“ጠ/ሚኒስትሩ የቂም-በቀል ሰንሰለትን ሰብረውታል!” ስዩም ተሾመ (ቃለ ምልልስ)

ግዮን፡- በአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወዴት እያመራ ነው ማለት ይቻላል?

ስዩም፡- የዜጎች መብት፣ ነፃነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይረጋገጥ የሚል ጥያቄ ይዞ ነው የተነሣው:: ያ ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ የትጥቅ ትግል ጀምሯል:: ድርጅቱም በአሸባሪነት ተፈርጇል:: አንዳርጋቸው በሽብርተኝነት ተፈርጇል:: በዚሁ አግባብ ነው እንግዲህ ከየመን ተይዞ፣ ታስሮ የሞት ፍርድ የተፈረደበት:: ሕጉ ምን ይላል? ወይም ደግሞ የተፈረደበት ምን ነበር? የሚለው ሳይሆን የአንዳርጋቸው ፅጌ የትግል መሠረታዊ ዓላማና ግብ ምንድነው? የዜጎች መብትና ነፃነት የተከበረበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ይገንባ የሚለው ነውና አንዳርጋቸው ሲታሰር የታሰረው አንድ ግለሰብ ወይም አንድ የፖለቲካ ቡድን መሪ አይደለም፤ የህዝቡ ጥያቄ ነው የታሰረው፤ ዴሞክራሲ ነው የታሰረው፤ ነፃነት ነው የታሰረው:: የህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እስካላገኘ ድረስ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተውን ግጭትና አለመረጋጋት ማስወገድ እንደማይቻል መንግሥት ተገንዝቦ እነዚህን የፖለቲካ መሪዎች የለቀቀበት ሁኔታ ነው ያለው:: ስለዚህ ህዝቡ ነው የተፈታው ማለት እንችላለን::

ግዮን፡- የአንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር መፈታት ጠቅላይ ሚንስትር ዓቢይ አህመድ “የፖለቲካ ምህዳሩን እናሰፋለን፤ በውጪም በሀገር ውስጥም ካሉት ጋራ ተረዳድተን እንሠራለን” ያሉበትን መንገድ ያሳምናል ብለህ ታምናለህ?

ስዩም፡- የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ሲባል ነፃና ገለልተኛ የሆነ የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች እንዲካሄዱ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር፣ ከመንግሥት አመለካከት ነፃ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር እና መሰል ነገሮችን ያካትታል:: ይህ እንዳለ ሆኖ ግን በቅድሚያ የመጀመሪያው ተግባር ከገዢው ፓርቲ የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ወገኖች በሀገሪቱ ላይ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል ሲሆን፣ በዚህ ረገድ የአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት አንዱ ነገር ነው:: ከዚህ አኳያ እነእስክንድር ነጋን፣ እነአንዷለም አራጌን ስትመለከት ተጨባጭ የለውጥ እየመጣ ነው ብለን ማለት እንችላለን:: አንዳርጋቸው ፅጌ እንዳይፈታ የሚፈልግ ወገን እንዳለ ሊሰመርበት ይገባል:: በዋናነት የህወሓት አባላትና ደጋፊ የሆኑ ወገኖች ይሄን ነገር በፅናት የሚቃወሙ ናቸው:: ዝም ብሎ ይህንን ህዝብ ለማስደሰት ብቻ የተወሰነ ውሳኔ ሳይሆን የተለያዩ ነገሮችን ጨምሮ ዲፕሎማቲክ ግንኙነቱን በተለይ የእንግሊዝ ዜጋ መሆኑ ከምግት ውስጥ ገብቶ የተለያዩ ጫናዎች እንደነበሩ ከግንዛቤ ማስገባት አለብን:: ስለዚህ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተወሰደው እርምጃ በእውነቱ ሊበረታታና ሊደነቅ የሚገባ ነው:: የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር ከማስፋት አንፃር ተጨባጭ የሆነ ለውጥ ሊያስገኝ የሚችል ነው::

ግዮን፡- ይህ ነገር ከተጀመረ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ድርድር ይቀጥላሉ ነው የምትለው?

