የአሜሪካኖች መቀየስና የህወሓቶች ማልቀስ ቀጥሏል!

በተንኮልና በስም ማጥፋት የተካኑትና ጭፍን የህወሓት ደጋፊዎች እና ደቃፊዎችን (ተቃዋሚ መሳይ ደጋፊዎችን) ከፌስቡክ ገፄ ላይ በብሎክ ጠራርጌ ሳስወግድ ከተረፉት ጥቂት ሰዎች ውስጥ ዳንኤል ብርሃኔ አንዱ ነው፡፡ ይህ የሆነው በይቅርታና ምህረት ሳይሆን የህወሓትን ቀጣይ አጀንዳና አካሄድ ስለሚጠቁመኝ ነው፡፡ ምክንያቱም በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በንቃት ከሚሳተፉ ቀንደኛ የህወሓት ደጋፊዎች ውስጥ እንደ ዳኒኤል ብርሃኔ ያለ አደገኛ ሰው የለም፡፡ የሚፅፋቸውና የሚናገራቸው ነገሮች በሙሉ የህወሓት የበላይነትን በማስቀጠል ላይ ማዕከል ያደረጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ላለፉት 4 ወራት ዳንኤል በአሜሪካኖች ላይ የጀርባ ቅማል ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ለምን?

ኣይተ ዳንኤል ብርሃኔ (ከቀንደኛ የህወሓት ደጋፊዎች አንዱ)

ዳኒኤል ብርሃኔ ከቀድሞዋ የአሜሪካ አምባሳደርና የፖለቲካ አማካሪ ከነበረው ግለሰብ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ነበረው። ነገር ግን፣ የእነ ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው ቡድን የህወሓትን የበላይነት ለማስወገድ መተባበርና መታገል ሲጀምሩ አሜሪካኖች ድጋፋቸውን ከህወሓት ወደ እነሱ ያዞራሉ። በተለይ ደግሞ ህወሓት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማወጅ የኦህዴድና ብኤዴን አመራሮችን እስር ቤት ለማስገባት የተግባር እቅድ ነድፎ መንቀሳቀስ ሲጀምር አሜሪካኖች በግልፅ መቃወም ጀመሩ። በዚያው ልክ ደግሞ ኦህዴዶችን አቋምና አካሄድ በግልፅ ደግፈው መንቀሳቀስ ጀመሩ። ምክንያቱም ህወሓቶች የራሳቸውን የስልጣን የበላይነትና ዘረፋ ለማስቀጠል ሲሉ ሀገሪቱን ወደ እርስ-በእርስ ጦርነት ሊያስገቧት እንደሆነ አሜሪካኖቹ ተገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ወደለየለት ግጭትና ጦርነት መግባት የአሜሪካኖችን ጥቅም ይፃረራል። ስለዚህ የህወሓቶች አካሄድ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን የአሜሪካኖችን ጥቅም ይፃረራል። በሌላ በኩል የህወሓትን የበላይነት ለማስወገድ የሚታገለው የእነ ለማና አብይ ቡድን የኢትዮጵያን ጥቅም ከማስከበር አልፎ የአሜሪካኖችን ዘላቂ ጥቅም ያስከብራል። በዚህ መሰረት አሜሪካኖች በግልፅ ኦህዴዶችን በመደገፍ ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ እንዲመረጥ ቀጥተኛና ግልፅ የሆነ ድጋፍ አድርገዋል።

በአንፃሩ ህወሓቶች የድርጅቱንና የሀገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን በኦህዴዶች እጅ እንዳይወድቅ የሞት-ሽረት ትንቅንቅ አድርገዋል። በዚህ ረገድ እንደ ዳንኤል ብርሃኔ ያሉ የህወሓት ደጋፊዎች “የኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳደር ውስጥ ማንነቱ በማይታወቅ “ህቡዕ” ድርጅት ቁጥጥር ስር ውሏል” በማለት አዲሶቹን የኦህዴድ አመራሮች በአጭሩ ለመቅጨት በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ተረባርበዋል። የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን ለማሰር የወጣው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውድቅ ሲደረግ አይናቸውን በጨው አጥበው “ፀድቋል” ብለው ተሟግተዋል።

በመጨረሻም የኢህአዴግ ሊቀመንበር ምርጫ ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ የኦህዴድ አመራሮችን ለማሰር የእስር ማዘዣ ማውጣታቸው ይታወሳል። የእስር ማዘዣው የወጣ ሰሞን የቀድሞ የደህንነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ኦቦ ለማ መገርሳን “እስር ቤት ትገባታለህ!” ብሎ እስከ ማስፈራራት ደርሷል። ይሁን እንጂ፣ ህወሓቶች እስር ቤት ሊያስገቧቸው የነበሩት ኦህዴዶች አሸናፊ ሆነው ወጡ። ዶ/ር አብይም የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ ተመረጠ።

