ቤኒሻንጉል ክልል አሶሳ ምን እየተካሄደ ነው? 

ከሁለት ቀን በፊት በክልሉ ርእሰ ከተማ አሶሳ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማጣራት በተደረገው ጥረት ክልሉ ታማኝ ምንጭ (የለውጥ አመራሩ ክንፍ ብየዋለሁ) ባደረሰኝ መረጃ መሠረት መንሥኤውን እንዲ አድርሶኛል።

“በፖለትካ ሜዳዉ ላይ የተሸነፈዉ ፀረ ለዉጥ ቡድ በቤኒሻንጉል ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ዉስጥ አሁን በአገራችን እየተደረገ ያለዉን የለዉጥ ዓላማ ያልተረዱ አንዳንድ የክልሉ አመራሮችን አወናብዶ በህቡዕ በማደራጀት አሁን በዶክተር አብይ እየተደረገ ያለዉ ለዉጥ 
1. “ለበርታ ህዝብ  (Barta Nation) አይጠቅምም”

2. “ህገመንግስቱ የሰጣችሁን መብቶች ይሽራል”

 3. “ክልልም እንዳይኖራችሁ ልያደርጋችሁ”  ነዉ እንዲሁም

4. “ምንም ነገር ባልተፈጠረበት ሁኔታ ራሳቸዉ ባደራጁት ሰዎች ግርግር እየፈጠሩ ከኦሮሚያ የመጣ ሚሊሻ እየወጋቹ ነዉ   በሚል የዉሸት ቅስቀሳ በህዝቦች መካከል እያሰራጩ ነው።”

ይህ ምንጭ እንደሚያሳየው ችግሩ በክልሉ ውስጥ ያለው አመራር በለውጥ ፈላጊ እና ለውጡን በማይፈልጉ፣ የለውጡን ዓላማ  “መጥፎነት” ከሌላ ወገን እየተረዳ ያል፣ በህቡእ የተደራጀ የአመራር ጎራዎች ተከፍሏል። 

ከዚህ የተነሳ ይላል ይህ ምንጭ፦

“ግጭት በመፍጠር የአገራችንን ሰላም ለማድፈረስ እና እየመጣ ያለዉን ለዉጥ ለመቀልበስ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ”።


ሥለ ለውጥ ኃይል ጎራው ሲናገር እንዲህ ይላል የደረሰኝ መረጃ፦


 “በመሆኑም በክቡር ጠቅላይ ሚነስትር አብይ አህመድ አመራር እየተወሰዱ ያሉት የለዉጥ እርምጃዎች አንዱን ጎድተው አንዱን ለመጥቀም ወይንም ከአንዱ ወስዶ  ለሌዉ ለመስጠት ሳይሆን  አገራችንን ወደ ተሻለ የልማት፣ ሠላምና ብልጽግና  ለመዉሰድ ያለመ መሆኑን በመገንዘብ እነዚህን ህዝብና ህዝብን በማጋጨት የሚያደርጉት እኩይ ተግባር ተባብረን በማክሸፍ  አገራችንን ወደ ላቀ የሰላም፣የልማትና የብልጽግና ልንወስዳት ይገባል”።ዘር ለይቶ ማጥቃት፣ ግድያ፣ ዘረፋ እና ማፈናቀል እየተካሄደ ነው። እስከ አሁን ባለኝ መረጃ የክልሉም ሆነ ሌሎች  የጽጥታ አካላት ለዚ መልስ አልሰጡም። 

የኔ ሀሳብ

ትላንት በፌሥቡክ ገጼ ለማሳሳብ እንደሞከርኩት አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ግን አሁንም በጽጥታ ዘርፉ አሁንም ክፍተቱ በግልጽ ይታያል። 

