የተመላሽ/ተጋባዥ ፖለቲከኞች ነገር…

ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ እንደ አደረ ገንፎ መስህብ አጥቶ የኖረው ፖለቲካችን ከሶስት ወር ወዲህ በሁነት የተሞላ እየሆነ ነው፡፡ ፋታ በሌለው ሁኔታ በላይ በላይ የሚግተለተሉት ታላላቅ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አንዳንዶቹ በተለይ ከዛሬ ስድስት ወር በፊት በሃገራችን ይከሰቱ ይሆን ብለው ለራስ ቢያስቧቸው እንኳን ሞኝ የሚያስመስሉ ነበሩ፡፡ለውጦቹ በአጭር ጊዜ የተደረጉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ከገታራው ኢህአዴግ ሰፈር መምጣታቸው ጆሮው የማይሰማ ሰው ድንገት ጆሮው ሲሰማ ተመልካችን የሚያስደንቀው ማስደነቅ አይነት ነገር አለው፡፡

የኢትዮጵያን ህዝብ መራራ ትግል የተቀላቀሉ የሚመስሉት የኢህአዴግ ክፋዮች አብይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስትር ማድረጉ ከቀናቸው በኋላ ህወሃት በሌለበት ብቻ ሊደረጉ የሚችሉ በጎ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ከነዚህ በጎ ጅምሮች አንዱ ህወሃት የሃገር ባለቤት ሆኖ “ውግዝ ከመአሪዎስ”ብሎ በሃገራቸው አጥረ-ገጥ እንዳይደርሱ ያደረጋቸውን ግለሰቦችም ሆነ ፓርቲዎች ሃገራቸው ገብተው እንዲታገሉ በገሃድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መጋበዛቸው ነው፡፡

እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ጠመንጃ ታጥቆ ወንበር ላይ መሰየም የበለጠ ኢትዮጵያዊ እንደማያደርግ፣ አልፎ ተርፎ የሃገርባለቤት ሆኖ የፈለገውን ከሃገር ለማባረር ያሻውን ወደሃገር ለማስገባት እንደማይበቃ መረዳትን ይጠይቃል፡፡ከሁሉ በላይ ባለጠመንጃ አዋቂዎችን አባሮ ጨርሶ ብቻውን ሃገር ማቅናት እንደማይችል የመረዳት ምልክት ነው!የሆነ ሆኖ ሃገር ወዳዶች ቀርቶ “ሃገር ትፍረስ” ሲሉ የነበሩ ሳይቀሩ ወደ ሃገራቸው ገብተው እንዲታገሉ መደረጉ ይበል የሚያስብል እርምጃ ነው፡፡

ከሁሉም ቀድመው ከስደት የተመለሱት የኦዴግ (ODF) አመራሮች

መንግስት ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ ከስደተኛ ፖለቲከኞች የሚሰጠው የቸኮለም ሆነ የዘገየ መልስ በባለቤቶቹ እስከታመነበት ድረስ በራሱ ስህተት አይደለም፡፡ግለሰቦችም ሆኑ ፓርቲዎች ባመኑበት ጉዳይ ላይ ያደረጉትን ውሳኔ ለምን አደረጉ ማለት የማንም መብት እንዳልሆነ እሙን ቢሆንም የውሳኔያቸውን ፖለቲካዊ አንድምታ አፍታቶ ማየትም አስፈላጊ ነው፡፡

