ይቅርታና ምህረት ዋጋ ሲያጣ ፍርድና ቅጣት ይከተላል፡ ለአንጋፋ የህወሓት ባለስልጣናት!

አንዳርጋቸው ፅጌ ዛሬ በቢቢሲ ቴሌቪዥን ¨Hardtalk” ፕሮግራም ላይ ቀርቦ ከተናገራቸው ነገሮች ውስጥ ስለ ጠ/ሚ አብይ አህመድና ከእስር የተፈታበት ሁኔታ የተናገረው ነገር እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር። በተለይ፣ አንደኛ፡- ዶ/ር አብይ “አንዳርጋቸው ፅጌ ከእስር ካልተፈታ ስልጣኔን እለቅቃለሁ” ማለታቸው፣ ሁለተኛ፡- አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አንዳይፈታ ህወሓቶች ይህን ያህል ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው፣ ሦስተኛ፡- አንዳርጋቸው ፅጌ በዶ/ር አብይ ላይ ያለው ፅኑ እምነትና በቀጣይ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ትግል ለማድረግ ያለው ቁርጠኝነት በዋናነት ይጠቀሳሉ።

ከላይ በተገለፀው መሰረት ዶ/ር አብይ አንዳርጋቸው ፅጌ እንዲፈታ የወሰዱት እርምጃና ከእስር ከተፈታ በኋላም በቤተ መንግስት ተቀብለው በማነጋገራቸው በሁለቱ መሪዎች መካከል የመተማመን መንፈስ ፈጥሯል። ይህ የመተማመን መንፈስ በሁለቱ መካከል ተወስኖ የሚቀር አይደለም። .ከዚያ ይልቅ፣ በኢህአዴግና አግ7 መካከል የጋራ መግባባትና መተማመን የሚፈጥር ነው። ከዚህ በተጨማሪ፣ የኢህአዴግ መንግስት በሀገር ውስጥና በውጪ ማህብረሰብ ዘንድ ያጣውን ቅቡልነት በከፊልም ቢሆን መልሶ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ከዚህ በተቃራኒ፣ ህወሓቶች አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን አንዳይፈታ ለማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል።

ጠ/ሚ አብይ አህመድ የግንቦት7 መስራች የሆኑትን ራሱ አንዳርጋቸውን እና ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን በደንብ ጠንቅቀው እንደሚያውቋቸው በቃለ ምልልሱ ተናግሯል። ይህ ሁለቱን በቀላሉ መነጋገርና መግባባት እንዳስቻላቸው መገመት ይቻላል። ነገር ግን፣ የህወሓት መስራቾችና አመራሮች በእድሜ ሆነ ከዚህ ቀደም በነበራቸው ግንኙነት አንፃር ብርሃኑ እና አንዳርጋቸው ፅጌን ይበልጥ የማወቅ እድል አላቸው። ሆኖም ግን፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ እና አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ገና የኢህአፓ ተዋጊዎች በነበሩበት ወቅት ህወሓት ታጣቂዎች ለስደትና እስራት ተዳርገዋል፣ በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ዳግም ለእስርና ስደት ተዳርገዋል፣ ከዚያ በመቀጠል በአንዳርጋቸው ፅጌ ላይ የሞት ፍርድ ተላልፏል፣ የመን ሰነዓ ድረስ በመሄድ አፍነው ካመጡት በኋላ በእስራት አንገላተውታል።

በዚህ መልኩ ህወሓቶች አንዳርጋቸው ፅጌን ለእስራት፥ ስደት፥ ጉዳትና እንግልት መዳረጋቸው ሳያንስ በምህረት እንዳይፈታ በጠ/ሚኒስትሩ ላይ ከፍተኛ ጫና ማድረጋቸውን አንዳርጋቸው ራሱ አረጋግጧል። በአንዳርጋቸው ላይ ይሄን ሁሉ ግፍና በደል ከፈፀሙ የህወሓት አመራሮች የቀድሞ የመረጃና ደህንነት ሃላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋ አንዱ ነው። ከእሱ በተጨማሪ ሌሎች የህወሓት ባለስልጣናት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳታፊ መሆናቸው እርግጥ ነው።

