ጠ/ሚኒስትሩ ሌባን “ሌባ” በሉ ብለዋል፡ እንሆ እነዚህን ድርጅቶች “ሌቦች” ብለናል!

አንዱ ዲያስፖራ ከወደ አሜሪካ ስልክ ደውሎ “ሃይ…እንዴት ነህ? ሁሉ ሰላም? ሁሉ ጤና? ምን አዲስ ነገር አለ?” አለኝ። እኔም “እህ…ምን አዲስ ያልሆነ ነገር አለ?” አልኩት። “ለምሳሌ ምን?” አለኝ። “ኧረ ባክህ ዶ/ር አብይ ሰርፕራይዝ በሰርፕራይዝ አድርጎናል። ትላንት ብቻ “የመንግስት ድርጅቶችን ፕራቬታይዝ አደርጋለሁ፣ የአልጄርስ ስምምነትን እቀበላለሁ” ብሎ አስገረመን። ዛሬ ደግሞ “ሙስና እና ኪራይ ሰብሳቢነት” በሚሉ ሽሙንሙን ቃላት ሲደነዝዝ በኖረ ጆሯችን እቅጭ-እቅጯን ነገረን እኮ። “ሙስና ‘የሞራል ዝቅጠት ያስከተለው የተደራጀ ዘረፋና ሌብነት ነው’” ማለቱን አልሰማህም እንዴ?
በእውነቱ እኔ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ሙስናን ለመታገል በቅድሚያ ሌባን “ሌባ” ማለት ያስፈልጋል። “አካፋን “አካፋ” ካላሉት ‘ማንኪያ ነኝ’ ብሎ ይፈተፍታል” እንደሚባለው፣ ሌባን “ሌባ”፣ ዘራፊን “ዘራፊ” ብለህ በግልፅ ካልነገርከው የፀረ-ሙስና ወይም እምባ ጠባቂ ኮሚሽን ኃላፊ መሆን ይቃጣዋል። ጠ/ሚኒስትሩ ሁላችንም የቃላት አጠቃቀማችንን መቀየር እንዳለብን ተናግረዋል።

የጠ/ሚኒስትሩ ንግግር በፋና ቴሌቪዥን አማካኝነት የቀረበ መሆኑን ለማሳየት በቪዲዮ ምስሉ ላይ የድርጅቱ አርማ (Logo) ይታያል። ይህን እንዳየሁ አንድ ወዳጄ ትላንት ማታ ስለ ፋና ያደረሰኝ መረጃ ትዝ… አለኝ። ነገሩ እንዲህ ነው። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የፓርቲ ይሁን የንግድ ድርጅት በግልፅ የማይታወቅ የሚዲያ ተቋም ነው። የፋና ራዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ማሰራጫ ድርጅቱ አዲስ አበባ ውስጥ ባስገነባው ትልቅ ህንፃ ላይ ይገኛል። ይህ ግዙፍ ህንፃ የሚውለው ድርጅቱ ለተቋቋመበት የብሮድካስቲንግ አገልግሎት ብቻ አይደለም። ከዚያ ይልቅ ከ300ሺህ እስከ 500ሺህ በሚደርስ ክፍያ አዳራሽ ያከራያል።

አንድ ኮርፖሬሽን በህግ ከተፈቀደለት ውጪ በሌላ ሥራና ተግባር መሰማራት አይችልም። ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሚዲያ ተቋም ነው። ስለዚህ ድርጅቱ የተቋቋመው በሚዲያ ሥራ ላይ ነው። በሕግ የተሰጠው ፍቃድ ሆነ ለመንግስት ግብር የሚከፍለው በሚዲያ ስራ በሚያመነጨው ገቢ ነው። ፋና ሆዬ ግን ትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ሰርቶ ለመንግስትና የግል ተቋማት እያከራየ ኪራይ ይሰበስባል። በመሆኑም በሕግ ከተፈቀደለት አግባብ ውጪ ሃብት በመሰብሰብ በተደራጀ ሌብነትና ዘረፋ ውስጥ ተሰማርቷል።

በሌላ በኩል የመንግስት ድርጅቶችና መስሪያ ቤቶች የራሳቸውን የስብሰባ አዳራሽ እንዲጠቀሙ፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ በሌሎች የመንግስት ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ አዳራሾችን እንዲጠቀሙ፣ በዚህም ለስብሰባና ሌሎች ዝግጅቶች የሚያወጡትን አላስፈላጊ ወጪ እንዲቆጥቡ መመሪያ መተላለፉ ይታወሳል። ሆኖም ግን፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ እና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ለአንድና ሁለት ቀን ስብሰባ እስከ 500ሺህ ብር በሚደርስ ወጪ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን የስብሰባ አዳራሽ ተከራይተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

በተደራጀ ሌብነት ላይ የተሰማሩ የግልና የመንግስት ድርጅቶች፦ ልክ እንደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ እና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር

በመንግስት ድርጅቶችና መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚገኙት የስብሰባ አዳራሾች ያለ ምንም ስራ ክፍት ሆነው እየዋሉ እነዚህ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አዳራሽ የማከራየት ሕጋዊ ፍቃድ ከሌለው የሚድያ ተቋም የስብሰባ አዳራሽ በመከራየት ሕገ-ወጥ ክፍያ ፈጽመዋል። በመሆኑም ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች ኤጀንሲ እና የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር ልክ እንደ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት “የተደራጁ ሌቦች” ብለናቸዋል።