ህወሓት “ከቆሞ ቀርነት” ወደ “በቁም መሞት” ተሸጋግሯል!

እንደ ህወሓት ያለ አስገራሚ የፖለቲካ ቡድን ያለ አይመስለኝም። በጣም ገራሚ ነው። ከአመታት በፊት ያስቀመጥከው ቦታ ቁጭ ብሎ ይጠብቅሃል። በራሱ ምንም ዓይነት ለውጥ እንዲመጣ አይሻም። ከራሱ ባለፈ በሌሎች ዘንድ ምንም ዓይነት ለውጥና መሻሻል እንዲኖር አይፈቅድም። ከሁለት አመት በፊት ህወሓት “ቆሞ-ቀር” እንደሆነ የሚገልፅ ፅሁፍ አውጥቼ ነበር። ዛሬም ቢሆን ከነበረበት ቦታ ንቅንቅ አላለም። ህወሓት ፀረ-ለውጥ ድርጅት ከመሆኑ በተጨማሪ ሥር የሰደደ የአመራር ችግር አለበት። በመሆኑም ህወሓት ራሱን ለለውጥ ማንቀሳቀስ ሆነ መምራት አይችልም።

በተለይ የመለስ ዜናዊ ህልፈትን ተከትሎ ህወሓት “በቁሙ መሞት” ጀምሯል፡፡ ከመለስ ዜናዊ ቀጥሎ የህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አባይ ወልዱ ናቸው። ሰውዬው እንደ መለስ ዜናዊ ሸርና አሻጥር መጎንጎን አልቻሉበትም። በመሆኑም የመለስ ዜናዊ የነፍስ አባት የሆኑት ኣይተ አባይ ፀሓዬ ወደፊት መጡ። ምን ያደርጋል ታዲያ ኣይተ አባይ ከኋላ ሆኖ ነገር መጎንጎን እንጂ ፊት-ለፊት መናገር አይችሉም። የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን በመቃወም በኦሮሚያ የተነሳውን አመፅና ተቃውሞ በመቀስቀስና በማቀጣጠል ረገድ ከጃዋር መሃመድ ያልተናነሰ አስተዋፅዖ አበርክተዋል። እሳቸውን ወደኋላ ጎተት አድርጎ አቶ ጌታቸው ረዳ ወደፊት ብቅ አለ። “እሳትና ጭድ” ቅብርጥስ ብሎ አባይ ፀሓዬ ባቀጣጠሉት እሳት ላይ ቤንዚን ጨመረ። በኦሮሚያና አማራ ክልል የተጀመረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ይበልጥ ተቀጣጠለ፣ እስር-በእርስ መጣመርና መተባበር ጀመረ።

ከዚያ በመቀጠል ለ35 ቀናት መቐለ ላይ ያደረጉት ስብሰባ “የመለስ ዜናዊ ራዕይ ውጣ!፣ የአቦይ ስብሃት ዘመድ ግባ!” በሚል ተጠናቀቀ። ባሉበት ለመቆም ያላቸውን ምኞት ዕውን ለማድረግ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን ዳግም ለማወጅ ስልት ነደፉ። በስብሰባው መሃል አቦይ ስብሃት ነጋ የወታደር ሽማግሌዎች አስከትለው ወደ ጎንደር ከሄዱ በኋላ “የኦሮማራ ጥምረት ዓላማው ምንድነው?” በሚል አምባጓሮ አስነሱ። በመጨረሻም ከብአዴኖች ጋር “አንቺ-አንተ” ተባብለው ተሰዳደቡ። በዚህም ለእርቅ ሄደው ፀብ ሸምተው ገቡ።

በተቃራኒው በባህር ዳር የተጀመረው የኦሮማራ ጥምረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቦይ ስብሃት የድርሻቸውን ተወጡ። ከእሳቸው ቀጥሎ ደግሞ ኣይተ ዘርዓይ አሰግዶም መጡ። በኦሮሚያና አማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ባለው አመፅና ተቃውሞ፣ እንዲሁም በብዓዴንና ኦህዴድ መካከል የተፈጠረው ጥምረት በህወሓቶች ስነ-ልቦና ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ እንደ ኣይተ ዘርዓይ አሰግዶም አሳምሮ ያወጣ ሰው ከቶ ከወደየት ይገኛል? ድሮ አቶ አባይ ወልዱ እያለ ህወሓት ራሱን ከውድቀት የመታደግ ዕድል ነበረው። ሌላው ቢቀር የንቅናቄው ፊትአውራሪ ከሆኑት ኦቦ ለማ መገርሳ ጋር ስልክ ደውሎ ማናገር ይችል ነበር። ከዚያ በተረፈ ያሉት የህወሓት ባለስልጣናትና ጄኔራሎች ፊትአውራሪውን በስልክ የማናገር ዕድል ተነፍጏቸው ነበር።

