አምስት ጥያቄ አለኝ፦ ይድረስ ለቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ

መቼም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሰው “ጤናህ እንደምን አለህ? እንዴት ሰንብተሃል? ኑሮ እንዴት ይዞሃል?… ወዘተ የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ አያስፈልግም። ለነገሩ እንዲህ ያሉ የሰላምታ ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ዓይነት ጥያቄ መጠየቅ መጠየቅ ተገቢ አይመስለኝም። ሆኖም ግን፣ ከኢትዮጵያና ኤርትራ ጋር በተያያዘ የሚነሱቱን ጥያቄዎች ከእርስዎ በስተቀር በተገቢ ሁኔታ የሚመልስ ሰው እስካሁን አላገኘሁም። ምክንያቱም ጥያቄዎቹ በአብዛኛው ከእርስዎ የፖለቲካ አመለካከትና ውሳኔ ጋር በቀጥታ የተያያዙ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ከኢትዮጲያና ኤርትራ ጋር በተያያዘ ያሳለፏቸው አንዳንድ ውሳኔዎች ከእርስዎ በስተቀር ማንም ሊረዳቸው ሆነ ምላሽ ሊሰጥባቸው አይችልም። በመሆኑም ትክክለኛ ምላሽ የማገኘው ከእርስዎ ብቻ እንደሆነ በማሰብ የሚከተለቱት አምስት ጥያቄዎች አቀርባለሁ፦

1ኛ፡- የአሰብ ወደብ የአዳል (አፋር) አውራጃ አካል እንደነበረ እያወቁ፤ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ወደብ-አልባ ልትሆን እንደማይገባ አበክረው እየተናገሩ፤ ኤርትራ ለወጪና ገቢ ንግድ የምትጠቀመው የምፅዋ ወደብን እንጂ አሰብን እንዳልሆነ እያወቁ፣ የሻዕቢያ መንግስት አሰብን የሚፈልገው የኢትዮጵያን የውጪና ገቢ ንግድ ለመቆጣጠር እንደሆነ መገንዘብ እየቻሉ፣ … ወዘተ የአሰብ ወደብ ለኤርትራ እንዲሰጥ የፈለጉበት፥ የፈቀዱበት ምክንያት ምንድነው? ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ከኢኮኖሚ ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ የነበራትን የፖለቲካና ወታደራዊ የበላይነት እንደሚያሳጣት እያወቁ “የወደብ ጥያቄ መነሳት የለበትም!” የሚል አቋም ሲያራምዱ የነበረበት ምክንያት ምንድነው?

2ኛ፡- የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ወደብ-አልባ ማድረግ የፈለገበት መሰረታዊ ምክንያት የሀገሪቱን የወጪና ገቢ ንግድ በበላይነት በመቆጣጠር ያልተገባ ጥቅም ለማጋበስ የነበረ ሲሆን በሀገራችን ላይ ወረራ የፈፀመው በተጠቀሰው መንገድ ሲያገኝ የነበረው ጥቅም ስለተቋረጠበት ወይም ስለተነካበት እንደሆነ ይታወሳል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ግጭት ከተፈጠረ የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ እንደሚስተጓጎል ሁሉ ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚላኩት የግብርና ምርት ውጤቶች ይቋረጣሉ። ኤርትራ በግብርና ምርት ራሷን ለመቻል የሚያስችላት የእርሻ መሬት እንደሌላት ይታወቃል። የኤርትራ መንግስት ወረራ ከፈፀመባቸው የጦር ግንባሮች በተለየ ባድመ ላይ ልዩ ትኩረት ያደረገበት ምክንያት በአከባቢው ሰፋፊ እርሻ በመጀመር ሀገሪቱ በግብርና ምርት ራሷን ለማስቻል እንደሆነ ግልፅ ነው። ስለዚህ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ወረራ የፈፀመው የኢኮኖሚ ብዝበዛውን ለማስቀጠል ወይም የባድመን መሬት በኃይል ለመቀማት እንደሆነ እየታወቀ እርስዎ ለምንና እንዴት “ከኤርትራ ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት የለብንም?” የሚል አቋም ሊይዙ ቻሉ?

