የሻዕቢያ የበላይነት እና የህወሓት የበታችነት፡ ከአሰብ እስከ ባድመ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ #የአልጄርስ ስምምነትን ሙለ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ መወሰኑ ለብዙዎች አነጋጋሪና ያልተጠበቀ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሁለቱ ሀገራት ለረጅም ግዜ በባላንጣነት ሲተያዩና አንዱ ሌላውን ጠልፎ-ለመጣል በተለያየ መንገድ ጥረት ሲያደርጉን ስለነበር በመካከላቸው ያለውን ውጥረትና አለመግባባት እንዲህ በቀላሉ ማስወገድ አይቻልም የሚል እምነት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አንድ ውሳኔ ለማሳለፍ የብዙ ቀናት ስብሰባ የማድረግ ባህል ያለው ድርጅት በ6 ሰዓት ስብሰባ እንዲህ ያለ ውሳኔ ማሳለፉ ለብዙዎች አስገራሚና ያልተጠበቀ አድርጎታል። አንዳንዶች “የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ የኤርትራ መንግስት አልቀበልም” ቢልስ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ሆኖም ግን፣ የኢትዮጲያና ኤርትራ ግንኙነት አስቸጋሪነት ሆነ ውሳኔው የተላለፈበት ሁኔታ ከዚህ የተለየ ነው።

በእርግጥ በኢትዮጲያና ኤርትራ መካከል ያለው ግንኙነት በጣም ውስብስብ እና አስቸጋሪ ነው። በሁለቱ ሀገራት መካከል ጦርነት የተካሄደበት፣ በጦርነቱ ወቅት የጠፋው የሰው ሕይወትና የሀገር ንብረት፣ በአልጄርስ ስምምነት ጦርነቱ ቆሞ ሰላም የጠፋበት ሁኔታ፣ …ወዘተ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት አስቸጋሪነትና ውስብስብነት ያሳያል። ሆኖም ግን፣ ችግሩን እንዲህ ውስብስብና አስቸጋሪ ያደረገው የግጭቱ ተሳታፊዎች ማንነትና ታሪካዊ ተቀናቃኝነት ነው። በመሰረቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ በህወሓትና ሻዕቢያ መካከል የነበረው የተዛባ ግንኙነት እና ተቀናቃኝነት ነው።

ኢሳያስ አፈወርቂ ለህወሓት ሆነ ለአመራሮቹ እንደ አንድ የፖለቲካ ቡድን የሚገባቸውን ቦታና ክብር ሰጥቶ አያውቅም። ህወሓትን ከአመሰራረቱ ጀምሮ በህወሓት የፖለቲካ አቋምና እንቅስቃሴ ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ እንደሚችል ያምናል። ሌላው ቀርቶ ህወሓት/ኢህአዴግን አዲስ አበባ አራት ኪሎ ቤተመንግስት እንዳስገባው ያምናል። ኤርትራ ከኢትዮጲያ የተገለጠለችው የሻዕቢያን ፍላጎትና ምርጫ መሰረት ባደረገ መልኩ ነው። በዚህ ረገድ የአሰብ ወደብ ለኤርትራ ተላልፎ የተሰጠበት ሂደት እንደ ማሳያ ሊጠቀስ ይችላል። በአጠቃላይ በሻዕቢያዎች ዘንድ ህወሓት ድርጅታዊ ቁመና ሆነ ፖለቲካዊ አቅም ኖሮት አያውቅም። ይህ በህወሓቶች ላይ የበታችነት ስሜት አሳድሮባቸዋል።

እነዚህ ሁለት ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች የኢትዮጲያን ሃብትና ንብረት ለመቀራመት በሚያደርጉት ሽሚያ በመካከላቸው የተፈጠረው ግጭት ለኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መነሻ ምክንያት ሆኗል። በእርግጥ ሻዕቢያዎች ኢትዮጲያን የወረሩት በወቅቱ ደካማ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አቅም የነበረውን ህወሓት ለመውጋት ነበር። ሆኖም ግን፣ የኤርትራ ጦር በትግራይ ላይ ጥቃት በመፈፀም የኢትዮጲያን ሉዓላዊነት ደፍሯል። በመሆኑም ችግሩ የህወሓትና ትግራይ ከመሆን አልፎ የኢትዮጲያና የኢትዮጲያዊያን ሆኗል። በዚህ ምክንያት መላው የኢትዮጲያ ህዝብ የተባበረ ክንዱን በኤርትራ ላይ በማሳረፍ ሉዓላዊነቱን አስከብሯል። ለኢትዮጲያኖች፤ ወራሪው የኤርትራ ጦር ተሸንፏል፣ የኢትዮጲያ ሉዓላዊነት ተከብሯል። የኤርትራ መንግስት ሽንፈቱን ተቀብሎ የሰላም ስምምነት ለማድረግ ለመፈረም ተገድዷል።

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከፍተኛ ሚና የነበራቸውና በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ጄ/ል ተፈራ ማሞ ከጊዮን መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ የኤርትራን ጦር በማሸነፍ ሻዕቢያ በህወሓቶች ላይ የፈጠረውን የበታችነት ስሜት በመግፈፍ ከሥነ-ልቦና ጫና እንዳወጧቸው ጠቅሰዋል። በእርግጥ በጦር ሜዳ ደረጃ ጄ/ል ተፈራ ያሉት እውነት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፣ የኤርትራ ጦር በኃይል ተሸንፎ ወደ ድርድር ጠረጴዛ ሲመጣ እንኳን በህወሓቶች ላይ የበላይነት ነበረው። ምክንያቱም የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ከነበረባቸው የበታችነት ስሜት መውጣት አልቻሉም። ኢትዮጲያዊያን በደማቸው ያስከበሩትን ዳር-ድንበር አቶ መለስ ዜናዊ እና ስዩም መስፍን በድርድር ለኤርትራ አሳልፈው የሰጡት ለዚህ ነው።