አሁን ላይ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካሄል ጠንካራ የፖለቲካ ክርክር ማድረግ ቀርቶ ሃሳባቸውን እንኳን በግልፅ ማስረዳት አይችሉም። ለምሳሌ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫን አስመልክቶ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ያደርጉትን ቃለ ምልልስ ተመልከቱ። በዚህ ቃለ ምልልስ ዶ/ር ደብረፂዮን “ለሊቀመንበርነት ሦስት ተወዳዳሪዎች እንደነበሩና እሳቸውም ከእነዚህ ውስጥ አንዱ መሆናቸውን በመጥቀስ ምርጫው በጣም ዴሞክራሲያዊ እንደነበር ይገልፃሉ። እኔ ግን “እንዳትመርጡኝ ብዬ ስቀሰቅስ ነበር” ብለዋል። በመጨረሻም መራጮቹ ያልኩትን ሰምተው ስላልመረጡኝ አመሰግናለሁ” ብለዋል። እንዲህ ያለ የምርጫ ቅስቀሳ በዓለም ታይቶም-ተሰምቶም የሚያውቅ አይመስለኝም። ያም ሆነ ይህ ነገሩ የሚያሳየው በህወሓት ውስጥ ያለው የአመራር አቅም ማነስ ነው።

ከላይ የተጠቀሱት መሪዎች በሙሉ አንድ ነገር በተናገሩ ቁጥር የህወሓትን መቃብር የሚቆፍሩ ናቸው። በዚህ በመማረር የህወሓት መስራችና በቻይና የኢትዮጲያ አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን በተራቸው ወደፊት መጡ። ግንቦት 20ን አስመልክቶ በመቐለ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ አቶ ስዩም በወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህ መድረክ “ፖለቲካዊ ስርዓቱ ያጋጠመው መሰረታዊ ችግር በአብዮታዊ ዴሞክራሲ እና በኪራይ ሰብሳቢነት መካከል የተፈጠረ ግጭት” መሆኑን ገልፀዋል፡-

እንደሚታወቀው የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አጀንዳ ዋና አራማጆች ህወሓቶች ናቸው፣ በሀገሪቱ ለተንሰራፋው ኪራይ ሰብሳቢነት ግንባር ቀደም ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ህወሓቶች ናቸው። ምክንያቱም ሀገሪቱን ለቀውስ የዳረጋት የህወሓትን የበላይነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተው የጠነዛ ፖለቲካዊ አቋምና አመለካከት ነው። ሆኖም ግን፣ አቶ ስዩም መቐለ ድረስ ሄደው የተናገሩት ነገር ሌላ ነው። አቶ ስዩም በህወሓት የበላይነትና የጠነዛ የፖለቲካ አመለካከት ምክንያት የተፈጠረውን ችግር በብዓዴንና ኦህዴድ ላይ ለማላከክ ጥረት ሲያድጉ ተስተውለዋል። ውይይቱ በአማርኛ የተደረገበት ምክንያት ደግሞ ከትግራይ ውጪ ላለው ማህብረሰብ “አለን፥ አልሞትንም” ለማለት ነው።

የፖለቲካ ቡድን ሕልውና የሚረጋገጠው ከወቅቱና ከሕዝቡ ፍላጎት ጋር አብሮ መለወጥና መሻሻል ሲችል ነው። ለአራት አስርት አመታት አንድ ዓይነት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት እያመነዠከ፣ ለለውጥና መሻሻል እንቅፋት የሆነ የፖለቲካ ቡድን “ቆሞ ቀር” ብቻ ሳይሆን “በቁሙ መሞት” የጀመረ ነው። ስለዚህ በዚህ አቋሙ ህወሓት ከሞት ወይም ውድቀት አፋፍ ላይ መሆኑ እርግጥ ነው።

3 thoughts on “ህወሓት “ከቆሞ ቀርነት” ወደ “በቁም መሞት” ተሸጋግሯል!

  1. በእውቀት የተመሰረተ ድርጅት እኮ አይደለም እንጂ ከሞተ ቆይቷል ችግሩ የእድሩ (ህዝቡ)ነው በወቅቱ ባለመቅበሩ፡፡

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