የህወሃት ኢኮኖሚ፣ የዶላር ሽሽትና የመንግስት ስጋት

ከደርግ ውድቀት ጀምሮ በሀገራችን በሁሉም መስክ የህወሃት/ትህነግ የበላይነት ነበር፡፡ ይህ የበላይነት ግን በአንዳንድ መስክ (በተለይ በፖለቲካው መስክ) ከቁቤው ትውልድ ቄሮ መምጣትና መነሳት በኃላ የተዳከመ ይመስላል፡፡ ዶ/ር አብይ የትህነግን የጀርባ አጥንቶች በተለያዩ ሰበቦች ከቤተ-መንግስቱ አካባቢ ዞር ማድረጋቸው ጥሩ ጅማሬ ቢሆንም ትህነግና መሪዎቹ ባለፉት 27 አመታት በህገ ወጥ መንገድ የመሰረቱትን ኢኮኖሚ ግን ለመቆጣጠር ጥረት ሲደረግ አልተስተዋለም (በውጪ ያላቸው አካውንት ይመረመራል ከማለት ውጪ)፡፡ ከዚሁ ጋር ተዳምሮ አሁንም የደህንነቱና የመከላከያው መዋቅር በትህነግ ቁጥጥር ስር መሆኑ ለመንግስታቸው ትልቅ ስጋት ነው፡፡

የተዳከመው ኢኮኖሚ…

የሳይንሳዊ ሶሻሊዝም አባት በሆነው ካርል ማርክስ እምነት ኢኮኖሚ የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ በአንድ ሀገር ወይም ማህበረሰብ ውስጥ ኢኮኖሚውን የተቆጣጠረ ማንኛውም አካል ሁሉንም ነገር እንደፈለገ መቆጣጠር ይችላል፡፡ ማንም መንግሰት የኢኮኖሚ የበላይነት ሳይኖረው የፖለቲካ የበላይነት ሊያመጣ አይችልም፡፡ ለዚህም ነው ሶሻሊስቶች ከሁሉ ነገር በፊት ኢኮኖሚን ለመቆጣጠርና በስራቸው ለማድረግ የሚሞክሩት፡፡ የካርል ማርክስ እምነት ትክክል እንደሆነ የተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ ያሳያል፡፡

በሀገራችን በቅርቡ የሚታዩት የተለያዩ ተስፋዎች እንዳሉ ሆነው ለዶ/ር አብይ መንግስት ትልቁ ውስጣዊ ተግዳሮት የሚመነጨው ከዶላር እጥረት ሊሆን ይችላል፡፡ የዶ/ር አብይ መንግስት የዶላር እጥረቱን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን ማድረግ ቢጠበቅበትም ብዙ ዶላሮችን የሸሸጉትን የትህነግ ሰዎችንና ጋሻ ጅግሬዎቻቸውን ዶላርና ዩሮ የማስመለሱን ጉዳይ ሊያስብበት ይገባል፡፡

በብዙ ቢሊዮንና የሚቆጠር ዶላር በትህነግ ሰዎች ስም በውጪም በሀገር ውስጥም ተሰውሯል፡፡ ሀገሪቱ በዶላር እጥረት በምትንገላታበት በዚህ ወቅት እንኳን የበዛ የዶላር ክምር ከሀገሪቱ ወደ ውጪ ሽሽት ይዟል (በቅርቡ ወደ ውጪ ሊወጣ ሲል የተያዘን ብዙ ዮሮና ዶላር ልብ ይሏል)፡፡ አሁን ከደረሰባ የፖለቲካ ኪሳራ አንጻር ትህነግ ይህንን ማድረጓ ብዙም አይደንቅም ነገር ግን የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት እንደዚህ አይነቱን የትህነግ እንቅስቃሴ በትኩረት መከታተል ካልቻለ አደጋው የከፋ ይሆናል፡፡

በዶላር እጥረቱ ምክንያት የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተቋረጡ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በዶ/ሩ ላይ ትልቅ ተጽህኖን ይዞ ይመጣል፡፡ የኑሮ ውድነቱ ደግሞ በዚህ ላይ ሲደረብ አደጋውን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ከ25 ዓመታት በኃላ የከፋ የፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ ያለችው ትህነግ ይህንን አጋጣሚ ሆን ብላ ልትጠቀምበት ወይም ይበልጡኑ በማባባስ የቀድሞውን ተጽህኖ ለማስመለስ መጣሯ አይቀሬ ነው፡፡

የትህነግና የኢህአዴግ ሰዎች በሀገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የውጪ ሀገራት ገንዘብ መሸሸግ ልማዳቸው እንደሆነ በተለያዩ ወቅቶች በእርስ በእርስ መጠላለፍ ውስጥ በገቡበት ሰአት ተመልክተናል፡፡ አሁንም ቢሆን የከሰሩ የትህነግም ሆነ የኢህአዴግ ሰዎች እንደዚሁ ያደርጋሉ፡፡ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም ከሀገር ውጪ በተለያየ መልኩ ሊያሸሹና ሊያስመልጡ ይችላል፡፡ እየነፈሰ ባለው አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ በስጋት ውስጥ ያሉት የደህንነትና የመከላከያ ተቋም አላፊዎች ለዚህ ስራ አይተባበሩም ብሎ ማለት አይቻለም፡

ስለዚህ የዶ/ር አብይ መንግስት ምንም ጊዜ ሳይሰጥ የቀድሞዎቹም ሆነ በስልጣን ላይ ያሉት ኃላፊዎች በውጪም በሀገር ውስጥም የሸሸጉትን የሀገርና የህዝብ ሀብት በሰላም እንዲያስረክቡ መጠየቅ ካልሆነም እንደ ሳውዲ አረቢያው ልዑል በግዳጅ እንዲመልሱ ካላደረገና ኢኮኖሚውን በቁጥጥሩ መድረግ ካልቻለ ተስፋው እንደ ጉም መትነኑ የማይቀር ነው፡፡

2 thoughts on “የህወሃት ኢኮኖሚ፣ የዶላር ሽሽትና የመንግስት ስጋት

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