በአጠቃላይ በአንዳርጋቸው ፅጌ ላይ ግፍና በደል የፈፀሙ የህወሓት ባለስልጣናት በጠ/ሚኒስትሩ ምህረት እንዳይፈታ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። እነዚሁ የህወሓት ባለስልጣናት እንደ አንዳርጋቸው ባሉ የፖለቲካ መሪዎችና የመብት ተሟጋቾች ላይ ግፍና በደል ለመፈፀም የሚገለገሉበትን የመንግስት ስልጣን በጡረታና በስንብት እንዲለቁ በመደረጋቸው ምክንያት “ክብራችን ተነክቷል” በማለት ለህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ድርጅቱም ትላንት ባወጣው መግለጫ የቀድሞ አመራሮቹ ተገቢው ክብር እንዲሰጣቸው ለማድረግ መወሰኑን ገልጿል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ “ክብር ተነፈጋቸው” ያላቸው የድርጅቱ መስራቾችና አመራሮች እነማን ናቸው? እስኪ በዕድሜ አንጋፋ የሆኑትን የድርጅቱ መስራች አቦይ ስብሃት ነጋን እንመልከት። እኚህ ግለሰብ ላለፉት 27 ዓመታት በሀገራችን ላይ የተጫነው የብሔር አፓርታይድ ዋና ጠንሳሽና አቀንቃኝ ሲሆን የትጥቅ ትግል ከጀመሩበት ዕለት አንስቶ በተለይ በአማራ ሕዝብ ላይ ቂም-በቀል ሲደግሱ የኖሩ፣ ይህ ሕዝብ በሀገሩ ላይ “ሀገር-አልባ” እንዲሆን ያደረጉ፣ በአጠቃላይ በብሔር ግጭቶችና ጥቃቶች በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ናቸው።

ሌላው የህወሓት አንጋፋ አመራር አቶ ስዩም መስፍን ናቸው። አቶ ስዩም መስፍን አሰብና ባድመን ለኤርትራ አሳልፎ በመስጠቱ ሂደት ከቀድሞ ጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በመሆን በሀገር ላይ ለፈፀሙት ክህደት (Treason) መከሰስ ነበረባቸው። ሌላው የህወሓት አንጋፋ አመራር አቶ አባይ ፀሓዬ ናቸው። እኚህ ግለሰብ የስኳር ኮርፖሬሽን አመራር በነበሩበት ወቅት ከ77 ቢሊዮን ብር እንዲባክን ያደረጉ፣ ስኳር በድብቅ ወደ ውጪ ሀገር የሚልኩ፣ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል ለተቀሰቀሰው ግጭትና አለመረጋጋት እና በዚህ ምክንያት በዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ግንባር ቀደም ተጠያቂ ናቸው።

በመጨረሻ በቅርቡ ከኃላፊነት የተነሱትን የቀድሞ የጦር ኃይል አዛዥ ጄ/ል ሳሞራ ዬኑስ እና የደህንነት ኃላፊው አቶ ጌታቸው አሰፋን እንመልከት። ጄ/ል ሳሞራ ዬኑስ፣ ሌላው ቢቀር፣ ባለፉት ሦስት አመታት ብቻ በእሳቸው የሚመራው የመከላከያ ሰራዊቱ በሺህ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎችን ላይ ላደረሰው የሕይወትና ንብረት ጉዳት ተጠያቂ ናቸው። በተለይ ደግሞ በዚህ አመት መጀመሪያ አከባቢ ወደ አንድ ሚሊዮን ዜጎች እንዲፈናቀሉ በማድረጋቸው ተከስሰው ዘብጥያ መውረድ ነበረባቸው። በተመሳሳይ አቶ ጌታቸው አሰፋ ላለፉት አስራ አመታት በደህንነት ሰራተኞች ለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዋና ተጠያቂ ነዋ። በብዙ ሺህ ዜጎች ላይ የፈፀመው ግፍና በደል ቀርቶ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጉዳይ ብቻ ለፍርድ ቀርቦ መቀጣት ነበረበት። ይሁን እንጂ፣ አንዳርጋቸው በምህረት እንዳይፈታ በጠ/ሚኒስትሩ ላይ ጫና ሲያደርጉ ከነበሩት ውስት አንዱ አቶ ጌታቸው ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ ትላንት ባወጣው መግለጫ “የሚገባቸውን ከብር ተነፍጓቸዋል” ያላቸው የድርጅቱ አንጋፋ አመራሮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ከላይ የተጠቀሱት ናቸው። እነዚህ የህወሓት አመራሮች ከላይ በተገለፀው መሰረት በዜጎችና ሀገር ላይ ለፈጸሙት ወንጀል ተከስሰው የሞትና እስራት ቅጣት የሚገባቸው ናቸው። ስለዚህ የተጠቀሱትና ሌሎች አንጋፋ የህወሓት አመራሮች ከሞትና እስራት ተርፈው ዛሬ ላይ በነፃነት መንቀሳቀስና መናገር የቻሉት ዶ/ር አብይን ጨምሮ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታና ምህረት ስላደረገላቸው ነው።