በእርግጥ ዶ/ር አብይ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ ከመመረጡ በፊት አሜሪካን ሄዶ ከሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በሚስጥር መገናኘታቸው ይታወሳል። ጠ/ሚኒስትር ከሆኑም በኋላም ከአሜሪኮኖች ጠንካራ ድጋፍ ማግኘቱ ይታወቃል። በዚያው ልክ ደግሞ ህወሓቶች ላይ ፊታቸውን አዙረዋል። ይህ እንዳይሆን ህወሓቶች አቶ ሽፈራው ሽጉጤን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ለማድረግ፣ የእነ ለማ መገርሳን ያለመከሰስ መብት በአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በመግፈፍ እስር ቤት ለማስገባት ቆርጠው ተነስተው ነበር።

ይሁን እንጂ፣ ለእስር ቤት የታጩት ቤተ-መንግስት ሲገቡ ላለፉት 27 አመታት ፈላጭ-ቆራጭ የነበሩት አንጋፋ የህወሓት አመራሮች ከቤተ መንግስት ተባረሩ። ህወሓቶች በዚህ መልኩ ተገዝግዘው ከመውደቃቸው በፊት የእስር ማዘዣ የወጡባቸውን የኦህዴድ አመራሮች ለምን አላሰሯቸውም? እንዴት ህወሓቶች ለ27 አመት በተጫወቱበት ሜዳ ላይ እንዲህ ሊሸነፍ ቻለ?

እዚህ’ጋ ብዙ ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶች ሊያነሱ ይችላሉ። ነገር ግን፣ ዋና እና ቁልፍ የሆነው ምክንያት የአሜሪካኖች ጣልቃ-ገብነት ይመስለኛል። በዚህ ረገድ የአሜሪካን ኮንግረስ የኤች-አር-128ን መፅደቁ ሊጠቀስ ይችላል። ምክንያቱም በዚህ አዋጅ (ሕግ) ግንባር ቀደም ተጠያቂ የሚሆኑት የህወሓት ባለስልጣናት መሆናቸው እርግጥ ነው። ይህ አዋጅ ተግባር ላይ ከዋለ ህወሓቶች ሀገሪቱን ከመምራት በተለያዩ የዓለም ሀገራት መንቀሳቀስ፣ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በመዝረፍ በውጪ ሀገራት ባንኮች ያስቀመጡትን ገንዘብ ማንቀሳቀስ አይችሉም። በዚህ መልኩ በስልጣን ላይ መቆየት ሆነ ሀገሪቱን ማስተዳደር አይችሉም። ከዚህ በተጨማሪ የአሜሪካን ደህንነት መስሪያ ቤት (CIA) በህወሓቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያደርግ እንደሚችል መገመት ይቻላል።

በአጠቃላይ አሜሪካኖች ህወሓትን አንቅረው ተፍተውታል። ስለዚህ አሜሪካኖች ኢትዮጵያን በተመለከተ ምንም ነገር ቢናገሩና ቢያደርጉ እነ ዳንኤል ብርሃኔን ክፉኛ ያበሳጫል፥ ያነጫንጫል። ባለፈው ዳንኤል ብርሃኔ “ዶ/ር አብይ ከተመረጠ በኋላ ሀገሪቱን በእጅ-አዙር እያስተዳደሩ ያሉት አሜሪካኖች ናቸው” በማለት የሉዓላዊት ጥያቄ ሲያነሳ ነበር። ዛሬ ደግሞ የአሜሪካን ምርመራ ቢሮ (FBI) በመስቀል አደባባይ የደረሰውን የቦንብ ፍንዳታ ለማጣራት አዲስ አበባ መግባቱን አስመልክቶ “የገለልተኝነት” ጥያቄ አንስቷል። ነገ ደግሞ አሜሪካኖች ሌላ ነገር ቢያደርጉ እነ ዳንኤል ሌላ ነገር ይላሉ። ሆኖም ግን፣ ምንም ነገር ቢናገሩና ቢያደርጉ የእነ ዳንኤል መነሻና መድረሻ የህወሓትን የበላይነት ተመልሶ እንዲያገግም ማድረግ ነው። ለእነዚህ ሰዎች የህወሓት የበላይነት ከኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት፣ ከሉዓላዊነት ሆነ ፍትህና ነፃነት ይበልጣል፡፡ የህወሓትን የበላይነት ለማስቀጠል ሀገር ሸጠዋል፣ ህዝብን በብሔርና ቋንቋ ከፋፍለዋል፣ ዜጎችን በጭካኔ ገድለዋል፣ … በሀገርና ህዝብ ላይ በጣም ብዙ ሸርና አሻጥር ሰርተዋል፡፡ እነ ዳንኤል ብርሃኔ ደግሞ ይህን ግፍና በደል ደግፈው ተከራክረዋል፥ ተሟግተዋል፣ ለወንጀለኞች ጥብቅና ቆመዋል፡፡ ዛሬም ይህንኑ እኩይ ተግባር መፈፀም ቀጥለዋል! ስለዚህ የአሜሪካኖች መቀየስና የህወሓቶች ማልቀስ ቀጥሏል!

