ለሁላችንም ደህንነት ሲባል ሴቶች ፍትሕን እንዲሰጡን መተው አለብን!

By Mulugeta B. Teferi

“ፍትሕን ማን ይሻል ቢሉ የተጠማ” የሚለው የፍትሕን ትርጉምና ፋይዳ በአጭሩ ያስረዳኝ አገላለፅ ነው። ምንም እንኳ ሰውየውን እና ሀሳቡን ለመረዳት እስካሁን እየትችገርኩ ብሆንም፣ “ሪፕብሊክ” (Republic) በተባለው የውይይት መፅሀፍ ውስጥ ስለፍትሕ ካለው ብዙ ነገር ውስጥ አንዱ እንዲህ ያለ ትርጉም ይሰጣል። ሰዎች እንደሚሉት ትክክል ያልሆነ ነገር ማደረግ በራሱ አስፍላጊ ነው። ከሁሉም በላይ ግን በሌሎች ትክክል ያልሆነ ደርጊት ምክንያት መጎሳቆልን ማንም አይፈልግም።

በክፉ አድራጊው ምክንያት የትጎሳቆልው ሰው ስቃይም፤ ክፉ አድራጊ ደረጊቱን በመፈፀሙ ካግኘው ጥቅም (ደስታ) ይበልጣል። በመሆኑም የሰው ለጅ በሁለቱም በኩል ሆኖ ያያል (ግፍ ሰርቶም፤ ተሰርቶበትም)። በተለይም ሁሌም ለነእርሱ ትክክል የሆነውን ብቻ በማድረግ፤ በሌላ አጋጣሚም የበደል ፅዋ ሳይጠጥጡ ለምቆየት (ሁሌ አሸናፊ፣ ቀሚ፣ ገዳይ) የሚያስተማምን ሃይል የሌላችው ለራሳቸው ብቻ የሚጠቅመውን አድርገው የሚያገኙትን ደስታም ለመተው፤ ሰዎችም በነርሱ ላይ መጥፎም እንዳያደርሱባቸው ውል ይግባሉ። ፍትሕ በሁለቱ መካከል ያለ ማቻቻል ነው (The Republic by Plato Book 2 Section 1)።

ይህ እንግዲህ በእኛ ሀገር አንድ ልማድ አንስተን ብናይ ዘመድ በሰው ተገድሎበት እያለ፤ በራሱ ስሜት ተመርቶ ገዳዩን የገደለ እና በህግ ያልተጠየቀ ሰው ሙሉ በሙሉ የልቡ የሞላል ማለት ነው። ሰው ሞቶበት ደም ለመመለስ አቅም ያጣ፣ ሕግም/ሽምግልናም ያልጠየቀለት ደግሞ ሀዘኑ እጥፍ ድርብ ነው። ሁሌም ጉልበት የለም እና የመጀመሪያው ሰው የሁለተኛው ሰው እጣ ይደርሰኛል ብሎ መስጋቱ አይቅርም። ሁለተኛው ሰውም ገዳይ በሕግ አልያም በሽምግልና ቢያዝለት አሁን ካለበት መሪር ሀዘን ያገግማል። በትክክል ማየት እንደሚቻለው ከአጥቂ ይልቅ ተጠቂ፣ ከጉልበታም ይልቅ (ኮሳሳ) አቅመ-ቢስ፣ ከበዳይ ይልቅ ተበዳይ ለፍትሕ ዘብ ናችው።

በግለሰቦች የተወሰንውን ይህን ዕይታ ግለሰብ የሚቧደንባቸውን ሌሎች መስፈርቶች ተከትለው የተለዩ ቡድኖችም ግንኙነታቸው ተመሳሳይ ነው። በሀገራት መካከል ብናይ አለም አቀፍ ህግን በአብዛኛው ሀያላን ትንንሽ ሀገራትን እንዳይወሩ አልያም እንዳያጠቁ ይረዳል። በዚህም ምክንያት ከሀያላኑ ይልቅ ትንንሽ ሀገራት የአለም አቀፍ ህግ ወጤት የሆነውን የተባበሩት መንግስታት ስርአት እንዲከበር አብዝተው ይሻሉ።

ማሕበረሰብ ራሱን በቡድን ከለየባቸው ቀደምት መስፈርቶች ውስጥ ፆታ የመጀመሪያው ነው። በአብዛኛው ማሕበረሰብ የነበረውን የሁለቱን ቡድኖች ግንኙነት ብናይ፣ ብዙ ጊዜ ሴት ክፉ ተደርጎባትም ያም ሳይካካስላት (ይህ ሁሌም አቅም ከማጣት ብቻ አልነበረም ሌሎች ምክንያቶችን ከታች እጠቅሳለሁ) ወንድ ለራሱ ብቻ የሚብጀውን በማድረጉ ምክንያት ካገኝው ደስታ የላቀውን ሀዘን በተደጋጋሚ አዝናልች። በዚህ መስፈሪያ ብቻ ሴት የፍትሕ እጦትን መራራነት ከወንድ በላይ ታቃለች። ስለዚህም ሙሉ በሙሉ ሳይበድሉ ወይም ሳይበደሉ ለመኖር የሚያስችል እንደ ፍትሕ የመሰለ ስምምንትን ትሻለች። ይህ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ምክንያቶች አሉት። ስለሆነም በሁሉም ማሕበርሰብ ውስጥ ያለ የሁለቱ ቡደኖች ግንኙነት ይሰራል። ከዛ ውጭ ደግሞ ሴቶች እና ወንዶች በየማህበረሰባቸው በሚሰጣቸው ሚና እንዲሁም ያሉበት ማህበሰብ እነዳለበት የዕድገት ደረጃ ለፍትሕ ያላቸው ቀናኢነት ሊፀና ይችላል።

