የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ኢህአዴግ፡ አዲሱን ወይን ባሮጌ አቆማዳ!

ባለፈው አመት፣ የኢህአዴግ መንግስት መውጫና መግቢያ በጠፋው ሰአት፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስተር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሚዲያ ላይ ቀርበው “በሀገር ውስጥ “በሰላማዊ መንገድ” ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር መደራደር እንፈልጋለን” አሉ፡፡ ይህንንም ጥሪ ተቀብለው በመጀመሪያ ከ20 በላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በድርድሩ ላይ ተሳታፊ ሆነው ቀረቡ፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ከድርድሩ በመውጣት 16 ተቃዋሚ ፓርቲዎች (በሂደት የወጡም አሉ) ከገዢው ኢህአዴግ ጋር በ12 አጀንዳዎች ላይ ድርድር ማድረግ ጀመሩ፡፡ የኢህአዴግ መንግስት በእነዚህ አጀንዳዎች ዙሪያ ለመወያየት ፍቃደኛ የሆነው የፖለቲካ ጫና ስለበረታበትና የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማስደሰት ነበር፡፡ የቄሮዎችና የፋኖዎች ትግል እየተፋፋመ ሲመጣና ኢህአዴግ ይህ ታክቲክ እንደማያዋጣ ተረድቶ “ድርድሩን” ገታ አደረገ፡፡ አሁን ደግሞ ይህን ድርድር “ከተቃዋሚዎች” ጋር አንደሚቀጥል በየሚዲያው እየተነገረ ይገኛል፡፡

ድርድር ከማን ጋር?

ዲ.ሪቻርድ “Bargaining for advantage:negotiation strategy for reasonable people" በሚለው ጽሑፉ እንዳስቀመጠው ድርድር ማለት በሁለት ጥንዶች ቅደም ተከተሉን ጠብቆ እንደሚደረግ ጥሩ የመድረክ ዳንስ ነው፡፡ ሁለቱም ዳንሰኞች ልምድ ያላቸውና ጥሩ ዳንሠኛ ከሆኑ ብቻ የመድረክ ዳንሱ የሚያምርና ማራኪ እንደሚሆን ሁሉ ተደራዳሪዎችም እኩል ካልሆኑና መርሁም በሰጥቶ መቀበል የተመሰረተ ካልሆነ ደርድር የሚፈለገውን ግብ አይመታም ይላሉ፡፡ ባለፈው አመት የተጀመረው በኢህአዴግና በተቀዋሚዎች መካከል እየተደረገ ያለው ድርድር በጣም ልምድ ባለው ዳንሰኛ ኢህአዴግና ምንም አይነት ልምድና አንዳች የሚሰጡት ነገር በሌላቸው ተቃዋሚዎች መካከል መደረጉ የዳንስ መድረኩን አጓጊ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የድርድር መድረክ

እውነቱን ለመናገር በኢህአዴግና በተቀዋሚ ተብዬዎች መካከል እየተደረገ ያለውን ድርድር በጅብ እና በአጋዘን መካከል እራትን በተመለከተ እንደሚደረግ አይነት ነው፡፡ በሁለቱ እንሰሳት መካከል ባለው ድርድር ሙሉ ለሙሉ ጅብ ሲያሸንፍ የአጋዘኑ መሸነፍ እርግጥ ነው፡፡

