“የነፃነት ታጋይ” መባልን እንጂ ነፃነትን የማንፈልግ ዜጎች ሞልተናል!

ዱካውን ማደን!

(በውቄ ስዩም: ከየረር በር)

በዶክተር አብይ አህመድ እና በግብረ አበሮቹ መሪነት እየተነቃቃ ያለው የርቅ እና የሆደሰፊነት ባህል አስደናቂ ነው:: በታሪክ ብርቅ ከሆኑ ክስተቶች አንዱን ያስታውሰኛል::

አንዳርጋቸው ፅጌ እና ጠ/ሚ አብይ አህመድ

በየጁ የምስፍና ዘመን ደጃዝማች ውቤ የተባሉ መስፍን የራስ አሊን መንግስት ለመቀማት ፈለጉ:: በግብጡ ጎረምሳ አቡነ ሰላማ አይዞህ ባይነት በራስ አሊ ላይ ዘመቱ:: ደብረታቦር ላይ ቅልጥ ያለ ጦርነት ተደርጎ ውቤ እና አቡነ ሰላማ ተሸንፈው ተማረኩ:: በጊዜው ልማድ የተማረከ ሰው ህይወቱን ያጣል:: በድል ነሺው እንዲኖር ከተፈቀደለት እንኳ እጁን ይቆረጣል፡ ወይም አይኑ በወስፌ ይፈርጣል::

በቅንነት ተገፋፍተው ይሁን ትርፍና ኪሳራውን አስልተው አይታወቅም-ራስ አሊ ግን ይህን ከማድረግ ታቀቡ:: ምርኮኞችን ምሳ ጋብዘው በምህረት ወደ ጥንቱ ሹመታቸው መለሷቸው:: ውቤ በዚህ ተደንቀው “ሲቻለው ማሪ፡ አሊና ፈጣሪ” ብለው በበገና ዘፈኑ:: የራስ አሊን ሌጋሲ ያስቀጣላችሁልን ያዝልቅላችሁ በማለት ወደ ቀጣዩ አንቀጽ ልዝለቅ::

አንዳንዶቻችን በለውጡ ጅማሬ መፈንደቅ ሲገባን ቢደብረን አትፍረዱብን:: ህልውናችን ማንነታችን የተመሰረተው በግጭት ላይ ነው:: ግጭቱ ሲፈታ መግቢያ እናጣለን:: ያጅሬ ታሪክ ደርሶብን ነው:: ከለታት አንድ ቀን: አጅሬ ምኒሽሩን አንግቦ በቅረርቶው መንደር እያናወጠ እልም ያለው ዱር ውስጥ ይገባል:: ከዚያ በዱሩ ውስጥ ሞፈር የሚቆርጥ ገበሬ ያገኝና እየተጀነነ” አዋ! እንዲያው እዚህ ግድም ያንበሳ ዱካ አይተሃል?” ይለዋል::

ገበሬው ዘና ብሎ “ዱካውን አይደለም:: ራሱ አንበሳውን አሳይሃለሁ” ብሎ መለሰለት:: አዳኝ መሳዩ ያልጠበቀው መልስ ስላገኘ ደነገጠ:: “ለጊዜው ዱካውን እንጂ አንበሳውን ለማደን አልመጣሁም” ብሎ ላሽ አለ:: አጅሬ የፈለገው “አያ እገሌ አንበሳ ሊያድን ጫካ ገብቱዋል” የሚለውን ወሬ እንጂ ጀብዱን አይደለም:: አንዳንዴ ዱካውን እንጂ አንበሳውን አንፈልገውም:: ድል የሚያሳድድ ሁሉ ድል የመሸከም ወኔ አለው ማለት አይቻልም:: የነፃነት ታጋይ መባልን እንጂ ነፃነትን የማንፈልግ ዜጎች ሞልተናል:: ተረዱን ለማለት ነው::

“ብየ ነበር” ማለት አገራዊ ልማድ ስለሆነ እኔም የሚከተለውን ብየ ነበር በማለት ልሰናበት::

“ተበዳይ መናፍስት፡ ታፍነው የኖሩ
ወደ አርነት መድረክ፡ በድንገት ሲጠሩ
ያለ ጠባቂ በር፡ ተከፍቶ ሳል በሩ
የገቡ አይመስላቸው፡ ቅጥሩን ካልሰበሩ”

(ስብስብ ግጥሞች)


ምንጭ፦ Bewketu Seyoum

3 thoughts on ““የነፃነት ታጋይ” መባልን እንጂ ነፃነትን የማንፈልግ ዜጎች ሞልተናል!

  1. freedom has given by free choice but we seek it from the man what it had taken it from us that is given naturally. since no one gives you freedom but returned it to you what is given from nature eventhough someone was taken. at this time it needs struggle and what you struggle the vale will be rising. if you not you lost the value by that rising amount.

    Liked by 1 person

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