አብይ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆኑ በኋላ ለስደተኛ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለሚያደርጉት የ’ኑግቡ’ ጥሪ ቀድመው ወይ ባይ ያገኙት ከተሰዳጅ የኦሮሞ ብሄርተኝነት አፓርቲ አመራሮች ነው፡፡ እነዚህ ቀድሞ አቤት ባዮች ኦነግን አዋልደው፣በሽግግር መንግስቱ ከህወሃት ጋር ያደረጉትን ካደረጉ በኋላ ፓርቲው እጃቸው ላይ ለሶስት እስኪፈረከስ ድረስ እድሜ አግኝተው የዘለቁ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ካህናት ናቸው፡፡ በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራው ይህ ተመላሽ ቡድን በአቶ ኃ/ማርያም ዘመነ መንግስትም መጥተው ከመንግስት በኩል ይሄን ያህል የሚጓጓላቸው ሰው ስላጡ እንደተመለሱ በወቅቱ ለቪኦኤ ተናግረው ነበር፡፡ በመስህብ አልቦው የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን ዘመን ሳይቀር ወደ ሃገርቤት መጥቶ ግባ ሚለው አጥቶ የተመለሰው የአቶ ሌንቾ ኦዴግ በሽግግሩ ወቅት ለምን ሄዶ በአቶ ኃ/ማርያም መንግስት ደግሞ ምን አይቶ መመለስን እንደ ከጀለ ግራ አጋቢ ነው፡፡አቶ ኃ/ማርያም መራሄ መንግስት የነበሩበት የሃገራችን ፖለቲካ በሽግግር ዘመኑ ወቅት ኦነግን አስመርሮ ካሰደደው የሃገራችን ፖለቲካ የሚለየው በአቶ መለስ ከምድር በታች መሆን ብቻ ነው፡፡

በርግጥ የአቶ መለስ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ መከላት ቀላል ዕድል አይደለም፡፡ ሆኖም ኦነግ ልመለስ ያለበት ዘመን አቶ መለስ ከሞቱ እጅግ ዘግይቶ ስለሆነ ምክንያቱ የአቶ መለስ መቀነስ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ አቶ ሌንጮ በቪኦኤ ቀርበው ሃገራቸው ሁለመና እንደናፈቃቸው እና ሃገርቤት መምጣት እንደፈለጉ የተናገሩትን እንደ ዋነኛ ምክንያት እንደውሰድ ቢባል ደግሞ ይህ የሚያሳምነው ሰውየው በግላቸው ለመምጣት ቢያስቡ እንጅ ፓርቲ ይዘው ለመታገል ለመምጣቱ በቂና አሳማኝም ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡

ከኦዴግ ምክንያቱ በውል የማይታወቅ ወደሃገርቤት ለመግባት አጥብቆ መዋተት በላይ አስገራሚው የኢህአዴግ የበዛ ኩራት ነው፡፡እንደሚታወቀው ኢህአዴግ እንደነ ሞላ አስገዶም ያሉ ከፓርቲያቸው አኩርፈው አንድ አስር ሃያ ሰው ቆንጠር አድርገው ከሚመጡ የተሰዳጅ ተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ጋር ታረቅኩ ብሎ የፕሮፖጋንዳ ነጋሪት የሚጎስም ፓርቲ ነው፡፡ የአቶ ሞላ አስገዶም መምጣት መቅረቱ ኢህአዴግ ያወራለትን ያህል ጥቅም ይኑረው አይኑረው ከአቶሞላ ንግግር ጀምሮ መረዳት ቀላል ነበር፡፡

እውነቱ ምንም ይሁን ምን ለኢህአዴግ ግን የአቶ ሞላ አስገዶም መምጣት ትልቅ ድል መስሎ ታይቶት ብዙ ብዙ አውርቶለታል፤አቶ ሞላም የጀግና አቀባበል ይገባቸዋል ተብለው በቀይ ምንጣፍ ተራምደዋል፡፡በተመሳሳይ ከኦብነግ ተሰንጥረው፣ከቤኒሻንጉል ነፃ አውጭ ግንባር ተብሎ ብረት አንግቶ ኤርትራ ከትሟል ከሚባለው በሰፊው ከማይታወቅ ፓርቲ የተወሰኑ ሰዎችን ተገንጥለው ሲመጡ፣የኢትዮጵያ አርበኞች ፓርቲ ከሚባል ስብስብ የተወሰኑ ሰዎችን አምጥቶ ‘ልማቱ አማሏቸው መጡ’ ብሎ ብዙ ፕሮፖጋንዳ ሲሰራ እንደኖረ የሚታወቅ ነው፡፡

