የኢሉ_አባቦራ ተፈናቃዮች ጉዳይ

ትላንት ከምራብ ሸዋ ቄያቸውን ለቀው አዲስ አበባ የመጡት አርሶ አደሮች “ወደ ቀበሌያቸው ተመለሱ” እንደተባለ ወዲያው “በኢሉአባቦራ ዞን የሚኖሩ አማራዎች ተፈናቀሉ” የሚል ዜና ተከተለ፡፡ ከዞኑ ተፈናቅለው በባህርዳር ከተማ የምግብ ዋስትና ቤሮ ከሚገኙት አርሶ አደሮች ውስጥ አንዱን በስልክ አነጋግሬዋለሁ፡፡ እንደ እሱ አገላለፅ፣ ከዞኑ የተፈናቀሉት ቁጥራቸው ወደ 200 የሚጠጋ ሲሆን የተፈናቀሉት ቀን ደግሞ ከ3ወር በፊት የካቲት 07/2010 ዓ.ም ነው፡፡ እዚህ ጋር 3 ነገሮችን ማንሳት ይቻላል፡፡

1ኛ) እነዚህ ሰዎች ወደ መሬታቸው እንዲመለሱ ተገቢው ሥራ ሳይሰራ ለ3 ወራት በምግብ ዋስትና ቤሮ እንዲቆዩ መደረጉ ፍፁም ተቀባይነት የለውም፡፡ የአማራና ኦሮሚያ ክልል ቢሮ ሃላፊዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት ባለመቻላቸው ተጠያቂ ናቸው፡፡

2ኛ) የችግሩን መንስዔ ለመረዳት ሰዎቹ የተፈናቀሉበትን ግዜ ማስታወስ ብቻ በቂ ነው፡፡ ከየካቲት 03 – 05/2010 ዓ.ም በመላው ኦሮሚያ አድማና ተቃውሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ህወሓት ደግሞ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በአርሲ ዞን የሃይማኖት ግጭት፣ በኢሉ_አባቦራ ደግሞ የብሔር ግጭት በመቀስቀስ አስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ የሚጣደፍበት ወቅት ነበር፡፡ ስለዚህ ሰዎቹ የተፈናቀሉት የካቲት 09/2010 ዓ.ም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ በተሰራው ሸርና አሻጥር ምክንያት ነው፡፡

3ኛ) ከምዕራብ ሸዋ የተፈናቀሉት ሰዎች ወደ ቀበሌያቸው እንዲመለሱ ጥረት እየተደረገ ባለበት ወቅት “ይሄው አሁንም አማራዎች ከኢሉ_አባቦራ ዞን ተፈናቀሉ” ብሎ ነገሩን ማባባስ ለአማራ ሆነ ለኦሮሞ ህዝብ አይበጅም፡፡ ችግሮች ይኖራሉ፣ በተለያየ አጋጣሚ ሰዎች ይፈናቀላሉ፡፡ ነገር ግን፣ እንዲህ ያለ ችግር ሲከሰት በተጨባጭ እውነታ ላይ ተመስርቶ መነጋገርና መፍትሄ መፈለግ ይገባል፡፡

ከግለሰቡ ጋር ያደረኩትን የስልክ ውይይት አንዲትም ቃል ሳልቀንስ አቅርቤዋለሁ! ከዚህ በተጨማሪ፣ የአማራ ክልል ምግብ ዋስትና ቢሮ ተፈናቃዮቹን የመዘገበበት የስም ዝርዝር፣ ለመሬታቸው ግብር የከፈሉበት ደረሰኝ እና ለኦሮሚያ ክልል ያቀረቡት አቤቱታ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ቀርቧል፡፡