የህወሓት አመራሮች የአሰብ ወደብን አሳልፈው በሰጡበት መንገድ ባድመን ለኤርትራ አሳልፈው ሰጡ። የኢትዮጲያን ጦር ያስገኘውን ድል ለኢሳያስ አፈወርቂ አሳልፈው ሰጡት። በዓለም-አቀፉ ማህብረሰብ ፊት ባድመን ለኤርትራ አሳልፈው መስጠታቸውን በፊርማቸው ካረጋገጡ በኋላ “ባድመ ለኢትዮጲያ ተወሰነ” ብለው ህዝቡን በአደባባይ ዋሹት። ውሸታቸው በይፋ ሲረጋገጥ ደግሞ “የአልጄርሱን ስምምነት አልቀበልም” በማለት ዛሬ ላይ ደርሰናል።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የተቀሰቀሰው በህወሓትና ሻዕቢያ መካከል ባለው ተቀናቃኝነትና የተዛባ ግንኙነት ነው። በተመሳሳይ የአልጄርሱ ስምምነት ተግባራዊ እንዳይሆን እንቅፋት የሆነው እነዚህ ሁለት ኃይሎች ናቸው። ላለፉት 20 አመታት የኢትዮጲያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አመታዊ ዕቅድ ውስጥ “በኤርትራ መንግስት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጣል ማድረግ” የሚለው ዓ.ነገር ሳይካተት ቀርቶ አያውቅም። በመሆኑም የኤርትራን መንግስት ከዓለም አቀፉ ማህብረሰብ መለየትና ዲፕሎማሳዊ ጫና ማድረግ የመስሪያ ቤቱ መደበኛ ተግባር ሆኖ ቆይቷል። በሌላ በኩል ኤርትራ ራሷን በኢትዮጲያ መንግስት ላይ የትጥቅ ትግል የጀመሩ የፖለቲካ ቡድኖች የጋራ መሰብሰቢያ ሆና ቆይታለች።

የኤርትራ መንግስት በጦርነት ተሸንፏል፣ በዓለም አቀፍ ሸንጎ ግን ባድመን ለኤርትራ በማስወሰን አሸንፏል። የኢትዮጲያ መንግስት በጦርነት አሸንፏል፣ በዓለም አቀፍ ሸንጎ ግን ባድመን ለኤርትራ አሳልፎ በመስጠት ተሸንፏል። የኤርትራ መንግስት ባድመን አሳልፎ ከሰጠ በሽንፈት ላይ ሽንፈት ይሆንበታል። የኢትዮጲያ መንግስት የአልጄርስ ስምምነትን ከተቀበለ ግን ኢትዮጲያ በጦርነት፣ ኤርትራ በድርድር አሸናፊ ይሆናሉ።

ኢትዮጲያ የአልጄርሱን ስምምነት ካልተቀበለች ግን አሸናፊም፥ ተሸናፊም በሌለበት የሁለቱ ሀገራት ፍጥጫ ይቀጥላል። ምክንያቱም የሻዕቢያ መንግስት በህወሓቶች ላይ ያለውን የሞራል የበላይነት ማጣት አይፈልግም፣ ህወሓቶች ደግሞ በበታችነት ስሜት የሰሩትን ስህተት መቀበል አይሹም። ስለዚህ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላም እንዲወርድ ከሁለቱ አንዱ የፖለቲካ ስልጣኑን ማጣት አለበት። ይህ ሲሆን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት የመቀየር እድሉ ሰፊ ነው። ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ሁለቱም ሀገራት ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይደሉም። ለዚህ ነው ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ በተመረጠበት ዕለት ህወሓቶች ለ20 አመታት መናገር ያቃታቸውን ነገር ቀለል አድርጎ የተናገረው።

በመጨረሻም ከአንድ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረባ ባገኘሁት መረጃ መሰረት፣ የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትላንት የአልጄርሱን ስምምነት ለመቀበል ያሳለፈው ውሳኔ የኢትዮጲያ መንግስት በተናጠል የወሰደው እርምጃ አለመሆኑን ለመረዳት ችያለሁ። ከዚያ ይልቅ፣ የኢትዮጲያ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ከኤርትራው ፕረዜዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር በአቡ-ዲያቢ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ጠ/ሚ አብይ በሳውዲ አረቢያ ያደረጉትን ጉብኝት ካጠናቀቁ በኋላ ወደ አቡ-ዲያቢ ተጉዘው እንደነበር ይታወሳል። በተመሳሳይ ወቅት የኤርትራው ፕረዜዳንት “ለሕክምና” በሚል ሰበብ ወደ አቡ-ዲያቢ ማቅናታቸው ይታወሳል። ከላይ የጠቀስኩት የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባልደረባ እንደነገረኝ ከሆነ ሁለቱ መሪዎች በአቡ-ዲያቢ ተገናኝተው መክረዋል። በመሆኑም የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጄርሱን ስምምነት ለመቀበል የወሰነው በተናጠል ሳይሆን በቅድሚያ ከኤርትራ መንግስት ጋር በመነጋገር የተወሰደ እርምጃ ነው።

One thought on “የሻዕቢያ የበላይነት እና የህወሓት የበታችነት፡ ከአሰብ እስከ ባድመ

  1. ወይ ከተከዜ አልያም ከአላማጣ አይመጡ ከሆነ ይስጧቸው ግን ግን ስንት አንገታም የኦሮሞና አማራ ልጆች አለቁ፡፡ መለስ የሰራው የዘራው ደባ፡፡

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