እንዲህ በፕሮፖጋንዳ ፍቅር የወደቀው ኢህአዴግ ራሱ በሩ ድረስ ሰተት ብሎ የመጣው ለዛውም እንደ አቶ ሌንጮ ለታ፣ ዶ/ር ዲማነገዎች፣አቶ ሌንጮ ባቲን ፣ዶር በያና ሶባን የመሰሉ በሰፊው ኢትዮጵያዊ ዘንድ የሚታዊቁ የኦዴግ አመራሮች በሩ ላይ ቆመው ሲያንኳኩ ለማይጨክንበት የፕሮፖጋንዳ ፍጆታ እንኳን ይጠቅሙኛል ሳይል በመጣችሁበት እግራችሁ ተመልሳችሁ ሂዱ እስከማለት ያደረሰው ነገር ለሰሚ አስገራሚ ነው፤ለነአቶ ሌንጮ ለታም ክብር አይደለም፡፡

የጠ/ሚር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ተቃዋሚፓርቲዎች ስማቸው ተቀይሮ ‘ተፎካካሪዎቻችን እንጅ ጣላቶቻችን አይደላችሁም’ ተብለዋል፡፡ወደ ሃገራቸው ገብተው እንዲታገሉ ጥሪ ሲቀርብም ጥሪው መሬት ሳይነካ አፈፍ ያደረገው ኦዴግ ነበር፡፡ አጥብቆ ወደ ሃገር ቤት ይናፍቅ የነበረው ኦዴግ ሃገርቤት ገብቶ ምን ማድረግ እንዳሰበ እስከ ዛሬ ዘርዘር ባለ ሁኔታ አላሳወቀም-እንዴው በደፈናው ወደ ኦህዴድ ሊዳበል እንደሚችል ፍንጭ ከመስጠቱ በቀር፡፡ ‘ሀገርቤት ለመግባት ቀደም ብየ ድርድር አድርጌ ነበር’ ይበል እንጅ በምን ጉዳይ ላይ ተደራድሮ ምን አማካይ ነጥብ ላይ እንደደረሰም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

እንዲህ በተድበሰበሰ ሁኔታ ሃገርቤት የገቡት የኦዴግ አመራሮች ነገረ-ስራ የሚያመላክተው ዋናው ጉዳያቸው ሃገራቸው መግባት እንደሆነ ነው፡፡ሃገርን መናፈቅ ደግሞ ተፈጥሯዊ ስሜት ነውና ፍርድ የለባቸውም፡፡አስቸጋሪው ነገር ግን እነሱ እንደ አርአያ እየተጠቀሱ ሌሎች ጠንከር ያለ የዲሞክራሲ እና አለፍ ያለ የዲሞክራሲያዊ መንግስት ምስረታ አላማ ያነገቡ ቡድኖችም ብድግ ብለው ሃገርቤት እንዲገቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጭምር በሰፊው እየተጠበቀ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ “መደመር” የሚለውን ሰሞንኛ የሃገራችን ፖለቲካ ቅኝት ዝምብሎ ወደ መዳበሉ እንዳይመራው ያሰጋል፡፡

“ሸማ በየፈርጁ ይለበሳል”

የሃገራችን ተቃውሞ ፖለቲካ ሃይሎችን በሰፊው ለሁለት ጎራዎች መክፈል ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ሰልፍ የወጡበትን ዘውግ ፖለቲካዊ ጥቅም ለማስከበር እንሰራለን የሚሉ የዘውግ ፖለቲካ አራማጆች ሲሆኑ ሁለተኞቹ ሰልፈኞች ደግሞ ወሰን ሳይከልሉ በመላው ሃገሪቱ ላሉ ህዝቦች የዲሞክራሲ ፀሃይ የሚወጣበትን መንገድ የሚቀልሱ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ የአላማቸው እየቅልነት አሁን ላለው የመደመር ፖለቲካ ጥሪ የሚሰጡትን መልስ የተለያየ ያደርገዋል፡፡ የዘውግ ፖለቲከኞች የዘውጋቸው ሰው ስልጣን ላይ መውጣቱ በራሱ የጥያቄያቸውን ብዙ ክፍል መልስ የያዘ ሁነት ሊመስላቸው ይችላል፡፡የዲሞክራሲ ምፅዓት ናፍቆ ትግል ውስጥ ያስገባው አካል ደግሞ ዋነኛው ትኩረቱ ስልጣን የያዘው ሰውየ ዘውግ ሳይሆን ዲሞክራሲን በተቋማዊነት ላይ ለመገንባት ያለው ቁርጠኝነት ነው፡፡