በማህበረስብ የተጣልባቸው ሚና ስንል ለምሳሌ ልጆች፣ አካል ጉዳትኞች፣ በዕድሜ የገፉ እና ሌሎች ለበደል እና ለኢ-ፍትሃዊነት ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች በነርሱ ደጋፊንት የሚኖሩ ከሆነ፤ በአንድ ማሕበረሰብ ያለ ኢ-ፍትሃዊነት ደጋግሞ ሴቶችን ያጠቃል። በነእርሱ ላይ ከሚደርሰው ይልቅ ከላይ በተጠቀሱት የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደርሰው ይበልጥ ያማቸዋል። ለምሳሌ በቅርብ አመታት በነበረው ግርገር ምክንያት ኑሯቸው እና ገፃቸው ላይ ቋሚ ጠባሳ ያረፈባቸው ሴቶች ስንት ናችው? ወንድ ስራ አጥ ወጣቶች፣ ወታደሮች፣ ተማሪዎች፣ ነጋዴ፣ መምህራን ሞተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሴቶች በሁለት ብኩል ተጎድተዋል። በኢኮኖሚ ጧሪ አጥተዋል፤ ምክንያቱም አሁንም በማሕበረሰባችን ውስጥ በአብዛኛው ገቢ አመንጭ ስራ የሚሰሩ ወንዶች በመሆናቸው፤ በስነልቦናም የነእርሱ የሚሉትን ያጡ እናቶች እና እህቶች እሰካሁን ሀዘን ላይ ናቸው። ከዚህ በተጭማሪ ሴቶችም ሞተዋል፣ ታስረዋል፡፡ በታስሩ እና ፍትሕ በተነፈጋቸው ወንድ ዘመዶቻቸው ምክንያት ሕይወታቸው ተመሰቃቅሏል። ቂሊንጦ እና ቃሊቲ ሄዳችሁ የሴት ጠያቂዎችን ፍዳ ተመልከቱ።

ሁለተኛው ነጥብ ማህበረስብ ያለበት የዕድገት ደረጃ ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ ያላደገ ማሕበረስብ ላይ ፍትሕ የመጏደል ዕድሉ ሰፊ ነው። ይህ የሚሆንው ደግሞ ፍትሕን የሚያሰፍኑ ጠንካራ ተቋማት ስለማይኖሩ ነው።ይህ ሲሆን ለበደል ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይጠቃሉ። ሴቶችም ካደጉ ማሕበረሰቦች ይልቅ ባላደጉት ዘንድ የመጎሳቆል እና የመበደል አጋጣሚዋ ሰፊ ነው። በተዘዋዋሪ ደግሞ ፍትሕ በሌለበት ማሕበረሰብ ስልጣኔ የመምጣት እድሉ ጠባብ ነው። ሰሞኑን ጥቅላይ ሚኒስትር አብይ የተናገሩትም እዚህ ላይ እውነት ነው። ሴት በምትበደልበት ማህበረሰብ ፍትሕ የለም፣ ፍትሕ በሌለበት ስልጣኔ አይታሰብም። ምክንያቱም ስልጣኔ ማህበረሰባዊ እንጅ ግለሰባዊ አይደለም፡፡ ማሕበረሰብም አንዱ ቀማኛ ሌላው ምንዳኛ ሆኖ ለማደግ አይችልም። ስለዚህ ማደግ የሚፈልግ ማህበረሰብ ፍትሕ ማስፈን አለበት። ፍትሕን ደግሞ የሚያሠፍናት ተበድሎ ያያት እና በርሱ ጥበቃ ያሉ ደካሞች (ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውይን፣ አካል ጉዳትኞች) ሲታመሙ አበሮ የታመመ ነው። በርግጥ የኢትዮጵያ እናቶች ስልጣን ቢሆን ኖሮ በለጆቻቸው እና በሕፃናት ላይ በተደጋጋሚ እስር እና እንግልት ያደርሱ ነበር? አይሆንም።

የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት ብቻ ከአንድ ፓርቲ አልፎ እኛ በአንድ እንደነበርነው በአንድ ሰው ቁጥጥር ስር እንዳለችው እንደ ሩዋንዳ ብዙ ሴቶች ወደ ፖለቲካ ወንበሮች ማቅረብ መሰረታዊ ችግራችንን አይፈታም። ከምዕራባዊያን ይልቅ እኛ የእናቶቻችንን አስተዳደር እንፈልገዋለን። ምክንያቱም እኛ ፈትሕ ተጠምተናል፤ በዚህም ምክንያት አልሰለጠንም፡፡ መሰልጠን የምንችለው ደግሞ ፍትሕ ሲኖር ነው። ከልብ ካለቀሱ እንባ አይገድም ነውና በኮታ ሴቶችን በየቦታው ከማጎር ተላቅን፣ በተፈጥሮ እና በታሪካዊ ፀጋቸው ፍትሕን እንዲሰጡን ሴቶችን እባካሁ ለቀቅ እናድርጋችው። የተለየ ድጋፍ በማድረግ ሰበብ ሁሉን ነገር ወደ ሗላ አንጎትተው። መጀመሪያውን ድጋፍ እንዲሹ የሚያስገድዳቸውን የኛው ማሰናክል እናቁም። ማሰናከል ስናቆም እነርሱ ማህበረሰቡን ያነሳሉ እኛም ያኔ እራሳችን ደገፍን ማለት ነው። በውጭ የሚመጣውን ፌሚኒዝም፣ ምናምን እና ሌላም ፖለቲካዊ ቀረርቶ ተውት። ለራሳችን ደህንነት ስንል ሴቶች ፍትሕን እንዲሰጡን መተው አለብን ባይ ነኝ።