ያለው አማራጭ ሕገ-መንግስቱን ማሻሻል ወይም የህወሓትን የበላይነት ማስቀጠል ነው!

“በሀገሪቱ ለተከሰቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መሰረታዊ መንስዔ ምንድነው?” ለሚለው መልሱ አንድና አንድ ነው። እሱም የህወሓትን የበላይነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተው መንግስታዊ ስርዓት ነው። በመለስ ዜናዊ ቦታ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ቢተካ፣ አባይ ወልዱ ወርዶ ዶ/ር ደብረፂዮን ቢመጣ፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ለቅቆ በዶ/ር አብይ ቢተካ፣ የፖለቲካ እስረኞችን ስለተፈቱ፣ የብሔርተኝነት ትርክትን በኢትዮጲያዊነት ስለተካ ወይም ዛሬ እንደተባለው የፀረ-ሽብር አዋጁን ቢያሻሽል፣ …ወዘተ የህወሓት የበላይነትን ከሀገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ውስጥ መንቀል አይቻልም። የችግሩን ስር-መንቀል እስካልተቻለ ድረስ “ሥር-ነቀል” ለውጥ ማምጣት አይቻልም። ስለዚህ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የሚቻለው የህወሓትን የበላይነት ከስሩ መንቀል ሲቻል ነው።

በጥቅሉ የአንድ ወገን የበላይነት የሚረጋገጠው ሌሎች የሚመሩበትን ሕጋዊ ስርዓት ከራስ ፍላጎትና ጥቅም አንፃር በመቅረፅ ነው። የሕጋዊ ስርዓቱ ለራስ መመሪያ ሳይሆን ሌሎች የሚመሩበት ነው። በመሆኑም የራስን የበላይነት ማረጋገጥ ሲባል ራሳችን የማንመራበት፣ ሌሎችን ግን የሚያስተዳድርበት የሕግ ማዕቀፍ ማውጣትና ተግባራዊ ማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር የህወሓት የበላይነት የተመሰረተው ለዚሁ ዓላማ ተቀርፆ ተግባራዊ በሆነው የኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት ላይ ነው።

ሕገ-መንግስቱ አምስት መሰረታዊ መርሆች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አራቱ መርሆች ከመሰረታዊ የዴሞክራሲ መርሆች ጋር አብረው የሚሄዱ ናቸው። ነገር ግን፣ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 8 ላይ የተጠቀሰው “የሕዝብ ሉዓላዊነት” የሚለው መርህ ፍጹም በተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በአንቀፅ 8 መሰረት “ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የኢትዮጲያ ሉዓላዊ ስልጣን ባለቤቶች” ናቸው። ይህ አንደኛ፡- ከአንቀፅ 9 – 12 የተዘረዘሩትን የሕገ መንግስቱን መሰረታዊ መርሆች በቀጥታ ይጥሳል፤ ሁለተኛ፡- ዜጎች በመንግስት ላይ ያላቸውን የስልጣን የበላይነት ሙሉ በሙሉ ይገፍፋል። በዚህ መሰረት ሕገ-መንግስቱ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የሚገድብ ከመሆኑ በተጨማሪ ራሱን በራሱ ይጥሳል።

በሕገ መንግስቱ ዜጎች በተግባር የማያስከብሩት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ተሰጥቷቸዋል። ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች ደግሞ በተግባር የማይጠይቁት ስልጣን ተሰጥቷቸዋል። መብቱን ለዜጎች፣ ስልጣኑን ለብሔሮች መስጠት ያስፈለገበት መሰረታዊ ምክንያት በብሔሮች ስም ዜጎችን በኃይል ለማፈን ነው። ብሔሮች በሕገ መንግስቱ የተሰጣቸውን ስልጣን በተግባር አይጠቀሙም ወይም መጠቀም አይችሉም። ዜጎች ደግሞ በመንግስት ላይ የስልጣን የበላይነት ከሌላቸው ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለማስከበር መንቀሳቀስ አይችሉም።

የተወሰኑ ዜጎች መብትና ነፃነታቸውን ለማስከበር መንቀሳቀስ ሲጀምሩ፤ ሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስታዊ ስርዓቱንና የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በሚል ሰበብ የኃይል እርምጃ ይወስዳል። ለዚህም የሚያገለግሉ የዜጎችን መብትና ነፃነት የሚገድቡ፣ ነገር ግን የህወሓቶችን የስልጣን የበላይነትና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ አዋጆች፥ ደንቦች፥ መመሪያዎች፥ መዋቅርና አሰራሮችን በማውጣት ተግባራዊ አድርጓል።

ሕገ-መንግስቱ እና የህወሓትን የበላይነት

ስለዚህ የተወሰኑ አዋጆች፥ ደንቦች፥ መመሪያዎች፥ መዋቅርና አሰራሮችን በመቀየር ወይም በማሻሻል ብቻ የሀገሪቱን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በዘላቂነት መቅረፍ አይቻልም። ከዚያ ይልቅ፣ ለእነዚህ ነገሮች መነሻ ምክንያት የሆነው እና የህወሓቶችን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ዓላማ ያደረገው ሕገ-መንግስት መሻሻል ይኖርበታል። ከዚህ ውጪ ያለ ማንኛውም ዓይነት የለውጥ እንቅስቃሴ “ጥገናዊ” ከመሆን አይዘልም። በአጠቃላይ “ሥር-ነቀል ለውጥ” ማለት የህወሓት የበላይነትን ከስሩ መንቀል ነው። ይህ ማድረግ የሚቻለው ደግሞ ሕገ-መንግስቱን በማሻሻል ነው።