ስለዚህ የ “ኑ ግቡ” ጉርሻው ሲጠቀለል ለሁሉም እንደየመጠኑ እንዲያጠግበው መሆን አለበት እንጅ በጅምላ የተጠቀለለው ግብዣ ሁሉንም አጥግቦት እኩል እያስሮጠ እንዲያመጣው መጠበቅ የለበትም፡፡ ጠ/ሚ/ር አብይ በቅርቡ ባደረጉት የፓርላማ ውሎ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን በስም ጠርተው ፓርቲያቸው እያደረገ ያለው የትግል አይነት ያለፈበት ፋሽን እንደሆነ ጠቁመው ሃገርቤት እንዲገቡ ያደረጉት ንግግር በግሌ አሳማኝም በሳልም ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ይልቅስ የተለመደው የኢህአዴግ ካድሬዎች ከመለስ ዜናዊ የወረሱት የነጋሪነት አባዜ የተስተዋለበት ነው፡፡

ዶ/ር ብርሃኑም ሆኑ ሌሎች ጓዶቻቸው ዛሬ ቀርቶ ያኔ የትጥቅ ትግሉን እንደ አንድ ስልት ለመጠቀም ሲወስኑ ነፍጥ የማንሳት ትግል ዘመናዊነቱ ስቧቸው እንዳልሆነ የታወቀ ነው፤እነሱም ደግመው ደጋግመው የቸገረው እርጉዝ ያገባል የሚለው ነገር ገጥሟቸው እንዳደረጉት ተናግረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ የትጥቅ ትግሉ ዋነኛ መሪዎቹን ከሚመጥናቸው ሙያዊ ስራ ወደ ነዲድ በረሃ የመውረድን ጨካኝ ውሳኔ የሚጠይቅ መሆኑ ብቻ ወደው መርጠው የሚያደርጉት ‘አንገታችን ላይ አስረነው እንሙት’ የሚያስብላቸው የድሎት ነገር እንዳለሆነ ግልፅ ነው፡፡ ሲቀጥልም እነዚህ ሰዎች ከጠ/ሚ/ር አብይ ያነሰ የነገሮችን ትርፍ ኪሳራ የመመርመር ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች አይደሉም፡፡ ስለዚህ ዝም ብሎ “ኑ ግቡ” ከማለቱ ባለፈ ከንቅናቄው አባላት ጋር ቁም-ነገር ያለው ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የንቅናቄው አባላትም በበኩላቸው ጠ/ሚ/ር አብይ የሚናገሩትን ንግግር ከማወደሱ፣ለበጎ ስራዎች አወንታዊ ድጋፍን ከመስጠቱ ባሻገር “ኑ” የሚለውን ግብዣ አስመልክቶ ከመምጣታቸው በፊት እንዲደረጉ የሚፈልጓቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ደጋግሞ መጥራት ላበዛው የጠ/ሚ/ አብይ መንግስትም ሆነ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግልፅ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህን በተመለከተ ከአርበኞች ግንቦት ሰባት በተሻለ በአቶ ዳኦድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ ግልፅ አቋም ወስዷል፤ የሽግግር መንግስት የማቋቋም ሃሳብ በሌለበት ሁኔታ ሃገርቤት መግባት እንደማይፈልግ ግልፅ አድርጎ ተናግሮ “ኑኑ” ማለት ላበዛው የኢህአዴግ መንግስት ትልቅ የቤት ስራ ሰጥቷል፡፡