5 thoughts on “የአሜሪካኖች መቀየስና የህወሓቶች ማልቀስ ቀጥሏል!

 1. ( ጠቅላይ ሚንስትራችን ሆይ ቶሎ ናልን )
  ኒዛር ዳጊ

  የስው ልጅ በተለያየ ምክንያት በጥፋቱም ያለጥፋት ሊታስር ይችላል ። በኩዌት በጫት ምክንያት የታስሩ ወገኖቻችን ግን ከዚህም ይበልጣሉ ።
  ስው እንርዳ ብለው ፣ መልካም አስበው ፣ ለስው አድርሱ ተብሎ ኢትዬጵያ ቦሌ ኤርፓርት ላይ በህሊና ቢስ ስዎች በተስጣቸው ዕቃ ውስጥ ኩዌት ኤርፓርት ላይ ጫት ሆኖ እየተገኝ ከሁለት ~እስከ አስር አመት የተፈረደባቸው ዜጎቻችን የእርሶን መምጣት በናፍቆት ይጠብቃሉ ።
  በጅቡተ ፣ በሱዳን ፣ በዩጋንዳ፣ በሳውዲ ፣ በዱባይ ፣ አሁን ደሞ በግብጽ እየሄዱ እንዳስፈቷቸው ዜጎቻችን ኩዌትም የፍት ሚዛን የተዛባባቸው ፍርደኞችና እኛ በኩዌት ምንኖር ኢትዬጵያኖች ስርክ ምኞታችን የእርሶ ኩዌት መምጣት ነው ።

  Like

 2. ስዩም ልክነህ፣ ዳንኤል ብዙ የሚያዉቀዉ ምስጢር ሰላለ የሱን ብሎግ አለመሰረዝህ ትክክለኛ እርምጃ ነዉ፡፡ዳንኤል ከሁሉም ሚዲያዎች ቀዳሚ ሆኖ ለሚያቀርበዉ መረጃ ምንጩ ራሱ አስቀድሞ የተሳተፈበት ስለሆነ ነዉ፡፡አብሮ ያሴራል፤ ከዚያ ብዙ ደክሞ ያኘዉ መረጃ አስመስሎ ያቀርባል፡፡የሚገርመዉ ደግሞ ከሌሎች የወያኔ ጋዘጠየኞች በተለየ እሱ ሃኛና ገለልተኛ ለገንዘብ ግድ የሌለዉ በማስመሰል በጥቅም ተጋሪዎች በኩል ስለራሱ ቅዱስነት ያስጽፋል፡፡ tigrai online ላይ ስለሱ የተጻፈዉን ፈልገህ አንብብ፤ባጠቃላይ ዳንኤል የጭቃ ዉስጥ እሾህ ነዉ፡፡ብዙ ሰወ አሳስቷል፡፡ለገንዘብ ብሎ ለራሱ ሰዎችም ምህረት የሌለዉ የቀን ጅብ ነዉ፡፡

  Like

 3. ኤርሚያስ ለገሰ ከሰሞኑ በኢሳት ቲቪ ላይ “የህወኃት ደጋፊ ቁጥር ከጠቅላላዉ የትግራይ ህዝብ መካከል ከሃያ ሺህ አይበልጥም፡፡ የቀረዉ በሙሉ የለዉጥ ደጋፊ ነዉ” ማለቱ በጣም አስገርሞኛል፡፤ራሱ ኤርሚያስ ከጥቂት ቀናት በፊት “በአዲስአበባ ብቻ ሃያ ሺህ የማያንስ መሳሪያ በየቤቱ ታጥቆ የሚጠባበቅ የሕወኃት ደጋፊ አለ” እንዳላለ ሳሬ ደግሞ ያን ረስቶ ነዉ ዝቅ አድርጎ መግለጹ፡፡ በመከላከያ ሰራዊት ዉስጥ ስንት የሕወኃት ደፋ አንዳለ አያዉቅም ማለት ነዉ፡፡?ከአዲ አበባ ጂቡቲ የሚመላለሱ ከባድ በሽሽ የሚቆጠሩ ተሸርካሪዎች ሾፈሮች እነማን እንደሆኑ የዘነጋ ይመስለኛል፡፤በየክልል በየዞኑ በመንገሰት መስሪያቤቶችና በግል ድርጅቶች የተሰገሰጉ ቁራዉ ብዙ ነዉ፡፤ሌላዉ ቀርቶ በርካታ ገንዘብ ተሰጥቶአቸዉ ዲሞብላይዝ ተደርገዉ በዳንሻ በሌሎች አካባቢ በእርሻ የሚተዳሩ ነባር ታጋዮች ቁጥራቸዉ ልክ የለዉም፡፤ህወኃት የሚዘርፈዉን ሁሉ ለትግራይ ህዝብ ያደርጋል ባይባልም ቢያንስ በተለያየ ደረጃ ተጠቃሚ የሆኑና ህወኃት ከሌለ ህልዉናቸዉ የሚያከትም አድርገዉ የሚያስቡ በርካቶች መሆናቸዉን መዘንጋት አልነበረበትም፡፡እጅግ አስገራሚዉና የሚናድደዉ ደግሞ የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ ነገርግን ትንሽ ጉርሻ የሚጣልላቸዉ የሕወኃት ደጋፊ የሆኖ ኦሮሞ ደቡብና አማራ አፋርና ሶማሌ መኖራዉንም ከግምት ማስገባት ነበረበት፡፡ለነገሩ የዚህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ከመድረሱ በፊት ጥናት ማድረግ ነበረበት እላለሁ፡፡ኤርሚስ ሊነግረን የፈለገዉ “ህወኃት ደካማ ነዉ” ለማለት ከሆነ በዚህ ተዘናግተን ለቀን ጅቦች እራት እንዳንሆን መጠንቀቁ ይበጀናል፡፡

