ኮማንድር ገብሩ እና የማዕከላዊ እስረኞች፦ ከማንጓጠጥ ወደ መለማመጥ!

ዛሬ የኮማንደር ገብሩ ፊት ከዓይነ-ህሊናዬ አልጠፋ ብሎ ቢያስቸግረኝ ይህቺን ፅኁፍ መከተብ ጀመርኩ። ኮ/ር ገብሩ በማዕከላዊ እስር ቤት አስተዳደር ኃላፊ ነው። ቁመተ ረጅም፣ እንደ እኔ ቦርጫም፣ ፊቱ ጨፍጋጋ፣ እግሮቹ ሸፋፋ ናቸው። ታዲያ በረጅም ቁመቱ ፊቱን አጨፍጎ፣ ቦርጩን አንዘርጦ ሲመጣ ጭልፊት እንዳየች ጫጩት ሮጩ ብርድ ልብስ ውስጥ እደበቃለሁ። ከእሱ ጋራ ዓይን ለዓይን መተያየት አልፈልግም። ለምን ቢባል ያለ ምንም ምክንያት ይሰድበኛል፣ ያበሻቅጠኛል፣ አስፈራራኛል፣ ….ብቻ ምን ቅጡ። ይህ በእኔ ላይ ብቻ አልነበረም። ለምሳሌ በተመሳሳይ ወቅት ጣውላ ቤት አምስት ቁጥር ታስሮ የነበረውን የኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊስ ምክትል አዛዥ በኮማንደር እያሱ አንጋሱን ይሰድበው፥ ያንጓጥጠውና ያመናጭቀው ነበር።

ኮ/ር ገብሩ ይህን ያደረገው በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ወቅት በታሰርነው ላይ ብቻ አይደለም። በቃ ወደ ማዕከላዊ እስር ቤት ከመጣ ግዜ ጀምሮ የኮ/ር ገብሩ ባህሪ አንድ ዓይነት ነው። በረጅም ቁመቱ ፊቱን አጨፍጎ፣ ቦርጩን አንዘርጦ ይመጣና፤ በዚያ ቆማጣ አማርኛው ይሳደባል፥ ይቆጣል፣ በዚያ ሸፋፋ እግሩ እስረኞችን ይመታል፥ ይራገጣል። አንድ ቀን ወደ እስረኞች መጠየቂያው ጋር በመሄድ ሊጠይቀኝ ከመጣው ከበፍቃዱ ሃይሉ ጋር እያወራን ሳለ ኮ/ር ገብሩ በተለመደው መልኩ እየተራመደ ገላምጦን አለፈ።

እኔም “ኡፍፍፍ… በፍቄ የዚህ ሰውዬ ስድብና ግልምጫ ነፍሴን ሊያወጣኝ ነው” አልኩት። በፍቃዱ በሚያስገርም የቁጭት ስሜት ውስጥ ሆኖ “የስርዓት ለውጥ ሲመጣ ይህን ሰውዬ ሕሊናው ዕረፍት እንዲነሳው፣ ቀሪ እድሜውን በፀፀትና ቁጭት እንዲኖር ነው የማደርገው… በክስ ወይም በሌላ ነገር አይደለም። እዚህ ጣውላ ቤት በእኔና በጓደኞቼ (ዞን9 ጦማሪያን) ላይ ሲፈፅም የነበረው ግፍ… የፈፀመብንን ግፍና በደል በደብዳቤ መልክ ፅፌ እሰጠዋለሁ። ከዚያ እድሜ ልኩን ‘ምንነው ባላደረኩት ኖሮ’ እያለ በፀፀትና ቁጭት ይኑር” አለኝ።

ይሁን እንጂ ዶ/ር አብይ ከተመረጠበት ዕለት አንስቶ የኮ/ር ገብሩ ባህሪ ፍፁም ተቀየረ። ቀድሞ አንገቱን ቀና አድርጎ ፀብ እያነፈነፈ የሚራመደው ሰውዬ ዛሬ ወደ መሬት አቀርቅሮ በሃሳብ ተክዞ መራመድ ጀምሯል። ዶ/ር አብይ ከተመረጠ ከተወሰኑ ቀናት በኋላ እኔና ኮ/ር እያሱ ከጣውላ ቤት ወደ ሸራተን (09) ተዘዋወርን። እዚያ ከታዬ ደንደኣ ጋር ሆነን ፖለቲካ መሰለቅ ጀመርን። ኮ/ር ገብሩ አንዳንዴ ወደ ሸራተን ብቅ ቢልም እንደ ቀድሞ አይሳደብም፥ አያመናጭቅም፥ አያስፈራራም።

