ይህ ክስተት “ታሪካዊ” ካልተባለ “ታሪክ” የሚባል ነገር የለም!

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ODF) አመራሮች አዲስ አበባ ሲገቡ የቀድሞ አፈ-ጉባኤ አባዱላ ገመዳና የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ ሺዴ አቀባበል አድርገውላቸዋል። በተለይ አቶ አባዱላ ገመዳ እና ሌንጮ ለታ ሲተቃቀፉ ማየት ለአንዳንድ የኦሮሞ ልሂቃን ልዩ ትርጉም አለው። ይህን አስመልክቶ የድህረ-ገፃችን ዋና ኢዲተር ዶ/ር መንግሥቱ አሰፋ ክስተቱን “ታሪካዊ” (Historic) በማለት ገልፆታል። እንደ ታምራት ነገራ ያሉ የፖለቲካ ተንታኞችና ልሂቃን ደግሞ ክስተቱ ይህን ያህል ትኩረት ሊሰጠው የማይገባ እንደሆነ በመግለፅ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አንፃር፣ የእነ ሌንጮ ለታ ወደ ሀገር ቤት መመለስን ፖለቲካዊ ፋይዳ በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

አቶ አባዱላ ገመዳ እና አቶ አህመድ ሽዴ ቦሌ አለም-አቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት ለኦዲኤፍ (ODF) አመራሮች አቀባበሎ ሲያደርጉ፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ እነዚህ የቀድሞ የኦነግ አመራሮች የኦሮሞን ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ለማረጋገጥ ለረጅም አመት የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። የደርግ መንግስት ሲወድቅ ደግሞ የሽግግር መንግስቱ አካል በመሆን በሰላማዊ ፖለቲካ የኦሮሞን ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ተንቀሳቅሰዋል። በዚህ መሰረት፣ ሕገ-መንግስቱን በማርቀቁ ሂደት ተሳታፊ ሆነዋል። ከዚያ ቀጥሎ በ1987ቱ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ ቅድመ-ዝግጅት አድርገዋል። ይህን ያደረጉት በወቅቱ አድራጊ-ፈጣሪ ከነበረው ህወሓት/ኢህአዴግ ጋር ከጫካ ጀምሮ የነበራቸውን የአቋምና አመለካከት ልዩነት ወደ ጎን በመተው ነው።

ህወሓት እስከ 1979 ዓ.ም ድረስ ከኦነግ ጋር ጥምረት ለመመስረት ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ በአባዱላ ገመዳና ኩማ ደመቅሳ መሪነት ኦህዴድን እንዳቋቋመ ይታወቃል። ከህወሓት ጋር ጥምረት መፍጠር ያልተቻለበት መሰረታዊ ምክንያት ኦነግ እንደ ኦህዴድና ብአዴን የህወሓትን የስልጣን ጥማት ለማርካት የተፈጠረ አለመሆኑ ነው። ከዚያ ይልቅ፣ የኦነግ ዓላማና ግብ የኦሮሞን ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት ማረጋገጥ ነበር። የሽግግር መንግስቱን የተቀላቀሉትም ይህን ዓላማ ዕውን ለማድረግ ያስችለናል በሚል እምነት ነበር። ሆኖም ግን፣ የ1987ቱ ምርጫ እየተቃረበ ሲመጣ የህወሓት የስልጣን የበላይነት ቀቢፀ-ተስፋ እየሆነ መጣ።

በወቅቱ ኦህዴድ/ኢህአዴግ በኦሮሞ ሕዝብና ልሂቃን ዘንድ የክህደትና ውርደት ምልክት፣ ኦነግ ደግሞ የኦሮሞ ነፃነትና እኩልነት “አርማ” ተደርጎ ይወሰድ ነበር። ኦነግ በ1987ቱ ምርጫ ተሳታፊ ከሆነ የኦህዴድ/ኢህአዴግ ሕልውና፣ የህወሓት የስልጣን ጥማት መና ሆኖ መቅረቱ እርግጥ ሆነ። ስለዚህ ኦነግ በምርጫው እንዳይሳተፍ ህወሓትና ኦህዴድ በኦነግ አባላትና አመራሮች ላይ የከፋ እርምጃ መውሰድ ጀመሩ። በመጨረሻ የኦነግ አመራሮች ሀገር ጥለው እንዲወጡ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ አባላትና ሰራዊት ሜዳ ላይ ተበትኖ በህወሓት/ኦህዴድ መራሹ ጦር ተጨፈጨፈ። በዚህ መልኩ የቀድሞ የኦነግ አመራሮች ሀገር ጥለው ሸሹ፣ ህወሓትና ኦህዴድ ምርጫውን በጉልበት “አሸነፉ”።