በአጠቃላይ ላለፉት አራት አስርት አመታት፤ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ሲጥሱና እንዲጣስ ሲያደርጉ የኖሩ የህወሓት አንጋፋ አመራሮች ዛሬ ስለ መብትና ዴሞክራሲ የሚናገሩት፣ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ክህደት የፈጸሙ ሰዎች ዛሬ ስለራሳቸው ክብርና ሞገስ የሚቆጩት፣ የአልጄርስ ስምምነትን በመፈረም ባድመን ለኤርትራ አሳልፈው የሸጡት ሰዎች ዛሬ ደርሶ ስለ ጉዳዩ “ሕዝብን ማወያየት ነበረብን” የሚሉት በምህረት ነው። በስልጣን ዘመናቸው ለፈፀሙት ወንጀል ሞት፥ እስራት፥ ስደትና እንግልት የሚገባቸው ሰወዎች ዛሬም የበደላቸውን ግፈት ቀማሽ በሆነ ሀገርና ሕዝብ መሃል በሰላም መኖራቸው በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ይቅርታ ነው። እስከ ዛሬ ከፈፀሙት ግፍና በደል ነፃ ሆነው ሳይሆን ምህረት ተደርጎላቸው ነው።

በስልጣን ዘመናቸው የበደሉት ሀገርና ሕዝብ ይቅርታና ምህረት አድርጎላቸው የሚኖሩ የህወሓት አንጋፋ ባለስልጣናት ናቸው እንግዲህ አንዳርጋቸው ፅጌ ይቅርታና ምህረት እንዳያገኝ በጠ/ሚኒስትር አብይ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያደርጉት። በአንዳርጋቸው ፅጌ ላይ ግፍና በደል መፈፀማቸው ሳያንስ ይቅርታና ምህረት እንዳይደረግለት ሲጥሩ የነበሩት እነዚህ ናቸው። በንፁሃን ዜጎች ላይ ግፍና በደል ሲፈፅሙ የኖሩ ሰዎች ናቸው ዛሬ “ክብራችን ተነክቷል” የሚሉት። በከዷት ሀገር፣ በበደሉት ሕዝብ ውስጥ እየኖሩ ነው “እኛ ያልነው ካልሆነ ኢትዮጵያ ትበጠበጣለች” የሚሉት።

የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ይቅርታና ምህረት ያደረገላቸው፤ የቂም-በቀል ሰንሰለትን ለመበጠስ፣ ስለ ነገ ተስፋና አብሮነት ብሎ እንጂ የፈጸሙበትን በደልና ግፍ ዘንግቶ፣ ቁስልና ሕመሙን እረስቶ አይደለም። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች በህዝቡ ላይ ተጨማሪ ቁስልና ሕመም የሚፈጥሩ፣ የቀድሞውን በደልና ግፍ ማስቀጠል የሚሹ ከሆነ በይቅርታና ምህረቱ ቦታ ፍርድና ቅጣት ይተካል። በሀገር ላይ ለፈፀሙት ክህደት፣ በሕዝብ ላይ ላደረሱት በደል ለፍርድ ይቀርባሉ። የህወሓት አንጋፋ ባለስልጣናት ከሚገባቸው በላይ ክብር የተሰጣቸው በበደሉት ሀገርና ሕዝብ መሃል በነፃነት እንዲኖሩና እንዲንቀሳቀሱ በመፍቀድ ነው። ይህ እጅግ በጣም ትልቅ ይቅርታ፣ የምህረት ጥግ ነው። ይህን ነገር ዋጋ ያሳጡት ዕለት ክብርና ሞገሳቸውን የሚገፍፍ ፍርድና ቅጣት ይከተላል።

One thought on “ይቅርታና ምህረት ዋጋ ሲያጣ ፍርድና ቅጣት ይከተላል፡ ለአንጋፋ የህወሓት ባለስልጣናት!

  1. ወያኔ “ነባር ታጋዮች የሚገባቸውን ከብር ተነፍጓቸዋል” ያለዉ እዉነቱን ነዉ፡፡”የዘረፍነዉ ገንዘብና የሰራነዉ ወንጀል ሳያንስ በነጻ ለዚያዉም በጡረታ ከምታሰናብቱን ልስታሩን ይገባችሁ ነበር” ማለታቸዉ እኮ ነዉ፡፡

    Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