በጭቁኖች ሀገር የመናገር ነፃነት ያላቸው “እብዶች” ብቻ ናቸው!

የአማርኛ መዝገበ ቃላት “ምሁር” የሚለውን ቃል “በትምህርት፥ በዕውቀት የበሰለ አዕምሮ ያለው ሰው” በማለት ይገልፀዋል። ነገር ግን፣ ትምህርት ሆነ ዕውቀት በማህብረሰቡ ሕይወት ላይ እሴት የማይጨምር ከሆነ ፋይዳ-ቢስ ነው። እንዲህ ያለ ትምህርት፥ ዕውቀት በማህብረሰቡ ዘንድ ዋጋና ክብር አይሰጠውም፣ ለራሳችንም ቢሆን እርካታ አይሰጥም! ስለዚህ “ምሁር” የሚባለው የተማረ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ያገኘውን ዕውቀትና ክህሎት ተጠቅሞ በማህብረሰቡ ዘንድ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚንቀሳቀስ ሰው ነው።

በእንግሊዘኛ “intellectual” የሚለውን ቃል “Edward Said” “በህዝቡ ውስጥ እየኖረ የህዝብን ጥያቄ (መልዕክት)፣ አመለካከት፣ ፍልስፍና ወይም ሃሳብ ለመወከል፣ ለመያዝና ለመግለፅ የሚያስችል ብቃት ያለው፣ በአደባባይ አሳፋሪ ጥያቄዎችን የሚያነሳ፣ ኋላቀር አመለካከቶችንና ግትር ቀኖናዊነትን በይፋ የሚጋፈጥ፣ እንዲሁም ለመንግስታትና ድርጅቶች ፍላጎት ተገዢ ያልሆነ” በማለት ይገልፀዋል፡-

“The intellectual is the individual endowed with a faculty for representing, embodying, articulating a message of you, attitude, philosophy or opinion to as well as for a public in public. This role has an edge to it, and cannot be played without the sense of being someone whose place it is, publicly, to raise embarrassing questions, to confront orthodoxy and dogma rather than to produce them, to be someone who cannot easily co-opted by governments and corporations.” Edward Said (1993): Representations of an Intellectual – Lecture 4, Reith Lectures 1993.

“Edward Said” “intellectual” ለሚለው ቃል የሰጠው ፍቺ እና በአማርኛ “ምሁር” የሚለው ቃል ፍቺ ፍፁም የተለያዩ ናቸው። የአማርኛው ፍቺ ከትምህርት ደረጃ እና ከዕውቀት ክምችት በዘለለ በማህብረሰቡ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ከማምጣት አንፃር ያለውን አስተዋፅዖ ከግምት አያስገባም። በእንግሊዘኛ “intellectual” ለሚለው ቃል የተሰጠው ፍቺ አብሮ የሚሄደው አቻ የአማርኛ ቃል “ምሁር” ሳይሆን “ሙር” የሚለው ነው። በአማርኛ “ሙር” ማለት “የተማረና ዕውቀት ያለው ሆኖ ወፈፍ ስለሚያደርገው ብዙ የሚለፈልፍና የሚናገር፥ ንግግሩ ግን ፍሬ ነገር ያዘለ ሰው ነው”

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት በአንድ ማህብረሰብ ውስጥ ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ “ምሁራን”፤ አሣፋሪ ጥያቄዎችን በአደባባይ ማንሳት እና ኋላቀር አመለካከቶችን መጋፈጥ፣ እንዲሁም የሕዝቡን ጥያቄና አመለካከት መወከል፥ መያዝና መግለፅ፣ ለመንግስትና ድርጅቶች ፍላጎት ተገዢ ያለመሆን ግዴታ አለባቸውም። ነገር ግን፣ የመጀመሪዎቹ ሁለት ተግባራት ወይም ባህሪያት ከማህብረሰቡ ጋር የሚያጋጭ ሲሆን የመጨረሻ ሁለቱ ደግሞ በስልጣን ላይ ካለው መንግስት ጋር ያጋጫሉ።

