የደቡብ ክልል የፌዴራል መዋቅር፡ የህወሃት ቁማርና ቀመር

በኢትዮጲያ የፌዴራል ስርአት ትልቁ አጨቃጫቂ ጉዳይ የደቡብ ብ/ብ/ህ/ክልል ጉዳይ ነው፡፡ የደ/ብ/ብ/ህ ክልል ከአጠቃላይ በሀገሪቱ ከሚገኙ 80 በላይ ብሔረሰቦች ከ70 ፐርሰንት በላይ የሚሆኑ ብሔረሰቦችን የያዘ ክልል ነው፡፡ የክልሉን አወቃቀር በተመለከተ ኢህአዴግ ላለፉት አመታት አጥጋቢ ምክንያት መስጠት አቅቶት በፕሮፖጋንዳ ብቻ የታጠረ መልስ ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ዶ/ር መራራ ጉዲና ‘’Ethiopia competing ethnic nationalism and the quest for democracy’’ በሚለው ጥናታዊ ስራቸው የደቡብ ክልል በቋንቋ፣ በባህልና በማንነት የሚለያዩ ህዝቦችን ይዞ የተዋቀረው በኢህአዴግ/ ህወሃት ፍላጎትና ጥቅም ሲሆን ይህም የሆነው ለኦሮሞ እና ለአማራ ህዝቦች ተመጣጣኝ ሃይል ለማበጀት ነው በማለት ይገልጻሉ፡፡ ህወሃት የሚወክለው ህዝብ ኦህዴድ እና ብአዴን ከሚወክሉት ህዝብ ብዛት ጋር ሲነጻጸር እጅጉን አነስተኛ ነው ስለዚህ ለሁለቱ ድርጅቶች ተመጣጣኝ ሃይልን ለመፍጠር ህወሃት ከዚያ በፊት በአምስት ክፍለ ሀገር የተከፋፈሉትን 56 ብሔረሰቦችን በአንድ በማምጣት ለሁሉቱ ድርጅቶች ተመጣጣኝ የሆነና በህወሃት በቀላሉ ሊሽከረከር የሚችል ሃይል በመፍጠር የደ/ብ/ብ/ህ ክልል ተዋቀረ፡፡

ደብብ ክልል ውስጥ ባሉ ህዝቦች መካከል ካለው ልዩነትና መሪ ድርጅቱ ደኢህዴን ውስጥ ባሉ አመራሮች ወጥ የሆነ አቋምና ፍላጎት አለመኖር ምክንያት ህወሃት ይህንን ቀመር ላለፉት 27 አመታ ስትጠቀምበትና ውጤታማም ሆናበት ቆይታለች፡፡

የክልል ጥያቄ

የደቡብ ክልል የተፈጠረው ከኢህአዴግ በፊት አምስት ክፍለ ሀገር የነበሩትን በአንድ በማምጣት ነበር፡፡ ክልሉ ሲዋቀር በአጠቃላይ የክልልሉ ነዋሪ ብዛት 14 ሚሊዮን ነበር፡፡ አሁን ግን የህዝቡ ቁጥር ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሯል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ህዝቡ ማንነትን በተመለከተ ያለው አመለካከትና የፖለቲካ ህውቀት እንደ ድሮው አይደለም፡፡ በክልሉ ባሉ የፖለቲካ ኢሊቶቹ መካከል በየወቅቱ የሚታዩት የፍላጎትና የጥቅም አለመጣጣምና በሀገሪቱ እየታየ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ተደምሮበት የደቡብ ክልልን የፌዴራል መዋቅር በህወሃት ፎርሙሉ የመመራቱን ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡

በአብዛኛው በክልሉ የሚከሰቱ ችግሮች ከማንነት፣ ከሀብትና ስልጣን ክፍፍል፣ በተለያዩ መዋቅሮች ውክልናና ከድንበር ይግባኛል ጥያቄ ጋር የተያያዙ መሆናቸው ሲታይ የፌዴራል ስርአቱ በህዝቦች የሚነሱ ጥያቆዎችን መመለስ አልቻለም እንዲባል መንገድን ይከፍታል፡፡

በወልቂጤና ቀቤና ማህብረሰብ መካከል የተፈጠረው ግጭት (ሰኔ 06/2010)

