“የፌደራሊዝም ስርዓቱ የሰላም ወይስ የግጭት መንስዔ ነው?” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሄደ

የሰላምና ልማት ማዕከል በአዲስ አበባ፥ ሃሮማያ፥ አምቦ፥ ጎንደርና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች “ዘላቂ ውይይት ፕሮጀክቶች” (Sustained Dialogue Project) አሉት፡፡ የፕሮጀክቱ ዓላማ በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል ዘላቂ የሆነ ውይይት በማካሄድ በመካከላቸው ያለውን ግጭትና አለመግባባት በንግግር መፍታት መቻል ነው፡፡ እንደሚታወቀው ባለፉት አመታት በተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በተማሪዎች መካከል አለመግባባቶችና ግጭቶች እየተለመዱ መጥተዋል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ “የዘላቂ ውይይት ፕሮጀክት” ተሳታፊ ተማሪዎች

የሰላምና ልማት ማዕከል በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚስተዋለውን የተማሪዎች ግጭትና አለመግባባት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችል ጥናት አካሂዷል፡፡ በዚህ መሠረት የችግሩ ዋና መንስዔ በተማሪዎቹ መካከል ግልፅና ገለልተኛ የሆነ ውይይትና የሃሳብ ልውውጥ አለመኖሩ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ስለዚህ ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው በተማሪዎች መካከል ግልፅና ገለልተኛ ውይይት በማድረግ ነው፡፡

ይህን መሠረት በማድረግ የሰላምና ልማት ማዕከል፣ በመጀመሪያ በ2001 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ “ዘላቂ ውይይት ፕሮጀክት” ጀመረ፡፡ ከዚያ በቀጠል በሃሮማያና አምቦ ዩኒቨርሲቲዎች፣ እንዲሁም በባህር ዳር አና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ከሁሉም ቀድሞ የተጀመረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ግዜ ተጠናቅቋል፡፡ በመሆኑም የፕሮጀክቱ ሥራ በተማሪዎች “የሰላም ክበብ” አማካኝነት እንዲከናዎን ርክክብ ተደርጏል፡፡ ፕሮጀክቱ በሃሮማያና አምቦ ዩኒቨርሲቲዎች ከተጀመረ የተወሰኑ አመታት ያስቆጠረ ሲሆን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክት ከተጀመረ ገና አንድ አመቱ ነው፡፡

ከፕሮጀክቱ ስም መረዳት እንደሚቻለው፣ በዘላቂ ውይይት ፕሮጀክት” (Sustained Dialogue Project) ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የመጡ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡና ከገቡ በኋላ ከብሔር፥ ቋንቋ፥ ፖለቲካ፥ ሃይማኖት፥ ባህልና ሌሎች ማህበራዊ እሴቶች ጋር በተያያዘ ያላቸውን የግል እምነትና አመለካከት በነፃነት የሚገልፁበት መድረክ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በፕሮጀክቱ ተሳታፊ የሆኑ ተማሪዎች 12 አባላት ባለው ቡድን ታቅፈው በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብና አስተያየት ይሰጣል፡፡ በዚህም በመካከላቸው ያለውን ልዩነትና አለመግባባት በውይይት ይፈታሉ፡፡

ፎቶ ከግራ ወደ ቀኝ: አቶ አይተን አንመው – የሰላምና ልማት ማዕከል ዋና ስራ አስኪያጅ፣ አቶ አስቻለው ተክሌ – ከፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ አቶ ስዩም ተሾመ – ከአምቦ ዩኒቨርሲቲ ወሊሶ ካምፓስ፣ አቶ ምስጋናው ሙሉጌታ – የህግ ባለሙያ፣ አቶ ውሄበግዜር ፈረደ – ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ

በተጠቀሰው የውይይት መርሃ-ግብር ተማሪዎች እርስ-በእርስ ይግባባሉ፡፡ ሁሉም ተማሪ የተሻለ ነፃነትና ህይወት እንደሚሻ ይረዳሉ፣ እያንዳንዱ ተማሪ ለራሱ የተሻለ ግምት እንዳለው ያውቃሉ፣ ከሌሎች ጋር በእኩል ዓይን መታየት እንደሚሻ ይገነዘባሉ… በአጠቃላይ በግልም ሆነ በማህብረሰብ ደረጃ ነፃነት፥ እኩልነት እና ፍትህ የሁሉም ጥያቄ እንደሆነ መገንዘብና መረዳት ይችላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለጋራ መግባባትና ስምምነት እንቅፋት በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡

በዚህ መሠረት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የዘላቂ ውይይት ፕሮጀክት ተሳታፊ ተማሪዎች በፌደራሊዝም ስርዓቱ ዙሪያ ያላቸውን ጥያቄ አቅርባዋል፡፡ ከፌደሬሽን ምክር ቤት፣ የህግ ተቋማትና ዩኒቨርሲቲዎች የተጋበዙ እንግዶች ከተማሪዎቹ በተነሳው ጥያቄ ዙሪያ የተለያየ ሃሳብና አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ ተማሪውቹም የተለያዩ ጥያቄዎች በማንሳት ግልፅና ነፃ የሆነ ውይይት ተካሄዷል፡፡ በተለይ “በብሔር ላይ የተመሠረተው የፌደራሊዝም ስርዓት የሰላም ወይስ የግጭት መንስዔ ነው?” በሚለው ዙሪያ አፅንዖት ተሰጥቶታል፡፡ በአጠቃላይ የሰላምና ልማት ማዕከል ባዘጋጀው መድረክ ውጤታማ የሆነ ውይይት የተደረገ ሲሆን በቀጣይም ተመሣሣይ የውይይት መድረኮች ሊዘጋጁ ይገባል፡፡

One thought on ““የፌደራሊዝም ስርዓቱ የሰላም ወይስ የግጭት መንስዔ ነው?” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ተካሄደ

  1. በተማሪዎች መካከል እንድህ ሀይነቱ ግንኙነት መጀመሩ ጥሩ ግባሀት ነዉና በሁሉም ዩንቨርስትዎች ብዳረስ ጥሩ ነዉ።ለላሁ ተማራዎቹ የሳይኮሎጂ መፂሀፎችን በማበብ እዉታቸሁን ማዳበር መልእክቴ ነዉ።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