ስዩም፡- አዎ! አሁን የፖለቲካ መሪዎች መፈታታቸው ብቻ አይደለም፤ ማህበረሰቡ በጠቅላላ እየተፈታ እኮ ነው:: ህዝቡም ሀሳቡን፣ ነፃነቱን፣ ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለማስከበር እንዲንቀሳቀስ ሁኔታዎች እየተፈጠሩለት ነው:: መሪዎቹን የምታስረው እኮ ህዝቡ የፖለቲካ ጥያቄ እንዳያነሣብህና የህዝቡን የፖለቲካ ናቅናቄ ለማኮላሸት ነው:: እናም መሪዎችን ስትፈታ ህዝቡን ነው የፈታኸው:: ህዝቡ መብቱን ለማስከበር መንቀሳቀስ ይችላል:: ፍትሐዊ ሕገ መንግሥት እንዲረጋገጥ ይጠይቃል:: ከዚህ አንፃር ስታስበው የፖለቲካ ምህዳሩ እየሰፋ፣ ፍርሃት እየጠፋ ይሄዳል:: ከዚህ አንፃር ላለፉት 27 ዓመታት የኋሊት የነበረውን የፖለቲካ ጉዞ አቁሞ ወደፊት አንድ እርምጃ መራመድ ይቻላል::

ግዮን፡- ብዙ ሰዎች እንደሚሉት መፈታት ብቻ አይደለም፤ ማንኛውም ሰው የታሰረበት የራሱ ዓላማ አለው፤ ቁጭ ብሎ ተደራድሮ ሀገሪቱ ላይ ሰላማዊ ነገር እንዲፈጠር ስለሚፈልግ ነው:: ኢህአዴግ ፈርቻለሁና በሚል አስሮ በመፍታት የማያቆም ከሆነ ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል የሚሉ አሉ፤ ያንተ ሀሳብ ምንድነው?

ስዩም፡- ይሄ በጣም ትክክል ነው፤ አንደኛው ነገር የፖለቲካ መሪዎች የሚፈቱት ሲጀመር መታሰር ስላልነበረባቸው፣ መታሰራቸውም ስህተት ስለነበር ነው:: ስለዚህ ያሰራቸው ማነው ስንል መንግሥት ነው፤ ያሰራቸውም በስህተት ነው:: አሁን መንግሥት እነዚህን ሰዎች በመፍታቱ ከዚህ በፊት የፈጠራቸውን ስህተቶች እያስተካከላቸው ነው:: ሆኖም ግን ይህ የለውጥ መጀመሪያ እንጂ የለውጥ እርምጃ አይደለም:: በተጨባጭ ሥር ነቀል ለውጥ ሊመጣ የሚችለው እነዚህ የፖለቲካ መሪዎች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ ጦማርያን የታሰሩበትን ምክንያት በማወቅ ሲሆን የታሰሩበት ምክንያትም የህዝቦች መብት፣ ነፃነትና ፍትሕ እንዲረጋገጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሕግ የበላይነት እንዲከበር የሚል ነው::

እነዚህ የፖለቲካ መሪዎች የታሰሩት ይህንን ጥያቄ በማንሳታቸው ነው:: አሁን እነዚህ ሰዎች ተፈትተዋል:: ይህ አንድ እርምጃ ነው፤ ስለዚህ የታሰሩበትን ዓላማ ለማሳካትና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ እድል ይፈጥርላቸዋል:: ህዝብም መብቱን ለማስከበር መጠየቅ ይጀምራል:: ስለዚህ የፖለቲካ ንቅናቄው መሽከርከር ይጀምራል ማለት ነው:: የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ካቢኔ ወይም አመራር ለውጥ ያመጣል ብሎ ዳር ቆሞ መጠበቅ ሳይሆን የተፈቱ ጋዜጠኞችም ሥራቸውን ይሥሩ፤ የተፈቱ የፖለቲካ መሪዎችም መተማመንን ይዝሩ፤ የሲቪል ማኅበራትም የሚጠበቅባቸውን ሚና ይወጡ:: ውጪ የቆሙ ሚዲያዎችም ወደሀገር ውስጥ መጥተው ለማህበረሰቡ በማሳወቅ ሚናቸውን ይወጡ:: የኢህአዴግም መንግሥት እንደመንግሥት ያፈረሳቸውን የዴሞክራሲ ተቋማት መልሶ ይሥራ:: ስለዚህ ድርሻው የመንግሥት ብቻ አይደለም፤ የሁላችንም ነው:: ከዚህ በፊት ዴሞክራሲን ለማምጣት የተሣነን መሪዎች ስለታሰሩ ነው፤ አሁን እነዚህ ሰዎች ተፈትተዋል:: ከስደትም እየመጡ ነው ያሉት:: ስለዚህ በፖለቲካ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና ይወጡ:: የዶክተር ዓቢይ አመራርም በተግባር ሊያስተካክላቸው የሚጠበቅበት በዋናነት ያፈረሳቸው የፖለቲካ ተቋማት እንዲሁም ደግሞ አፋኝ የሆኑ አዋጆች አሉ:: የፀረ ሽብር ሕጉ አለ:: የበጎ አድራጎት መመሪያ አለ:: የሚዲያ አዋጅ አለ:: እንዲሁም የደህንነት ተቋም አሠራር አለ፤ ከዚህ አልፎ ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለ:: የሕግ የበላይነት መስፈን አለበት:: ለህዝቡ ተጠቃሚነት መንቀሳቀስ አለባቸው:: በኢኮኖሚው በራሱ እድገቱን በተጨባጭ ማስመዝገብ አለበት:: እነዚህ ነገሮች ይጠበቃሉ:: እነዚህ እንግዲህ በመንግሥት ደረጃ የሚጠበቁ ሥራዎች ሲሆኑ፣ ሌላው የፖለቲካ ማህበረሰብም የሚጠበቅበት ሥራ አለ:: አሁን በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በጋዜጠኞችና በሌሎች እየታየ ያለው ጠባቂነት ነው:: ዳር ቆሞ ይህን ያድርግ፣ ይተው ከማለት በዘለለ በተጨባጭ እያደረጉት ያለ ነገር የለም:: ከአዲስ አበባ ወጥተው በመላው ሀገሪቱ መዋቅራቸውን እየዘረጉ ነወይ? በአደረጃጀታቸው እየሠሩ ነወይ? ስንል ይህ ሁኔታ የለም:: ስለዚህ እኛም የቤት ሥራችንን መሥራት አለብን ብዬ ነው የማምነው::