አቶ አባዱላ ገመዳ እና አቶ ሌንጮ ለታ (ከግራ ወደ ቀኝ)

“ኦህዴድ ከምስረታ ጀምሮ አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ትልቁን የመሪነት ሚና የተጫወተው ማን ነው?” ቢባል ያለ ምንም ጥርጥር አቶ አባዱላ ገመዳ ነው። አቶ አባዱላ ገመዳ ከጦር ጄኔራልነት እስከ ፕረዜዳንትነት፣ ኦነግን ከሀገር በማስወጣት ሆነ ወደ ሀገር በማስገባቱ ረገድ ግንባር ቀደሙን ሚና ተጫውቷል። ከማንም በፊት በአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከማቋቀም ጀምሮ ከሌሊቱ አስር ሰዓት ከጠባቂዎቹ ጋር ወደ አቃቂ በመሄድ በአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ ክልል መካከል የድንበር ችካል እስከ መትከል ደርሷል።

አቶ አባዱላ ገመዳ በውጪ ከሚገኙ የኦሮሞ ልሂቃን ጋር ባለው ጥብቅ ግንኙነት በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተገምግሞበታል፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የደህንነት ሹም የሆነው ጄኔራል ከስልጣን ካልወረደ በሚል ከአፈ-ጉባኤነት ወርዷል። በመጨረሻም ጠ/ሚ አብይ አህመድ እና አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ለኦሮሞ ሕዝብ ነፃነትና እኩልነት የሚታገሉ ብዛት ያላቸው የኦህዴድ አመራሮችን አፍርቷል። እነዚህ አዳዲስ የኦህዴድ አመራሮች አባዱላን “ጃርሳው” ወይም “ሽማግሌው” በሚል የቅፅል ስም ይጠሩታል። መቼም፥ በምንም ምክንያት ቢሆን የጃርሳውን ውለታ እንደማይዘነጋ ጠንቅቀው ያውቁታል።

እንግዲህ የቀድሞ የኦነግ መሪ የሆነው ሌንጮ ለታ ወደ ሀገር ቤት ሲገባ አቀባበል ሊያደርግለት የተገኘው አባዱላ ገመዳ ነው። ይሄ ምን ትርጉም አለው? በመጀመሪያ ደረጃ የህወሓትን የስልጣን ጥማትና የኢኮኖሚ ዘረፋ ለማሳካት በሚል የአባዱላ ኦህዴድ የኦነግን ሌንጮ ለታ ከሀገር አስወጣው። ውሎ-ሲያድር የህወሓት ዓላማና ግብ ምን እንደሆነ ለአባዱላና ኦህዴድ ተገለጠላቸው። በመቀጠል አባዱላና ኦህዴድ ከቄሮዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር የህወሓትን የስልጣን ጥማትና የበላይነት በማኮላሸት የመሪነት ስልጣኑን በእጃቸው አስገቡ።

በመጨረሻም በግፍ ከሀገር ያባረሯቸውን የቀድሞ የኦነግ፣ አሁን ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ODF) አመራሮች ወደ ሀገራቸው ገብተው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቀረቡላቸው። የODF አመራሮች ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ ከሀገር እንዲወጡ ያደረጋቸው የኦህዴድ መሪ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ በመሄድ አቅፎ እየሳመ ተቀበላቸው። በህወሓት የስልጣን ጥማትና የበላይነት ምክንያት የተጣሉ የኦሮሞ ልጆች “እንኳን ደህና መጣህ?” እና “እንኳን ደህና ቆየህኝ” ተባብለው “ይቅር” ተባባሉ። ይህ ክስተት “ታሪካዊ” ካልተባለ “ታሪካዊ” የሚባል ነገር የለም!

One thought on “ይህ ክስተት “ታሪካዊ” ካልተባለ “ታሪክ” የሚባል ነገር የለም!

  1. It is true that was historic mistake this one is historic event. We Always learn from our mistake, people like Lencho Letta are wise and their struggle for Oromo people should be respected. TPLF elite are very dangerous and greedy fish. They are not trusted their game us over the Oromo family is United to form greater and United Ethiopia. History made by two brothers.

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