በርግጥ የኢትዮጵያ መንግስት ብረት አንጋች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በብቸኝነት ከምታስጠልለዋ ጎረቤት ኤርትራ ጋር የጀመረው የሰላም ጉዞ እንደ አርበኞች ግንቦት ሰባት ያሉ አንድ እግራቸውን ኤርትራ ያደረጉ ፓርቲዎች አጣብቂኝ ውስጥ መክቱ አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ሃገር ቤት ያለውን የዜጎችን ጎሳ ተኮር መተራረድ ከማስቆሙ አስቸኳይ ስራ ሳይቀር አስቀድሞት ከኤርትራ ጋር ሰላም ማውረዱ ላይ የሚሟሟተው ብረት አንጋች ተገዳዳሪዎቹን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ሊሆን እንደሚችል መገመት ስህተት የለውም፡፡በዚህ ላይ አርከበ ዕቁባይን የመሰሉ በደባ እና በማስገደድ ፖለቲካ የተካነው የህወሃት ዋና ሰዎች ከጠ/ሚ/ር አብይ ጉያ ጨርሰው ያልጠፉ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን የለውጥ ሃይልም ሊሆኑ ይችላሉ እየተባሉ መሆኑ ለጥርጣሬው ግብዓት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ጋር የሰላም ኑሮ ለመጀመር ጉዞ የጀመረችው ኤርትራ ዛሬ ላይ በሰላም ልትጎራበተው ያሰበችውን መንግስት ውጅግራ አንስተው የሚወጉ ቡድኖችን ብታስጠልል በኢትዮጵያ ከሚዘወረው ትንሹ ኢጋድ ጀምሮ እስከ ትልቁ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ድረስ ለሚሰነዘርባት ወቀሳ የምትመልሰው የላትም፡፡ስለዚህ ወዳም ይሁን ተገዳ፣ፈጥናም ይሁን ዘግይታ የኢትዮጵያ ሸማቂዎችን ከምድሯማስወጣት አለባት፡፡ ይህ ደግሞ ለአርበኞች ግንቦት ሰባት ቀላል ፈተና አይደለም፡፡ ሆኖም ፋታም መፍትሄም የሌለው ችግር አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ እና ኤርትራም የሰላሙን ጉዞ ጀመሩት እንጅ አልጨረሱትም፡፡ ቢያንስ ኤርትራ እና የኢትዮጵያ የድንበር ማስመር ጉዳይ እስኪጠናቀቅ ድረስ አርበኞች ግንቦት ሰባት ጦሩን ኤርትራ ማቆየት ይችላል፡፡ ስለዚህ ሃገር ቤት ገብቶ በመታገሉ ዙሪያ ያለውን ፍላጎት አስመልክቶ ከመምጣቱ በፊት ሊሟሉለት የሚፈልጋቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በግልፅ አስቀምጦ የቤት ስራውን የጨረሰ ያህል ተሰምቶት “ሁሉም ወደ ሃገርቤት” እያለ ላለው የጠ/ሚ/ር አብይ መንግስት የቤትስራ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡

ጦሩን በተመለከተም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ጦር አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመሰለ ሰው የርዕዮት ዓለም ስልጠና የወሰደ በመሆኑ ለወደፊቷ ኢትዮጵያ የሚመጥነውን የዲሞክራሲያዊት ሃገር መከላከያ ሰራዊት ግንባታ ስራ ጥሩ ግብዓት ስለሚሆን በለውጥ ጎዳና ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ጥሩ እድል ወስዶ የመከላከያ ሰራዊቱ አካል ቢያደርገው ጥቅሙ ለሃገር ነው፡፡ በዚህ የማይስማሙ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ወታደሮች እጣፋንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መደራደሩም የፓርቲው ሌላ ስራ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው አርበኞች ግንቦት ሰባት ዝምታውን ሰብሮ ሃገርቤት እንዲባ የሚደረግለትን ጥሪ አስመልክቶ በበኩሉ እንዲሟሉ የሚፈልጋቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች ሳይፈጥንም ሳይዘገይም በግልፅ ማቅረብ ሲችል ነው፡፡