በቅርቡ ወደ አገር ቤት የተመለሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን በምርጫ ቦርድ አልተመዘገቡም

አዲስ አበባ፡- በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባደረጉት ጥሪ መሰረት ወደ አገር ቤት በመግባት ላይ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን የመመዝገብ ጥያቄ አለማቅረባቸውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡

በቦርዱ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ጥሪውን ተከትሎ ወደ አገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ቦርዱ በመምጣት ምዝገባ አላካሄዱም፡፡

ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ መሆን የሚያስፈልጋቸው የተቀመጠውን መስፈርት ሲያሟሉ መሆኑን የገለጹት አቶ ወንድሙ፣ መመስረት የሚፈልጉት አገር አቀፍም ይሁን ክልላዊ መሆኑ የሚታወቀው ወደ ቦርዱ ለመመዝገብ ሲመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ምክትል ኃላፊው ገለጻ፤ ተመዝጋቢዎች ማሟላት ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል ሊያቋቁሙት የፈለጉት ፓርቲ መርሃ ግብር፣ የመተዳደሪያ ደንብና የመስራች አባላት ብዛት ይጠቀሳሉ፡፡ መስራች አባላቱ ለአገር አቀፍ ፓርቲ 1 ሺ 500 አባላት፣ ለክልላዊ ፓርቲ ከሆነ ደግሞ 750 አባላት ማስፈረም ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ያለፈን ፓርቲ ቦርዱ በማጽደቅ ሰርተፊኬት የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ይህ ህግ አሁን እየሰሩበት ያለው ሲሆን፣ አዲሱ ህግ ውይይት ተደረገበት እንጂ ገና አልጸደቀም፡፡

ምክትል ኃላፊው በአሁኑ ወቅት ወደ አገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች መመዝገብ አለባቸው ተብሎ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ እንደሌለ አብራርተው፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በፈለገው ጊዜ የመደራጀት መብት እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ መደራጀትና ሰላማዊ ትግል ማድረግ እፈልጋለሁ ካለ በሚያቀርበው ጥያቄ መሰረት ቦርዱ እውቅና እንደሚሰጠውም አመልክተዋል፡፡

ወደ ቦርዱ በመምጣት ምዝገባ እስካልተደረገ ድረስ ግን እውቅና የማያገኝ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ወንድሙ፣ አንድ አገር አቀፍ ፓርቲ ነኝ የሚል ፓርቲም ቢያንስ አራት ክልሎች አካባቢ መንቀሳቀሱን ማረጋገጥ እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡ ለመመዝገብ ለሚመጡ የፖለቲካ ኃይሎች ምንጊዜም በሩ ክፍት መሆኑንም ጠቁመው፤ ቦርድ የሚፈልገው የመመዝገቢያ አዋጁ በሚፈቅደው መሰረት የሚጠበቅባቸውን እንዲያሟሉ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ በአገሪቱ የተጀመረውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ለማጠናከር የፖለቲካ ፓርቲዎች መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ ደግሞ የቦርዱ ኃላፊነት ወደ እርሱ የሚመጡ የፖለቲካ ኃይሎች የሚፈልገውንና ህጉ የሚጠይቀውን መስፈርት እንዲያሟሉ ማድረግ ብቻ ነው፡፡

አሁን ወደ አገር ወስጥ የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች መሰባሰብ፣ አባላትንም ማሰባሰብ እንዲሁም የት የት አካባቢ መንቀሳቀስ ስላለባቸው ጉዳይ እና በመሳሰሉ ነገሮች ላይ እንደሚዘጋጁ ጠቅሰው፣ በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ አገር ቤት የገቡና በመግባት ላይ ላሉም ሆነ በአገር ቤት ውስጥ ሆነውም ለመደራጀት ለሚያስቡ የፖለቲካ ኃይሎች የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለመኖሩን ገልጸዋል

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ እውቅና ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላላ ቁጥር 62 ሲሆን፣ አገራዊ ፓርቲዎች 22፣ ክልላዊ ፓርቲዎች ደግሞ 40 መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ምንጭ፦ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፌስቡክ ገፅ (አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ሰኔ 27 ቀን 2010 ዓ.ም)