የቁጥር ፖለቲካ፦ የኦሮማራ ጥምረትና የአናሳዎች መብት

እንደ አቶ አባይ ያሉ ፅንፈኛ የህወሓት አባላትና አመራሮች “ቁጥር አራቱን የሂሳብ ስሌቶች ለመጠቀም የሚያገለግል ነገር ነው፡፡ ይሁን እንጂ እውነታው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቱም “ቁጥር” በራሱ ነባራዊ እውነታ (Numerical Fact) ነው! ከፖለቲካ አንፃር ቁጥር “Majority rule, Minority right” የሚለው የዴሞክራሲ መርህ ነው! ከኢኮኖሚ አንፃር ደግሞ ቁጥር ማለት “ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ወይም የበጀት መጠን ነው፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ ጥያቄ የፖለቲካ መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ነው፡፡ ስለዚህ የህዝቡ ጥያቄ ቁጥር ነው፡፡ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ቁጥር የሚጠሉት የህዝቡን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቀ ላለመመለስ፥ ለማድበስበስ ወይም ለማስቀየስ ነው፡፡

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ኮንፍረስ፣ ጅማ ዩኑቨርሲቲ፣ ግንቦት 25/2010 ዓ.ም

አብላጫ ቁጥር እና አብላጫ ድምፅ

የኦሮሞ ህዝብ አብላጫ ቁጥር አለው እንጂ አብላጫ ድምፅ (50%+1 ድምፅ) የለውም፡፡ ኦሮሞና አማራ ከተፎካከሩ ሌሎች ብሔሮችን በመቀራመት አብላጫ ድምፅ ለማግኘት ይጥራሉ፡፡ በሀገሪቱ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ላይ የራሳቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ እርስ-በእርስ ይሽቀዳደማሉ፥ ይጠላለፋሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በፖለቲካው ላይ ያላቸውን አብላጫ ድምፅ ያጣሉ፡፡ ከአናሳ ብሔር የመጡ የፖለቲካ ቡድኖች ስልጣኑን ይቆጣጠራሉ፡፡ ይህንን ደግሞ ላለፉት 27 አመታት በተግባር አይተንዋል፡፡

በሌላ በኩል ኦሮሞና አማራ ሲተባበሩ አብላጫ ድምፅ ይኖራቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት “Majority rule” የሚለው የዴሞክራሲ መርህ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ይህን ደግሞ በኦህዴድና ብአዴን ጥምረት በተግባር ተመልክተናል፡፡ “Majority rule” ተግባራዊ ሲሆን “Minority right” የሚለው ይከተላል፡፡ የአናሳ ብሔር ተወላጆች ፖለቲካዊ መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ካልተረጋገጠ “Majority rule, Minority right” የሚለው የዴሞክራሲ መርህ ተግባራዊ አይሆንም! መንግስታዊ ስርዓቱ ይህን መሠረታዊ የዴሞክራሲ መርህ ከሳተ ፍፁም አምባገነንና ጨቋኝ ይሆናል፡፡

በኦሮማራ ጥምረት ወደ ስልጣን የመጣው የዶ/ር አብይ አመራር ቀጣዩ አቅጣጫ የሌሎች ብሔሮችን መብትና ነፃነት፣ እንዲሁም ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ አመራሩ የሌሎች ብሔሮችን መብትና ነፃነት ማረጋገጥ ከተሳነው በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች አክራሪ ብሔርተኝነት ያቆጠጣል፡፡ ፖለቲካዊ ግጭትና አለመረጋጋት ይከሰታል፡፡ በሂደት የኦሮሞን ህዝብ መብት ትርጉም አልባ ያደርገዋል:-

“Democracy therefore requires minority rights equally as it does majority rule. Indeed, as democracy is understood today, the minority’s rights must be protected no matter how alienated a minority is from the majority society; otherwise, the majority’s rights lose their meaning.” democracyweb.org