3ኛ፡- ከሰው ሕይወትና ንብረት አንፃር ከፍተኛ የሆነ ዋጋ ቢያስከፍላትም ኢትዮጵያ ጦርነቱን በድል ማጠናቀቋ ይታወሳል። የኤርትራ ጦር ከተሸነፈ በኋላ በወረራ የተያዙትን አከባቢዎች ከማስለቀቅ ባለፈ ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ያላቸውን የኤርትራ መሬቶች፣ በተለይ ደግሞ የምፅዋና አሰብ ወደቦችን በኃይል መቆጣጠር ያስፈልጋል። የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈፀመው ሀገሪቱን ወደብ-አልባ በማድረግ ቀድሞ የነበረውን የኢኮኖሚ ብዝበዛ ለማስቀጠል፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ለእርሻ የሚሆን ለም መሬት ከኢትዮጵያ በኃይል ለመቀማት ስለሆነ፤ አንደኛ፡- የኤርትራ መንግስት በወረራ በያዛቸው ቦታዎች ላይ የይገባኛል ጥያቄ እንዳያነሳ ለማድረግ ስትራቴጂካዊ የሆኑ ቦታዎችን ይዞ መደራደር ያስፈልጋል፣ ሁለተኛ፡- የኢትዮጵያ ጦር ሁለቱንም የኤርትራ የባህር በሮች በኃይል በመያዝና በመደራደር የአሰብ ወደብን በማስመለስ ራሷን ከኢኮኖሚ ብዝበዛ መከላከል አለባት። ይሁን እንጂ፣ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በእርስዎ ትዕዛዝ የኢትዮጵያ ጦር የተቆጣጠራቸውን የኤርትራ መሬቶች በአስቸኳይ ለቅቆ እንዲወጣ ተደርጓል። ለምን ይህን ትዕዛዝ እንዳስተላለፉ ሊነግሩኝ ይችላሉ?

4ኛ፡- በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 55(12) መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “የሕግ አስፈፃሚው አካል የተዋዋላቸውን ዓለም-አቀፍ ስምምነቶች ያፀድቃል” ይላል። በዚህ መሰረት፣ ምክር ቤቱ ሕግ አስፈፃሚው አካል የተዋዋላቸው ዓለም-አቀፍ ስምምነቶች በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 86 ላይ ከተደነገጉት “የውጪ ግንኙነት መርሆች” አንፃር መርምሮ የሀገሪቱን ጥቅምና ሉዓላዊነትን የማይፃረሩ ከሆነ ተቀብሎ ያፀድቃል። ነገር ግን፣ ኢትዮጲያና ኤርትራ አልጄርስ ላይ የሰላም ስምምነት ከመፈራረማቸው አራት ቀናት በፊት የስምምነቱ ማፅደቂያ አዋጅ ቁጥር 225/2000 በኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ ተደርጓል። አንደኛ፡- የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ያልፈረሙበትና የስምምነቱ ይዘት በግልፅ ተለይቶ በማይታወቅበት ሁኔታ ምክር ቤቱ በምን ላይ ተወያይቶ ነው የማፅደቂያ አዋጅ ያወጣው? ሁለተኛ፡- የአልጄርስ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተነሳውን የድንበር ይገባኛል ጥያቄ የሚመለከት የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ኮሚሽን እንዲቋቋም የሚለው አንዱ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት የድንበር ኮሚሽኑ የሚያስተላልፈው ውሳኔ የመጨረሻና ይግባኝ የሌለው መሆኑ ይታወቃል። በሁለት ሀገራት መካከል የተነሳን የይገባኛል ጥያቄ በመመልከት የሚሰጥ ውሳኔ እንዴት ይግባኝ የሌለው እንዲሆን ይደረጋል?

