ተቃ እና ተካ፦ “አያጅቦን ተባብረን እናባርረዋለን ወይም ነጣጥሎ ይበላናል!”

“ተቃ” እና “ተካ”
ፌስቡክ ላይ ስለ ሀገራችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ከሚፅፉ ወዳጆቼ ውስጥ አንዱ ዶ/ር ደረጀ ገረፋ ነው። ይህ ወዳጄ የእነ ለማ ቡድን ወደ አመራርነት እስኪመጣ ድረስ ኦህዴዶችን እንደ እኛ ባይቃወማቸው እንኳይ በግልፅ አይደግፋቸውም ነበር። አዲሱ የኦህዴድ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ ዕለት ጀምሮ ግን ጭልጥ ያለ የኦህዴድ ደጋፊ ሆነ። በዚህ ድርጊቱ ከብዙዎቻችን ትችትና ነቀፌታ ደርሶበታል። በእርግጥ ዶ/ር ደረጀ ከሁላችንም ቀድሞ አዲሱን አመራር መደገፍ የጀመረው ውስጥ አዋቂ ስለሆነ ነው። ይህንንም ፌስቡክ ላይ ከሚያወጣቸው ፅሁፎች መረዳት ይቻላል። እኔ ግን አዲሱን የኦህዴድ አመራር በግልፅ እንድደግፍ ያደረገኝ ሌላ ሳይሆን የህወሓት አካሄድ ነው። በዚህ መሰረት አብዛኞቻችን ከተቃዋሚነት (ተቃ) በአንድ ግዜ ወደ ተተኪ ካድሬነት (ተካ) ተቀይረን የኦቦ ለማ መገርሳ ቡድንን መደገፍ ጀመርን።

አያጅቦ

አያ ጅቦ እስኪነክስ ያነክስ
በእርግጥ ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን በላይ ስለ ህወሓት ባህሪና አካሄድ ደጋግሜ አስባለሁ፥ እፅፋለሁ፥ እናገራለሁ። ምክንያቱም የሀገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ችግሮች በዋናነት ከህወሓቶች የፖለቲካ አመለካከትና ተግባራት ጋር በቀጥታ የተያያዙ መሆናቸውን አውቃለሁ። ከሕገ-መንግስቱ እስከ ተቋማዊ አሰራር ድረስ የህወሓትን የበላይነትና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ ካወቅኩ ቆይቼያለሁ። በአጠቃላይ መንግስታዊ ስርዓቱ በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የአፓርታይድ ስርዓት የባሰ መሆኑንና የፖለቲካ ቡድኑም ፍፁም ቆሞ-ቀርና ፀረ-ለውጥ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ።

በዚህ መሰረት አዲሱ የኦህዴድ አመራር የህዝቡን ጥያቄ ተቀብሎ ለማስተናገድ ገና “ሀ” ብሎ መራመድ ሲጀምር ህወሓት ልክ እንደ “ጅብ” እነ ለማን ሊበላቸው ተነሳ። ይሄን ግዜ ለዶ/ር ደረጀ “እነ ለማን ተረባርበን ካልታደግናቸው ህወሓት ይበላቸዋል። እነሱን በልቶ ሲጨርስ እኛን ይፈጀናል!” የሚል መልዕክት ላኩለት። ከዚያ በኋላማ ሁላችንም በእጃችን ላይ ያለውን ነገር ሁሉ መወርወር ጀመርን። ያው አያጅቦ ብዙ ግዜ የሚባላው ጭለማን ተገን አድርጎ ነው። “አያ ጅቦ እስኪነክስ ያነክስ” እንደሚባለው ህወሓት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ “ጭለማ” እስኪመጣ ድረስ እያነከሰ ይጠባበቅ ጀመረ።

ራሱን ከጅብ ለመከላከል ኦቦ ለማ መገርሳ ወደ ባህር ዳር በመሄድ ከኦሮማራ ወንድሞቹ ጋር መከረ። ዶ/ር አብይ ደግሞ ወደ ሐዋሳ በመሄድ ከጎረቤቶቹ ጋር “አያ ጅቦ ይብላን ወይስ ተባብረን እንዳን?” ብሎ ተናገረ። በሌላ በኩል አያጅቦ ደግሞ ጭለማን ለማንገስ የኢህአዴግ ሰብሰባዎችን ይቧጥጥ፣ አርጅተው የተጣሉ የሕግ አዋጆችን ማገላበጥ ያዘ። በመጀመሪያ በዚህ ዓመት የጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ኦሮሚያና ሶማሌ ክልል ላይ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማወጅ ሞከረ። ከኦህዴድና ብአዴን በገጠመው ጠንካራ ተቃውሞ ሳይሳካ ቀረ። ቀጠለና ያረጁ አዋጆችን ሲያገላብጥ ያገኘውን “የብሔራዊ ደህንነት አዋጅ” የሚል ነገር ይዞ መጣ። ነገር ግን፣ ወታደሮችና ፖሊሶች ተሰባስበው ያቋቋሙት ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ጭለማን ማንገስ ተሳነው።

