የጥላቻ ፖለቲካ ባህላችን መቀየር አለበት! (በድሉ ዋቅጅራ)

የጥላቻ ፖለቲካ ስር አጎንቁሎ፣ መሬት ይዞ መጽደቅ የጀመረው በደርግ አገዛዝ ዘመን ነው፡፡ የዘመነ ደርግ ፖለቲካ የአንድ እናት፣ የአንድ ሀገር ልጆች ወገን ለይተው የተገዳደሉበት የጭካኔና የጥላቻ ፖለቲካ ነበር፡፡ ደርግ የተካው የኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ጥላቻው አብቦ አፍርቷል፡፡ . . . . ጥላቻ የማሰብን ሀይል ይሰልባል፤ ለተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታችን እንድንታወር ያደርጋል፡፡ ጥላቻ ከመረዘው ህሊና የሚመነጩ ተግባራትን በጤነኛ ተጠየቃዊ መንገድ ለመረዳት አዳጋች ነው፡፡
.
በጥላቻ የተመረዘ ዘመንና ትውልድ ዜጎች ለፍትህና ለነጻነት የሚከፍሉትን ዋጋ ሳይቀር አሳንሶ የጥላቻ ሰለባ ያደርጋል፡፡ . . . የአንድ ሀገር ዜጎች ሆነን፣ ከጎሳ ዣንጥላ በላይ ለማየት አለመፍቀድ የጥላቻ ፖለቲካ ፍሬ ነው፡፡ . . . ሚዛናዊ ሆነን ማሰብ አልቻልንም፡፡ የጠላነውን የወደደ ጠላታችን፣ የጠላነውን የጠላ ወዳጃችን ነው፡፡ . . . ከብሄራችን ውጭ ጀግናን ለማንገስ የጥላቻ ፖለቲካችን አውሮናል፡፡
.
እዚህ ላይ ጥያቄዬ፣ ‹‹ለፍትህና ለነጻነት መታገል፣ መታሰር፣ መሞት ሽልማቱ ምንድነው?›› የሚለው ነው፡፡ . . . እኛ ‹‹ለፍትህና ለነጻነት – ለህዝብ የታገሉትን›› ከዜግነት ልእልና ጎትተን፣ የአንድ ብሄረሰብ ጀግና እንዲሆኑ፣ በቁሳ ቁስ እንደልላቸዋለን፡፡ የእነዚህ ሰዎች እውነተኛ ሽልማት የሚሆነው የፍትህና የዲሞክራሲያዊ ስርአት መስፈን ብቻ መሆኑን ረስተን እያስረሳናቸው ነው፡፡ . . . . ተፈናቃይ ወገኖቻችን በየሜዳውና በየደጀሰላሙ ተበትነው፣ የምግብና የመጠጥ ውሀ ችግር እየተሰቃዩ፣ ለህዝብ እንታገላለን ብለን እየፎከርን፣ በሚለየን ብሮች የቅንጦት መኪና ለግለሰቦች መሸለም፣ ‹‹የጥላቻ ፖለቲካችን ረቂቅ ፍሬ ሰለባዎች ለመሆናችን ማረጋገጫ ነው›› ከማለት ውጭ ምንም ተጠየቃዊ ምክንያት ላገኝለት አልቻልኩም፡፡ . . . . በመሆኑን ቆም ብለን እናስብ እላለሁ! ገዚዎቻችን በቅብብሎሽ ካሰረጹብን የጥላቻ ፖለቲካ ፍሬ ለመላቀቅ ካልጣርን የምንከፍለው ዋጋ ቀላል አይሆንም፡፡

ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ (መምህርና ደራሲ)

ምንጭ፦ Bedilu Wakjira Facebook Page

One thought on “የጥላቻ ፖለቲካ ባህላችን መቀየር አለበት! (በድሉ ዋቅጅራ)

  1. You said freedom is human right.and you and Hitler friend gudu are killing tigrigna,afar, snnprs,gambelas,other people’s and nationalities like your predecessor derg.I think you are young and married I don’t think and expect that history to repeat it self after 40 years.
    God bless great ethiopia

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