ከኢህአዴግ ጋር ለድርድር የተሰየሙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድነት ከአጠቃላይ የሀገሪቱ ህዝብ 0.5% ድጋፍ የሌላቸው፣ አንዳንዶቹ እንኳን እስከነ መኖራቸው እንኳን የማይታወቁ፣ በቅጡ አባላትና አማራጭ ፖሊስም ሆነ እስትራቴጂ የሌላቸው፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የኢህአዴግ ሰዎች እራሳቸው በእጅ አዙር የሚያሽከረክሯቸው መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ የተወሰነ ህዝባዊ ድጋፍ ያላቸው እንደ መድረክና ሰማያዊ ፓርቲ ያሉ ተቃዋሚዎች በድርድሩ አለመኖራቸውና አጠቃላይ ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውንና ወታደራዊ የበላይነቱን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ ለድርድር መቅረባቸው ሁኔታውን የጅቡንና የአጋዘኑን ድርድር ያስመስለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜያት በፊት እንዳየነው በሀገራችን ሁለት አይነት ሀይሎች ታይተዋል፡፡ በአጠቃላይ የመንግስታዊውን መዋቅር የተቆጣጠረው የኢህአዴግ ሃይልና ጥቂት የሚባሉ ግለሰቦችና ፓርቲዎች ያገኙት የህዝብ ሃይል፡፡ በቀድሞ ታሪካችን እንዲሁም በባለፉት ሶስት አመታት በተግባር እንደታየው ከሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ይልቅ የህዝብ ሃይል ያሸንፋል፡፡ ይህ አሸናፊ አካልም (ህዝብ) ተሸናፊውን አካል (ኢህአዴግን) እኔ ከደገፍኳቸውና ከምፈልጋቸው አካላት ጋር ተደራደሩ እንጂ ከማላውቃቸውና ከማያውቁኝ አካላት ጋር ተቀመጡ አላለም፡፡

ዶ/ር አብይ ገና ወደ ስልጣን ከመጡበት ቀን ጀምሮ እየወሰዷቸው የሚገኙትና ካለፉት መሪዎች የተለዩ እርምጃዎች ይህንኑ የህዝብ ፍላጎት ያከበረ፡፡ ነገር ግን፣ ባለፈው አመት ለችግር ማምለጫ ተብሎ የተጀመረውንና አንዳንድ መኖራቸው እንኳን ከማይታወቁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የሚደረገው ድርድር መቀጠሉ በአሮጌ አቆማዳ አዲስ ወይን ጠጅ እንደማስቀመጥ ይቆጠራል፡፡ ኢህአዴግ እንዳለው ድርድሩ ሁሉንም የፖለቲካ አይሎች ያሳተፈና የህዝብን ፍላጎት መሰረት በማድረግ እንዲሁም የዲሞክራሲ ባህልን ለማሳደግ ከታሰበ ህዝቡ ጋር ደርሰው ከማያውቁትና ህዝቡም ከማያውቀቸው ተቃዋሚዎች ጋር መደራደሩ ፋይዳ-ቢስ ነው፡፡

ሀገሪቱ እንደ ዲሪቶ የተተበተቡ ብዙ ችግሮች እያሉባት በቀላሉ የማይደረስ ፖለቲካዊ ፍላጎትን ወይም ድርጅታዊ አስተሳሰብን አሁንም በዚህ ዘመን ማራመዱ የትውልድ ተወቃሽ ያደርጋል፡፡ ኢህአዴግ ለሀገሪቱ እና ህዝቡ ካሰበ በትክክል ከማን መደራደር እንዳለበት ይጠፋዋል ብዬ አላስብም፡፡ በዋነኝነት ግን አሁንም የሀገራችን ችግር የሚፈታው እኔ ብቻ አሸናፊ ልሁን (zero-sum game) የሚለውን ጊዜ ያለፈበት ድርድር ዘዴ ትተን ባለው ከትክክለኛው አካል ጋር ግልፅና አሳታፊ በሆነ መልኩ ድርድር ሊካሄድ ይገባል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ድርድር የሚባለው ነገር ሰሚ-አልባ ጩኸት ሆኖ ይቀራል፡፡

One thought on “የፖለቲካ ፓርቲዎች ድርድርና ኢህአዴግ፡ አዲሱን ወይን ባሮጌ አቆማዳ!

  1. ጃብ old model car Mercides benz1924 ነው ህወሓት የሚተነፍሰውን አየር የተቃጠለ ስለሆነ አየር በክሏል ስለሆነም እባከዎ ጠሚው ያስወግዱልን?እርሰዎንም ሳያስወግደዎት!!

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