ግዮን፡- ግንቦት 21/2010 ዓ.ም. ክሳቸው የተቋረጠው የፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና የጃዋር መሃመድ እንዲሁም የኦ ኤም ኤን እና የኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ክስ መነሣትን እንዴት ታየዋለህ?

ስዩም፡- ይህ ደስ የሚል ዜና ነው፤ ወደሀገሪቱ ውስጥም መጥተው ቢሮአቸውን ከፍተው እንዲሠሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል:: ኢሳትም ሆነ ኦ ኤም ኤን ከዚህ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ቢሮአቸውን ከፍተው ነፃና ገለልተኛ የሆነ ዘገባ በቀጥታ ላለማቅረብ ምንም ምክንያት ያላቸው አይመስለኝም:: ከዚህ በኋላ መጥተው የማይሠሩ ከሆነ ከራሳቸው ድክመትና የሚጠበቅባቸውን ግዴታ
ካለመወጣት በዘለለ ሌላ ተጨባጭ ምክንያት ማቅረብ የሚችሉ አይመስለኝም::

ግዮን፡- ይህንን ማመን ይቻላል፤ ኢህአዴግን ላለፉት 27 ዓመታት ጠንቅቀው የሚያውቁት በመሆኑ ጥሪ ስለተደረገ ብቻ ትክክለኛው ነገር ይደረጋል ተብሎ ይታመናል? ቅድመ ሁኔታ መኖር የለበትም?

ስዩም፡- ሁሉም ነገር ተመቻችቶና ተስተካክሎ ባለበት ሁኔታ መጥተን እንኖራለን ብሎ መጠበቅ በፍፁም አግባብነት የለውም:: ምክንያቱም አውቃለሁ፤ ይህ መንግሥት ጨካኝና አፋኝ ነው፤ ከሃዲም ጭምር ነው፤ በተግባርም አይተነዋል:: ውጪ ያለው ማህበረሰብ የራሱን ሚናና አስተዋፅዖ አበርክቷል:: ሆኖም ግን አገሪቱ ውስጥ እኔና አንተ እዚህ ኢህአዴግ ፊት ቆመን ክህደቱንም፣ ዱላውንም፣ መከራውንም እየተቀበልን ኖረናል፤ ስለዚህ ዴሞክራሲው ተረጋግጦ ለመኖር የሚመጣበት ከሆነማ እሱ ሽርሽር ነው:: ይህ ግን ፖለቲካ ነው፤ ፖለቲካ ውስጥ መሥራት የማትችልበት ሁኔታ ብቻ ሲኖር ነው አገር ጥለህ የምትሰደደው:: ልትሠራ የምትችልባት አንዲት ቀዳዳ ከተፈጠረች ያቺን ቀዳዳ በአግባቡ ተጠቅመህ ከህዝቡና ከሀገሪቱ የሚጠበቅብህን ግዴታ መወጣት መቻል አለብህ:: የኢህአዴግ መንግሥት ገና ቃሉን ሊያጥፍ ይችላል ብሎ ዳር ቆሞ ማህበረሰቡን ለተቃውሞ መቀስቀስ
ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም:: በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ዋጋና ተቀባይነት ያሳጣቸዋል:: ከሀገር እንዲሰደዱ ያደረጋቸው መንግሥት ወደሀገራችሁ ኑ ብሏቸዋል:: አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው የቀድሞው የኦነግ አመራሮች ሀገር ውስጥ ገብተዋል:: አሸባሪ ተብሎ የሞት ፍርድ የተፈረደበት አንዳርጋቸው ፅጌ ተፈቷል:: ይህንን በተግባር አይተናል:: ከእስር ቤት
ገብተን ወጥተናል:: ይህ ሂደት እንዳይቀለበስ
ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል የሚጠበቅበትን
መወጣት አለበት:: የኢህአዴግ መንግሥት ቃሉን ያከብራል ብሎ ዳር ቆሞ መጠበቅ በፍፁም ኃላፊነት የጎደለው ነገር ነው::

ግዮን፡- የአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት የማን ተፅዕኖ ነው ትላለህ?