በተለያዩ አካባቢዎች ማለትም

በምሥራቅ ኦሮሚያና ኢትዮ ሱማሌ አዋሳኝ ቦታዎታች፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በደቢብ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ክልል፣ በአማራ ክልል) የሚታዩ የጽጥታ ችግሮች፣ የብሔር ግጭቶች እና የሕዝቦች መፈናቀሎች እለት ተእለት አሳሳቢ መኾናቸው አልቀረም። የሰው ሕይወት፣ ንብረት፣ የመንግሥትና የሕዝብ ተቋማት እየጠፋ ነው። የኽ ነገር የለውጡን ፍጥነትና ሁለንተናዊ ጥቅምን ጥያቄ ውስጥ ይከትታል። 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሴክተሮች ማሻሸያ እና ለውጥ እያረጉ ባሉበት በአሁኑ ሰዓት የጽጥታ ዘርፉ ግን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። 
አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የጸጥታ ዘርፉ ለውጥና ማሻሸያ ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
ከላይ እስከታች ድረስ ያለውን ለውጥና ማሻሸያ እስኪጠናቀቅ እና ዘላቂ መፍትሔ እስኪበጅ ድረስ አሁን ያለው ኹኔታ የሚታየውን ብሩኽ ተስፋ አደጋ ላይ ይጥላል የሚል እምነት እለኝ። 

መፍትሔ፥አንድ ከዚህ በፊት የጽጥታ ችግርን ይፈታል ተብሎ የተቋቋመ ተቋም አለ። በብዙ የራሱ የጽጥታ ሃይሉ ችግር ምክንያት መፍትሄ ሊሆን አልቻለም ነበር። እሱም ብሔራዊ የጽጥታ ምክር ቤት (NATIONAL SECURITY COUNCIL) ይሰኛል። 

የተዋቀረው።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት

ከመከላከያ ሚኒስቴር

ከፌዴራል ፖሊስ

ከመረጃና እና ደኅንነት ኤጄንሲ 

ከክልል የጽጥታና አስተዳደር ቢሮዎች እና 

ከክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች እና ሌሎች የጸጥታና አስተዳደር  አካላት ነበር። 
አሁንም ይህንን ምክር ቤት እንደገና በአጭር ጊዜ ውስጥ በመሰብሰብና፣ ማደራጀትና ማሰማራት ግድ ይላል።
የአዲስ አበባና ደሬዳዋን ጨምሮ ከፌዴራልና ክልል አካላት ጋር በጥብቅ እንዲሰሩ መደረግ ይኖርበታል። 
ከዚ በፊት የዚህ ምክር ቤት ድካም የማኅበረሰቡ የፌዴራል ፖሊስ እና መከላከያው እምነት ማጣት እንደነበረ በዚሁ ዓመት ወርሃ ጥር ላይ ይኸው ምክር ቤት ባካሄደው ግምገማ አስታውቆ ነበር። 
ከዚህ በፊት ችግር ፈቺ መኾን ያልቻለብትን ችግር ለመቅረፍ ምክር ቤቱ አሁን በአዲስ መልክ እንደ ግብረ ኃይል ወይም ባለው የምክር ቤትነት ቁመና አዲስ አደረጃጀት ተደርጎለት ወደ ሥራ መግባት አለበት። 

በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች የሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች እና የብሔር ግጭቶች ዞሮ በተለያዩ እርከን ያሉ የአመራር አካላት መኖራቸው ማስተዋል አይከብድም። ነገር ግን በሕግ ሲጠየቁ ሳይሆን የመሪነት ሽግሽግ እና ቦታ ለውጥ ሲደረግ ብቻ ነው የሚታየው። ይህ ደግሞሥርዓት አልበኝነት (Lawlessness) እና የከፋ የወንጀለኞች አለመቀጣት ባሕል (Culture of Impunity) እንዲበዛ ያደርጋል። ስለዚህ የተጠያቂነት ጉዳይ በፍጹም ችላ ሊባል አይገባም። 
የአስተዳደር እና የጸጥታ አካላቱ ይኽ ጉዳይ ከፓርቲ ወገኝተኝነትና ከሥልጣን ሽኩቻ በላይ በሀገር ኅልውና፣ በዜጎች ደኅንነትና ሰላም እንዲሁም በወደፊት አብሮነታችን ላይ የተጋረጠ መኾኑን ተረድተው ሊሠሩበት ይገባል። 
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዚህ ምክር ቤት አደረጃጀትና አመራር ኃላፊነት ስላለባቸው በአፋጣኝ ወደ ሥራ መግባት አለባቸው።||

ለአስተያየትና ጥቆማ 

FACEBOOK || መንግሥቱ አሰፈ ||

EMAIL servezking@gmail