መንግስትን መተቸት የምሁራን መብት ሳይሆን “ግዴታ” ነው!

ዩጋንዳዊያን “የዝሆን ኩምቢ ያለ ቅጥ የረዘመው በትችት እጦት ነው” የሚል አባባል አላቸው። የተለያዩ ማህበራዊ፥ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ስር የሚሰዱት በትችት (Criticism) እጦት ምክንያት ነው። ችግሮችን ቀድሞ መለየትና በዚያ ላይ የሰላ ትችት መሰንዘር ጉዳዩ በሚመለከተው አካል ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝና የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ ያስችላል። የሃሳብና አመለካከት ነፃነት በሌለበት ማህብረሰብ ዘንድ ችግሮችን በግልፅ የመተቸት ልማድ አይኖርም። በዚህ ምክንያት ችግሮች የሚለዩትና ትኩረት የሚሰጣቸው ስር ከሰደዱ፣ ከነባርና አዳዲስ ችግሮች ጋር ተዳምረው ውስብስብ ከሆኑ በኋላ ነው። እንዲህ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን ደግሞ በቀላሉ መፍታት አይቻልም።

ኢትዮጲያ ውስጥ፤ እንደ ግለሰብ፥ ቡድን፥ ማህብረሰብ፥ ሕዝብና መንግስት የተለየ ሃሳብና አስተያየትን በቀናነት የመቀበል ልማድ የለንም። ይህ ደግሞ ችግሮችን ገና ከጅምሩ በመለየት የሰላ ትችት የመሰንዘር ባህል እንዳይኖር አድርጓል። በመሆኑም ችግሮቻችን ትኩረት እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ብዙ ጥረት ይጠይቃል፣ አላስፈላጊ ዋጋ ያስከፍላል። በዚህ መልኩ ትኩረት የተሰጣቸው ችግሮች በጣም ሥር የሰደዱና የተወሳሰቡ በመሆናቸው ምክንያት በቀላሉ ማስተካከል ሆነ መፍታት አይቻልም። የሀገራችን ማህበራዊ፥ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እርስ-በእርስ በመጠላለፍ ውስብስብ የሆኑት በትችት እጦት ምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።

አምባገነናዊ መንግስት የሚጠፋውና የሚፈጠረው በትችት መኖርና አለመኖር ነው። የሃሳብና አመለካከት ነፃነት በተከበረበት፣ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በመንግስት ላይ የሰላ ትችትና አስተያየት በሚሰጥበት ሀገር አምባገነናዊ ስርዓት ቦታ የለውም። ምክንያቱም የአምባገነን መንግስት ሕልውና የተመሰረተው ዜጎችን በፍርሃት ቆፈን በመለጎም ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት እንዳይገልጹ በማድረግ ላይ ነው። በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት የሰላ ትችትና ነቀፌታ የሚሰነዘር ከሆነ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ አንፃር በዜጎች መካከል ያለው ልዩነት ይታወቃል። በዚህ ምክንያት ዜጎች የፖለቲካዊ መብት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ያነሳሉ።

የመብትና ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በተገቢው ግዜና ሁኔታ ምላሽ መስጠት ከቻለ መንግስታዊ ስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል። እነዚህን ጥያቄዎች በኃይል ለማፈንና ለማዳፈን ጥረት የሚያደርግ ከሆነ ደግሞ አምባገነናዊ ይሆናል። መንግስት ይበልጥ አፋኝና ጨቋኝ እየሆነ በሄደ ቁጥር በመንግስት ላይ የሰላ ትችትና ነቀፌታ የሚሰነዝሩ ተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ይፈጠራሉ። በመንግስታዊ ስርዓቱ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማጋለጥ ሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ያደርጋሉ። ንቅናቄው ከግዜ ወደ ግዜ እየተጠናከረ በመምጣት በመጨረሻ መንግስት በሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ወይም በትጥቅ ትግል ከስልጣን ይወገዳል።