ይህንን የ27 አመት የደቡብ ክልል መዋቅርን ባለበት ማስቀጠል ከባድ ነው ምክንያቱም ብዙ ቦታዎች ማንነትን በተመለከተ ጥያቄዎች እየተነሱ ስለሆነ፡፡ ለዚህም ይመስላል በቅርቡ ደኢህዴን ባደረገው ስብሰባ በክልሉ ያሉ ዞኖችንና ወረዳዎችን በአዲስ መልኩ ለማዋቀር ስራ እንዲጀመር የወሰነው፡፡

የደቡብ ክልል ካለው የቆዳ ስፋት፣ ህዝብ ብዛት፣ የህዝቦች ልዩነትና የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የዞንና የወረዳ ሪፎርም ማድረጉ ብቻ በቂ አይመስለኝም፡፡ ሲዳማ እና ጉራጌ የክልል እንሁን ጥያቄቸውን ከምንን ጊዜም በላይ አጧጡፈውታል፡፡ ይህ የደኢህዴን ውሳኔ ምን አልባት ክልል ጥያቄ ያቀረቡትን አካባቢዎች ለመከፋፈልና ለማዳከም ያስችለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የክልል ጥያቄን ለመቀልበስ ይመስላል በአዋሳና በወልቄጤ በግልጽ የውጪ አካል እጅ እንዳለበት በሚያሳውቅ መልኩ ቀውጢ ለመፍጠር የተሞከረው፡፡

ምንም እንኳን እንደ ኦሮሚያው ኦፍኮ ወይም እንደ አማራው አብን ለቀጣይ ምርጫ ደኢህዴንን የሚቀናቀን ፖለቲካል ፓርቲ በደቡብ ክልል ባይፈጠረም በተለያዩ ምክንያቶች የደኢህዴን ተቀባይነት በክልል እየቀነሰ ይገኛል፡፡ ደኢህዴን በብዙ የክልሉ ኢሊቴች የህወሃት ተለጣፊ ተደርጎ እየታየ ይገኛል (ይህ ጉዳይ በተለይ የኢህአዴግን መሪና ጠ/ሚኒስትር ለመምረጥ በተደረገው ሂደት በኃላ ጎልቶ ታይቷል)፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሶስት አመታት በመላው ሀገሪቱ የለውጥ ንፋስ ሲሽከረከር በክልሉ ግን ምንመ ለውጥ አለመታየቱና ደኢህዴንም እንደተቀሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በለውጥ ሂደቱ ዋና ተዋናይ አለመሆኑ ደኢህዴን እንደ ከዚህ ቀደሙ ክልሉን መምራት አስቸጋሪ ሊያደርግበት ይችላል፡፡

ደቡብ እና ግጭት

በቅርቡ በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የተያዩ ግጭቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ዶ/ር አስናቀ ከፈለ “Federalism and Ethnic conflict in Ethiopia: a comparative regional study’’ በሚለው ጥናታዊ ጽሁፋቸው በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ ግጭቶችን ሀገሪቱ ከምትከተለው ብሔር ተኮር የፌዴራል ስርአት ጋር ማየቱ ጠቃሚ ነው ይላሉ፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በደቡብ ክልል ከሌላው የሀገሪቱ ክፍል በተለየ የማንነት ጥያቄ (የክልል እንሁን ጥያቄ ጨምሮ) ተጧጠፎ የሚቀጥል ይመስላል፡፡ እነዚህን ጥያቄዎ በአግባቡ መመለሱ አስፈላጊና ተገቢ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ከዚህ ቀደሞቹ እነዚህን ጥያቄዎች በሃይልም ሆነ በመከፋፈል ለማስቀረት መሞከሩ አደጋው የሚከፋ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የፌዴራል መንግስቱም ሆነ የክልሉ መንግስት እነዚህን ጥያቄዎች በብልሃትና በስልት መመለስ መቻል አለባቸው፡፡

በክልሉ የሚታየው ውስጣዊ ልዩነቶች (Sharp internal social divisions) ማለትም እንደ ቋንቋ ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ማንነትና ሌሎች ማህበራዊ ልዩነቶችን በተገቢው መልኩ ማስተናገድ የፌደራል ስርአቱ የተዋቀረበት ዋና አላማ እንደመሆኑ መጠን ለዚህም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ልዩነቶች በተገቢው መልኩ መያዝ ካልተቻለና የቆሞ ቀር ፖለቲከኞች መጠቀሚያ ከሆነ ወደ አላስፈላጊ ግጭት ሊያመራ ይችላል፡፡