“የትግራይ ህዝብን ለምን ትጠላለህ?”፤ “‘ተሳስተሃል’ እያለ ‘ትጠላለህ’ ጋር ምን ወሰደህ?”

በተደጋጋሚ ለመግለፅ እንደሞከርኩት.፣ “በሀገራችን ለታየው የፖለቲካ ቀውስ ግንባር ቀደም ተጠያቂ ማን ነው?” መልሱ አጭርና ግልፅ ነው። እሱም፡- “ህወሓትና ህወሓት ነው” የችግሩ መሰረታዊ መንስዔ በህወሓት የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ላይ የተመሰረተው መንግስታዊ ስርዓት ሲሆን ዓላማውም የህወሓትን የበላይነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው። ነገር ግን፣ አንዳንድ የትግራይ ልሂቃን “ህወሓት” የሚለውን ከራሳቸው ወይም ከብዙሃኑ የትግራይ ሕዝብ ጋር አያይዘው ይወስዱታል። በተመሳሳይ “የትግራይ መሪዎች” ስል ነገሩን ከትግራይ ሕዝብ ጋር አያይዞ የመመልከት ዝንባሌ በስፋት ይስተዋላል።

በመሰረቱ እንደ አንድ የፖለቲካ ቡድን ህወሓት የራሱ አባላትና ደጋፊዎች ይኖሩታል። እነዚህ የህወሓትን የፖለቲካ አቋምና አመለካከት አውቀውና ደግፈው የሚከራከሩ፣ ድርጅቱ በዘረጋው አድሏዊ አሰራር ያለአግባብ ተጠቃሚ የሆኑ ናቸው። እነዚህ ወገኖች “አፍንጫ ሲነካ አይን ያለቅሳል ለካ” እንደሚባለው ህወሓት ሲነካ ማለቃቀሳቸው ያለና የተለመደ ነገር ነው። ብዙሃኑ የትግራይ ህዝብ ግን የህወሓት ጋድሬዎች ከሚያደርሱበት ወከባና ጫና ተርፎ ለህወሓት ጥብቅና ሊቆም የሚችልበት እንጥፍጣፊ አቅም የለውም።

ህወሓት ለትግራይ ሕዝብ ጥቅም የቆመ በማስመሰል ብዙሃኑን መጠቀሚያ በማድረግ ጥቂቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የፖለቲካ ቡድን ነው። እነዚህ ጥቂቶች ደግሞ ህወሓት ለብዙሃኑ ሕዝብ ጥቅም እንደቆመ አድረገው በማቅረብ የራሳቸውን ጥቅምና ተጠቃሚነት ለማስቀጠል ዘወትር ይታገላሉ። እነዚህ የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ከሌሎች የሀገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ለየት የሚያደርጋቸው ነገር ቢኖር እንወክለዋለን ለሚሉት የትግራይ ሕዝብ ፍፁም ደንታ የሌላቸው መሆናቸው ነው።

ለእነሱ “የትግራይ ሕዝብ” ማለት በራሳቸው ዙሪያ (ሰርክል) ያሉት የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች ናቸው። ሀገርም ሆነ መንግስታቸው ህወሓትና ህወሓት ብቻ ነው። ፓርቲው ትክክል ያለውን ነገር ይደግፋሉ፣ የተቃወመውን ነገር ይቃወማሉ። የህወሓትን ሥራና ተግባር ስትተች “የትግራይ ሕዝብን ይጠላል” ይሉሃል። በሃሳብ ስለሞገትካቸው ብቻ በድብደባ ብዛት ቆዳህ እንዲላጥ ሌት ከቀን ይወተዉታሉ። የሚያመልኩት ድርጅት ሆነ የሚመሩበት አመለካከት ፍፁም ዘረኛ እንደሆነ ስትናገር እንድትታሰር፥ እንድትሰደድ ወይም እንድትገደል የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፍቱብሃል።

እንዲህ ያለ ስርዓት በሀሰት መረጃ ማንነትህን (ስምና ክብርህን) ካጠፋ በኋላ (Character assassination) ከዚያ ቀጥሎ ወይ አድራሻህን ወይም ነፍስህን ሊያጠፋ ይመጣል። ያኔ ከወዳጅ ዘመዶችህ በስተቀር “አይዞህ፥ አለሁልህ” የሚል ሰው ይጠፋል። ምክንያቱም ስምና ክብርህ ከተገፈፈ በኋላ የራስህ የሆነ ማንነት የለህም። ስምህን አጥፍቶ ስጋህን ቢገድል ከአንድ ሰሞን እዬዬ ባለፈ ማንም ዞር ብሎ ስለ አንተ አይጠይቅም።

የቀድሞ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ የፕሮቶኮል ሹም የነበሩትን ግለሰብ እስኪ እንመልከት። መቼም ይህ ግለሰብ የህወሓት አፈ-ቀላጤዎች እንዳሉት “ሻይ አፍዪ”፣ “ስጋ ቆራጭ” ወይም “አትክልተኛ” እንዳልሆነ ታውቃለህ። ምክንያቱም ጠ/ሚኒስትሩ አሜሪካ ኒውዮርክ ድረስ ሻይ በፔርሙዝ፥ ጥሬ ስጋና አዋዜ አሊያም አትክልተኛ ይዘው እንደማይሄዱ ልቦናህ ያውቃል። የአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ቃለ-ምልልስ ከማድረጉ በፊት የግለሰቡን ማንነትና የያዘውን መረጃ ተዓማኒነት የሚያረጋግጥበት የራሱ የሆነ አሰራር እንዳለው ትገምታለህ። ከዚህ በተጨማሪ የተጠቀሱት ግለሰብ የተናገሩት ከህወሓት ባህሪና ተግባር ጋር አብሮ ሊሄድ እንደሚችል ትገምታለህ።