በዚህ ምክንያት፣ የላቀ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች ከማህብረሰቡና ከመንግስት ጫና እና ቅጣት ራሳቸውን ለመታደግ እንደ ወፈፌ ወይም የስነ-አዕምሮ ችግር፥ መዛባት ያለበት፣ በአጭሩ እንደ “እብድ” መሆን አለባቸው። በእርግጥ የዳበረ ዴሞክራሲ በሌለበት ሀገርና የሰለጠነ ማህበራዊ ግንኙነት በሌለው ማህብረሰብ ዘንድ የሃሳብና አመለካከት ነፃነት ያላቸው “እብዶች” ብቻ ናቸው።

በዘመናዊ የስነ-ፅሁፍ ታሪክ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት የሐዲስ ዓለማየሁ “ፍቅር እስከ መቃብር” እና በዓሉ ግርማ “ደራሲው” የተሰኙት ልብወለድ መፅሃፍት፣ እንዲሁም የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን “ሀ ሁ.. በስድስት ወር” እና በቅርቡ የወጣው የበረከት በላይነህ “እያዩ ፈንገስ” የሚለው ቲያትር እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይቻላል። ለምሳሌ በሎሬት ፀጋዬ ገ/መድኅን ተደርሶ በአንጋፋው ተዋናይ ወጋዬሁ ንጋቱ የቀረበው “ሀ ሁ.. በስድስት ወር” በሚለው ቲያትር ትምህርትና ዕውቀት ለእብደት የሚዳርግ “ልክፍት” እንደሆነ ይገልፃል፡-

በአጠቃላይ የተለየ ሃሳብና አመለካከት እንደ ጥፋትና ወንጀል በሚወሰድበት ሀገር ዕውቀትና ነፃነት እንደ “እብደት” ይቆጠራል። በእንዲህ ያለ ማህብረሰብ ዘንድ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችል የተለየ ሃሳብና አስተያየት የሚሰጡት ወይም ትክክለኛ እውነት የሚናገሩት “እብዶች” ብቻ ናቸው።

ከላይ በተጠቀሱት የሥነ-ፅሁፍ ስራዎች ዋና ዋና ገፀ-ባህሪያት በማህብረሰቡ ዘንድ “ወፈፌ” ወይም “እብድ” የሚባሉ ናቸው። ሆኖም ግን፣ የሥነ-ፅሁፉ ጭብጥ ያለውና የሚተላለፈው በእነዚህ ገፀ-ባህሪያት ድርጊትና ንግግር ውስጥ ነው። ደራሲዎቹ በማህብረሰቡ ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያስችለውን ሃሳብ የሚያስተላልፉት በእነዚህ እብዶች አማካኝነት ነው። ለምሳሌ በበረከት በላይነህ ተደርሶ በግሩም ኤርሚያስ ከቀረበው “እያዩ ፈንገስ” ቲያትር ውስጥ የሚከተለውን እንመልከት፦

2 thoughts on “በጭቁኖች ሀገር የመናገር ነፃነት ያላቸው “እብዶች” ብቻ ናቸው!

  1. ለመንግስትና ድርጅቶች ፍላጎት ተገዢ ያለመሆን ግዴታ አለባቸውም ምን ማለት ነው? የመንግስት አፈጻጸም ትክክል ካልሆነ ልትቃወም ትችላለህ እንዲሁ በደፈናው ተገዢ አለመሆን ማለት ያስቸግራል፡፡ መንግሰት ማለት አፈጻጸሙ ላይ ብንለያይም ብዙሀን የሚስማሙበት ህጎቸች ያሉበትና ለእነዛ ህጎች ተገዢ መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ምሁር የተባለው ቡድን ሌላ የተሸለ ሃሳብ ካለው በተሸለ ህግ ማስቀየር ይችላል፡፡

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