እናባርረው ወይስ እንበላ
በአንድ በኩል እንደ እኔና ዶ/ር ደረጀ ያሉት የለማ ወንድሞችና ጎረቤቶች አንድ ላይ ተባብረው እንዲቆሙ፣ አለበለዚያ አያጅቦ ተራ በተራ ቅርጥፍጥፍ… አድርጎ እንደሚበላቸው መወትወት ያዝን። በሌላ በኩል እነ ዳንኤል ብርሃኔ “ኦሮሚያ ውስጥ ምንነቱ ያልታወቀ “ህቡዕ” የሚባል አውሬ ገብቷል” በማለት አያጅቦን “ሳትቀደም ቅደም” እያሉ መወትወት ያዙ። “Tigrayonline” የሚባለው ድረገፅ ደግሞ በየቀኑ “እዚህ ቦታ ሕዝብ አለቀና ተላለቀ” ብሎ እያላዘነ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጅ አለበት እያለ ይለፍፋል።

በእርግጥ ደረገፁ እንደ ውሻ ሲያላዝን “ኤጭ ይሄ ምን መዓት ያወራል” እያልን ስናጣጥለው ነበር። ከአስር ወራት በኋላ ሲገባን ለካስ “Tigrayonline” የሚያላዝነው በትክክል ንፁሃን ሲገደሉ ኖሯል። ምክንያቱም ድረገፁ ሰዎች በብሔር ግጭት የመገደላቸውን ወሬ የሚሰማው ከገዳዮቹ አንደበት ነው፣ እኛ ደግሞ ሰዎች መገደላቸውን የምንሰማው ከሞት ከተረፉ ተፈናቃዮች ነው። ከአለፉት አስር ወራት የተማርነው ነገር ቢኖር “Tigrayonline” ሲያላዝንና ግልገል ጅቦች ሲያማርሩ የሆነ ቦታ አያጅቦ ሰዎችን እየበላ እንደሆነና ይህን ተክትሎ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ እንደሚመጣ ነው።

ነገር ግን፣ ባለፈው ሳምንት “Tigrayonline” ሲያላዝን ብዙዎቻችን ትኩረት አልሰጠንውም። ወዲያው ግን አያጅቦ በሐዋሳ፥ ወልቂጤ፥ ምስራቅ ሐረርጌ፥…ወዘተ ሰዎችን መብላት ጀመረ። በማግስቱ የአያጅቦ ቃል-አቀባዮች የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መታወጅ እንዳለበት ተናገሩ። በዚህ ሁኔታ እስከ መቼ ከአያጅቦ ጋር እየተጠባበቅን እንኖራለን? አያጅቦን አንድ ላይ ተሰባስበን እናባርረዋለን ወይም ደግሞ የቀናው ዕለት ቀረጣጥፎ ይበላናል። በአጠቃላይ አያጅቦን ወይ አንድ ላይ ተባብረን እናባርረዋለን ወይም አንድ ቀን ጠብቆ ይበላናል።

6 thoughts on “ተቃ እና ተካ፦ “አያጅቦን ተባብረን እናባርረዋለን ወይም ነጣጥሎ ይበላናል!”

 1. ስዩም አንተ አስቃቂዉ የወያኔ አስርቤትና ማእከላዊ የማይበግርህ ጀግና ነህ፡፡አንድ ቀን የኢትዮጵያ ህዝብ ዉሌታህን ይከፍልሃል፡፡አድርባይነት የሌለብህ ማመሰል የማታዉቅ ሁልጊዜም እዉነቷን ፍርጥርጥ አድርገህ ለህዝብ የምትገልጽ ደፋር የህዝብ ልጅ ነህ፡፡በርታ፤ለዶ /ር አብይ ወደ አመራር መምጣት ያንተ ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን እናዉቃለን፡፡

  ጨኑ ጫንያለዉ ነኝ ከታቦር ተራራ ስር

  Like

 2. ስዩም አንድ ነገር ልጠቁምህ፡፡የወያኔ ድሬገጾች በተለይ ኤጋ ፎረምና ትግራይ ኦንላይን ወዘተ እያረገ ያለዉን ጸረ ኢትዮጵያ ደባ እየተከታተልክ ማጋለጡንና ህዝቡን መስጠንቀቁን ችላ ማለት አይኖርብህም፡፡

  Like

 3. እንዴት የሚያስጠላ ጅብ ነው፡፡ እስከዛሬ ስንቱን ቀረጣጥፎ ይሆን? ከዚህ በኋላ ጅቡ እንዳይበላን አንበሣ እንሁን፡፡!!!!

  Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