ባድመ እና የአልጀርሱ ስምምነት፡ “እውን ህዝበ ውሳኔ ያስፈልጋል?”

በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን አድርጎ ለሀገራችን እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ትልልቅ ውሳኔዎችን አሳልፎ ወቷል፡፡ ከእነዚህ ውሳኔዎች አንዱ የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመቀበል የተደረሰው ውሳኔ ነው፡፡

በትክክል ውሳኔ መስጠት ያለበት ማን ነው?

ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘባት ቀን አንስቶ በአገራችን መንግስት፣ ኢህአዴግ፣ ስራ አስፈጻሚው፣ ማሀከላዊ ኮሚቴ የሚባሉት አካላት የመወሰን ጥግና ልዩነት በትክክል ማስቀመጥና ማወቅ ከባድ ነው፡፡ ያለፉት 27 አመታት የሀገራችን ታሪክ እንደሚያሳየን የስራ አስፈጻሚ ወይም የመሀከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ የመንግስትና የኢህአዴግ ውሳኔ ናቸው፡፡ ይህ ከትህነግ የበረሃ ልምድ የተወረሰው ይህ አስተሳሰብ ለ27 አመታት የሄድንበት የፖለቲካችን ባህል ነው፡፡ በዚህ ኢደት የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት እንዲሁም የአልጀርሱም ጉዳይ ጨምሮ ብዙ ውሳኔዎች ተወስነዋል፡፡ በቅርቡም የተወሰነው ውሳኔ እንዲሁ የሆነና ያለፈው ስራ አስፈጻሚ የወሰነውን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የተሞከረ ነው፡፡

የአልጀርሱን ስምምነት በተመለከተ የዶክተር አብይ የሚመሩት መንግሰትም ሆነ የሚመሩት ግንባር ጉዳዩን ለውይይት ማቅረብ አይጠበቅበትም ምክንያቱም ጉዳዩ የተበላ እቁብ ነውና፡፡ ለውሳኔውም አላፊነቱም አይወስድም፡፡ ነገር ግን ለውሳኔው በኃላፊነት መጠየቅም ካለበት በማንኛውም አግባብ የአሁኑ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሳይሆን መጠየቅ ያለበት እንደ ተራ ነገር ሀገር ቆርሶ ለመስጠት ተስማምቶ የመጣውና በሟቹ ጠቅላይ ሚኒስተር ይመራ የነበረው ስራ አስፈጻሚና እራሱ ትህነግ ናቸው፡፡

የአልጀርሱ ስምምነትና

ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ጦርነት ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የአለማችን ታሪክ እንደሚያሳየን ህዝበ ውሳኔ ተሰቶባቸው ወደ ጦርነት የተገባበት ወቅት የለም፡፡ ልክ እንደዚሁ ጦርነቶች በአንድ ወገን ድል አድራጊነት ሲጠናቀቁም ሆነ አሸናፊ በሚጠፋበት ሰአት ጦርነቱን ለማቋረጥ ህዝበ ውሳኔ የሚባል ነገር ተደርጎ አይታወቅም፡፡ ጦርነትን የመጀመርም ሆነ ጦርነትን አቁሞ ወደ ድርድር የመግባትን ውሳኔ የሚሰጠው በመንግስት ነው (በተለይ በስራ አስፈጻሚውና ፓርላማው)፡፡ ነገር ግን ህዝብ ወይም ማንኛውም አካል ተጽህኖ አያሳድርም ማለት አይደለም፡፡

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት በግልጽ እንኳን ምክንያቱ በማይታወቅበት (በትህነግና ሻዐቢያ የቂል እልህ መጋባት) ሁኔታ ጦርነት ተጀምሮ ብዙ ሺ ወጣቶች ከሁለቱም ወገን በከንቱ ደማቸውን አፍስሰዋል፡፡ በኢትዮጲያ በኩል የጦርነቱ ፈላጭ ቆራጭ የነበረውና በዘመኑ ባለ ጊዜ የነበረው ትህነግ ጦርነት አስጀመረ፣ ቀጥሎም ብዙ ወጣቶችና ሀብት ወደመ ከዚያም ጦርነቱ ይብቃና ወደ ስምምነት እንግባ ተባለ፡፡

ያለ ማንም ህዝበ ውሳኔ በትህነግ አዝማችነት የተፈረመው የአልጀርሱ ስምምነት ባህርይ እንደሚያሳየው በሁለቱ ሀገራት ድንበርን በተመለከተ እንዲዳኝ የሚቋቋመውን ኮምሽን ውሳኔ ሀገራቱ ያለ ምንም ይግባኝ ለመቀበል ቃል ገብተዋል፡፡ ይህንንም በፍርማቸው አረጋግጠዋል፡፡

የአለም አቀፍ ህግ በአንድ ሀገር ካለ ህግ በእጅጉ ይለያል፡፡ ሀገራት ማንኛውንም የአለም ህግም ሆነ ስምምነት በበጎ ፈቃድ የመፈጸም እንጂ ሌላ አሰገዳጅ አካል (ልክ ሀገር ውስጥ እንዳለ ፖሊስ ) የለም ፡፡ ስለዚህ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ማንኛውም ሀገር ለገባው ቃል መታመንና ስምምነቶችንም የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ በዚህ መሰረት ባድመን ለኤርትራ የሚሰጠውን ውሳኔ ኢትዮጲያ አስቀድማ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ በኩል ፈርማለች ስለዚህ የማክበርም ግዴታ አለባት፡፡ በተጨማሪም ውሳኔው ከተሰጠ በኃላ ሀገራቱ ውሳኔውን ለማስፈጸም ምንም አይነት ህዝበ ውሳኔም ሆነ የፓርላማ ውይይት አያስፈልጋቸውም ምክንያቱም የአለም አቀፍ ህግ እንደዛ እንዲደረግ ስለማይፈቅድ፡፡

የህዝቡስ ፍላጎት

በደንበር አካባቢ ያሉት ህዝቦችን ፍላጎትና የሀገራቱን ፍላጎት ለማጣጣም ከሁለቱም ሀገራት መንግስትታት ብልሀት የተሞላበት ድርድር ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ሰአት በኢትዮጲያ ግዛት ውስጥ ያሉና በኢደት ስምምነቱን ተከትሎ የዜግነት ለውጥ ሊያደርጉ የሚችሉ ህዝቦችን የተለያዩ ፍላጊቶችና መብቶች በጥብቅ ማጥናት፣ ወዲህና ወዲያ ያሉትን ህዝቦች ትስስር በምን መልኩ ማስቀጠል ይቻላል በሚሉና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በተመሳሳይ መልኩ ችግሮችን የፈቱትን የአውሮፓ ሀገራትን ልምድ በመውሰድ የህዝቡን ፍላጎት መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡

One thought on “ባድመ እና የአልጀርሱ ስምምነት፡ “እውን ህዝበ ውሳኔ ያስፈልጋል?”

  1. በትክክል ተገልጾኣል ። ኢህኣዴግ የወሰደው ኣቋም ወደ መፍትሔው ሊወስደን የሚችል መንገድ ነው ። ኣለዚያ : በህዝበኝነት መንፈስ ኣካኪ ዘራፍ ብንል ከችግሩ ኣዙሪት መውጣት ኣንችልም ።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