ብዙዎቻችሁ “የፖሊስ ኮማንደር ከእሱ ሥራና ተግባር ጋር በቀጥታ በማይገናኝ የፖለቲካ ምርጫ ምክንያት ለረጅም አመታት የነበረውን ባህሪ አንዴት በአንዴ ሊቀይር ይችላል?” የሚል ጥያቄ እንደምታነሱ እገምታለሁ። በእርግጥ ጥያቄያችሁ አግባብ ነው። ነገር ግን፣ ስህተቱ ኮ/ር ገብሩን እንደ “ፖሊስ ኮማንደር” መመልከታችሁ ነው። ይህ ሰው እንደ ማንኛውም የፖሊስ ኮማንደር በሕግ የተሰጠው ድርሻና ኃላፊነት አለው። ይሁን እንጂ፣ ኮ/ር ገብሩ ራሱን የሚመለከተው እንደ መደበኛ የፖሊስ ኮማንደር ብቻ ሳይሆን የመንግስታዊ ስርዓቱ ጠበቃና ጠባቂ አድርጎ ነው።

ማዕከላዊ እስር ቤት ከሚገቡት አብዛኞቹ የፖለቲካ እስረኞች ናቸው። ኮ/ር ገብሩ ደግሞ የመንግስታዊ ስርዓቱ ጠበቃና ጠባቂ ስለሆነ እነዚህን የፖለቲካ እስረኞች በዓይነ-ቁራኛ ነው የሚመለከታቸው። ስለዚህ እነዚህን “ፀረ-ሰላም፥ ፀረ-ሕዝብ፥ ፀረ-ልማት” የሆኑ የመንግስታዊ ስርዓቱ ቀንደኛ “ጠላቶች” ባገኘው አጋጣሚ አካላቸውን ሆነ ሞራላቸውን ድባቅ ለመምታት ጥረት ያደርጋል። ይህን በማድረጉም ለህወሓት መራሹ መንግስት ዋስትና የሆነ፣ የስርዓቱን ሕልውና ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን አስተዋፅዖ ያበረከተ መስሎ ይሰማዋል። በአጠቃላይ ኮ/ር ገብሩ በማዕከላዊ የሚንቀሳቀሰው እንደ ፖሊስ ኮማንደር አሊያም የአስተዳደር ኃላፊ ሳይሆን የህወሓት/ኢህአዴግ ጠባቂና መከታ ሆኖ ነው።

ስለዚህ በአህዴድ መሪነት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ የህወሓትን የስልጣን የበላይነት ገፍፎ እርቃኑን ሲያስቀረው የኮ/ር ገብሩ ሕልምና ዓላማ ነው የተቀጨው። ለዚህ የዶ/ር አብይ መመረጥ በኮ/ር ገብሩ ላይ ሀዘንና ትካዜ የለቀቀበት። እስረኞችን ከመሳደብ ስለ ወደፊቱ ማሰብ፣ እስረኞችን ከማንጓጠጥ ወደ መለማመጥ፣ በመንግስት ስም ከመራገጥ ከተጠያቂነት እንዴት እንደሚያመልጥ፣… ወዘተ ማሰብና ማሰላሰል ጀመረ። ኮ/ር ገብሩ እስረኞችን ከማስደንገጥ ይልቅ ለራሱ መደንገጥ የጀመረው በዚህ መልኩ ነው።

ለምሳሌ አንድ ቀን (አስታወስኩት… የስቅለት ዕለት) ተረኛ ፖሊሶች በጠዋት መጥተው “እቃችሁን ያዙና ለመሄድ ተዘጋጁ!” አሉን። ሁላችንም ልንፈታ እንደሆነ በማሰብ ከመኝታችን ተስፈንጥረን በመነሳት ዕቃችን እየሰበሰብን በኩርቱ ፌስታል መጠቅጠቅ ጀመርን። እንዲህ በደስታና ጉጉት ተወጥረን ሳለ በመሃል ኮ/ር ገብሩ ቦርጩን አንዘርጦ፣ ፊጡን አጨፍግጎ፣ ሸፈፍ-ሸፈፍ እያለ መጣና ምን ቢል ጥሩ ነው? “ፍራሻችሁንም ያዙ!” የፈጣሪ ያለህ እስኪ ምን አለበት ይህንን የመጀመሪያዎቹ ፖሊሶች አሊያም ሌሎች ፖሊሶች መጥተው ቢነግሩን? “ፍራሻችሁን ያዙ!” ሲል “ወደ ሌላ እስር ቤት ልትዛወሩ ነው” ማለቱ እንደሆነ ሁሉም ያውቃል። ስለዚህ በቅፅበት ውስጥ ደስታችን ወደ ሃዘን፣ ጉጉታችን ወደ ሰቀቀን ተቀየረ።

