ከሰሞኑ ግጭትና አለመረጋጋት በስተጀርባ የህወሓት እጅ አለበት!

አንዳንድ ግዜ በጣም ግራ የሚያጋቡ ፖለቲካዊ ክስተቶች ይከሰታሉ። ፍፁም ያልተጠበቁ በመሆናቸው የተከሰቱበትን ምክንያትና የሚያስከትሉትን አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ በቀላሉ መገመት አስቸጋሪ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ፖለቲካዊ ክስተቶችን መንስዔና ውጤት ለመረዳት ዝርዝር መረጃዎችን ከማሰባሰብና በተጨማሪ ከመሰረታዊ የፖለቲካ መርህ አንፃር መመልከት ያስፈልጋል። ለምሳሌ ባለፉት ጥቂት ቀናት በደቡብ ክልል ዲላ፣ ሐዋሳ፥ ወልቂጤ፥… ወዘተ በመሳሰሉ ከተሞች ያልተጠበቀ ግጭትና አለመረጋጋት ተከስቷል።

አብዛኞቻችን ከእነዚህ ግጭቶች በስተጀርባ የማን እጅ እንዳለና ዓላማው ምን እንደሆነ ከግምትና ጥርጣሬ በዘለለ ተጨባጭ ማስረጃ የለንም። ምክንያቱም በዚህ መልኩ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርስ አካል ሥራና ዓላማውን በግልፅ አስቀምጦ አይንቀሳቀስም። በመሆኑም ግጭትና አለመረጋጋት እንዲቀሰቀስ የሚያደርግበት ሂደትና ዓላማ በግልፅ ለመረዳት ዝርዝር መረጃዎችን ከማሰባሰብ በተጨማሪ በመሰረታዊ የፖለቲካ መርህ ላይ የተመሰረተ ትንታኔ ያስፈልጋል።

በዚህ መሰረት ሰሞኑን በዲላ፥ ሐዋሳ፥ ወልቂጤና በመሳሰሉት የደቡብ ክልል ከተሞች ግጭትና አለመረጋጋት የተቀሰቀሰበት መሰረታዊ ምክንያት መረዳት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ በተጠቀሱት ከተሞች ግጭትና አለመረጋጋት የተቀሰቀሰው በዋናነት ቦምብ በማፈንዳት እና የብሔር ግጭት በመቀስቀስ ነው። ስለዚህ የግጭቱ መንስዔ ብቻ ሳይሆን ዓላማውም በዜጎች ላይ ሽብርና ፍርሃት መፍጠር ነው።

ታዲያ በዜጎች ላይ ሽብርና ፍርሃት የሚፈጥረው ምን ዓይነት የፖለቲካ ቡድን ነው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በፖለቲካ ሳይንስ ዘርፍ ግንባር ቀደም የሆነውን “Politics” የሚለውን የአርስቶትል መፅሃፍ ዋቢ እናድርግ። እንደ አርስቶትል አገላለፅ፣ የሽብርና ፍርሃትን መጀመር የሚወስነው ተራ ዜጋ (ordinary man) ሳይሆን የመንግስት ባለስልጣን ነው። በዜጎች ላይ ሽብርና ፍርሃት በመፍጠር ፖለቲካዊ ትርፍ የሚያገኙ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ያሉ ባለስልጣናት ናቸው?

እንደ አርስቶትል አገላለፅ፣ ግጭትና ሁከት በመቀስቀስ በዜጎች ላይ ሽብርና ፍርሃት የሚፈጥሩ ባለስልጣናት፤ አንደኛ- ለረጅም አመታት የቆዩበትን ቦታ ላለመልቀቅ የሚታገሉ የስልጣንና የጥቅም ሱሰኞች፣ ሁለተኛ፡- በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት ያጣውን ሕገ-መንግስት ሕዝብን በማስፈራራት ለማስከበር የሚንቀሳቀሱ ባለስልጣናት ናቸው፡-

“…it is not easy for a person to do any great harm when his tenure of office is short, whereas long possession begets tyranny in oligarchies and democracies. For the aspirants to tyranny are either the principal men of the state, who in democracies are demagogues and in oligarchies members of ruling houses, or those who hold great offices, and have a long tenure of them.
…Constitutions are preserved when their destroyers are at a distance, and sometimes also because they are near, for the fear of them makes the government keep in hand the constitution. Wherefore the ruler who has a care of the constitution should invent terrors, and bring distant dangers near, in order that the citizens may be on their guard,… No ordinary man can discern the beginning of evil, but only the true statesman.” Source: Politics – Aristotle, Tran. by Jowett, B. BOOK_5|8 VIII, Page 108 – 109

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለረጅም ግዜ በስልጣን ላይ በመቆየታቸው ምክንያት በከፍተኛ የሞራል ዝቅጠት ውስጥ የወደቁት፣ በዚህም ሕግና ስርዓትን እንዲያስከብሩ የተሰጣቸውን ስልጣን ለሌብነትና የኮንትሮባንድ የሚያውሉት፣ እንዲሁም የዴሞክራሲያዊ መብትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ የሚያነሱ ዜጎችን በወታደራዊ ጉልበት የሚያዳፍኑት፣ በዚህም ፍርሃትና ሽብር በመፍጠር ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ለማስከበርና ስልጣናቸውን ለማራዘም ጥረት የሚያደርጉት ህወሓትና ህወሓቶች አይደሉምን?

በአጠቃላይ ሰሞኑን በደቡብ ክልልና ሐረሪ፣ ከዚያ በፊት ደግሞ በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ፥ ኦሮሚያ፥ አፋር፥…ወዘተ ግጭትና አለመረጋጋት የሚቀሰቀሰው በህወሓት ባለስልጣናትና ተላላኪዎቻቸው ነው። ምክንያቱም፣ አንደኛ፡- በዜጎች ላይ ሽብርና ፍርሃት በመፍጠር የፖለቲካ ትርፍ የሚያገኙት ህወሓቶችና የእነሱ ተላላኪዎች ብቻ ናቸው። ሁለተኛ፡- ላለፉት 27 አመት የተዘረጋው መንግስታዊ ስርዓት ሆነ የህወሓት ባለስልጣናት ያላቸው ተቀባይነት ከሕዝብ ፍቃድና ምርጫ ይልቅ በወታደራዊ ጉልበትና የበላይነት ላይ የተመሰረተ ነው። በመሆኑም በዜጎች ላይ ሽብርና ፍርሃት በመፍጠር ካልሆነ በስተቀር ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ከዚህ አንፃር በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ለሚቀሰቀሱት ግጭቶችና አለመረጋጋቶች የህወሓቶች እጅ አለበት። በተለይ ከትላንት ጀምሮ ከወልቂጤና ሐዋሳ የሚመጡት መረጃዎች ይህንን የሚያረጋግጡ ናቸው።

One thought on “ከሰሞኑ ግጭትና አለመረጋጋት በስተጀርባ የህወሓት እጅ አለበት!

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