋችንን የታሪክ ድርሳናት ይገልጻሉ፡፡ ይህ ማለት ከአክሱም ስልጣኔ ውድቀት በኃላ ባሉት አመታት በአማካኝ በአራት ቀን አንዴ የእርስ በእርስ ጦርነት በሀገራችን ተስተናግዷል ማለት ነው፡፡ በእነዚህ የእርስ በእርስ ጦርነቶች ወንድማማቾች እርስ በእርስ ተገዳድለዋል፣ የአንዲት ደሃ ሀገር ውድ ሀብት ጠፍቷል በዚህ ደግሞ እንደ ሀገር ተጎዳን እንጂ ማንም አሸናፊ አልነበረም የለምም፡፡ ለዚህም ይመስላል የሀገራችን ነገስታ በሰላምም ሆነ በጦርነት የንግስናውን ቆብ ሲደፉ ታሪክ እንደሚያሳየን አንዳቸውም ያለፈውን ጦርነት እንደ ድል በመቁጠር በየአመቱ ሲያከብሩት አልተስተዋለም፡፡

በመጀመሪያ በጸረ-አማራነትና ጸረ-ደርግ አስተሳሰብን አላማ አድርጎ የተመሰረተው ትህነግ (ህወሃት) 4 ኪሎ ከገባ እለት አንስቶ ላለፉት 27 ዓመታት ከማናቸውም ያለፉት ስርአት በተለየና በበለጠ መልኩ ያለፈውን ሰርአት (ደርግን) ጥላሼት ሲለቀልቅና ብዙ ሺ የአንድ እናት ልጆችን ደም ያፋሰሰውን የእርስ በእርስ ጦርነቱ ያበቃበትን ግንቦት 20ን በሀገራችን ከሚከበሩ ብሔራዊ በሀላት በተለየ መለኩ ሲከበር ኖሯል፡፡

ደርግ እና ትህነግ

ማንኛውም መንግሰት/ስርአት በዘመኑ ለመፈጸም የሚያስበውንና የሚፈልገው የራሱ አላማ አለው፡፡ ይህንን አላማውን ለመፈጸም የተለያዩ መንገዶችና ዘዴዎችን የሚጠቀም ሲሆን ይህንን አላማ የሚደግፉ ቡድኖች ወይም ግለሰቦችን ከጎኑ ሊያሰልፍ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ይህንን በመቃወም ሌሎች ወገኖች ሊነሱ፣ ብዙዎችን ሊያሰልፉና ባለው ስርአት/መንግስት አላማና መንገድ ላይ ተቃውሟቸውን በሰላም ወይም በኃይል ሊቀጥሉ ይችላላ፡፡ ሁለቱም ግን የቆሙለት አላማና መንገድ አላቸው ይህንኑ በመደገፍ ብዙዎች ከጎን ተሰልፈዋል፡፡ ይህ በማንኛውም ሀገር ያለ ፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡

በቤተ-መንግስት ጥበቃ ላይ ሳለ የተገደ የቀድሞ ወታደር እና የህወሓት/ኢህአዴግ ታጣቂዎች ወደ 4ኪሎ ቤተ መንግስት ሲገቡ፣ ግንቦት 20/1983 ዓ.ም Photo Credit: Eduardo Byrono

ደርግ በዘመኑ አንድ ሀገር ኢትዮጲያ የሚል አላማ ነበረው (ሌሎች ቸግሮች እንዳሉበት ሆነው) ህወሃት ደግሞ ትግራይንና ኤርትራን በመገንጠልና በማስገንጠል የራሱን ሪፐብሊክ የመመስረት አላማው ነበር፡፡ የደርግንም የትህነግን አላማ በመደገፍ ሺዎች ከሁለቱም ተቃራኒ ሃይላት ጎን ተሰልፈው ሞተዋል፥ ተሰውተዋል፡፡ ሁለቱም ግን የተለያየ አላማ ያላቸው የአንድ ሀገር፣ የአንድ እናትና የአንድ ቤተሰብ ልጆች ናቸው፡፡ ደርግ ተሸነፈ ትህነግ አሸነፈ፡፡ ለአንዲት እናት ግን የሁለት ልጆቿ ግጭት በምንም መስፈሪያ ድል የለውም ፋሲካም ሊደረግ ፈጽሞ አይገባም፡፡

ግንቦት ሃያ እና አዲሱ ስርአት/ትውልድ

ባለፉት 26 አመታት ትህነግ መራሹ ኢህአዴግ ግንቦት ሃያን “ተራሮችን ያንቀጠቀጠውን ትውልድ” ታሪክ በተለየ መልኩ በመደስኮርና እነርሱ ባይኖሩ ኖር ሀገራችን አፈር ከድሜ ትበላ እንደነበረ እየነገረን አሳልፈናል፡፡ አሁን ግን የግንቦት ሃያ ትክክለኛ ውጤት ታይቷል፡፡ ጭቆናን፣ እስር፣ ስደት፣ መከፋፈል፣ ህዝቦች ጠላትነት መተያየት የመሳሰሉ ብሶቶች ላለፉት 26 አመታት በግንቦት ሃያ ያልተነገሩ የሀገራችን ሀቆችና የግንቦት ሃያ ፍሬዎች ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ “ለአዲሲቱ ኢትዮጲያና ለአዲሱ ትውልድ” ግንቦት ሀያ በአሳዛኝ መልኩ የበዙ ወንድሞቻችንና ሀብታችንን ያጣንበትና ከአንድ ስርአት ወደ ሌላ ስርአት የተደረገ ሽግግር እንጂ ምንም የተለየ ትርጉምም የለውም፡፡

ጥልቅ አፍቅሮተ ግንቦት ሃያ ካለባቸው ያለፉት የኢህአዴግ መሪዎች በተለየ መልኩ የህዝብ ብሶት ለወለደው ለዶ/ር አብይም መንግሰት ግንቦት ሃያ እንደ ከዚህ በፊቱ የድል ቀን ሳይሆን መሆን ያለበት የስህተታችንና የመከፋፈላችን ጅማሬ እንደመሆኑ፤ አዲስ በሆነ መልኩ አዲሲቱን ኢትዮጲያ በተሻለ መልኩ ለመገንባት ለምናደርገው ጉዞ የይቅርታ መጠያየቂያ፣ ግንቦት ሃያን ተከትሎ በመጣው ስርአት ምክንያት በእስር ቤት ያሉ ወገኖቻችንን በመፍታት፣ በየአካባቢው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን መፍትሄ በመስጠትና የግንቦት ሃያ ስህተቶችን ለማረም ቃል የሚገባበት መሆን ይኖርበታል፡፡

አዲሱ ትውልድ ከዚህ ቀደም ትህነግ ታደርግ እንደነበረው አይነት ግንቦት ሃያን ማየት አይፈልግም፡፡ “ትህምክተኛና ጠባብ” እየተባለ ሲለፈፍ ስንት አመት ቁጭ ብለን ሰማን፡፡ ግንቦት ሃያ መከበር ካለበት በአዲስ መልኩ ያለፉት ሶስት አመታት የተካሄዱ ህዝባዊ ፍልጎቶችንና መስዋህቶችን በመዘከርና በእነርሱም ዙሪያ በመወያየት ወደ ተሻለ ዲሞክራሲና አንድነት ወደሚያደርሱን መግባባቶች በመፍጠር መከበር ይኖርበታል፡፡