5ኛ፡- በኢትዮጲያና ኤርትራ መካከል የነበረው የድንበር ይገባኛል ጥያቄ በዋናነት ያተኮረው በባድመ ላይ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ደግሞ የኤርትራ መንግስት ወረራ ከፈፀመበት ምክንያት ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው። በመሆኑም የኢትዮጲያ መንግስት ባድመ የኢትዮጵያ መሆኗን የሚያረጋግጡ አሳማኝ ማስረጃዎች ማቅረብ ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ በአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የተፈረሙ የድንበር ስምምነቶች ተመራጭ ናቸው። ምክንያቱም፣ አፄ ሚኒሊክ በ1900፣ በ1902 እና በ1908 ዓ.ም ከአውሮፓ ቅኝ-ገዢዎች ጋር የተፈራረሟቸው የድንበር ስምምነቶች፤ አንደኛ፡- ባድመ የኤርትራ ይሁን የኢትዮጵያ ስለመሆኑ በግልፅ የማያሳዩ ናቸው፣ ሁለተኛ፡- አፄ ሚኒሊክ በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የፈረሟቸው ናቸው፣ ሦስተኛ፡-አፄ ኃይለስላሴ ከተባበሩት መንግስታትና ከኢጣሊያን መንግስት ጋር በፈረሟቸው ስምምነቶች የተሻሩ ናቸው፣ አራተኛ፡- ከአፄ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በፊት ባድመ ሰው አልባ ወይም ምድረ በዳ ስለነበረ የሰው ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፣ አምስተኛ፡- የባድመ ከተማ የተመሰረተችው በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን በራስ ስዩም መንገሻ ድጋፍ እንደሆነ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል። ከእነዚህ በተቃራኒ የእርስዎ መንግስት በድንበር የይገባኛል ጥያቄው ላይ በ1900፣ በ1902 እና በ1908 ዓ.ም በአፄ ሚኒሊክ የተፈረሙትን የድንበር ስምምነቶች በማስረጃነት ያቀረበበት ምክንያት ምንድነው? ሌላው ቢቀር፣ ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ እንኳን የባድመና አከባቢዋ ነዋሪዎች በ1987 ዓ.ም በተካሄደው ሀገራዊ ሕዝብና ቤት ቆጠራ በኢትዮጵያ ስር የተቆጠሩ እንደመሆናቸው የነዋሪዎቹን ስም ዝርዝር፣ እንዲሁም በተመሳሳይ አመት በተካሄደው ሀገራዊ ምርጫ እንደመሳተፋቸው የመራጮች ስም ዝርዝርን ለድንበር ኮሚሽኑ ለምና እና እንዴት በማስረጃነት ሳተቀርቡ ቀራችሁ?

አመሰግናለሁ!

4 thoughts on “አምስት ጥያቄ አለኝ፦ ይድረስ ለቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ

  1. The late pm has never been for Ethiopia his goal was To make Eritrea strong nation on the cost of Ethiopian resources and join them when he accomplished his mission but death takes him over . It’s himself who suggested to Isayas to invade Badime when the Tigray nationalists block the border for Eritrea to pay us they wishes to make Eartrea strong nation

    Liked by 1 person

  2. ስዩሜ ኢሳያስ እኮ ስላለ ይነግረናል ያወሩትን ሁሉ ግን አበበ ገላው ኢትዮጵያ ቢገባ ይነሳ ነበር ያው ደንግጦ ካልጠፋው፡፡

    Liked by 1 person

  3. ሠዉ ጥራ ቢሉት ራሱ መጣ ይባላል። ይህንን የክፋት ጎሬ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት፣ ለጥፋት የመጣ ሠዉ፣ የሥነ ልቦና ምሁራን ምን እንደምሉ ባላዉቅም የአእምሮ በሽተኛ የሆነ ሠዉ ነዉ። እና ሆን ብሎ time bomb ያስቀጠን ምን ተብሎ ይጠየቃል? እንደፈረደብን መላ መሻት ነዉ ተመካክረን።

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