የዶ/ር አብይ ሂሳብ፡ (ኢትዮጲያ – ባድመ)+ (ኤርትራ – የጦር ሰፈር) = የኢትዮጲያ ባህር ሃይል

ሰሞኑን ጠ/ሚ አብይ ሀገራችን የራሷ የባህር ሃይል እንደሚኖራት መጠቆማቸው ይታወሳል፡፡ በእርግጥ ዶ/ር አብይ የባህር ሃይል ስለማቋቋም በይፋ የተናገሩት አንድ ተጨባጭ ምክንያት ቢኖራቸው ነው፡፡ እንደ እኔ ግመት ዶ/ር አብይ አቡ ዲያቢ ላይ ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ካነሷቸው ነጥቦች አንዱ ኤርትራ ውስጥ የጦር ሰፈር መገንባት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ከባህር ጠረፍ ላይ የጦር ሰፈር ከሌለ የባህር ሃይል ማቋቋም ትርጉም የለውም፡፡ ጅቡቲ ላይ ፈረንሳይና አሜሪካን የጦር ሰፈር አላቸው፡፡ በሶማሊላንድ በኩል የተሻለ ዕድል ቢኖርም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታው ውስን ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የኢትዮጲያን ባህር ሃይል መልሶ ማቋቋም ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ የሚኖረው ቀይ ባህር ላይ የጦር ሰፈር መገንባት ሲቻል ነው፡፡

በመሠረቱ የኢሳያስ አፈወርቂ መደራደሪያ ሃሳብ ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጠኝነት “የአልጄርሱን ስምምነት ተቀበሉና ባድመን አስረክቡን” የሚል ይመስለኛል፡፡ ዶ/ር አብይ ደግሞ የራሱን መደራደሪያ ሃሳብ ያቀርባል፡፡ የመጀመሪያው የአሰብ ወደብን መጠቀም ነው፡፡ ነገር ግን፣ የአሰብ ወደብን መጠቀም ጥቅሙ ከኢትዮጲያ ይልቅ ለኤርትራ ነው፡፡ ምክንያቱም የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ከአንደ የወርቅ ማውጫ በአመት የሚያገኘው $100ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ኢትዮጲያ የአሰብ ወደብን ብትጠቀም በአማካይ በአመት $300ሚሊዮን ዶላር ያገኛል፡፡

በነገራችሁ ላይ በዚህ አመት በሱዳን በኩል የመጣች ኤርትራዊ እንደነገረችኝ ከሆነ ኤርትራ ከተገነጠለች ወዲህ አስመራ ውስጥ የተገነቡትን ህፃዎች ብዛት 4 (አራት) ብቻ ናቸው፡፡ አስመራ ከተማ ስሟ እንጂ ትልቅ ስፋቷ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ከተማዋ ከጫፍ እስከ ጫፍ ብትለኳት 7 ኪሎ ሜትር ናት፡፡ ስለዚህ የከተማ እድገትና መስፋፋት ብሎ ነገር የለም፡፡ በመጨረሻ አስመራ ውስጥ ስንት ፋብሪካ ያለ ይመስላችኋል? በደንብ የሚንቀሳቀሱት ሁለት (2) ፋብሪካዎች ሲሆኑ እነሱም አንድ ቢራ ፋብሪካ እና አንድ ውሃ ማሸጊያ ናቸው፡፡ ኢትዮጲያ የአሰብ ወደብን ብትጠቀም በአንድ አመት አስመራ ውስጥ ስንት ህንፃና ፋብሪካ እንደሚገነባ አስባችሁታል?