ስዩም፡- ባለፈው እነበቀለ ገርባና እነእስክንድር ነጋ ሲፈቱ ተናግሬያለሁ:: እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር አይደለም አደባባይ የወጡት:: የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር ብለው አይደለም ከዚህ ጨቋኝ መንግሥት ጋራ ፊት ለፊት የተጋፈጡት:: እነዚህ ሰዎች የዜጎች መብትና ነፃነት ይከበር ብለው አደባባይ ወጥተው ነው መሥዋእት የከፈሉት፤ ለእስርና ለስደት፣ ለመከራም የተዳረጉት:: ጥያቄው የእነሱ የግል ጉዳይ አይደለም፤ የህዝብ ጉዳይ ነው፤ የህዝብ ጥያቄ ነው፤ እነሱ ሲፈቱ ህዝቡ ነው የሚፈታው:: አንዳርጋቸው ፅጌ የፖለቲካ
መሪ ነው፤ ያነሳውም የህዝብ ጥያቄ ነው፤ የተፈታውም የህዝብ መሪ በመሆኑ በህዝብ ጥያቄ እንጂ በኢህአዴግ መንግሥት ፈቃድና ችሮታ፣ አሊያም በይቅርታ ወይም በሌላ ነገር አይደለም:: በህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በተፈጠረ ጫናና ግዴታ አስገዳጅ ሁኔታ ስለሆነ ያስፈታው ህዝቡ ነው:: አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ በስደት ላይ ያሉት የፖለቲካ መሪዎች ሁሉም ወደዚህ ደረጃ አደረሱት:: አንዳርጋቸው ፅጌን መፍታት ብቻ አይደለም ዶ/ር ዓቢይን ጨምሮ አዲሱ የመንግሥት የፖለቲካ ቡድን
በአጠቃላይ ዛሬ የአመራርነት ሚና የያዘው በህዝቡ አመፅ፣ በህዝቡ ተቃውሞ፣ በህዝቡ መሥዋእትነት ነው::

ግዮን፡- ጠቅላይ ሚንስትሩ አቶ አንዳርጋቸውን በቤተ መንግሥት መጋበዛቸውን እንዴት ትረዳዋለህ

ስዩም፡- አንዳርጋቸው እንደሚታወቀው የሞት ፍርድ የሚጠብቅ ግለሰብ ስለነበር ይቅርታ ከማግኘቱ በላይ ቤተ መንግሥት ተጠርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማግኘትና መወያየት መቻሉ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ለዘመናት እየተከታተለ ሲመጣ የነበረውን የቂም በቀል ሰንሰለት ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሰበረው ይመስለኛል:: ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ ሥርዓቱን የተቃወሙ ሰዎች እነ መንግሥቱ ንዋይ፤ እነ በላይ ዘለቀ፤ እነ ጀነራል ደምሴ ቡልቱ፤ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ እነፕሮፌሰር አስራትና ሌሎችም የሞቱት እንዲሁም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌና ዶ/ር ብርሃኑ ለእስርና ለስደት የተዳረጉበት ምክንያት መንግሥትን በመቃወማቸውና የተለየ የፖለቲካ አቋምና አመለካከት በማራመዳቸው ነው:: ካለፉት ሦስት ሥርዓቶች በጣም የተለየ አካሄድ ነው አሁን ያለው:: ይህ ደግሞ ለሀገሪቱ ትልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ ይኖረዋል::

ግዮን፡- አንዳርጋቸው ጽጌ በምን ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር እንደተወያዩ ሊገልጹ አልፈለጉም፤ ለምን ይመስልሃል?

ስዩም፡- በመጀመሪያ ደረጃ አንዳርጋቸው ፅጌ ማንን ወክሎ ነው የሚናገረው? የግንቦት ሠባት መሥራችና መሪ ነው:: ግንቦት ሠባት ደግሞ አሁን በሀገሪቱ ተግባር ላይ ባለው ሕግ መሠረት በአሸባሪነት የተፈረጀ ነው:: የግንቦት ሠባትን መሪ ቤተ መንግሥት ቁጭ አድርገህ አናግረህ፤ በተወያየበት ጉዳይ ላይ ሀሳብ፣ አስተያየት፣ ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጥ መጠበቅ የለብንም:: ይሄ የለውጥና የትብብር ምልክት ነው::


ይህ ቃለ ምልልስ በመጀመሪያ ለህትመት የበቃው ጊዮን መፅሄት የአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታትን አስመልክቶ ባወጣው “ልዩ እተም” ላይ ነው!