“የህወሓት ሲንድሮም” ተጠቂዎች በራሳቸው ምንም የረባ ነገር መስራት የማይችሉ ናቸው!

የትግራይ አስተዳደር ፎረም (Tigray Governance Forum (TGF)) ትላንት በሐርሞኒ ሆቴል የመጀመሪያ ስብሰባውን አድርጓል። በትግራይ የአስተዳደር ፎረም ላይ ከተሳተፉት ውስጥ፤ ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል፣ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ጀ/ል ፃድቃን ገብረተንሳይ፣ ጀ/ል አበበ ተክለሃይማኖት፣ አቶ ዳዊት ገ/እግዚያብሔር፣ ኢንጂነር አሰፋ አብርሃ፣ አቶ አብርሃ ደስታ፣ አቶ መሃሪ ዮሃንስ፣ ዘፅዓት ሴቭአድና አናኒያ፣ አስራት አብርሃም፣ ዓብለሎም መለስ፣ አውሎም ወልዱ፣ የማነ ዘርዓይ፣ ዳንኤል ብርሃኔ፣ ፍፁም ብርሄኔ፣ አስፋው ገዳሙ፣ ሰይፈ ሃይለስላሴ፣ ጎይቶም ፀጋዬ፣ አብረሃ ሃይለዚጊ፣ ኪዳነ አማነ፣ ጌታቸው አረጋዊ እና ቢሊሊኝ ሃብታሙ ይገኙበታል። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹን በአካልና በሚዲያ አውቃቸዋለሁ።

በአጠቃላይ ከተዘረዘሩት 22 ሰዎች ውስጥ ግን ብስለት ያለው ዕውቀትና ቅንነት ያላቸው ሁለት ብቻ ናቸው። እነሱም፡- ጄ/ል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) እና አስራት አብርሃም ናቸው። ከሁለቱ በስተቀር የተቀሩት በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ በህወሓት ሲንድሮም (TPLF Syndrome) የተለከፉ ናቸው። በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች ምንም ነገር እንዴትም አድርገው ቢሰሩ ለትግራይ ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለውጥና መሻሻል ማምጣት አይችሉም። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች በማንኛውም አስተዳደራዊ ጉዳይ ላይ አስተያየትና ምክር ከመስጠታቸው በፊት በቅድሚያ ከህወሓት በሽታ መዳን አለባቸው። የትግራይ ልሂቃንን እንዲህ በጅምላ የሚያጠቃው የህወሓት ሲንድሮም ምንድነው?

የህወሓት ሲንድሮም በዋናነት በፍርሃት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ አመለካከት ነው። እንደ ህወሓት ያሉ የፖለቲካ ቡድኖች የትጥቅ ትግል ለመጀመር በቅድሚያ ህዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር አለባቸው። ለትጥቅ ትግል የሚያስፈልገውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ለመፍጠር ደግሞ የብሔርተኝነት ስሜትን በማህብረሰቡ ውስጥ ማስረፅ ያስፈልጋል። ወጣቶችን በትጥቅ ትግል ለማሰማራት ለራሳቸው ማህብረሰብ አብልጠው እንዲያስቡና እንዲቆረቆሩ (ራስ-ወዳድ እንዲሆኑ) ከማድረግ በተጨማሪ ለሌሎች ጥላቻ ሊኖራቸው ይገባል። ምክንያቱም ሰዎች ሌሎች ሰዎችን ተኩሰው ለመግደል በውስጣቸው ስር-የሰደደ ፍርሃትና ጥላቻ ሊኖር ይገባል። እነዚህ በፍራቻና ጥላቻ የሚመለከቷቸው ወገኖች ደግሞ በጥቅሉ “ጠላቶች” ተብለው ይፈረጃሉ።

በዚህ መልኩ የተጀመረው የትጥቅ ትግል በሂደት ወደ መግደልና መገደል ይቀየራል። በመሆኑም ጦርነቱ እየተካረረ በሄደ ቁጥር መጀመሪያ ላይ ማህብረሰቡ ውስጥ የሰረፀው የራስ ወዳድነት ወደ ጭፍን ወገንተኝነት ይቀየራል። በተመሳሳይ በውጣቸው የነበረው ፍራቻና ጥላቻ ደግሞ በጦርነቱ ወቅት ወደ ፍፁም ጠላትነትና ፍርሃት ስሜት ይቀየራል። በዚህ መሰረት በጦርነቱ መጨረሻ ፅንፍ ባወጣ ራስ ወዳድነትና ወገንተኝነት፣ እንዲሁም በጭፍን ጥላቻና ስር-የሰደደ ፍርሃት የናወዘ የፖለቲካ ቡድን ይፈጠራል። ስለዚህ ከጦርነቱ በኋላ የፖለቲካ መሪዎቹ ቀዳሚ ተግባር ይህን ፅንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት ከቡድኑ አባላትና ደጋፊዎች ውስጥ አንጠፍጥፎ ማስወገድ ነው። ይህን ማድረግ ከተሳናቸው ግን ይህ ፅንፈኛ አመለካከት በፖለቲካ መሪዎችና ልሂቃኑ ውስጥ ይሰርፃል።

እንዲህ ያለ ፅንፈኛ ቡድን የፖለቲካ ስልጣን ከያዘ ደግሞ አስተዳደራዊ ስርዓቱ ከሞላ-ጎደል በቂም-በቀል ላይ የተመሰረተ፣ ወገንተኛና አድሏዊ፣ ጨቋኝና አፋኝ፣ እንዲሁም ፀረ-ለውጥ ይሆናል። የፖለቲካ ቡድኑ በራሱ መለወጥ አይችልም፣ ሌሎችም እንዲለወጡ አይፈቅድም። የተለየ የፖለቲካ አመለካከት ተቀብሎ ማስተናገድ አይችልም፣ በራሱ የተለየ ሃሳብ ማመንጨት አይችልም። ከህዝብ ይልቅ የራሱን ተጠቃሚነት ያስቀድማል፣ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የራሱን ስልጣን ለማስከበር ይታገላል። በአጠቃላይ የህወሓት ሲንድሮም (TPLF Syndrome) ማለት በራስ ወዳድነትና ወገንተኝነት፣ እንዲሁም የጠላትነትና ፍርሃት ስሜት የናወዘ የፖለቲካ አመለካከት ነው።ከላይ የተጠቀሱት የትግራይ ልሂቃን የዚህ ዓይነት ፅንፈኛ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ናቸው። በመሆኑም እነዚህ ሰዎች ምንም ነገር እንዴትም አድርገው ቢሰሩ ለትግራይ ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የረባ ነገር መስራት አይችሉም።