በዚህ መልኩ፣ አዲስ የፖለቲካ ኃይል ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላም ቢሆን የሃሳብና አመለካከት ነፃነት ሊከበር፣ በመንግስት ላይ የሰላ ትችት ሊሰነዘር ይገባል። ምክንያቱም የሃሳብና አመለካከት ነፃነት በሌለበት በመንግስት ላይ የሰላ ትችት መሰንዘር አይችሉም። በመንግስት ላይ የሰላ ትችት የማይሰነዘር ከሆነ ደግሞ በሥራና አሰራሩ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን በተገቢው ግዜ መለየትና የማስተካከያ እርምጃ መውሰድ አይችልም። በመሆኑም በማህብረሰቡ ዘንድ ያሉትን ችግሮች፣ እንዲሁም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሚነሳውን ጥያቄ መረዳትና ምላሽ መስጠት ይሳነዋል። የብዙሃኑን ፍላጎትና ጥያቄ መረዳት፣ በተጨባጭ ያለውን እውነታ መገንዘብ የተሳነው የፖለቲካ ቡድን በዜጎች ሕይወትና ግንኙነት ላይ ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይችልም። ለውጥና መሻሻል ማምጣት የተሳነው የፖለቲካ ቡድን ደግሞ በሰላማዊ መንገድ አሊያም በኃይል ከስልጣን ይወገዳል።

ትችት ለተቀሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች ዴሞክራሲያዊ መብት ሊሆን ይችላል፣ ለምሁራን ግን ግዴታ ነው። የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሕልውና የተመሰረተው በሁለቱ ወገኖች መለያየት ላይ ነው። ምክንያቱም የፖለቲከኞች መደበኛ ስራ አስተዳደራዊ ውሳኔ መስጠት ሲሆን የምሁራን ድርሻ ደግሞ የዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እና የመንግስት አመራርና አስተዳደር በዕውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል ነው። ለዚህ ደግሞ ምሁራን በማህብረሰቡ ኑሮና አኗኗር እና በመንግስት ሥራና አሰራር ውስጥ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በመለየት የሰላ ትችት መሰንዘር አለባቸው።

በእርግጥ ምሁራን የመንግስት ስልጣንና ኃላፊነት በመያዝ፣ በዚህም የመንግስትን አቋምና አፈፃፀም በመደገፍ መከራከር ይችላሉ። ነገር ግን፣ ባለስልጣን እስካልሆኑ ድረስ የመንግስትን ሥራና ተግባር በመደገፍ የባለስልጣን አፈ-ቀላጤ መሆን የለባቸውም። ምክንያቱም ምሁራን ልክ እንደ ተሿሚ ወይም የፖለቲካ ፓርቲ አባል የመንግስትን ሥራና ተግባር በመደገፍ፣ ጥሩን እያጋነኑ፥ መጥፎውን እየሸፋፈኑ የሚያቀርቡ ከሆነ በሕዝብና መንግስት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እጅግ የከፋ ነው። የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ምሁራን፤ የተለያዩ የመንግስት አካላት የሚያሳልፋቸው የብዙሃኑን እኩልነትና ተጠቃሚነትን የማያረጋግጡ እቅዶችና ውሳኔዎች እንዳይሻሻሉ፣ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚገድቡ አዋጆችና ደንቦች ማሻሻያ እንዳይደረግባቸው፣ የሕዝብ ጥየቄና ቅሬታዎችን እንዳይሰሙ፣ የመንግስት ኃላፊዎች ያለባቸውን የግንዛቤ እና የብቃት ማነስ ችግር እንዳይቀርፉ እንቅፋት ይሆናሉ። በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ውስጥ የምሁራንን ሚና “John Stuart Mill” እንደሚከተለው ገልፆታል፡-

“….Their part is to indicate wants, to be an organ for popular demands, and a place of adverse discussion for all opinions relating to public matters, both great and small; and, along with this, to check by criticism, and eventually by withdrawing their support, those high public officers who really conduct the public business…. There are no means of combining these benefits except by disjoining the office of control and criticism from the actual conduct of affairs” John Stuart Mill, Representative Government, Ch.5: Page 8