በተለይ እኔ፥ ታዬ ደንደኣ እና ኮ/ር እያሱ በጣም ነበር የተበሳጨነው። ከዚያ ወዲያው “ወደየትና ለምን እንደሚወስዱን ሳይነግሩንና ይህንንም ለቤተሰቦቻችን ስልክ ደውለን ካላሳወቅን ከዚህ ግቢ ንቅንቅ ብለን አንወጣም!” በማለት የአድማ ጥሪ አቀረብኩ። በተለይ በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ እና በፀረ-ሽብር አዋጁ ተከሰው የታሰሩት በሙሉ ተበሳጭተው ስለነበር ጥሪውን ተቀበሉት። ከዚያ በኋላ ተረኛ ፖሊሶች “ቁርስ ውሰዱ” ሲሉን “እምቢ ቀርስ አንበላም” አልን። “ለምን?” ሲሉ ለምንና የት እንደሚወስዱን ካልነገሩንና ለቤተሰብ ካላሳወቅን ቁርስ እንደማንበላ እና ከእስር ቤቱ እንደማንወጣ ተናገርን።

ወዲያው ለኮ/ር ገብሩ ተነገረውና እየተንሻፈፈ መጣ። ለእሱም ከእስር ቤቱ እንደማንወጣ ስንነግረው የድሮ ባህሪው ድንገት ብልጭ አለበትና “ቧ! ወደህ ሳይሆን በግድህ ትወጣለህ” አለ። ይህን ግዜ ከኋላ ታዬ ይሁን ሌላ ሰው “እንደውም ከአንተ ጋር አንነጋገርም!” አለው። ይህን ግዜ እየተጣደፈ ሄዶ የእስር ቤቱን የበላይ ኃላፊዎች ይዟቸው መጣ። ከኮ/ር ከብሩ ጋር የመጡት ሦስት ኃላፊዎች ሲሆኑ ሦስቱም ትግሬዎች (ተጋሩዎች) ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ አንዱ በትግሪኛ አክሰንት ኦሮምኛ በደንብ ይናገራል። (በሌላ ቀን እንደታዘብኩት፣ የማዕከላዊ መርማሪዎች በብዛት ትግሬዎች ሲሆኑ ከእነሱ ውስጥ አብዛኞቹ ኦሮምኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ። ይሄ በራሱ እንደ ኮ/ር ገብሩ ባህሪ በጣም አስገራሚና አስቀያሚ ነው)

እና እላችኋለሁ የስቅለት ዕለት ኮ/ር ገብሩን በአለቆቹ ፊት ሰቅለን የቃላት ውርጅብኝ አወረድንበት። “አንተ ማን ስለሆንክ ነው ‘ወደህም ሳይሆን በግድህ ትወጣለህ!’ የምትለው?!” እያልን ደነፋንበት። እንኳን እስረኛ ነገር ፈልጓቸው እንዲሁም “እሰሩ፥ ደብድቡ፥ ጥፍር ንቀሉ፥ ወፌላላ በሉ” የሚላቸው የማዕከላዊ መርማሪዎችና ኃላፊዎች ያን ዕለት “እጅግ በጣም ይቅርታ! የምትሄዱት እዚሁ ሦስተኛ ነው! ቤተሰብ እንዳይሰጋ ከማዕከላዊ በር ላይ ፖሊስ እንመድባለን። ቤተሰቦቻችሁ ሲመጡ ወደ ሦስተኛ እየመራ ያደርሳቸዋል” እያሉ ይለምኑን ጀመር። እኛም በተለይ ኮ/ር ገብሩ እቅፍ… እያደረገ ሲለማመጠን ግዜ አሳዘነንና ወደ ሦስተኛ ለመዘዋወር ፍቃደኛ ሆንን።

በማግስቱ እንደተረዳሁት የማዕከላዊ ኃላፊዎች እንደዛ የተሸቆጠቆጡት “ማዕከላዊ እስር ቤት ተዘጋ” በማለት በ7፡00 ሰዓቱ የዜና እወጃ ለማስነገር ነው። ይሁን እንጂ የማዕከላዊ መዘጋትም፣ የኮ/ር ገብሩ መሽቆጥቆጥም፣ የእኛ በአድማ መተበትም፣… በአጠቃላይ ሁሉም ነገር ከህወሓት መሸነፍና መጨንገፍ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። ላለፉት ሦስት አመታት በተካሄደው “ዝምተኛው አብዮት (¨The Silent Revolution) የህወሓት አከርካሪ ባይመታና የእነ ኮ/ር ገብሩ ቅስም ባይሰበር ኖሮ ማዕከላዊን መዝጋት አይታሰብም፣ ኮ/ር ገብሩም አይሽቆጠቆጥም፣ እኛም አንተብትም። በእርግጥ ኮ/ር ገብሩ ማዕከላዊ ውስጥ የሚሰራ አንድ ፖሊስ ነው። ሥራና ምግባሩ ግን የአብዛኞቹ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ሥራና ምግባር ነው። የኮ/ር ገብሩ ግራ-መጋባትም በብዙሃኑ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ላይ በግልፅ የሚንፀባረቅ መሆኑ እሙን ነው።

አቶ ታዬ ደንደኣ እና ስዩም ተሾመ (ከማዕከላዊ እስር ቤት መውጫ በር ላይ)