ሆኖም ግን፣ ከላይ የተጠቀሰውን ከማድረግ በፊት የህወሓት አባላትና ደጋፊዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፍታሉ። ሰውዬው ሻይ ሲቀዳ፣ ስጋ ሲቆርጥና አትክልት ሲንከባከብ የሚያሳዩ ምስሎች እየሰሩ ይለጥፉበታል። በስም ማጥፋት የግለሰቡን ማንነትና ተዓማኒነት ከነጭራሹ ያጠፉታል። ይህ የህወሓትን ስህተትና ጥፋት ለማጋለጥ በሞከሩ ሰዎች ላይ የሚፈፀም ደባ ነው። ይህን የሚያደርጉት ደግሞ የህወሓት አመራሮች ሳይሆን የድርጅቱ ደጋፊ የሆኑ ልሂቃን ናቸው። ስለዚህ ህወሓት በፖለቲካ መሪዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ ጋዜጠኞች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥… ወዘተ ላይ ግፍና በደል ሲፈፅም የህወሓት አባላትና ደጋፊ ልሂቃኖች በቀጥታ ተሳታፊዎች ናቸው። የብዙ ኢትዮጵያዊያን ደምና እምባ በእጃቸው ላይ አለ።

ትላንት፥ ዛሬና ነገም የህወሓት ግፍና በደል፣ ጥፋትና ስህተት በተነሳ ቁጥር በእጃቸው ላይ የንፁሃን እምባና ደም ያንቀዠቅዣቸዋል፣ በፍርሃት ያርዳቸዋል። በዚህ ምክንያት እንኳን ህወሓትን በራሳቸው ስም ብትጠራቸው የሰደብካቸው ይመስላቸዋል። “ተሳስታችኋል፥ ተቀየሩ፥ ተሻሻሉ፥…” ብለህ ስትመክራቸው “ዘረኝነት ነው” ይሉሃል። ከህወሓት የቀሰሙት የቂም-በቀል ፖለቲካ ሁሉንም ነገር ጠላትና ጦርነት አድርጎ ይስልባቸዋል። በፍቅርና ቅንነት ያልከውን፥ ያደረከውን ነገር በሙሉ በጥላቻና ዘረኝነት ሲፈርጁ ይውላሉ። የትግራይ ልሂቃን ህወሓት ከጫነባቸው የአስተሳሰብ ባርነት ነፃ ካልወጡ ገና ጥሩ እና መጥፎን መለየት ይሳናቸዋል።

“የትግራይ ህዝብን ለምን ትጠላለህ?” ሲሉኝ መልሴ “ሲጀመር ‘ተሳስተሃል’ እያለ ‘ትጠላለህ’ ጋር ምን ወሰደህ?” የሚል ጥያቄ አነሳለሁኝ። መቼም የትግራይ ሕዝብን በጥላቻ ስደበድብ፥ ስገድል፥ ሳፈናቅል፥… ወዘተ አይተህም ሆነ ሰምተህ አታውቅም። ያደረኩት ነገር ቢኖር በራሴ አመለካከት ትክክል የመሰለኝ ነገር እናገራለሁ፥ እፅፋለሁ። የገለፅኩት ሃሳብና አመለካከት ስህተት ከሆነ “ተሳስተሃል” እንጂ “ትጠላለህ” አይባልም። በራዲዮ ሆነ በቴሌቪዥን፣ በጋዜጣ ወይም በድረገፅ በተናገርኩና በፃፍኩ ቁጥር “ተሳስተሃል” ብሎ ከማረም ይልቅ “ትጠላለህ” ብሎ የሚፈርጀኝ ሰው ችግሩ ከእኔ ሳይሆን ከራሱ ነው። ስህተቴን በምክንያት ለማስረዳት አቅም ሳይኖራቸው እኔን በጥላቻና ዘረኝነት የሚፈርጁኝ ሰዎች የህወሓትን ውሸትና ጥፋት እንድቀበል የሚሹ ደካሞች ናቸው።

2 thoughts on ““የትግራይ ህዝብን ለምን ትጠላለህ?”፤ “‘ተሳስተሃል’ እያለ ‘ትጠላለህ’ ጋር ምን ወሰደህ?”

  1. … አልሸሹም ዘወር አሉ ! በሀሳብ በአመለካከት የምታምን ከሆነ አሁንም አንተ በተቆፈረልህ ጉድጓድ ገብተህ ለምን ትንደፋደፋለህ ! አንተም ከምትከሳቸው ጋር አንድ ነህ , የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ !!!!…. ከብሔር ከግለሰቦች ጀርባ ላይ ውረድና ሀሳብ አመለካከት ራዕይ ላይ ተንጠልጠል … በሰው ቁሡል እንጨት አትጨምር …. በማር የተለወሰ መርዝ ….

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