አሁን የጅቡቲ ወደብን እንደምንጠቀመው ወደፊት የአሰብ ወደብን ከፍለን ነው የምንጠቀመው፡፡ ስለዚህ የአሰብ ወደብን መጠቀም ለኢትዮጲያ መደራደሪያ ሊሆን አይችልም፡፡ “አሰብ ወደብ ላይ የጦር ሰፈር ማቋቋም” የሚለውስ? ይሄ ትክክለኛ መደራደሪያ ነው፡፡ ኤርትራ ይህን አልቀበልም አትልም፡፡ እንኳን ለእኛ ለግብፅና ኳታርም ፈቅዳለች፡፡ ኢሳያስ የሚፈልገው የውጪ ምንዛሬ የሚያገኝበት እንጂ ሌላ ነገር አይደለም፡፡ የትኛውም ሀገር ሊሰጠው ከሚችለው የገንዘብ ድጋፍ ከኢትዮጲያ የውጪ ንግድ እንቅስቃሴ የሚያገኘው ይበልጣል፡፡

ከዚያ በተጨማሪ የኢትዮጲያ ህዝብና መንግስት ከኳታርና ግብፅ ይቀለዋል፡፡ ምክንያቱም ከፖለተካ አንፃር የአረብ ሀገራት ኤርትራን መጠቀሚያ የሚያደርጏት ሲሆን ከኢትዮጲያ ጋራ ግን የጋራ ጥቅም ይኖራታል፡፡ ኢትዮጲያ አሰብ ላይ የጦር ሰፈር እንድታቋቁም መፍቀድ በኢኮኖሚ ሆነ በፖለቲካ ረገድ ለኤርትራ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ እንግዲህ ለዚህ ይመስለኛል ዶ/ር አብይ “የባህር ሃይል አናቋቁማለን” ብሎ በተናገረ ማግስት የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የአልጄርስ ስምምነትን የተቀበለው፡፡

እነአንቶኔ የድንጋይ ፍትፍት የሞላትን ባድመ “ሄደች፥ ቀረች” እያሉ ይቃዣሉ፡፡ እኛ ቀይባህር ላይ የቀድሞውን የኢትዮጲያባህር_ሃይል መልሰን ስለማቋቋም እያሰብን ነው፡፡ ለማንኛውም ይህን በቀድሞ የኢትዮጲያ ባህር ሃይል (Ethiopian Navy Force) ባልደረባ የተዘጋጀ የቪዲዮ ቅንብር በመጋበዝ እሰናበታለሁ፡፡

2 thoughts on “የዶ/ር አብይ ሂሳብ፡ (ኢትዮጲያ – ባድመ)+ (ኤርትራ – የጦር ሰፈር) = የኢትዮጲያ ባህር ሃይል

 1. በቅድሚያ ኤርትራን በተመለከት በሀይለስላሴ መንግስት እና በመለስ ዜናዊ አድሎአዊ አገዛዝ የነበረውን የተዛባ ፖሊሲ አንድ ነጥብ ብቻ ልጥቀስ… (የደርግ ያው ውድመት ብቻ ነበር)

  • ምሳሌ -1- (ብጻይ መለስ)
  በወቅቱ 4ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ለነበራት የቀድሞ ክፍለሀገር ኤርትራ ለአሰብ ወደብ ኪራይ ብቻ ኢትዮጵያ በያመቱ ከ$2ቢሊዮን ዶላር (20 ቢሊዮን የኢትዮ ብር) በላይ ትገብር የነበረ ሲሆን፤ በወቅቱ ከ20 ሚሊዮን ህዝብ በላይ የሚኖርበት የኦሮሚያ ክልል አመታዊ በጀት 1.4 ቢሊዮን ዶላር (14 ቢሊዮን የኢትዮ ብር) ብቻ ነበር። በመሆኑም የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ በሚያገኘው የወደብ ኪራይ ብቻ ከኦሮሚያ ህዝብ ከአምስት (5) እጥፍ በላይ ገቢ (500%) ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማግኘት ይኖር ነበር።

  • ያውም…
  (1. • ብጻይ መለስ ዜናዊ መጠኑ በህግ የማይታወቅ ገንዘብ ወደ ኤርትራ ባንክ በማዛወር የኢትዮጵያን ባንክ ባራቆተበት)

  (2. • ብጻይ መለስ ዜናዊ የራሱን ታማኝ ባለሀብቶች እስከሚፈጥር ድረስ በአዲስ አበባ የሚገኙ የኤርትራ ተወላጆች ከውጭ ሀገር እቃዎችን ያለቀረጥ እያስገቡ አዲስ አበባ ላይ በፈለጉት ዋጋ ሲሸጡ አውቆ ዝም በማለት ህጋዊ ኢትዮጵያዊ ባለሀብቶችን በማዳከም ከጥቅም ውጭ ባደረገበት)

  • ምሳሌ -2- … ትላንት (ሀይለ ስላሴ)
  1. • በሀይለ ስላሴ መንግስት ፈዴሬሽኑን በማፍረስ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር በመኖር እንዲጸና በመፈለግ በወጣ ሚዛን ያልጠበቀ ደንቆሮ ኢኖሚያዊ ፖሊሲ መሰረት 65% የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ በኤርትራ እንዲተከል በተደረገበት)

  2. • የሀይለስላሴ መንግስት “ኤርትራን ከእናት ሀገርዋ ለማዋሀድ” በሚል ተልካሻ (ያልሰራ) ፖለቲካዊ ፖሊሲ መሰረት ፈዴሬሽኑን በማፍረስ “ትዋሀድ” ብለው ፒቲሺን ለፈረሙ በመላ ኢትዮጵያ ለተሰማሩና ለሚሰማሩ ለያንዳንዱ የኤርትራ ተወላጆች እንደምርጫቸው 1/ ተሳቢ ያለው የነዳጅ ቦቴ መኪና ወይም 2/ ተሳቢ ያለው የጭነት መኪና ወይም ደግሞ በፈለጉት ከተማ ሆቴል ወይም ጋራዥ እንዲገነቡ በወቅቱ ከዶላር እኩል ምንዛሪ የነበረ $10ሺ ብር ለያንዳንዳቸው በመስጠት በሀገሪቱ ጥሩ ሀብታሞች በሆኑበት) (• ለዚህም ነው 1. የኤርትራ ተወላጆች የሆቴል፤ የጋራዥ፤ የነዳጅና የጭነት ተሳቢ መኪና ንግድን በስፋት የያዙት 2. በኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የነጣ ደሀ የኤርትራ ተወላጅ የማይታይበት ምክንያቱም ይህ ነው)

  • ዛሬ… ዶ/ር አቢይ
  (የባድመ ጦርነትን ያደረሰው የሰብአዊና የኢኮኖሚ ከፍተኛ ክስረት ገና በውል ባልተጠናበት… ኢትዮጵያ ጦርነቱን ባለመጀመርዋ ለደረሰው የጦርነት ውድመት ኪሳራ ለኢትዮጵያ ካሳ እንዲከፈል ስምምነት እንደሚደረግ ባልተረጋገጠበት) ዛሬ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ ከሕወሀት/ኢህአዴግ በመውጣት አዲስ የአመለካከት የለውጥ አየር በማናፈስ የበሰበስውን TPLF/EPRDF ስርአት ለህዝብ ወገን ወደሚሆን አዲስ ስርአት ለመቀየር ደፋ ቀና የሚሉት አዲሱ ጠ/ሚር አቢይ አህመድ የአልጀርሱን ስምምነት በመቀበል የሚመጣው ለውጥ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት የሚያረጋግጥ ካልሆነ “እንደመር” እያሉ “መቀነስ” እንዳይሆንባቸው እሰጋለሁ።

  I pray that let God help this genuine Ethiopian PM Abiy Ahmed Ali !!!

  Like

 2. የተከበርክ ኣቶ ስዩም የጻፍከውን ኣንብቢያለው። ኣሁን መልስ ለመስጠት የፈለግኩት ግን ስለ ያንተ በጦማሩ ላይ ያለው ኣስተያየት ሳይሆን። ኣንዳንድ መታረም ያለባቸው ማስረጃዎች እንዳሉ ለማስታወስ ነው። ከኤርትራ ነጻነት ቡሃላ በኣስመራ ስለተሰሩ ቤቶች ኣንዲት ሴት የነገረችህ ብዛት ትክክል ኣይደለም። ኣዎ እንደ ኣዲስ ኣበባ ባይሆንና እንደተፈለገውም ባይሳካ ብዙ ቦታዎች ብዙ ቤቶች ተሰርተዋል። ትልቁ ፕሮጀክት በኮርያውያን የተሰራው እንዳኮርያ ተብሎ በሚጠራ ቦታ እስከ መቶ የሚደርስ ኣፓርታማዎች ተሰርተዋል። በዛ ኣካባቢም ከሱ የተለዩ ብዙ ፎቆች ተሰርተዋል። ለምሳሌ ሚሆንም ኢንተርኮንቲነንታል ሆቴል ይጠቀሳል። በሌላ ቦታዎችም የተሰሩ ቤቶች ኣሉ በየኣካባቢው። ለምሳሌ ስፐስ፣ ማይተመናይ፡ ቀሓውታ፡ ሓዝሓዝ፡ ሰምበልና ሌሎችም ኣሉ። ኣሁንም በውስጣዊ ዓቅምና ከጣልያን ኩባንያ ጋር በትብብር የሚሰሩ እስከ መቶ የሚደርሱ ኣፓርታማዎች ኣሉ። እቺ ሴትዮ ኣለችኝ የምትለኝ ግን የሚገባኝ ከሆነ፡ ኣስመራ በኣርትዴኮ የተሰራችና በUNESCO የተመዘገበች ናት። በዛ በኣርትዴኮ ክልል ደሞ 4 የሚሆኑ ኣርትዴኮውን የሚያበላሹ ፎቆች ተሰርተዋል። እንደ ስተትም ተቆጥሯል። ኣንዱ ናቅፋ ሃውስ ተብሎ የሚጠራ ትልቅ ህንጻ ነው። ሴትዮው እየተናገረች ያለችው ስለዚ እንዳይሆን። ኣስመራ ኣዎ ትንሽ ናት፡ ለመረጃ እንዲሆንህ የኣስመራ የቆዳ ስፋት 17.37mi2 ሲሆን የኣዲስ ኣበባ ደሞ 203.5 mi2 ነው። ስለዚ ኣዲስ ኣበባ ከኣስመራ በ12 እጥፍ ትልቅ ናት። ስለ ፋብሪካዎች የጠቀስከውም በጣም ኣጋነነከው ወንድሜ፡ ለሰው የተሳሳተ መረጃ ማድረስ ነው። ስንት ፋብሪካዎች እንዳሉ በትክክል ባላውቅም ቱባ ቱባዎቹን በደምብ ሚንቀሳቀሱትን ልዘርዝርልህ፡ እንዳልከው 1 ፋብሪካ ቢራ፡ ከ10 የሚበዙ የውሃ መሸጊያዎች፡ 1 የኮካኮላ ፋብሪካ፡ በኢጣልያዊ ዜጋ የሚተዳደር የጨርቃጨርቅ ኢንዳስትሪ፡ ሌላ ባራኮ የሚባል ወታደራዊና የተማሪዎች ዩኒፎርም የሚያቀርብ ፋብሪካ፡ ሌላ ኣስመራ ቴክስታይል የሚባል ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ፡ Asmera Soap Factory፡ የተለያዩ የማተምያ ድርጅቶች፡ የዓይን መነጽር ፋብሪካ ……. ቆይ ራስህ እንድትዳስስ ሊንኩን ልስጥህ፡ https://en.wikipedia.org/wiki/Asmara
  http://www.asmera.nl/asmara-offices.htm
  እና ራስህም የመረጃ ዘመን ነውና፡ ጎግል google ኣርግ
  ስለ የጦር ሰፈር ያልከው፡ እንዳልከው የኳታርና የግብጽ የጦር ሰፈር የለም፡ ያለው የተባበሩት ኣረብ ኢማራት ነው።
  የምትፈልገውን ኣሳብ መጦመር የሚቻል ቢሆንም የተዛባ መረጃ መስጠት ግን ክብር ኣይሰጥምና፡ በተቻለህ መጠን እውነተኛና የተጠና መረጀ ብዙ ኣድማጭ ካለህ ኣንተ የሚጠበቅ መሆኑን እንዳትረሳ። ስላነበብከው ኣመሰግናለው።

  Liked by 1 person

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