  Like

 4. ጋዘጤኛ ፍቃዱ ኃይሉ “ሚዲያውን ለቀቅ፣ ቃልኪዳኑን ጠበቅ”… በሚል ርእስ መረጃ ኮም ላይ በከተባት ጽሁፍ ቅር ተሰኝቻለሁ፡፡በዚያዉ ድረ-ገጽ ላይ መልስ መስጠት ስላላቻልኩ ነዉ የናንተን መጠቀሜ፡፡ ፈቃዱ በጋዜጤኝነቱ ብዙ እንግልት የደረሰባትና ብዙ የተሰቃየ እንደሆነ እዉቃለሀ፡፤ግልጽና ደፋርም ነዉ፡፤ሆኖም አንዳንዴ የሚሰጣቸዉ አስተያየቶች ማመዛዘን የሚጎላቸዉ ናቸዉ፡፡ስሜተዊነት ይታይበታል፡፡ በተጠቀሰዉ ጽሁፍም ተመሳሳይ ግድፈት አይቸበታለሁ፡፡በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ህዝቦች በታላቅ ስሜት የሚከታታሉትን ለክቡር ጠ/ሚኒስትሩ የተደረገዉን ታላቅና መድር አንቀጥቅጥ የሆነ ዝግጅት በቀጥታአለማስተላላፍ ብቻ ሳይሆን ለጥቂት ደቂቃዎች እንኳ በመሃል ዜና ያልሰሩ ቴሌቪዥኖች መካከል ትግራይ ቲቪ ኢትዮጵያ ሶማሌና ኢኤን.አን ይገኙበታል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለዜናነት የማይበቃ ስለነበረ ሳይሆን ጠ/ሚኒስትሩ ተቃዋሚ በመሆናቸዉና ህወኃትን ለማስደሰት አስበዉ በእቅድ የሆነ ነዉ፡፡እናም አዲሱ ጠብሮድካስትን ባለስልጣን በዚህ ጉዳይ ማብራሪያ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱ ስርጭት እንዲያቆሙ ፈቃድ መከልከልም ይችል ነበር፡፡ ወንድሜ ፈቃዱ በእለቱ በተፈጠረዉ አደጋ የተሰማዉን ድንጋጤ ስሜት ሳያጋራን በጣም የጠጨነቀዉ የወያኔ አገልጋይ የሆኑት ሚዲያዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ መጠየቃቸዉ ነዉ፡፡አቶ ዘርአይ ቢሆን ኖሮ እኮ ምን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ሳያዉቀዉ ቀርቶ አይመስለኝም፡፤ስለዚህ የሀዝብ ጭንቀት ኢንኤንና ትግራይ ቲቪ ለጥያቄ መቅረባቸዉ ሳይሆን ይህን ታሪካዊ ከስተት ለምን እንዳልዘገቡ ማወቁ ላይ ነዉ፡፤ተግባባን?

  Like

  1. እንደ ዘርአይ ለመሆን ከሆነ ዲሞክራሲን የምንደሰኩረው ገና ያልገባን ብዙ ነገር እንዳለ ያሳያል።ፍቃዱ ማለት የፈለገው የሚመስለኝ ሚዲያው የመንግስት ጣልቃ ገብነት ይቅርለት እንጅ የጉዳዩ አስፈላጊነት ጠፍቶት አይደለም።

   Like

አስተያየቶቹ ተዘግተዋል፡፡